Print this page
Saturday, 19 September 2020 13:47

የሁለቱ ሰዓሊያን ትውስታ

Written by  ሠዓሊ ታደሰ መስፍን
Rate this item
(0 votes)

     የ25 ሳንቲም እና የ50 ሳንቲም የሥነጥበብ ሥራዎች የማናቸው?
                         
          ‹‹--ከብዙ ወራት በኋላ የኢትዮጵያ የብር ኖቶችና ቅንስናሽ ሳንቲሞች የመቀየራቸው ወሬ በሰፊው መወራት ጀመረ፡፡ ያን ጊዜ ጥርጣሬዬ ጨመረ፤ ‹እነዚያ በክብ ውስጥ የሠራኋቸው ንድፎች ለሳንቲሞቹ ይሆን እንዴ? … ብዬ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ‹…በኋላ ውጤቱን ስታየው ደስ ይልሃል … ይህንን አገራዊ ምስጢር እንድትጠብቅ ጥብቅ ትዕዛዝ ተላልፏል!› የሚለው የሻምበሉ በማስጠንቀቂያ የተጠቀለለ መልዕክት በአዕምሮዬ ይመላለስ ነበር፡፡ ከሆነ ጊዜ በኋላ፣ ሳንቲሞቹ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቤት እንደወጡ ሰማሁ። ተጣድፌ ሳንቲሞቹን ሳያቸው ሥራዎቼ ቁልጭ ብለው ወጥተዋል፤ በሃያ አምስትና በሃምሳ ሳንቲሞች ላይ፡፡ የሆነ ግምብ ተደግፌ ደግሜ፤ ደጋግሜ ሳንቲሞቹን አየኋቸው፡፡ ሰዎች ከርቀት ሲመጡ ሳይ፣ እየተደናበርኩ እጓዛለሁ፡፡ ሰው አጠገቤ አለመኖሩን አረጋግጥና እንደገና ሳንቲሞቹን ከኪሴ አውጥቼ ዳግም እመለከታቸዋለሁ፡፡ እንደ ልጅም ሳያደርገኝ የቀረ አይመስለኝም። ሳንቲሞች ላይ ስለወጡት ምስሎቼ ከእኔ ቀድመው ያወቁት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ሠራተኞች ናቸው፡፡ በቅርብ የሚያውቁኝና የሚቀርቡኝ ሰዎች ሁሉ ይጠይቁኝ ነበር፤ ነገር ግን የኔ ሥራዎች ናቸው ብዬ ለመመለስ አልደፈርኩም፡፡ አገራዊ ምስጢር እንድጠብቅ ጥብቅ ትዕዛዝ ተላልፏል፡፡: ይህንን ትዕዛዝ መተላለፍ ምን እንደሚያስከትልብኝ አውቃለሁና … በዝምታ ምላሽ ሳልሰጥ መደበኛ ሥራዎቼ ውስጥ ተደበቅሁ›› ይላሉ፤ ሠዓሊ ታደሰ መስፍን፡፡
‹‹ሩስያ ለትምህርት በሄድኩ ጊዜ፣ ለጓደኞቼ ሳንቲሞቹን ሳሳያቸው በጣም ይደነቁ፤ ይደመሙ ነበር፡፡ በተረፈ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለ ጉዳዩ አያውቅም ነበር፡፡ ለነገሩ የሚያውቅበት መንገድም፤ ምክንያትም አልነበረም፡፡ የብር ኖቶችና ሳንቲሞች ምስሎችን በተመለከተ ሚዲያም ሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ትንፍሽ ያሉት ነገር አልነበረም፡፡ እኔም ለጊዜው ነበር እንጂ ያን ያህል ቦታ አልሰጠሁትም። ምክንያቱም እኔ የማስበውና የማልመው ነፃ የፈጠራ ሥራ የምሠራበት የግል ስቱዲዮ እንዲኖረኝ ብቻ ነበር››
ሠዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ደግሞ በተመሳሳይ ዘመን፤ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ በባህል ፖሊሲ ጥናትና አፈጻፀም ክትትል መምሪያ ጊዜያዊ አስተባባሪ ነበሩ፡፡ እሳቸውም ሠላሳ ዓመት በሃሳብ ወደ ኋላ ተጉዘው ትውስታቸውን አወጉኝ።
‹‹በ1968 ዓ.ም. ዋዜማ ላይ የባህል ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትርና ከሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ከተውጣጡ ባለሙያዎች ጋር የመስከረም ሁለት በዓልን ለማክበር እየተዘጋጀ ነበር፡፡ በበአሉ ላይ አርቲስቶች ሥራቸውን የሚያቀርቡት በክፍት መኪና ላይ በተሰራ መድረክ ነበር። ሚኒስቴሩ የፈለገን የተንቀሳቃሽ መኪናውን መድረክ የሚሸፍን ገጸ ሥዕል (Float) እንድንሰራ ነበር። በዚህ መሰረት፤ እኔና ሠዓሊ ታደሰ መስፍን በጋራ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ትንሿ አዳራሽ ከጀርባ ሆነን ሥራውን ሠርተን አስረከብን፡፡ መስከረም 2 ቀን 1968 ዓ.ም. በቀድሞ አብዮት አደባባይ በአሁኑ መስቀል አደባባይ ለእይታ ቀረበ፡፡ የሠራነው ሥራ በተመልካቾችና በባለሙያዎች የተወደደ ሥራ እንደነበር ተነገረን፡፡
ሥራውን ሰራን እንጂ ሁለታችንም ወደ አብዮት አደባባይ፤ (መስቀል አደባባይ) አልሄድንም ነበር፡፡ ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ ‹ጊዜውን እርግጠኛ አይደለሁም› … እኔና ሠዓሊ ታደሰ መስፍን የሰራነው ሥራ፣ በሃያ አምስትና በሃምሳ ሳንቲሞች ላይ ወጡ። በጣም ገረመኝ፡፡ ብዙ ሰዎች ‹እናንተ የሰራችሁት ሥራ በሳንቲሞች ላይ ታትሞ ወጣ› ብለው አድናቆት አጎረፉልን።››
‹‹የኢትዮጵያ የብር ኖቶችና ቅንስናሽ ሳንቲሞች ከተቀየሩ በኋላ ከሠዓሊ ታደሰ መስፍን ጋር ስለ ጉዳዩ አውርተን ነበር። ሥዕሎቹን ወደ ሳንቲሞች፤ በክብ ቅርፅ የቀየረውን ባለሙያ ሁለታችንም ለማወቅ አልቻልንም›› አሉ፡፡
ሠዓሊ ታደሰ መስፍን፤ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተደረገለት ቃለ መጠይቅ፤ የሠላሳ ዓመት ምስጢሩን አወጣ … ‹‹በተንቀሳቃሽ ምስል ከሠዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ጋር ሰርተናቸዋል። ወደ ሳንቲም እንዲቀየር የሠራኋቸው ግን እኔ ነኝ፡፡ በ1969 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሳንቲሞችና የብር ኖቶች ከወጡ በኋላ ግን እኔ ነኝ ለማለት አልደፈርኩም» በማለት።
*   *   *
ሠዓሊ ታደሰ ‹አገራዊ ምስጢር እንዲጠብቅ ከደርግ ጽሕፈት ቤት የተላለፈለትን ጥብቅ ትዕዛዝ ማክበሩ ግድ ነበር፡፡ ይሁንና ሥራዎቹ በሳንቲሞችና በብር ኖቶች ላይ ታትመው ከወጡ በኋላ ‹‹የኔ ናቸው» ለማለት አለመድፈሩ ግን ጥያቄን አጫረብኝ። ‹‹ለምን ይሆን?» ስል ጠየቅኩት።
‹‹ደርግ ጽሕፈት ቤት ተጠርቼ ትዕዛዝ ስቀበል፤ ‹ይህንን ሥራህን ለጓደኛህ፣ ለቤተሰቦችህ፣ ለራስህም ሆነ ለእግዚአብሔር እንዳትናገር፡፡ የምትሠራው ሥራ ከባድ ሀገራዊ ምስጢር ነው፡፡ ይህንን ትዕዛዝ ተላልፈህ ብትገኝ አብዮታዊ እርምጃ እንደሚወሰድብህ ሕሊናህም ያውቀዋል› ተብያለሁ፡፡ በዚህ መሠረት እንኳን ለጓደኛዬ፤ ለሙያ አጋሬ፤ ለሠዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ይቅርና ለእግዚአብሔር እንኳን አልተናገርኩም» በማለት ምላሹን ሰጠኝ አርቲስቱ …
ጥቂት ስንጨዋወት ቆይተን፣ በስተመጨረሻ ሠዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ማጠቃለያ ሀሳብ ሰነዘሩ፦
‹‹አንድ ሳንቲም፣ አምስት ሳንቲምና አሥር ሳንቲም ላይ ያሉ ምስሎችን የሠሩ የምገምታቸው ሠዓሊያን አሉ፡፡ እነርሱን እንደኛ ፈልገህ፤ በርብረህ አናግራቸው፡፡ አንደኛ ሠዓሊ ቦጋለ ይመስለኛል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ወንድማማቾቹ አሰፋ የማነብርሃንና ሰረቀ የማነብርሃን ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሦስተኛው ግምቴ ያልታወቀ ሠዓሊ ሊሆን ይችላል፡፡ ፕሮግራምህ አየር ላይ ከዋለ በኋላ ‹እኔ ነኝ፣ እኛ ነን› ብለው የሚመጡ ሠዓሊያን ይኖራሉ›› አሉና ለነገ የማያድር የቤት ሥራ ሰጡኝ፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ቢሮ አመራሁና አንጋፋው ሠዓሊ ቦጋለ በላቸውን ስለ ጉዳዩ አናገርኳቸው። ‹‹በኢትዮጵያ የብር ኖቶችና ቅንስናሽ ሳንቲሞች ላይ የጥበብ አሻራ የለኝም። ድርጅታችን ግንቦት 1 ቀን 1978 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሳንቲሞች መታሰቢያ አምስት ዓይነት ቴምብሮች አሳትሞ አሰራጭቷል። የቴምብሮቹ ሥዕሎች በሙሉ የእኔ ናቸው።›› ሲሉ ነበር በአጭሩ ምላሻ የሰጡኝ፡፡ ወንድማማቾቹ፤ ሠዓሊያን አስፋ የማነብርሃንና ሰረቀ የማነብርሃን አራት ኪሎ ቅድስተ ማርያም ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ስቱዲዮ ነበራቸው። የሙያ አጋሮቻቸው፤ ወንድማማቾቹ - የጥበብ ፈርጦች እንደነበሩ ይመሰክራሉ፡፡ የወንድማማቾቹን አድራሻ፤ ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ ያልፈነቀልኩት ድንጋይ አልነበረም። ከሠላሳ ዓመታት በፊት የነበረውን መረጃ ለመተንተንና ወንድማማቾቹንና ቤተሰቦቻቸውን ለማግኘት ያደረግሁት ጥረት ግን አልተሳካም። ‹‹በሁላችንም ኪስ ውስጥ የሚገኝ ሰው›› የተሰኘው የቴሌቪዝን ፕሮግራም አየር ላይ ከዋለ በኋላ፣ እንደጠበቅነው ‹እኛ ነን› ብለው የመጡ ሠዓሊያን አልነበሩም፡፡ ወንድማማቾቹን ሠዓሊያን ‹እናውቃቸዋለን፣ እዚህ ናቸው› የሚል ሰውም ብቅ አላለም፡፡
(በቅርቡ ለህትመት ከሚበቃው የጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን "የጉዞ ማስታወሻ" መጽሐፍ )



Read 2354 times