Monday, 14 September 2020 00:00

ቀታሪ ግጥም

Written by  ከአንለይ ጥላሁን ምትኩ
Rate this item
(1 Vote)

  ደቂቀ ብርሃንን----
ውበት----ፍቅር-----እውነትን
ለመገላገል ነው፣ የዘወትር ምጤ፡፡
(በደበበ ሰይፉ፤ አይደለም (የዘወትር ምጤ)
ግጥም የአደይ አበባ ናት፤ ብቅ ስትል ነፍስ ታለመልማለች፡፡ ልብ ይፈካል፡፡ ልቦናም ብሩህ ይሆናል፡፡ ታዲያ ለአጠቃላዩ እውነት ማሰሪያ፤ መጠቅለያ ናት፡፡
የግጥም ውበት በውስጣችን ይነግሳል፡፡ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው፤ “ከሥፍር ባሻገር” ግጥሙ ያሰፈረውን  ቀንጭበን መጥቀስ ተገቢ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ እነሆ፦
     “እሱ ውበት ነው እሱ ውበት
       በፍኝ እማይሠፈር
       እማይመተር ፤
       በስንዝር እማይለካ
       እማይነካ
       እማይከነዳ ነገር እማይከነዳ
       የውበት ረቂቅነት  ዕዳ
       ችግር
        የሥፍር ባሻገር ምሥጢር፡፡”
(ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው፤ ውስጠት፤ ፲፱፻፹፩፤ ገፅ 59)
የሰው ልጅ የሚያሸበርቀው በእሷ ነው፤ በግጥም፡፡ ሙሉነትን ከመላበሱ ባሻገር  አድራጊም፣ ፈጣሪም ነው፡፡ የማይጠግነው የህይወት መልክ ተፈልጎ አይገኝም፡፡ ለጨለማ ብርሃንን ይፈነጥቃል፡፡ ለታመመ ፈውስ ይሆናል፡፡ ለፅንፈኛ አካሂዶች ሁሉ ሰቀቀን ነው፤ ግጥም፡፡ የተጣመመ ያቃናል፡፡
በእርግጥ በግጥም ቅፅበት ዘላለማዊ ሆኖ ይቀረፅበታል፤ ይህም ነው የከያኒ ብቃቱ፡፡ የተፈጥሮን ልዩነት ያዋህዳል ወይም ሙሉውን ህልውና ባዶ ያደርገዋል፡፡ እናም የሰው ልጅ አዕምሮ ጅምናስቲክ የሚሰራው በግጥም ይመስለኛል፡፡ በለዚህም ነው፤ “አለሁም የለሁም” አጠይቆት በጥበብ የሚስተናገደው፡፡
[ቀታሪ÷ስሩ ቀተረ ነው፡፡ ቀተረ÷እኩል ለመሆን ተከታተለ÷ተቀታተረ÷ተመለካከተ÷ተወዳደረ÷ተተካከለ÷ተመዛዘነ÷ተፈካከረ÷ተፈላለገ (አስ) ከባለ ቀትር አትቀታተር፡፡ ( ከሣቴ ብርሃን ተሠማ÷ የዐማርኛ መዝገበ ቃላት÷ገፅ ፫ ፻ ፹ ፬÷2008 ዓ.ም)  ግጥም ምንጩ ህይወት ነውና (ቋንቋው (መንገዱ) አዕምሮን፣ ስሜቱ ልብን እና መልዕክቱ ልቦናን ይቀትራል።) አዕምሮን፣ ልቦናንና ልብን የቀተረ ከምናብ የሚፈለቀቅ የፀነነ የጥበብ ውጤት ነው፡፡ መቀተሩ ከልማድ ጋር የሚደረግ ግብግብ ነው። ፈጠራ ደግሞ ልማድን መሻገር ይጠይቃል። ከልማድ ያልተሻገረ ግጥም ነፃ አያወጣም፡፡ አይታኘክም - የተመጠጠ ነውና፡፡]
                          * * * 11
                 አይደለም (የዘወትር ምጤ)
አይደለም ለክብረት ለንዋይ ተዳምሮ
አይደለም ለሹመት ለተጫፍሮ ኑሮ
አይደለም ለዝና ለጠፊ ውሎ አድሮ፤...
ለትሁት ሕይወት ነው፣ እኔ መሯሯጤ
በዘልማድ መንገድ ጉዞ አለመምረጤ፤
ደቂቀ ብርሃንን____
ውበት____ፍቅር____እውነትን
ለመገላገል ነው፣ የዘወትር ምጤ፡፡
ይኸው ነው መስቀሌ
ይህም ነው አክሊሌ
ይኸው ነው ድክመቴ
ይህም ነው ብርታቴ፡፡
(ደበበ ሰይፉ፤ የብርሃን ፍቅር (ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ)፤ ፳፻፲ ዓ.ም፤ ገፅ 191)
ግጥሙ ረቂቅ ሀቅ ያስሳል፡፡ ስውር መልኮችን ያምጣል፤ ይወልዳል እንጂ አይፈልጋቸውም፡፡ ይቀርፃቸዋል፡፡ በምናቡ ካማጠ በኋላ የታየውን ሀቅ ይጨብጣል፡፡ አይሻም፡፡ ያውሳል እንጂ፤ አይዋስም፡፡ ስለሆነም “ ውበት___ፍቅር____እውነት” ምንጫቸው ግለሰብ እንደሆነ አስረግጦ ይነግረናል፡፡ እነሆ፦
“ደቂቀ ብርሃንን___
ውበት____ፍቅር____እውነትን
ለመገላገል ነው፣ የዘወትር ምጤ፡፡” በማለት የራሱን የህይወት ማዕዘናት ለመቅረፅ መድከሙን አስረግጦ ይነግረናል ፤ ተራኪው፡፡
በርግጥ ምን አነሳሳው?  ካልን ደግሞ “ግላዊ ተብሰልስሎት” መሆኑን እንረዳለን፡፡ ይህ ተብሰልስሎት (ተመስጦ) የላቀ የህይወት መርህ ይፈነጥቅለታል ፤ የኑሮን መልኮች ደርድሮ ዋጋቸውን ካነፃፀረ በኋላ የደረሰበት ሐቅ ነው፡፡ ድምዳሜው እንደሚከተለው ተሰናኝቷል፡፡
“ለትሁት ሕይወት ነው፣ እኔ መሯሯጤ
በዘልማድ መንገድ ጉዞ አለመምረጤ፤”
በርግጥም የትህትናው መሰረቶች “ውበት፣ ፍቅር እና እውነት” መሆናቸውን እንገነዘባለን። እነዚህ ላይ በመመስረት የላቀ ሰብዕና ባለቤት መሆን የሚቻለው በከፍተኛ ምጥ፤ በዘወትር ተብሰልስሎት መሆኑን እንረዳለን። በእርግጥም ፈረንጆች፤ ”Humility is the mother of all virtues” (ትህትና የፀጋዎች ሁሉ እናት ናት) የሚሉት --ለዚህ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ትሁት ሰው የተጠያቂነት መንፈስ ስለሚያድርበት አይታበይም፡፡ ዋጋን ያውቃል። የድርጊቶቹ  ውጤት ምንም ይሁን ምንም ይቀበላል፤ ሀላፊነት ይወስዳል፡፡ ለሰው ያለው ፍቅር  በምንም አይተካም ፤በመሆኑም የላቁ ተግባራትን ይፈፅማል፡፡ ያፀድቃል፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ይሆን ዘንድ የደራሲያንን ሰብዕና በሚመለከት “በመድበለ ጉባኤ” መፅሐፍ ላይ የሰፈረውን የዶ/ር ዮናስ አድማሱ’ን አስተያየት ልጥቀስ “በመጨረሻም፣ ደራሲያን ትሑት ሁነው ትሕትናን የሚያስተምሩ መሆን አለባቸው የሚል ጽኑዕ እምነት አለኝ፡፡...” (ገፅ 19)
የግጥሙ የመጨረሻ አንጓ የሁሉም ነገር ማሰሪያ ነው፡፡ የህይወት ግብ ተቃርኖ መሰረቱ ትህትናችን (ሰብዕናችን) የተገነባባቸው አምዶች መሆናቸውን ያስረግጣል፤ ብርታትና ድክመት፣ መስቀልና አክሊል የሚሉት ቃላት የተሸከሙት ይኸው ነው፡፡ የህልውና ተቃርኖ ምንጭ ናቸው። መለያ ጌጥ፣ አዳኝ ሀይል፣ ብርታት፣ ነፃ መውጣት እና  ሀይል መላበስ “ይኸው ነው መስቀሌ / ይህም ነው አክሊሌ” በሚሉ ስንኞች ተወክለዋል--ተገልፀዋል፡፡ እነዚህ የውስጥን ምልከታ፤ የግለሰቡን እምነትና እውነት የሚጠቁሙ ናቸው፡፡ ህሊና “የሚሰራባቸው” ጡብ ናቸው፡፡ ወደ ውስጥ የመመልከት ውጤቶች ናቸው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የማንነት ሚዛን ከውጭ አካል ሲሰነዘር (ሲመዘን) ተቃራኒ ነገሮችን እንደሚያስተናግድ የሚጠቁሙት ስንኞች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፡፡ እነሆ፦
“ይኸው ነው ድክመቴ
ይህም ነው ብርታቴ፡፡”
በማለት ውጫዊ ፍርድ ይሰጣል፣ ይጠቁማል። ይህ ፍርድ ግለሰባዊ ፣ማህበረሰባዊ፣ ተፈጥሯዊና መለኮታዊ ሊሆን ይችላል፡፡ በግል (ተራኪው) የያዘው አቋም (የእውነት፣ የፍቅርና የውበት ምልከታ) በሌላ ወገን ዘንድ ሊያስነቅፈውም ሆነ ሊያስተቸው እንደሚችል ይጠቁማል፡፡
በስንኞቹ መጀመሪያ ተደጋግመው የሚገኙ ሀረጎች (አይደለም፣ ይኸው ነው፣ ይህም ነው) የራሳቸው የሆነ ኪናዊ ፋይዳ አላቸው፡፡ ከነዚህም መካከል የህይወትን መልከ ብዙነት ማመልከት (አንድም እንደዚህ...አንድም  እንደዚህ እንደ ማለት) በሌላ በኩል ደግሞ ለአፅንዖት (የስሜት ብርታትንና ፅናትን ለመጠቆም)  የገቡ ናቸው፡፡
የግጥሙ የመጀመሪያ አርኬ ሶስት ስንኞችን ያካተተ ሲሆን “ተራኪው”  ለንዋይ (ሀብት)፣ ለሹመትና ለዝና  ያለውን አመለካከት ያሰፈረባቸው ናቸው፡፡ ለውጫዊ ኑሮ (ህይወት፣ ዓለም) ዋጋ መስጠት የሚያስከትላቸውን ውጤቶችንም ጠቁሟል፡፡ ሁሉም  ጠፊ፣ አላቂና አጫፋሪነት ናቸው --ይለናል፡፡
ግጥሙ የአራት አርኬዎች ውህደት (ኪናዊ ስንስል) ውጤት ነው፡፡ የመጀመሪያው አርኬ በሰው ልጅ ውጫዊ ዓለም ላይ ሲያተኩር፣ ሁለተኛው አርኬ ደግሞ በሰው ልጅ  ውስጣዊ  ዓለም (የላቀ ሰብዕና) ላይ ያተኩራል፡፡ ያፀድቃል፡፡ ያለመልማል፡፡ እንዲሁም ሶስተኛው አርኬ የግለሰቡ አቋም (ምርጫው)፤ የማንነት መስፈሪያው መሆኑን ያስረግጣል፤ “እኔ እንዲህ ነኝ!“ እንደ ማለት --ነው፡፡ የመጨረሻው አርኬ ደግሞ የጠንካራና የደካማ ጎኔ ምንጭ ይህ አቋሜ (ግንዛቤዬ) ነው --ይላል፤ ተራኪው፡፡
“የዘውትር ምጤ” ዜማዊ ግጥም ነው። ይሞግታል፡፡ መስቀልህ፣ አክሊልህና ድክመትህም ሆነ ጥንካሬህ የሚመሰረቱት ፈቅደህ ባፀደቅሀቸው የራስህ እውነቶች፣ እምነቶችና ውበቶች ላይ ነው -- የሚል ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም ሁላችንም የራሳችን እውነቶች ባሪያዎች ነን፤ ለማለት ነው፡፡
አሰኛኘቱ የተስተካከለ ነው፡፡ ከሰፊ ዓለም ወደ ጠባብ ዓለም የሚደረገውን የሰብዕና ቀረፃ ይነቅፋል፤ ይደልዛል፡፡ እምቅና ጥልቅ ሀሳቦችን አዝሏል፡፡ የግጥሙ ውበት ያማልላል፡፡ ልክ እንደ አደይ አበባ ነው፡፡ የማይደበዝዝ ሀቅ ፣ ውበት ተሸክሟል፡፡
(መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልን !! እንኳን አደረሳችሁ!! ከሀገሬ የተፈጥሮ ውበት ፣ ፍንደቃ ...ከጋራ ሸንተረሯ ፍልቅልቅታ ብዙ እንማር!!!  አጥፊና ጠፊ እንደ ፀደይ ወቅት አሸብርቀው ተዋህደው ውበት የሚሆኑበት ጊዜ ይናፍቀኛል)
ከአዘጋጁ፡- ፀሐፊውን በኢ-ሜይል አድራሻቸው፦ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 572 times