Print this page
Saturday, 12 September 2020 15:15

ከልሂቃን አንደበት

Written by 
Rate this item
(4 votes)

     “….በዓለም ላይ በርካታ ሰዎች አሜሪካ የምድር ገነት ናት ብለው ያስባሉ፡፡ በአሜሪካ ያሉቱ ግን ፈጽሞ እንደዚያ ዓይነት ሃሳብ የላቸውም፡፡ የሌላ አገር ዜጎች ወደ አሜሪካ ለመግባት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ ደቡባዊ የአገሪቱ መግቢያ ቢከፈት፣ ነገ ጠዋት 2 ሚሊዮን ሰዎች ወደ አሜሪካ ይጐርፋሉ፡፡ ለምን? አገሪቱን ገነት አድርገው የሚቆጥሩ አያሌዎች ናቸው፡፡ እዚህ አሜሪካ የምትኖሩ ግን ፈጽሞ ገነትን እያጣጣምን ነው አትሉም፡፡  ምክንያቱስ? ገነትና ሲኦል መልክአ ምድራዊ ሥፍራ አይደለም፡፡ ገነትና ሲኦል ራሳችሁ የምትፈጥሩት ጉዳይ ነው፤ በአዕምሮአችሁ፡፡ በምድር ላይ ህይወታቸውን ሲኦል የሚያደርጉ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሰዎች አሉ፡፡ እዚህ ምድር ላይ ገነት ያላችሁ መስሎ ከተሰማችሁ፣ ወደ መንግስተ ሰማያት ለመግባት የምትመኙ ይመስላችኋል?! ለምን ብላችሁ!!....”
 (ሳድህጉሩ፤ህንዳዊ ሚስቲክ፣ባለ ርዕይና ደራሲ)
 “…በዚህ ምድር ላይ የሰው ልጆች ትልቁ ችግር፣ ሁልጊዜ እኛ ብቻ ትክክል ነን ብለው ማሰባቸው ነው፡፡ በዓለማችን ላይ የሁሉም ቅራኔዎች ወይም ግጭቶች መነሻ “እኔ ትክክል ነኝ፤ አንተ ግን ስህተት ነህ” የሚለው እምነትና አስተሳሰብ ነው፡፡ አይደለም እንዴ? “እኔ የማምነው ትክክል ነው፤ አንተ የምታምነው ስህተት ነው” የሚለው ሙግት፣ የሁሉም ችግሮች መነሻ ነው፤ በቤተሰብ ይሁን በማህበረሰብ አሊያም በመላው ዓለም፡፡ ከሁሉም በፊት ማወቅ ያለባችሁ …የያዛችሁት እምነት የራሳችሁ (ኦሪጅናል) አለመሆኑን ነው፡፡ ከወላጆቻችሁ ወይም ከማህበረሰባችሁ የወረሳችሁት ነው፡፡ እናታችሁ ወይም አባታችሁ አሊያም ሌላ ሰው ነው እናንተ ውስጥ ያሰረፀው፡፡ ስለዚህ እውነቱ ላይ ለመድረስ የምትሹ ከሆነ… መጀመሪያ ማረጋገጫ ከማታገኙለት እምነታችሁ መፋታት ይኖርባችኋል፡፡ ያኔ ነው ሃቁን የምታገኙት…”                                            
(ሳድህጉሩ፤ህንዳዊ ሚስቲክ፣ባለ ርዕይና ደራሲ)
“…ፍርሃት፣ ቁጣና ተስፋ ማጣት የሚወለደው ከተሳሳተ አተያይ ወይም ግንዛቤ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ስለ ራሳችንና ስለ ሌሎች የተሳሳተ አተያይና ግንዛቤ ይኖረናል፡፡ ይሄ ደግሞ የግጭት፣ የብጥብጥና የጦርነት መነሻ ነው፡፡ ጥላቻንና ግጭትን ለማስወገድ ብቸኛው መንገድ፤ ራስን በሌላው ጫማ ውስጥ አድርጐ የሌላውን ስሜትና ሁኔታ ለመረዳት መሞከር ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ጥልቅና ልባዊ አድማጭ መሆንን ይጠይቃል፡፡ እናም ተበደልኩ የሚለውን ወገን እንዲህ ብለን ማናገር ይገባናል፡-- “ውድ ወገኔ፡- ብዙ መሰቃየትህን እናውቃለን፡፡ ነገር ግን ችግርህንና ስቃይህን በቅጡ ሳንረዳ ቀርተናል፡፡ የበለጠ ስቃይ እንዲደርስብህ ፍላጐታችን አይደለም፡፡ ይልቁንም ፍላጐታችን በተቃራኒው ነው፡፡ እናም እባካህን… ስለ ስቃይህና ችግርህ በደንብ ንገረን፡፡ ስለ ሁሉም ነገር በጥልቀት ለማወቅና ለመረዳት እንሻለን…; በእንዲህ አይነት የፍቅር ቋንቋ ነው መጀመር ያለብን፡፡ ንግግራችን ከልብና ከምር ከሆነ፣ እነሱም ልባቸውን ከፍተው ስቃያቸውን ያጋሩናል፡፡ በዚህ ልባዊ የማድመጥ ሂደትም ስለ ራሳችንና ስለነሱ አተያይ ብዙ ልንማር እንችላለን፡፡ ይሄ ነው ትክክለኛውና ብቸኛው ሽብርተኝነትን ማስወገጂያው መንገድ፡፡…”
ቲክ ናት ሃን
(የቡድሃ መነኩሴና የአያሌ መፃሕፍት ደራሲ)
“…ትላንትናችሁ የዛሬውንም ሆነ የነገውን ህይወታችሁን እንዲቆጣጠር አትፍቀዱለት፡፡ የትላንትናውን ክፉ ሁሉ እርሱት፡፡ ያለፈውን ስቃይና ህመማችሁን አሽቀንጥራችሁ ጣሉት፡፡ ይህን በማድረጋችሁ…የነገ ህይወታችሁን ከብልሽት ትታደጉታላችሁ፡፡ ያለፈውን ጨለማ ዘመን ወደ ኋላችሁ ትታችሁት ተሻገሩ፤ የመጪውን ብሩህ ዘመን ብርሃን እንዳይጋርድባችሁ፡፡ ያለፈው አንድ ጊዜ አልፏል፡፡ ጉዳዩ ኢ-ፍትሐዊ፣ አረመኔ ወይም በጭካኔ የተሞላ አሊያም ደግሞ ምንም ነገር ሊሆን ይችላል፡፡ ዛሬ ጉዳዩን ማንሳት ግን አንድም በጐ ውጤት አያመጣላችሁም፡፡ አንድ ግለሰብ ወይም ቡድን አንዳች ክፉ ነገር ሰርቶባችሁ ከሆነ፣ ያንን ማሸነፊያው ብቸኛው መንገድ ጉዳዩን መርሳትና ወደፊት መቀጠል ነው፡፡ በጥላቻ ውስጥ የምትዳክሩ ከሆነ ግን አሸናፊዎቹ እነሱ ይሆናሉ - ክፉ አድራጊዎቹ፡፡ በተበዳይነት ትርክት ውስጥ የምትኖሩ ከሆነም ድሉ የነሱ ነው፡፡ እናንተ ማሸነፍ ከፈለጋችሁ… መጪውን ዘመናችሁን በመገንባት ላይ ብቻ አተኩሩ፡፡ ያንንም ዛሬውኑ ጀምሩት፡፡ አሁኑኑ!! ያለፈውን ዘመን ሸክም ከትከሻችሁ ላይ አራግፉ፡፡ ያለፉና አሁን የሌሉ ኹነቶች፤ ይህቺን ቅጽበት በደስታ ከመኖርና ከማጣጣም እንዲያግዷችሁ አትፍቀዱላቸው፡፡;
(ከ#Fearless soul” ዩቲዩብ)


Read 2101 times
Administrator

Latest from Administrator