Print this page
Saturday, 26 September 2020 00:00

የአቶ ልደቱ አያሌው ዋስትና ታገደ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 አላስፈላጊ እስር ማስቀረትና የዋስትና መብት ማስከበር ያስፈልጋል - ኢሰመኮ

           የምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት፣ አቶ ልደቱ አያሌው በመቶ ሺህ ብር ዋስ ከእስር እንዲወጡ የሰጠው ትእዛዝ በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት የታገደ ሲሆን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በበኩሉ፤ አላስፈላጊ እስር ማስቀረትና የዋስትና መብት ማክበር ያስፈጋል ብሏል።
ህጋዊ ፈቃድ የሌለው የጦር መሳሪያ ይዞ በመገኘት ወንጀል ተከሰው በእስር ላይ ሆነው ሲከራከሩ ከቆዩ በኋላ መስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም የምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በ100 ሺ ብር ዋስ ተለቀው ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ፈቅዶላቸው ነበር፡፡
ይሁን እንጂ በተለያዩ ምክንያቶች ለ3 ቀናት የዋስትና መብታቸው ሳይፈፀም ከቆየ በኋላ ከትናንት በስቲያ የዋስትና መብታቸው በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ምስራቅ ሸዋ ተዘዋዋሪ ምድብ ችሎት መታገዱ ተሰምቷል።
የታገደውም የአዳማ ፍትህ ቢሮ አቃቤ ህግ በዋስትናው ላይ ይግባኝ በመጠየቁ ነው የተባለ ሲሆን አቶ ልደቱ መስከረም 19 ቀን 2013 ዓ.ም በቀጠሯቸው መሠረት ከማረፊያ ቤት እንዲቀርቡ ነው የታዘዘው፡፡
የአቶ ልደቱ በተደጋጋሚ የዋስትና መብታቸው መጣሱ ያሳሰበው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በበኩሉ የሰብአዊ መብቶች መከበር ዋና ዋስትናው የፍ/ቤት ውሳኔ መከበር መሆኑን አስገንዝቧል።
“አቶ ልደቱ አያሌውን ጨምሮ በፍ/ቤት የዋስትና መብት ተፈቅዶላቸውና የዋስትና ሁኔታውን አሟልተው ከእስር እንዲለቀቁ ፍ/ቤት ትእዛዝ የሰጠላቸው ታሳሪዎች በሙሉ በአስቸኳይ እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር ሊፈቱ ይገባል” ሲሉ ነው ኮሚሽነሩ ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ያስገነዘቡት።
ቀደም ብሎ አቶ ልደቱ አስይዘው ከእስር እንዲወጡ የተጠየቁትን 100 ሺህ ብር የዋስትና ገንዘብ መክፈላቸውንም ለማወቅ ተችሏል።  


Read 3990 times