Print this page
Tuesday, 15 September 2020 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(0 votes)


               ወደ አዲስ ዘመን እየተሸጋገርን ነው፡፡ በሁለት እግራቸው የቆሙ፣ በእግዜርም፣ በመንግስትም፣ በጥቅምና በዝምድና ተጽእኖ የማያሸበርኩ፤ ነፃ የፍትህና የዴሞክራሲ ተቋማትን በመገንባት ለሰላም፣ ለአንድነትና ለነፃነት በጋራ በመቆም፤ ዕድገትና ብልጽግና የናፈቃት፣ ስደትና መከራ ያደባያት አገራችን፣ በተሃድሶ ጉዞ ወደተሻለ ስርዓት እንድታመራ በትጋት መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ወደ ስልጣኔ ጎዳና!
ወዳጄ፡- ተሃድሶ የነብር ጭራ ነው፡፡ አጥብቀው ከያዙት ራሱን ለማዳን ሲል ወደፊት ይገሰግሳል፡፡ ከለቀቁት ግን ዞሮ ይናከሳል፡፡ ምርጫው የኛ ነው፡፡ ምርጫው ማሰብ ወይም አለማሰብ ነው! በትክክል ማሰብ ከቻልን አንቆምም!!
የሲስተም ተሃድሶ ለመፍጠር ግለሰባዊ የአስተሳሰብ ዓቅም ያስፈልጋል፡፡ በታሪክ ውስጥ ያየናቸው የተሃድሶ እንቅስቃሴዎች የተመሩት ታላላቅ አእምሮ ባላቸው ግለሰቦች ነው፡፡ የጀርመኑ ሪናይሳንስና የጣሊያኑ ሪፎርሜሽን ለምስክርነት ይቆማሉ፡፡ ፈረንሳይ ደግሞ ሁለቱንም የሆነችው በቮልቴር ነው፡፡ በኛም ሀገር በየትኛውም የፖለቲካ ማህበር ውስጥ የሚንቀሳቀሱም ሆኑ ነፃ ግለሰቦች፣ በግልም ሆነ በመንግሥት ስራ የተሰማሩ፣ በሀገርም ሆነ በውጭ አገር የሚኖሩ፣ ዓለም አቀፍ አመለካከት ያላቸው፣ ታላላቅ ሃሳብ የሚያመነጩ አገር ወዳድ ምሁራንን አግባብቶ ወደ “ኮክ ፒት” ማምጣት ከተቻለ አገራችን ወደ ምኞቷ ለመድረስ የምታደርገው ጉዞ ይፋጠናል፡፡ አለበለዚያ ችግሯ እየተደራረበ ዳገቱ ይፈትናታል፡፡ ተሃድሶው ጥርስና ጥፍር የሌለው አንበሳ ይሆናል፡፡ ሙሰኞች አይፈሩትም፡፡ ሙሰኝነት የተሃድሶ እንቅፋት ነው፡፡ ሙሰኝነት በህግ ካልተረታ ሪቮሉሽን አይቀሬ ነው!!
ወዳጄ፡- “የመካከለኛው ዘመን ቤተ እምነቶች አስተዳደራዊ ተቋማት ከጊዜው ጋር መራመድ ያቃታቸውና ሙሰኛ ስለነበሩ የተሃድሶ በትር ደርሶባቸዋል” ይላል፤#የተሃድሶ ታሪክ; የሚለው መጽሐፍ፡፡ በዘመኑ የነበሩ ብዙ የዕምነት መሪዎች ባለውሽሞች እስከመሆን ድረስ ህገ ደንብ ያላገዳቸው፣ በተለያየ መንገድ የራሳቸውን ጥቅም በማሳደድ ላይ ብቻ ያተኮሩ ነበሩ፡፡ በወቅቱ “ልጅህ ጋጠ-ወጥ ወይም ባለጌ መሆኑን የምታውቀው ቄስ ከሆነ ነው” እየተባለ የዘመኑ ካህናት በመጥፎ ተግባር ምሳሌነት ይጠቀሱ ነበር፡፡ ከመጥፎ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ሲመከሩም ተቃዋሚዎቻቸውን በማግለል (ex-communicate በማድረግ) እና የጭካኔ እርምጃዎችን በመውሰድ ለመታረም አሻፈረኝ በማለታቸው የተሃድሶ ንቅናቄ ከመሃከላቸው ሊፈነዳ እንደቻለ ታላቁ ዊልዱራንት #የስልጣኔ ታሪክ” በሚለው መጽሐፉ ያሰፈረ ሲሆን በዘመኑ የነበሩት ሊቃውንት መነኮሳት ዕፀፆቹን በዓይን ምስክርነት አብራርተው ጽፈዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ኤራስመስና ማኪያቪሌ ይጠቀሳሉ፡፡
የተሃድሶው የጠዋት ኮከብ (Morning star of the reform) በመባል የሚታወቀው ቄስ ጆን ዋይክሊፍ (1330-1384) የላቲኑን መጽሐፍ ቅዱስ ወደ እንግሊዝኛ የተረጐመ ሊቅና በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የቲዮሎጂ ፕሮፌሰር ነበር፡፡ ዋይክሊፍ በተፈጥሮ ህመም በ1384 ዓ.ም ህይወቱ ቢያልፍም የሱ ተከታይና የፕራግ ዩኒቨርሲቲ መምህር የነበረው፣ የቼክ ተወላጅ ቄስ ያን ሃስ በፀረ ተሃድሶ ባለሟሎች እ.ኤ.አ በ1415 ዓ.ም ተቃጥሎ እንዲሞት ሲፈረድበት፣ የሱም ዐፅም ከሰላሳ ዓመታት በኋላ ከተቀበረበት ወጥቶ አብሮ እንዲቃጠል ተደርጓል፡፡ ያን ሃስም እንደ ዋይክሊፍ ከተሃድሶ እንቅስቃሴው እንዲቆጠብ ሙሰኞቹ ሊያግባቡት ሲሞክሩ፤ “እየታመሙ ከመኖር በጤንነት መሞት; (It is better to die well than to live ill) ይሻላል በማለት መስዋዕትነትን ተቀብሏል፡፡
ሌላው የህዳሴ ፋና ወጊ ጂኖራሎ ሳቮናሮላ ነው፡፡ ጂኖራሎ የዶሚኒካን ተወላጅ ሲሆን በጣልያን በሚገኘው ፍሎረንስ ገዳም መነኩሴና አገልጋይ ነበር፡፡ እሱም እንደ ሌሎቹ ተሃድሷውያን ከሙሰኞቹ የቀረበለትን ማግባቢያ አሻፈረኝ በማለቱ ከታሰረና ብዙ ስቃይ ከደረሰበት በኋላ በተወለደ በአርባ አራት ዓመቱ እ.ኤ.አ በ1499 ዓ.ም በስቅላት እንዲሞት፣ አካሉም እንዲቃጠል ተፈርዶበታል፡፡ ጂኖራሎ ፍርዱን ሲሰማ “ለሃጢአቴ ለሞተልኝ ጌታ ክብር ምስኪን ነፍሴን መስጠቴ በእጅጉ ያስደስተኛል” በማለት ለፈጣሪው ያለውን ክብር አረጋግጧል፡፡
የህዳሴው ንቅናቄ ተስፋፍቶ ከብዙ ትግል፣ ውጣ ውረድና መስዋዕትነት በኋላ በአሸናፊነት የወጣው በዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ ሲኒየር ዘመን ነው፡፡ ማርቲን ሉተር ኦክቶበር 31 ቀን 1517 ዓ.ም በጀርመን ሃገር፣ ሳክሶኒ ግዛት ውስጥ በሚገኘው የዊቲን በርግ ቤተ እምነት በር ላይ የለጠፋቸው ዘጠና አምስት ቲሰሶች (Disputation for clarification of the power of indulgences) ወይም #ከሃጢአት ነጽቷል ወይም ሃጢአቱ ተሰርዞለታል” እየተባለ በገንዘብ የሚሸጠው የምስክር ወረቀት የዋስትና መድህንነቱ ተዓማኒነት ባስነሳው ግብ ምክንያት በምዕመኑ ላይ የፈጠሩት አንደምታ የህዳሴው ንቅናቄ እመርታ ለመሆን በቅተዋል፡፡
ወዳጄ፡- የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ሙሰኝነት በማህበራዊ ኑሮ፣ በፖለቲካም ሆነ አምልኮታዊ ጉዳዮች ላይ ያለውን አፍራሽ ገጽታ ለማስታወስ ብቻ ስለሆነ ሐይማኖታዊ ጉዳዮችን ወደ ጐን ትተን፣ ወደ ራሳችን ሃሳብ እንዞራለን፡፡
የዙረት ነገር ከተነሳ እግረ መንገዴን ድሮ የሰማኋትን ቀልድ ነግሬአችሁ፣ ወደ ጀመርነው የማርቲን ሉተር ማንነት እንመለሳለን፡፡ ሰውየው በዓይን ለሚያውቃቸው ጠና ያሉ ሰው አውሮፓና አሜሪካ እንደተማረ፣ በህንድና በካይሮ የሙያ ስልጠና እንደወሰደና አንዳንድ የህይወቱን ገጠመኞች ያጫውታቸዋል፡፡ እሳቸውም ደስ ብሏቸው ሲሰሙት ቆይተው፡-
“አሁን እዚህ ነው የምትኖረው?” በማለት ጠየቁት፡፡
“ተመልሼ እሄዳለሁ፣ እዚህ የማስጨርሰው ጉዳይ አለኝ” አላቸው፡፡
“የኛ አገር ጉዳይ መቼ ያለ ገንዘብ፣ ያለ ሰው ወይ ያለ ፖለቲካ ንክኪ በአግባቡ ያልቃል ብለህ ነው?!” ሲሉ በጥያቄ የታጀበ አስተያየት ይሰነዝራሉ፡፡
“እውነትዎትን ነው፣ እንደውም አሁን አንድ ባለስልጣን ቀጥሮኛል፣ ወደዛ መሄዴ ነው” ብሎ ተነሳ፡፡
እሳቸውም “ውይ ልጄ ይቅርታ ጨዋታህ ጣፍጦኝ በወሬ ያዝኩህ” ብለው ሲያሰናብቱት አጅሬው አሰብ አደረገና ፀጉሩን እያሻሸ፡-
“መሄድ እሄዳለሁ፡፡ ግን በአጋጣሚ የኪስ ቦርሳዬን ረስቼ ስለወጣሁ አስር ብር ለትራንስፖርት አበድሩኝ” አላቸው፡፡  
ሰውየው ደንግጠው ምን እንዳሰቡ ታውቃለህ? መጨረሻ ላይ እነግርሃለሁ፡፡
*   *   *
ወደ ተሃድሶ ንቅናቄው ስንመለስ፣ መነኩሴው ስኮላር ማርቲን ሉተር ኪንግ ሲኒየር የተወለደው በ1483 ዓ.ም ጀርመን ውስጥ ሲሆን የቪተንበርግ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰርና የቲዮሎጂ ዶክተር በመሆን አገልግሏል፡፡ ዶክተር ኪንግ በግሪክና በሂብሩ ቋንቋዎች የተፃፈውን መጽሐፍ ቅዱስ በመሳጭ አቀራረብ ወደ እንግሊዝኛ ተርጉሟል። መጽሐፉ እንደ ኪንግ ጀምስ ጥራዝ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ስላተረፈ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ 5.000 ኮፒ፣ በአስራ ሁለት ዓመት ደግሞ 20.000 ኮፒ ተሸጧል፡፡
ማርቲን ሉተር እ.ኤ.አ በ1521 ዓ.ም መነኩሲቷን ካተሪና ፎንቦራን አግብቶ ስድስት ልጆች አፍርቷል፡፡ ለጋብቻው ምክንያት ስለነበሩ ሶስት ነገሮች ሲያብራራ፡- “በመጀመሪያ አባቴን ለማስደሰት፣ ቀጥሎ ደግሞ ለሙሰኞቹና ለሰይጣን ያለኝን ንቀት ለማሳየትና ለእምነቴ ስል ለደረሰብኝ መከራ ካሳ እንዲሆነኝ ነው” ብሏል፡፡
ወዳጄ፡- የኛም አገር የሙሰኝነት መስፋፋት ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ከወዲሁ ለመገመት ነቢይነትን አይሻም፡፡ የሙስና ኮሚሽን ከሰሞኑ በሰጠው ማብራሪያ፤ 180 የመንግስት ባለስልጣናት ሃብትና ንብረታችንን አናስመዘግብም፣ በማለታቸው ከህግ በላይ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ክስ እንዲመሰረትባቸው ፋይሉን ወደ ዓቃቤ ህግ መ/ቤት ለመላክ እንደተዘጋጀ በሚዲያ ሰምተናል። ኢዜማ የተባለው የፖለቲካ ፓርቲም፤ በከተማችን ውስጥ ከፍተኛ የመሬት ወረራ እንዳለና ለጋራ መኖሪያነት የሚገነቡ ቤቶችም ህግና አግባብ በሌለው ስርዓት እንደሚደለደሉ በጥናት አረጋግጬ፣ አጥፊዎቹ በወንጀል እንዲጠየቁ ሰነዱን ለሚመለከተው የመንግስት አካል አቅርቤአለሁ ሲል አስታውቋል፡፡ በዚህም ሳቢያ የአዲሱ ዓመት ጥያቄ፡- የመንግስት መዋቅር ውስጥ ባሉ ግለሰቦችና ደላሎች እንደነዚህ ዓይነት ወንጀሎች ሲፈፀሙ ሃይ የሚላቸው ማን ነው? ሙስና የህዳሴ ጠር በመሆኑ ንቅናቄውን እንዳያኮላሽና ወደ ኋላ እንዳይመልሰን አያሰጋም ወይ? የሚል ነው፡፡ ፈጣን ምላሽም ይሻል፡፡
*   *   *
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፡- አጅሬው ሰውየውን አስር ብር አበድሩኝ ሲላቸው ደንግጠው ያሰቡት፡-
“ለካስ ትንሽም ቢሆን ገንዘብ ለማግኘት ይኸን ሁሉ ዓለም መዞር ያስፈልጋል” በማለት ነበር፡፡ ወዳጄ፡- ዞሮ ዞሮ ይኸም ሙስና ነው ቢባል ምን ትላለህ?
መልካም አዲስ ዓመት!
ሠላም!  


Read 513 times