Saturday, 26 September 2020 00:00

በካፊያ የሚደነግጥ የዶፉን ዕለት መጠጊያ ያጣል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

  ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ ትልቅ ጫካ ውስጥ አንድ ነብርና አንድ ዱኩላ አንድ ላይ ይኖሩ ነበር፡፡ በየፊናቸው ሌሎች አውሬዎችን በማደን የእለት ምግባቸውን እያሟሉ ነበር፡፡ ድኩላው ነብሩ እንዳያገኘው እየተጠነቀቀ በአንድ አቅጣጫ ይሸሻል፡፡ ነብሩም ድኩላው ካገኘው ሊወጋው እንደሚችል በማሰብ፣ በአንድ አቅጣጫ ይሸሻል፡፡ ውሎ አድሮ ግን እንዲህ በየአቅጣጫው እየሸሹ መኖር ሁሌ አይሳካምና፣ አንድ ቀን ፊት ለፊት ተገናኙ፡፡ ይሄኔ ነብሩ አንድ ሃሳብ ብልጭ አለለት፡፡
“አያ ድኩላ እንደምታውቀው በዚህ ጫካ ውስጥ ለብዙ ዘመን ኖረናል፡፡ ሆኖም ሁለታችንም አንዳችን አንዳችንን በመፍራት እየሸሸን በሥጋት ስንሸማቀቅ እንደ ልባችን ተዘዋውረን የፈለግነውን አድነን ያለ ሃሳብ የተንቀሳቀስንበት ምንም ጊዜ አልነበረም፡፡ አሁን ግን አንድ የአኗኗር ለውጥ ብናደርግ ጥሩ ይመስለኛል፡፡” አለው፡፡
ዱኩላ፤ “እኔም’ኮ ተገናኝተን ብንነጋገርና በጋራ ተመካክረን፣ ያለመፈራራት ብንኖር ጥሩ ነበር እያልኩ ብዙ ጊዜ አስባለሁ፡፡ ነገር ግን እንዳለመታደል ሆኖ አለመገጣጠም አለመቻላችን ብዙ ዓመታት አለፉ፡፡”
ነብሩም፤ “እንደዚህ ያለ ቀና አሳብ ካለህማ አንድ ስምምነት ብናደርግ መልካም ነው፤ በቃ ከእንግዲህ በክፉ አይን ላንተያይ በክፉ ላንፈላለግ፣ በጫካው ያሉትን አውሬዎች በጋራ እየተመገብን ኑሯችንን ልንገፋ እንስማማ”
ድኩላ፤ “በጣም ደስ የሚል ነገር ነው፡፡ አየህ መመካከር እንደዚህ ያለ ጥሩ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ይጠቅማል፡፡ እንደዚህ ያለ ሰፊ ጫካ ለኔና ለአንተ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም እንስሳት የሚተርፍ ሀብት ያለው ነውና፣ ከእንግዲህ ያለ ሥጋት እንኑር፡፡ እንደውም ሌላ አውሬ ቢመጣብን በጋራ ሆነን እየተከላከልን ማጥፋት አለብን፡፡” አለው፡፡ በዚሁ ተስማሙና መኃላ ፈፀሙ፡፡ መሃላቸውም፤ “ከእንግዲህ አንነካካም፤ ብንነካካ ግፉ በልጅ ልጆቻችን ይድረስ” የሚል ነበር፡፡
ነብሩና ድኩላ በስምምነትና በፍቅር ተስማምተው ይኖሩ ጀመር፡፡ ሆኖም በጫካው የሚኖሩት የሚታደኑት እንስሳት ቀስ በቀስ ቁጥራቸው እየተመናመነ መጣ፡፡ በመጨረሻም ጨርሶ አንድም የሚታደን አውሬ ጠፋና ምን እናድርግ ተባባሉ፡፡ “ወደ ጐረቤት ጫካ እንሂድና እናድን እንጂ፤ እዚህ እየተራብን መቀመጥ የለብንም”፡፡ አሉና ራቅ ወዳለው ሌላ ጫካ ዘመቱ፡፡ እዚያም ያገኙትን እየተመገቡ ሰንብተው ያለውን በልተው ጨርሰው፣ ፆማቸውን የሚያድሩበት ጊዜ መጣ፡፡ ድኩላው ማናቸውንም ቅጠላ ቅጠል ለመብላት ስለሚችል ብዙ አልተጐዳም፡፡ አያ ነብሮ ግን ሥጋ - በል ብቻ በመሆኑ በረሃብ ተሰቃየ፡፡
አንድ ቀን ዱኩላው ቅጠል ለመብላት ዛፍ ላይ በሁለት እግሩ ተንጠራርቶ ሲቀነጣጥስ፣ ነብር ከመሬት ተኝቶ የድኩላውን  ጭንና ታፋ ተመለከተ፡፡ “ይሄን የመሰለ ሥጋ እያለልኝ በረሃብ መሞት የለብኝም ብሎ አሰበና ባለ በሌለ ኃይሉ ቸር ብሎ ወደ ድኩላው ተወረወረ፡፡ ሆኖም ጉልበቱ እጅግ ፈጣንና ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ የድኩላውን አካል አልፎ በሆዱ ቀንዱ ላይ አረፈ፡፡ የድኩላው ቀንድ ነብሩ ሆድ ተሰክቶ አንጀቱን ዘረገፈው፡፡ አያ ነብሮ ሊሞት በማጣጣር ላይ ሳለ፣ አያ ድኩላ “ምነው እንዳንነካካ ተማምለን አልነበረም?”  አለው፡፡
ድኩላም “አያ ነብሮ፤ የኛ አያት ቅድመ አያቶች “እንዳንነካካ ግፉ በልጅ ልጆቻችን ይድረስ” ተባብለው ተማምለው እንደሆነ፤ ማን ያውቃል?” አለው ይባላል፡፡
*   *   *
ከአያት ቅድመ አያት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ መሃላ ታሪክ፣ ባህላዊ እሴት፣ ለተከታይ ትውልድ ይደርሳል፡፡ መንገዱ ይለያይ እንጂ አይቀሬ ነው፡፡ ያንን መሃላ አክብሮ እንደ ቃሉ መፈፀም የተረካቢው ማህበረሰብ ኃላፊነት ነው፡፡ ብዙ ብርቅና ድንቅ የሚሰኙ ታሪካዊ ሃብቶችና እሴቶች ልማዶች፣ እንዲሁም ከሌሎች ሀገሮች የሚለየኝን ቅርሶች አሉን፡፡ እነዚህን ቅርሶች ተንከባክበን፣ ይሁነኝ ብለን… መጠበቅና ለልጅ ልጆቻችን ማቆየት ታላቅ ነገር ነው፡፡ ስለዚህም በመጀመሪያ ምን ምን እንደሆኑ መለየት፣ ከነዚያ ውስጥ እንደየ ደረጃቸው ውድቅና ብርቅ የሆኑትን መርምሮ በመልክ በመልክ መደርደር፣ ከዚያም የማይባክኑበትንና የማይዘረፉበትን ሁኔታ በማመቻቸትና ተገቢነት ያለው የማስቀመጫ ቦታ በማዘጋጀት ጥበቃ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ቀደም አያሌ በየቤተክርስቲያናቱ በየገዳማቱና በተለያዩ ተቋማት ውስጥ በተበታተነ ሁኔታ የተቀመጡ ሃብቶች ይሰባሰቡ ተብሎ ለነ ዶ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት አማካኝነት፣ በኢትዮጵያ የጥናቶች ኢንስቲቲዩት በዩኒቨርስቲ እንዲሰባሰቡ ተደርጐ ነበር፡፡ ሆኖም ተሰባስበው የተቀመጡበት ቦታ ምቹ ባለመሆኑና ተደራርበው አንድ ላይ ታፍገው በመቀመጣቸው ምክንያት በእርጥበትና በመዘበራረቅ እንዲሁም በመፈጋፈግ ኦርጅናሊ መልካቸውን በማጣት አንዳንዶቹ ከናካቴው ከጥቅም ውጪ በመሆናቸው ዶ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት ፤ “We are victims of our own success” (የራሳችን ድል ሰለባዎች ሆንን እንደማለት ነው) ተብሎ ተነግሮ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ነው፡፡ የቅርሶች ማከማቻ የሚሆን ህንፃ እንዲገነባ ተብሎ የመሠረት ድንጊያ የተቀመጠው፡፡ በሀገራችን ብዙ በዘመቻ የሚሰሩ ነገሮች የመኖራቸው ነገር መቼም ሰው ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም ዋና ችግራችን የአንድ ሰሞን ሞቅ ሞቅ ብቻ ሆኖ መቅረታቸው ነው፡፡ ችግኝ ለመትከል ከፍተኛ ርብርብ ይደረጋል፡፡ ማደጋቸውን መከታተልና የት ደረሱ የማለት ባህል ግን ገና በቅጡ አላዳበርንም፡፡ ብዙ መኖሪያ ቤቶች ይሰራሉ፤ በምን ሁኔታ ላይ ናቸው?  እንዴት እየተከታተልናቸው ነው? የሚለውን ጥያቄ ግን ተከታትሎ አስፈላጊውን የሚያደርግ የለም፡፡ ይህንን ስራዬ ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ እንደ ሁልጊዜው ዛሬም በተደጋጋሚ ይነገር እንጂ በቅጡ ምላሽ ያላገኘ አንገብጋቢ ጥያቄ - የትክክለኛውን ሰው በትክክለኛው ቦታ አለመመደብ አባዜ ነው፡፡ (The right man at the right place እንዲል) በቂ የሰው ኃይል አለመኖር እንደ አንድ ችግር ተጠቃሽ ሆኖ ሳለ፣ ያለውን የሰው ኃይል በተገቢው ቦታ አለመደልደል ደግሞ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ያደርገዋል፡፡ “ይህንን ችግር ካለብን የተማረ የሰው ኃይል እጥረት ጋር እንደ አቅማችን አጣጥመን በማስተዋል በጽሞና ለመፍታት መጣጣር፣ እጅግ ወሳኝ መሆኑን የሚመለከተው ክፍል ሊያስብበት ይገባል፡፡ ሁሉንም በአንድ ጊዜ ወይም በአንድ ድንጋይ መምታት እንደማይቻል መቼም  ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ (Defacto እንዲሉ) ሆኖም ብርቱ ጥረት ከተደረገ የማይፈታ ችግር የለም፡፡ በሚል ሁሉንም የሚያግባባ አረፍተነገር ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ ከዛ ቀጣዩ ነገር እንደ ቅደም ተከተል መሰናዶ ጉዳይ ነው፡፡ (prioritizion እንዲሉ) በየደረጃው የትኛው እጅግ ወቅታዊ፣ በጣም ወቅታዊና ወቅታዊ ብሎ ከፋፍሎ… ማየት በጣም ቁልፍ ነገር ነው፡፡ ይህ ደግሞ በፈንታው ረብ - ያለው ጥናት ማድረግን ግድ ይላል፡፡ ጥናቱ ደግሞ አጥኚ መፈለጉ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የነዚህ ሁሉ ማሰሪያ ደግሞ የማቀናጀትና የማዋሃድ ተግባር ነው፡፡ (coordination and integration እንዲል መጽሐፍ) እንግዲህ በተባ አእምሮና በቀና ልቦና በተቻለ ብቃት ከተጋን የምኞታችንን ማሳካት ይቻለናልና ጥናቱን ይስጠን እንላለን፡፡
አዲሱ ዓመትና የመስቀል በዓል የመልካም ምኞት መግለጫ ብቻ ሳይሆን ደግ ደጉን የመተግበሪያና የማሳኪያ እንዲሆን ከወዲሁ አስበንበት ታጥቀን ስንነሳ፣ በመልካም ትጋት ጥንካሬና ብስለት እንዲሆን ከመመኘት ጋር ነው፡፡ በትናንሽ ችግሮች ባለመደናገጥ ለመጓዝ ጥረት እናድርግ!
“በካፊያ የሚደነግጥ የዶፉን ዕለት መጠጊያ ያጣል” እንዲሉ፡፡
መልካም የመስቀል በዓል!




Read 9499 times