Saturday, 19 September 2020 13:36

በህገወጥ የሐዋላ አገልግሎት አገሪቱ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ታጣለች

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(6 votes)

  በአገሪቱ ከባንክ ስርዓት ውጭ ከ113 ቢሊዮን ብር በላይ ይንቀሳቀሳል
                          
          በአገር ውስጥና በተለያዩ የአለማችን አገራት በግለሰቦች በህገወጥ መንገድ የሚሰጡ የሐዋላ አገልግሎቶች አገሪቱን በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እንደሚያሳጣት የተጠቆመ ሲሆን ይህም የአገሪቱን ኢኮኖሚ በእጅጉ እንደሚጐዳው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡
በአገሪቱ ከባንክ ስርዓት ውጪ የሚንቀሳቀሰው ገንዘብ መጠን ከ113 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል ተብሏል፡፡
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶ/ር ተካልኝ ፋንቱ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ በህገወጥ መንገድ የሚሰጡ የሐዋላ አገልግሎቶች አገሪቱን ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ የሚያሳጡ ሲሆን በአገር ውስጥ ከሚደረጉ የጥቁር ገበያ ምንዛሬዎች ይልቅ በውጪ አገር በግለሰቦች የሚሰጡ የሐዋላ አገልግሎቶች በአገሪቱ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳሉ ተብሏል፡፡
በህገወጥ መንገድ የሐዋላ አገልግሎት የሚሰጡና የፈረጠመ ክንድ ያላቸው በርካታ ግለሰብ ባንኮች በመላው አለም አገራት የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ አገራትም መካከል አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ ካናዳ፣ ኖርዌይ፣ ዱባይና ሳውዲ አረቢያ ይጠቀሳሉ፡፡
በአሜሪካ ዋና ዋና ከተሞች የሐዋላ አገልግሎት የሚሰጡና በየዕለቱ እጅግ በርካታ ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱ አያሌ ግለሰቦች መኖራቸውን የጠቆሙን በአሜሪካ ሜሪላንድ ከተማ ነዋሪ ኢትዮጵያዊ፤ እንደነገሩን፤ በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች ውስጥ በስፋት የሚታወቁና በየዕለቱ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱ ሐዋላ መንዛሪዎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ መንዛሪዎች አገር ውስጥ የተደራጁና ከእነሱ ጋር በቅንጅት የሚሰሩ አዲስ አበባ ውስጥ ቢሮ ከፍተው የሚንቀሳቀሱ መንዛሪዎች ይገኛሉ፡፡
በመላው የአሜሪካ ከተሞች የሚኖር አብዛኛው ኢትዮጵያዊም በህጋዊ ባንክ በመላኩ የሚያጣትን አነስተኛ ጭማሪ በማየት፣ ወደነዚህ ህገወጥ የሐዋላ አገልግሎት ሰጪዎች በብዛት ይመጣል ብለዋል፡፡
በስዊድን ጉቱንበርግ ከተማ ውስጥ ነዋሪ የሆኑት ሌላ ኢትዮጵያዊ እንደነገሩን፤ ስዊድንን ጨምሮ በመላው የአውሮፓ አገራት በህገወጥ መንገድ የሐዋላ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙና በየዕለቱ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች በአብዛኛው የላኪነት ፈቃድ አውጥተው የባልትና ውጤቶችን ወደ የአገራቱ የሚወስዱና የሚሸጡ ሲሆን የባልትና ውጤቶች መሸጫ ድርጅቶቻቸውን የሐዋላ አገልግሎት ለመስጠት ይጠቀሙባቸዋል ብለዋል፡፡
በየዕለቱም በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ያንቀሳቅሳሉ ይላሉ፡፡ ከዋና ዋና የሐዋላ አገልግሎት ሰጪዎቹ በተጨማሪ አገልግሎት ፈላጊዎችን የማያገናኙና የኮሚሽን ክፍያ የሚከፈላቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ደላላዎችም በድርጊቱ እንደሚሳተፉ እኚሁ ምንጫችን ጠቁመውናል፡፡
ዱባይን ጨምሮ በተለያዩ የአረብ አገራትም በተመሳሳይ መንገድ የሐዋላ አገልግሎት ሰጪ የግለሰብ ድርጅቶች እንደ አሸን መፍላታቸውንና ከፍተኛ ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱ መሆኑን የጠቆሙን ምንጮች፤ እነዚህ ህገወጥ የሐዋላ አገልግሎት ሰጪዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በአገር ውስጥ ከባንክ ውጪ ይዘው እያንቀሳቀሱ  በመሆኑ መንግስት በብር ለውጡ ሳቢያ ይህንን በሚሊኖች የሚቆጠር ገንዘብ ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆን ያደርገዋል ብለዋል፡፡ ይህ ደግሞ ህገወጥነትንና በህገወጥ መንገድ የተሰበሰበ ሃብትን ጥቅም የሚያሳጣ በመሆኑ ሊደገፍ የሚገባ ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡
እነዚህ ሕገወጥ የሐዋላ አገልግሎት ሰጪ ግለሰቦችና ድርጅቶች በሚገባ የሚታወቁ በመሆኑም መንግስት በህገወጦቹ ላይ ጠንካራ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባም ምንጮች ይገልፃሉ፡፡
ከአዲሱ የብር ኖት ለውጥ ጋር በተያያዘ በእነዚህ በህገወጥ የሐዋላና የገንዘብ ምንዛሪ አገለግሎት በሚሰጡ የአገር ውስጥና የውጪ አገር ተቋማትን ለመቆጣጠር እየተወሰደ ስላለው እርምጃ ማብራሪያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የብሔራዊ ባንክ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አቤል - መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡   


Read 19700 times