Saturday, 19 September 2020 13:02

አለመረጋጋት የውጭ ኢንቨስትመንት ላይ ተጽእኖ አሳድሯል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

የምርጫ መራዘምና የፖለቲካ አለመረጋጋት የፈጠረው ውጥረት በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ያሰቡ ኢንቨስተሮች ከውሣኔ ላይ እንዳይደርሱ እንቅፋት እየሆነ መምጣቱን “ሙዲስ” የተሰኘው የአሜሪካ የፋይናንስና ኢንቨስትመንት ምርምር ማዕከል አስታውቋል፡፡
በአለምአቀፍ ደረጃ በሚሰራቸው ፋይናንስና ኢንቨስትመንት ተኮር ምርምሮች ከአለም ሦስት ዋነኛ ተጽእኖ ፈጣሪ ተቋማት አንዱ የሆነው “ሙዲስ” ከሰሞኑ ባወጣው ሪፖርቱ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ምርጫን ማራዘሙና የፖለቲካ አለመረጋጋት የፈጠረው ውጥረት ኢንቨስት ሊያደርጉ ያቀዱ የውጭ ኢንቨስተሮችን ከመጨረሻው ውሣኔ ላይ እንዳይደርሱ እያደረገ ነው ብሏል፡፡
ባለፈው አመት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶችና የፖለቲካ አለመረጋጋት ያስከተለው ውጥረት የኢትዮጵያን ቀጣይ የፖለቲካ ሁኔታ አስጊ ያደርገዋል ብሏል - ሙዲስ፡፡
በህዳሴ ግድብ ጉዳይ ከግብጽና ሱዳን ጋር ስምምነት ላይ አለመደረሱ፣ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ የተመናመነ መሆኑ እንዲሁም የአሜሪካ መንግስት ለሀገሪቱ ከሚያደርገው ድጋፍ ከፊሉን መቀነሱ የውጪ ኢንቨስተሮች ውሣኔ ላይ ተጽእኖ ያሳድራሉ በሚል ተጠቅሷል በሪፖርቱ፡፡
“ሙዲስ” የተሰኘው ተቋም በተጨማሪም በሀገራት ብድር ጉዳይ ላይ ምርምሮችን በማድረግ ሪፖርት የሚያወጣ ሲሆን አይኤምኤፍን ጨምሮ በርካታ ለጋሽ ሀገራት የተቋሙን መረጃ መሠረት በማድረግ ከሀገራት ጋር በብድር ጉዳይ ላይ የሚኖራቸውን ግንኙነት እንደሚወስኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡



Read 746 times