Monday, 14 September 2020 00:00

የወፍዬ አምላክ አያሙሌን በወፍ በረር

Written by  በሥንታየሁ ዓለማየሁ
Rate this item
(2 votes)

  “..እስቲ እራሳችንን እንጠይቅ፤ ስንት ባለ ጥበብ በጥበታችን ገደልን፣ በስንቱ ንቃት ላይ በመዘንጋት እንቅልፍ ወደቅንበት ፣ በስንቱ ፍካት ላይ በጭካኔና ባለማወቅ ተጋደምንበት?”
         
        በዘመናት መካከል ከስንት አንዴ የሚፈጠሩ በመንፈስም በእውቀት ጥበብም ከፍታ ላይ የሚገኙ ድንቅ ሰዎች አሉ፡፡ ከነዚህ አይነት ሰዎች መካከል አንዱ ባለቅኔ ሙሉጌታ ተስፋዬ ነው ብንል ማጋነን አይሆንም፡፡ አያ ሙሌ ማለት ማህጸነ ለምለሟ ሃገራችን ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ጠቢባን አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ አያ ሙሌ ካረፈ እነሆ 16 ዓመት ሞላው፡፡ በ1996 ዓ.ም በያዝነው ወር በዚህ ሳምንት ነሐሴ 29 ቀን ነበር ያረፈው፡፡  እንደ ሙሉጌታ ያሉት ብርሃናት በሰው ልጅ ልብ ውስጥ ዘላለማዊ ሆነው ይኖራሉ እንጅ ከቶውንም ሞተዋል የሚል ቅጥያ ከስማቸው ጎን አይጻፍም፡፡ አያ ሙሌም ቢሆን ሲናገር “የኔ ሃገርና መዳረሻ የሰው ልጅ ልብ ነው” ማለት ያበዛ ነበር፡፡ የተናገረውን ነው ሆኖ ያለፈው፤ ይኸው እኛም ለዝንታለም በልባችን ሙዳይ ላይ ስላተምነው ባሰኘን ቁጥር ያሻንን ያህል ከልባችን እየቀዳን ከጥበቡ እንምጋለን፡፡
በብዛት ባለቅኔዎች፣ ጥልቅ ሃሳብን እያነሱ ከፍ ባለ ስሜትና ቋንቋ መድበል የሚያሰናዱ ገጣሚዎች የሙዚቃ ግጥም ሲጽፉ አይስተዋልም፡፡ አያ ሙሌ ግን በሁለቱም የተካነ፣ እንደውም በመጨረሻ የእድሜ ዘመኑ አካባቢ ሙሉ በሙሉ ወደ ሙዚቃ ግጥም ያደላበት አጋጣሚ ነበር፡፡ ብዙዎቻችን ከምንወዳቸው ብዙ የሙሌ የሙዚቃ ግጥሞች መካከል ለዛሬ በሁለቱ ላይ ብቻ አያ ሙሌን ለማስታወስ ያህል በወፍ በረር እናያለን፡፡ ወፍዬ እና አደራ ልጄን የተሰኙትን፡፡
ወፍዬ እንደኔ አመለካከትና እንደኔ የእውቀት መጠን ምናልባትም በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ አይቼው ፣ ሰምቼው፣ ተረድቼው የማላውቀው አንዳች የሃሳብ ምጥቀትና ጥልቀት የተላበሰች ስራ ናት፡፡ ወፍዬ በአበበ ተካ ድምጽ አብባ እንዲህ ትንቆረቆራለች ....
……
ጭራ ጭራ የምታድረው (2)
ጭራ ለቅማ የምታድረው (2)
እንዴት አስናቀችኝ
ቀድማኝ ጎጆ ወጥታ ጎጆ አስተማረችኝ
ጎጇቤት ጎጆ እኔን ወፍዬ አስቀናችኝ
……..
ምነው ባደረገኝ
የሷ ጋሻ ጃግሬ
እንደምንም ብዬ እኔም ጥሬ ግሬ
ያገዳ ጎጆዬን ባቆምኳት ማግሬ
አጉል በቃኝ ላይል
አይን አይቶ ገምቶ
ወይ ሞልቶ ላይሞላ
ጆሮ አይችሉ ሰምቶ
እንዴት ጎጆ ይቅር
አርሶና ሸምቶ
……..
በዚህ ውስጥ ያለ አንዳች ትልቅ ምኞት አለ፣ ምኞቱ ሰው መሆን ነው ፣ ሰው የመባል መለኪያው ደግሞ መስፈርቱ ጎጆ መቀለሱ ፣ እራስን መቻሉ፤ አልፎ ተርፎም ለሌሎች ደጀን መሆኑ ነው፡፡ ይህንን ማድረግ አልተቻለም፤ ስላልተቻለ ደግሞ አንዳች ቁጭት አለ ...
እንዴት ጎጆ ይቅር
አርሶና ሸምቶ
የሚያስብል ቁጭት አለ፣ ስጋዊ ህመም አለ:: ከዚህ እልፍ ብለን ያየነው እንደሆነ ደግሞ መለኮታዊ ጥግም ይታከካል ሃሳቡ፡፡
ገመና ከታቹን የሳር ቤት ያማረሽ
ሚስጥረ መለኮት ማነው ያስተማረሽ (2)
ካፈር ክዳን ጎጆ መሬቱን ፈልፍሎ
ከሰማይ ቤት እጣሽ ማን በሰጠኝ ከፍሎ (2)
…..ይሄ አያ ሙሌ በጣም የሚወዳትን ቅድስት ድንግል ማርያምን የሚገልጽ ሃሳብ ይመስለኛል:: እራሱ ሙሉጌታ ተስፋዬ ሲናገር ወፍዬ ማለት፤ “እኔና ወላዲተ አምላክ፣ እኔና እናቴ፣ እኔና ብዕሬ ማለት ነው” ብሏል፡፡ እና ከላይ ያሉትን ስንኞች እንዳለው የወላዲት አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያም አወላለድና ነገረ ስራ የሚያትት ይመስለኛል፡፡ ሚስጥረ መለኮትን ተረድታ በማይገባት ስፍራ መውለዷንና ተራኪው ወዲህ በምድር የተነፈገውን ሰው ሰራሽ ጎጆ በመለኮት ሃይል ታግዞ ያሸንፈው ዘንድ ...
ከሰማይ ቤት እጣሽ ማን በሰጠኝ ከፍሎ
አላት፡፡
እኔን እኔን እኔን ይብላኝ (2)
እኔን አይኔን እኔን ይብላኝ (2)
የቀን ሰው ሌት አፈር
ልቤ እሩቅ አሳቢው
ቅርብ አድሮ ሲደፈር
ምን ነበር ቢቆጨው ጎጆ አጥቶ ከማፈር
………ከሞት በኋላ ሕይወት አለ ብሎ ለሚያምን አንድ አማኝ፤ እንዲህ ያለ ጸሎት መሰል ትካዜ፣ ስጋዊ ወመንፈሳዊ ኪዳን ማድረሱም አይቀርም፡፡ ይህንን ነው በዚህ የሚያወጋን፡፡
ፈጣሪዋን አምና ያፏን ጥሬ ሰጥታ
ለጭሮ አዳር ውሎ በዝማሬ ወጥታ
አዳኝ እንዴት ያጥቃት ፍርድና ዳኛ አጥታ
አጣው ነጣው ብላ እንደሰው ባይከፋት
ምፅዋት ባትለምን ትርፉን ባንደግፋት
ጎጆዋ ለቻላት ምን ነበር ባንገፋት
………
ታማ ትንፋሽ አጥሯት ደክማ ስታጣጥር
ማን ያቃናት ይሆን ውለታ ሳይቆጥር (2)
ወልዶ ማሳደጉን ብዙ ሰው ቢያውቅበት
ያፉን ማን ይሰጣል የጁ ሲርቅበት (2)
እህህ ወፊቱ እሁሁ ወፊቱ እህህ ወፍዬ እህህ ወፊቱ እህህ ወፍቱ (8)
ይህ ደግሞ የአንዲት ምስኪን ኢትዮጵያዊት እናት ሃቅ ነው፣ ትርክት ነው፣ ቁስል ነው፡፡ የራሱ የባለቅኔው እናትን ጨምሮ፣ የኔን፣ የናንተን፣ የነሱን እናቶች ልፋትና የሚመለስላቸው ውለታና መሰል ተግዳሮቶችን ነው፤ እህ ህ እያለ በዜማው ያስታመመው፡፡
 በአጠቃላይ
ወፍዬ ከሁለት ልጆቼ ቀጥላ ሦስተኛ ልጄ ናት የሚለው አያ ሙሌ ፤ ማንም አማርኛ ተናጋሪ ፍጡር በህይወት ዘመኑ ወፍዬን ቢያንስ አንድ ግዜ ሊሰማ ግድ አለበት ይላል፡፡ እውነትም ግድ እንዳለብን ማሳያ የሆነ ድንቅ ሃሳብ የተሸከመ ሙዚቃ ነው ለኔ፡፡ ወፍዬ ከሙዚቃም በላይ ነው፡፡ በህይወት ተክለ ሰውነት ላይ ያለን የፍትህ መጓደል በስንኞቹ መነፅር አሳይቷል ፣ ስለ ህይወት ውጣ ውረድና እንግልት ተርኳል ፣ ተመስገን ብሎ ስለ ማደር ሰማያዊ ህይወትን ስለ መሻትም አትቷል፤ ስጋዊ ወመንፈሳዊ ሃቅንና መተሳሰርን በምናቡ ርቀት አመላክቷል፡፡ ቅኔንና ሰውኛ ዘይቤን ከዜማ ጋር አብኩቶ በለሆሳስ አብልቶናል፡፡
ወፍዬ ላይ ካለችው እናት ቀጥላ ደግሞ የእናትነትን ጥግና ከፍታ፣ ድካምና ልፋት እንዲሁም እጹብ ድንቅ ስጦታ የሆነውን ልጇን፡ የህጻንን ሳቅና ትንፋሹን፣ ጠረኑን ሙሌ፣ በምን አይነት ውበት እንደገለጸው "አደራ ልጄን አደራ" እያለች በእንባ ታጅባ ብጽአት ስዩም ያዜመችውን እንመልከት፡፡
…አደራ እንግዲህ አደራ
አደራ ልጄን አደራ
ሆዴን ልጄን አደራ
ልጄን ሆዴን አደራ
ልጄን አደራ
(2)
...ባለቅኔና ገጣሚ ሲኮን ፣ በተለይም እንደ ሙሉጌታ ተስፋዬ ያለ ሰው ሲኮን ፣ እውነት ወዲያ ማዶ ካለ ከእርሱ ውጭ ከሆነ ገላ ላይ አይደለም የሚቀዳው፤ ከራሱ ከልቡ ውስጥ ትኩሳት እንጂ። ይሄ አደራ ልጄን የተሰኘው ሙዚቃም ሙሌ የገዛ ልጁን እያሰበ ፣ ከውስጡ መብሰልሰል ጋር እየተፋተገ ያኖረው መልዕክት ይመስለኛል። አያ ሙሌ ልጆቹን ትቶ እንደ ዲዮጋን በብቻው ዓለም ውስጥ ሲሰደድ፣ አቅሉ ግና ልጆቹን ያስታውስ ዘንድ ግድ ብሎታልና፣ እሱም ለታላቅ ጥበብ ተጠርቷልና፣ የልጆቹን ጉዳይ ለኛ አደራ ማለት ነበረበት፤ እንዲያም ነው ያደረገው በዜማ።
ደግ ነው መሰንበት እኔም እንደናቴ
ዘጠኝ ወር አርግዤ ተንበርክኬ አምጬ
ፈጣሪ አያልቅበት አይኔን ባይኔ አየሁት
ልጄን ሆድ አንጀቴን ከጎኔ አስቀምጬ
ያን ግዜ እንዳክርማ ስከፈል ለሁለት
ጭንቅ ጥብብ ስል ሽሉ ሲያጣድፈኝ
የት ይገኝ ነበረ የወላጅ አዋላጅ
አብሮኝ የሚሰቃይ አዝኖ የሚደግፈኝ
...እዚህ ዘንድ ደግሞ እናት የመሆንን ጸዳልና በልጅ ውስጥ ስለሚገኝ አንዳች ብርሃን ያትታል።
ዘጠኝ ወር አርግዤ ተንበርክኬ አምጬ
ፈጣሪ አያልቅበት አይኔን ባይኔ አየሁት
የሚለው አባባል ደግሞ ከስጋዊ መወለድም በላይ የሚዘልቅ ቅኔ አለው። ሰው ዘጠኝ ወር አርግዞ ልጅ ብቻ አይደለም የሚወልደው፣ ይልቁንስ ሃሳብም ይወለዳል፣ ጥበብም ይወለዳል፣ ለሃገር የሚበጅ ከፍ ያለ መንፈስም ያረግዟል። ምናልባት አይኔን ባይኔ አየሁት ሲል አንድም ለልጆቹ አንድም ፈቅዶና ወዶ ለሚኖርላት አሲያ ጨብራሬ እያለ ለሚጠራት ጥበብ ሊሆን ይችላል።
ወልደህ እየው ብሎ ወላጅ የመረቀው
ለልጅ ሲንሰፈሰፍ ያኔ ነው የሚያውቀው
እርብትብት ከንፈሩ ያንገቱ ስር ሽታ
ከሞትም ያድናል እንኳን ከበሽታ
..እዚህ ጋ ደሞ ቀጥ ብሎ መስማት ፣ መመሰጥ ግድ ይላል ፡ ስለ ልጅ ትንፋሽና ፈገግታ የወለደ ያውቀዋል።
እርብትብት ከንፈሩ ያንገቱ ስር ሽታ
ከሞትም ያድናል እንኳን ከበሽታ
የሚለው አገላለጽ የልጅን ሁለመና ጠረን ተወዳጅነት ፣ አምላካዊ በረከቱን ፣ የተፈጥሮን ልዩ ሚስጥር ፣ ልጅ የመሆንንና ልጅ የማግኘትን ልዩ ዕድል ያትታል። ይህን ካለ በኋላ ደግሞ በድጋሚ በግልጽ አደራ ይለናል፦
እንደሰው እስኪያልፍለት እንደምንም አስታውሱት
እንግዲህ ልጄን አደራ ሌላው ቢቀር ፊት አትንሱት
(2)
…….ተመልከቱልኝ የሃሳቡን ምጥቀት ፡ እንደ ሰው እስኪያልፍለት እንደ ምንም አስታውሱት ማለት ቀላል የሚመስል ነገር ከሰሩት ታላቅ ነገር ካልከወኑትም ከባድ ውርደት መሆኑን ያስገነዝባል። በሰው ዘንድ እንደ መረሳት፣ እንደ መዘንጋት ያለ ምን ነውር አለ? ምንም። ይህ እንዳይሆን ነው አደራ የሚለን ሙሌ። ከዛም እንዲህ አለ ሙሌ……
ሌላው ሁሉ ቢቀር ቢያንስ ፊት አትንሱት። ፊት መነሳትን አስቡት እስቲ ፣ መረሳትን አስቡት እስቲ፣ ከሰው መድረክ መወገድን አስቡት እስቲ፤ ይሄ ከገንዘብና ከቁስ እጦትም በላይ ነው፣ ይሄ ከመገፋትም ሁሉ መገፋት እኮ ነው። በተለይ እንደኛ ባለ ሁሉ ነገርን ተቀራርቦና ተሰባስቦ እገሌ ምን ይለኝ እየተባባለ በሚኖር ማህበረሰብ ውስጥ መረሳትና ፊት መነሳት ያለውን ዋጋ ሁላችንም እናውቀዋለን። ለዚህ ነው ዋናውን ነገር አትንሱት እያለ በዜማ መልክ አደራ ያለን ሙሌ።
ድምፃዊዋ ብጽአት ስዩም እራሱ በአንድ ወቅት ስትናገር፦
"እንደሰው እስኪያልፍለት እንደምንም አስታውሱት እንግዲህ ልጄን አደራ ሌላው ቢቀር ፊት አትንሱት የሚለው ስንኝ ላይ ስደርስ እንባዬ ግጥም ይላል፤ አልችልም”ብላለች።
ስለ መረሳትና ስለ ፊት መነሳት ሳስብ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን "ቴዎድሮስ" በተሰኘው ተውኔቱ ውስጥ አንዲት ገለጻውን አስታውሳለሁ። ልጅ ዓለማየሁ ቴዎድሮስ፤ አባቱን አፄ ቴዎድሮስን ይጠይቃል።
ዓለማየሁ…..”ደሃ ማለት ምን ማለት ነው አባዬ?” ይለዋል።
አፄ ቴዎድሮስም እንዲህ ይመልሳሉ…….”አዬ ልጄ ምን ብዬ ላስረዳህ፡ ደሃ ማለት ልጄ ከሰው ፊት ወግድ መባል ነው፣ እያለህ መረሳት ነው፣ ከሰው ክበብ መገለል ነው…” እያለ ይቀጥላል።
አያችሁ አይደል ጠቢባኑ እንዴት ድህነትን እንደሚገልፁት? አያ ሙሌም በራሱ ላይ የደረሰውን ፊት የመነሳት፣ የመገፋትና የመረሳት ህመም ስለሚያውቀው ነው ሌላው ቢቀር ፊት አትንሱት ሲል ልጆቹን አደራ ያለን።
እንዲህ እንዲህ እያለ አያ ሙሌ ከዚህ በታች ያለውንም አይነት ስንኝ በመቀኘት፣ ለእናቱ ያለውን ክብር አኑሯል፤ ሴት ልጅ እናት ስትሆን በእንዴት ያለ ሁኔታና መጠን መልሳ እናቷን እንደምታመሰግን አሳይቷል። የወልደህ/ሽ ቅመሰው/ሽው አባባል ምርቃት ይሁን እርግማን ሚስጥርንም አሳይቷል።
ማሪኝ እማምዬ ለኔ ያለሽ ፍቅር
በወጉ ሳይገባኝ አንቺን ያሞኘሁት
ብድር በምድር አይቀር
አራስ ቤት ተኝቼ ለልጅ ስንሰፈሰፍ
ወልጄ አገኘሁት
እኔም እንደ ሄዋን ተሰጥቶኝ አጥብቼ
ዙሬ ተቀብቼ እስካሳልፍልሽ
ውለታሽንማ በተራየ እንዳንቺው
ካልወለድኩሽ በቀር ብድርሽን አልከፍልሽ
ባልማዝና በእንቁ በከበረ ድንጋይ
በከበረው ድንጋይ
አሽቆጥቁጬ አኑሬሽ በሆንኩሽ አገልጋይ
በሆንኩሽ አገልጋይ
ምናለ ለምዬ ውሃ ሽጬስ ባድር
ውሃ ሽጬስ ባድር
ማን ውጪ እንዳይለኝ ካገርና ከእድር
ካገርና ከእድር
እንደሰው እስኪያልፍለት እንደምንም አስታውሱት
እንግዲህ ልጄን አደራ ሌላው ቢቀር ፊት አትንሱት
(2)
ጋዜጠኛና ገጣሚ ቴዎድሮስ ፀጋዬ ስለ አያ ሙሌ የተናገረውን ድንቅ ንግግር ላቅርብና ላብቃ፡-
“የጀንበርን ያህል አብርቶ የኩራዝም ያህል ስላልታየ እጹብ ሰው ለመናገር ስነሳ፣ በልቤ ውስጥ ብዙ ሃሳቦች ይንገዋለላሉ። ያልታየው ከብርሃኑ መብዛትና ከንጽብርቆሹ ማጥበርበር የተነሳ ነው? ወይስ ከተመልካቹ የልቦና ዐይን ማጣት ነው የሚል ጥያቄ ....እንዲያ የሚበራም የሚያበራም ብዕር ባለቤት የነበረ ሰው እንደዋዛ የመረሳት አቧራ የጋረደው በእሱና በብዕሩ መርቀቅ ምክንያት ነው ወይስ በተደራሲው ዐይነ ህሊና ላይ በተጋረደው ሞራ ምክንያት ነው የሚል ጥያቄ አለኝ።
ከባለ ብርሃኑ ወይስ ከባለ ዐይኑ? ያው የሚያይ ሁሉ ስለማያይ ማለት ነው” ይልና ዝቅ ብሎ ደግሞ....
“..ስቲ እራሳችንን እንጠይቅ፤ ስንት ባለ ጥበብ በጥበታችን ገደልን፣ በስንቱ ንቃት ላይ በመዘንጋት እንቅልፍ ወደቅንበት፣ በስንቱ ፍካት ላይ በጭካኔና ባለማወቅ ተጋደምንበት”ይላል፤ ጋዜጠኛና ገጣሚ ቴዎድሮስ ጸጋዬ፡፡

Read 818 times