Saturday, 19 September 2020 13:53

የሰላም ዘመን ናፍቆናል!!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ዓመት ሄደ፣ ዓመት መጣ…እንዲህ ነው ነገሩ እንግዲህ፡፡ የመልካም ምኞት መግለጫ ስንለዋወጥ ነው የሰነበትነው፡፡ ልባችን ውስጥ ተቀብሮ የተፋቀ እለት ብቅ እንደሚለው ሳይሆን ቢያንስ፣ ቢያንስ እንደተጻጻፍነው ምኞታችንን ያድርግልን!
ያው ደጋግመን እንዳልነው … በአብዛኛው በጣም ከባድ ሆኖ ያለፈ ዓመት ነው፡፡ ደግነቱ ችግር ቢበዛም ራሳችንን ማባበያ አናጣም… ቤት ውስጥ የድስት ጥራጊው ቢጠፋ… አለ አይደል…  “ሁሉም ነገር ጨለማ አይደለም፡፡ ወጡ ቢጠፋ ቢያንስ፣ ቢያንስ ድስቱ አለኝ፣” አይነት ማጽናኛ ይኖራላ!
ስሙኝማ… ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ …“መጪው ዓመት ለአንተና ለቤተሰብህ የሰላም ዓመት እንዲሆን እመኛለሁ፣” የሚል መልእክት ታገኛላችሁ፡፡ ነገርዬው ቀሺም የሚሆንባችሁ የሰውዬውን ስም ስታዩ ነው። ሰላም የተመኘላችሁ ሰውዬ እኮ ዋነኛው የእናንተና የቤተሰባችሁ የሰላም አፍራሽ ነው። ዓመቱን ሙሉ ሊጥላችሁ ሲገዘግዛችሁ የከረመ፣ ዓመቱን ሙሉ በየደረሳችሁበት ቀድሞ መንገዳችሁ ላይ እሾህ ሲበትን የከረመ፣ ዓመቱን ሙሉ አንዴ በፖለቲካ፣  አንዴ በምናምን እያነካካ “ደህና አድርገው በነከሱልኝ!” ከሚላቸው ግለሰቦችና ክፍሎች ጋር ሊያላትማችሁ ሲሞክር የከረመ ሰው… አለ አይደል… ‘ሰላም’ ሲመኝላችሁ “ኢሮ፣ ልብ ገዛ!” ብሎ ለማጨብጨብ አስቸጋሪ ነው፡፡
እናማ… እናንተም “መሳቁን ይስቃል፣ ጥርሴ መች አረፈ፣” እያላችሁ ትመልሳላችሁ… “ለአንተና ለቤተሰብህም መልካም የሰላም ዓመት ይሁንላችሁ….” በማለት፡፡ ይቺም እኮ ‘ስንተዋወቅ፣ አንተናነቅ’ ነገር ነች፡፡ ልክ ነዋ…ስንትና ስንት ጊዜ እኮ የብሩስ ዊሊስን ‘ዳይ ሀርድ’ ፊልሞች አይነት ቀውጢ እንዲደርስበት ስትመኙ ነው የከረማችሁት።
‘አፈር እያቃምነው’ ያለውን ሰው “አፈር ልብላልህ!” አይነት ‘ዲፕሎማሲ’ ቀሺም  ነው። አለ አይደል… “የሰላም ዓመት ይሁንልህ/ይሁንልሽ…” መባባሉ አሪፍ ነው። ግን እኮ አፈር እያስቃምነው ያለነውም፣ ሰላሙንም እየነሳነው ያለነውም እኛው ነን እኮ! የሚገርም ዘመን እኮ ነው፡፡ የእኛን ግድግዳ ከመገንባት ይልቅ እኮ ‘ቅድሚያ የምንሰጠው’ የዛኛውን ሰው ግድግዳ ማፍረስ የሆነ የሚመስልበት ዘመን ነው፡፡    
እናላችሁ…መልካም አዲስ ዓመት ስንመኛኝ የነበረው እውነት ከልባችን ነው ወይ የሚለው ነው ጥያቄው፡፡ በሰው አፍ ላለመግባት ነው ወይስ ከአንጀት?! ዘንድሮ እኮ ብዙ ነገር ‘ቲራቲር’ ሆኗል፡፡ እውቅና ሰጥቶ… “ለመሆኑ፣ ምን አስቂኝ ገጠመኝ አለህ/አለሽ?” ብሎ በጥያቄ ‘የሚያፋጥጠን’ የቲቪ ጋዜጠኛ አጥተን ነው እንጂ የወጣልን ተዋናዮች እኮ በሽ ነን፡፡ እናላችሁ… ሰሞኑን ያንን ሁሉ የመልካም ምኞት መልዕክት ስናዥጎደጉደው… ፋቅ፣ ፋቅ የሚያደርግ ቢኖር ኖሮ ስንት ጉድ በወጣ ነበር፡፡  
እንበልና እሷና እሱ አሉ፡፡ እናላችሁ…እሱ ስንት ነገር እያሰበ እያለ እሷዬዋ መሀል መንገድ ላይ አስጥታዋለች፡፡
“ስማ ያቺ እንትና…”
“ብቻ በህልሜ መጣችብኝ እንዳትለኝ!”
“የበዓል ቴክስት አትልክልኝ መሰለህ!”
“ምን ብላ?!”
“የሰላም ዓመት እንዲሆንልህ እመኛለሁ…”
“ታዲያ የበዓል ላከችልኝ ከምትለኝ አሾፈችብኝ አትለኝም! ሰላምህን ብትፈልግ ኖሮ አውላላ ሜዳ ላይ አስጥታህ ትሄድ ነበር?!”
እናላችሁ… አሱዬው…አለ አይደል… ገራገር ቢጤ ከሆነ ትንሽ ተስፋ ሊያደርግ ይችላል፡፡
“ምናልባት ሃሳቧን ለውጣ ቢሆንስ?!”
ከሦስት ዓመት ከሰባት ወር በኋላ! እኔ የምለው… በ‘እሷና እሱ’ ግንኙነት ‘ሪሳይክሊንግ’ የሚባል ነገር አለ እንዴ!
ስሙኛማ… ስለ መልካም ምኞት መግለጫ ስናወራ አሁን፣ አሁን ትንሽ ሰልቸት ወደ ማለት እየተቃረበ የመጣ ነገር አለ፡፡ ማለት….በትልቁም ደረጃ፣ በትንሹም ደረጃ ያሉ ባለስልጣናት አስተላለፉ የሚባለው የመልካም ምኞት መግለጫ ሁሉ በሚዲያ መነበብ አለበት እንዴ!? አሀ…የአየር ሰዓት ‘ያለህ’ የሚያስብሉ አጄንዳዎች አሉብና!
“የሲያምርሽ ይቅር ወረዳ የኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሀላፊ የሆኑት አቶ ሳይቀድሙኝ ደረስኩ፣ ለዘመን መለወጫ በዓል መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል፡፡; እና እንዲህ ያለውን ነገር ስንት ሚሊዮን ህዝብ ዘንድ በሚደርስ ሚዲያ ላይ መስማት አለብን! እዛው ለሲያምርሽ ይቅር ወረዳ ነዋሪዎች ከቻሉ በሜጋፎን፣ ካልሆነም የእድር ጡሩምባ ተውሰውም ቢሆን ይንገሩዋ! የወረዳው ህዝብ እኮ ምናልባትም “የሙሶሊንን ወታደሮች መንቀል እንኳን ይሄ  ሰውዬ እንደ መንቀል አላስቸገረም፣” እያለ ሊሆን ይችላል!
ለምሳሌ እነኚህ የሰማይ ስባሪ የሚያካክሉት ተቋማት በቴክስት “እንኳን አደረሳችሁ፣” ሲሉን አይደል የሰነበቱት! ኸረ ለቆሽታችን እዘኑለት! ስታበግኑት የከረማችሁት፣ አሁንም እያበገናችሁት ያላችሁት ቆሽታችንስ! (ላለፉት ሳምንታት የዚህን ጸሀፊ ቆሽት ስታበግኑትና፣ የውጪዎች እንደሚሉት ‘ኸልፕለስ’ እያደረጋችሁት የከረማችሁ አገልግሎት ሰጪዎች…‘ውድ ደንበኛ’ እያላችሁ የምትልኳቸው መልእክቶች የቆሽት ብግነትን የማባባስ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ለመጠቆም ያህል ነው።)
እናላችሁ… ምን መሰላችሁ…በየእለቱ መከራችንን የሚያበሉን ተቋማት “እንኳን አደረሳችሁ…” እያሉ ‘መልካም ምኞታቸውን’ ሲገልጹልን፤ “እነኚህ ሰዎች ከአንጀታቸው ነው ወይስ ሲያሾፉብን ነው?” ብንል ይፈረድብናል!
የዘንድሮ አዲስ ዓመት አገባብ ቀለል ብሎ ነው ያለፈው ማለት ይቻላል…ከሞላ ጎደል። የገበያውን ነገር ተዉት ማለት ይበቃል፡፡ እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… በቺስታነታችን ሁሉም ነገር እንዲህ ጣራ የነካው መካከለኛ ገቢ የሚባለው ቦታ ስንደርስ ምን ልንሆን ነው አያሰኝም! (ጥያቄ አለን…መካከለኛ ገቢ የምትባለው የፈረንካዋ ቁጥር ስንት ላይ ሲደርስ ነው? አሀ…ነገና ከነገ ወዲያ የመደብ ትግል ምናምን የሚል ነገር እንደገና ብቅ ቢል ‘ለአመዳደብ’ እንዲያመቸን ነው! እነ እንትና…ደግሞ ምን ቢያስብ ነው ‘የመደብ ትግል’ የሚል ቋንቋ ያመጣው ብላችሁ…‘ያለፈው ስርአት ናፋቂ’ ምናምን የሚባል ቡድን ውስጥ እንዳትከቱኝማ!)
የምር እኮ ከዚህ በፊት እንዳወራነው ሰላምታችን ሳይቀር ተለውጧል…“ሰላም ነው?” የሚለው እኮ… “በጎ አደርክ?”  “እንዴት ከረምሽ?” መባባልን እንዴት ነው የሚተካው?! እንደ ጠያቂው ማንነት ወይም ምንነት “ሰላም ነው?” የሚለው አነጋገር መረጃ ሊሆን ይችላል፣ ‘ምርመራም’ ሊሆን ይችላል፡፡ “ሰላም መሆን ወይም አለመሆንን አሁን ካልተናገርክ የውስጥ እንትንህን እንሶስላ የተቀባ እስኪመስል ነው የምጠበጥብህ!” አይነት ነገር ማለት ነው፡፡ ወይ ደግሞ… “ምን አዲስ ነገር አለ?” ብንባባል ይሻላል፡፡   
እንደ አፈር ፍርስርስ ለሚለው ገላችን
እንደ ድንጋይ ስብር ለሚል አጥንታችን
የእኛ መንቀባረር ከቶ ለምንድነው
የቤት መለሰኛ ጭቃ ለምንሆነው
የምትል ዘመን የማይሽራት ስንኝ አለች። ብዙዎቻችን እንዳይሆን፣ እንዳይሆን እያደረገን ያለው ይህን ሀቅ ስለምንረሳ ነው፣ በትንሽዬ ነገር መንቀባረር ስለምንጀምር ነው፡፡ የባንክ ደብተሩ ወፈር ሲል “ማን ደፍሮ ዝምቤን እሽ እንደሚል አያለሁ!” አይነት ፉከራ ስለምንጀምር ነው፡፡ ሚጢጢ፣ ግፋ ቢል ከወረዳ የማታልፍ ስላጣን ሲኖረን “ከናፖሊዮን ጎን ዙፋን አመቻቹልኝ፣” አይነት ባህሪይ ስለምናመጣ ነው፡፡
ከአንገታችን ሳይሆን ከአንጀታችን አንዳችን ለሌላኛችን መልካም መተሳሰባችን የቀነሰው “የቤት መለሰኛ ጭቃ ለምንሆነው” የምትለዋን ሀቅ ስለምንረሳ ነው፡፡
የሰላም ዓመት ይሁንልንማ! የሰላም ዘመን ናፍቆናልና!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1502 times