Sunday, 13 September 2020 00:00

ለማ ጉያና ዘመን አይሽሬ ሥዕሎቻቸው

Written by  ታደለ ገድሌ ጸጋየ
Rate this item
(1 Vote)

    ሠዓሊ ለማ ጉያ ገመዳ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ታላላቅ የጥበብ ሰዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚሰለፉ ባለሙያ ናቸው:: ሠዓሊ ለማ የዘመናችን እውቅ የሥዕል ባለሙያ ከመሆናቸው ባሻገር የቅንነት፤ የደግነት፤ የጨዋነት፣ የጀግንነትና የአርቆ አስተዋይነት መንፈስ ያላቸው አባት ሲሆኑ ጨዋታ አዋቂ፤ የፍቅር ሰው፤ ቀልደኛ፤ ተጨዋች፤ የሰውን ልጅ ሁሉ የሚያከብሩና አገር ወዳድ ሰው ናቸው፡፡ በአሁኑ ሰዓት በ91ኛ ዓመት እድሜ ላይ የሚገኙት ሠዓሊ ለማ ጉያ፤ በ1921 ዓ.ም ከአባታቸው ከአቶ ጉያ ገመዳና ከእናታቸው ከወይዘሮ ማሬ ጎበና በቀድሞ አጠራሩ በሸዋ ክፍለ ሀገር አድኣ ሊበን ውስጥ ልዩ ስሙ ደሎ ገበሬ ማኅበር ነው የተወለዱት፡፡ ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ ጡረታቸውን አስከብረው  ከባለቤታቸው ከወይዘሮ አስቴር በቀለ መካሻ ጋር በቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ በመኖር ላይ የሚገኙት ሠዓሊ ለማ ጉያ፤ በትዳር ዘመናቸው ከአብራካቸው ስድስት ልጆችን ያፈሩ ሲሆን ሁሉም ልጆቻቸው ሠዓሊዎች ናቸው፡፡ በተለየ የሙያ ዘርፍ  ከተሰማሩት አቶ ተሰማ ጉያ በስተቀር የሠዓሊ ሻምበል ለማ ጉያ ወንድሞችም ሠዓሊዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ሠዓሊ አሰፋ ጉያና ቱሉ ጉያ የዚሁ ሙያ ባለቤቶች ናቸው፡፡ ድምጻዊው ታምራት ሞላ
ቤተሰቤ ሁሉ የእጅ ሙያ አላቸው፤
ለእናት ሀገራቸው የሚያኮሩ ናቸው፡፡
…ብሎ ያንጎራጎረው ለሠዓሊ ለማ ጉያና ቤተሰቦቻቸው ዓይነቶቹ ነው ብንል ያስኬዳል:: ሠዓሊ ለማ ጉያ፤  በቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ በስማቸው የሥነ ጥበብ ማእከል (ቋሚ ጋለሪ) ያቋቋሙ ሲሆን የሥዕል ማስተማሪያ ትምህርት ቤት ከፍተውም  በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡
በአንድ ወቅት ለቃለ ምልልስ በቢሾፍቱ የሥዕል ጋለሪያቸው በተገኘንበት ወቅት ሠዓሊ ለማ ጉያ የተቀበሉን በተለመደው የአባትነት ፍቅራቸውና ፈገግታ በማይለየው የእንግዳ አቀባበል ልምዳቸው ነበር፡፡ የተረጋጋ መንፈስ ያላቸው ሠዓሊው፤ ስለ ውትድርና ሕይወታቸው፤ ስለ አገራችን ታሪክ፤ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት እርሳቸውን ጨምሮ ኮሙኒስታዊ አስተሳሰብ ስለነበራቸው የአየር ኃይል መኮንኖች፤ ስለ ሜጫና ቱለማ ማኅበር አመሠራረት፤ ስለ ደርግ መንግሥት የፖለቲካ ርምጃና ስለ ኢሕአዴግ መንግሥት አሠራር፤ በአጠቃላይ ከኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያለውን የሀገራችንን ታሪክ ሲተነትኑ ያላቸው እውቀት እንደ ባሕር ውኃ ተጠልቆ የሚያልቅ አይደለም፡፡ ሁሉ ነገር ልክ ዛሬ እንደተደረገ በሚመስል ትረካ ሳያዛንፉ የዘመንን ሂደት ያትታሉ፡፡
ለተጠየቁት ርእሰ ጉዳይ ሁሉ መልስ አላቸው፡፡ ጠያቂ ካልደከመው በስተቀር እርሳቸው አይደክማቸውም፡፡ እርሳቸው በትዝታ መነጽር ወደ ኋላ እያዩ እንዳጫወቱኝ፤ የተወለዱባት ዶሎ መንደር የዛሬ 90 ዓመት፣ ነሐሴ 12 ቀን 1921 ዓ.ም በዕለተ ሚካኤል አንድ ታሪክ ተስተናግዶባታል፡፡ ይኸውም በሀገራችን ታሪክ የመጀመሪያ የሆነው አውሮፕላን ከጂቡቲ በጠዋት ተነሥቶና የባቡር ሐዲዱን ተከትሎ እየበረረ ድሬዳዋ  ይደርሳል፡፡ ወሬውም በነፋስ ስልክ ገፈርሳ ላይ አቀባበል ለማድረግ  ከነመኳንንቶቻቸው ከአብራሪው ሚስት ጋር  ተሰልፈው ሲጠባበቁ ለነበሩት ለአልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን ይደርሳል፡፡ ንግሥት ዘውዲቱም ወሬውን በዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ሆነው ይጠባበቃሉ፡፡ የፈረንሳዊው አብራሪ ባለቤት አስቀድማ ከጂቡቲ ወደ አዲስ አበባ በባቡር የገባችው ታሪካዊውን አውሮፕላን የሚያበርረውን ባለቤቷን ከኢትዮጵያ ባለሥልጣኖች ጋር ተሰልፋ ለመቀበልና ብራቮ ብላ አድናቆቷን ለመግለጽ  ነው፡፡ አውሮፕላኑም ሐዲዱን እያነጣጠረና ከድሬዳዋ እየበረረ አዋሽ ይደርሳል፡፡ በአጋጣሚ ከጠዋቱ 5 ሰዓት ላይ  ናዝሬት (አዳማ) ሲደርስ  ጥቁር ደመና መንገዱን ይዘጋበታል፡፡
ለማየት የማይችልበት ሁኔታ  እንደተፈጠረ  አብራሪው መድረሻ ያጣል፡፡ በዚህ ጉዳይ የተጨነቀው ፈረንሳዊው አብራሪ በድንገት ገላጣ ቦታ ሲያይ አውሮፕላኑን ቁልቁል እያምዘገዘገና ባወጣ ያውጣው እያለ  ሠዓሊው ከተወለዱባት ዶሎ የገጠር መንደር ላይ በሚገኘው በበጅሮንድ ውብእሸት መሬት ላይ  ያሳርፈዋል፡፡ ይህም ለራስ ተፈሪ መኮንን በነፋስ ስልክ ይነገራቸዋል:: አውሮፕላን ቀርቶ መኪና በቅጡ አይቶ የማያውቀው የዶሎ ሕዝብም ምን ጉድ ነገር መጣ እያለና እየተጠራራ ወደ አውሮፕላኑ በደመ ነፍስ ሲሮጥ የሕፃን ለማም ቤተሰቦች  የተፈጠረውን ጉድ ለማየት  ጥለዋቸው  ወደ አውሮፕላኑ ይሮጣሉ፡፡ ያኔ ለማ የስድስት ወር ልጅ ነበሩ:: እናም ዶሎ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጀመሪያውን አውሮፕላን ተቀብላ ያስተናገደችና ያሳረፈች የገጠር መንደር  ኤርፖርት ናት ማለት ነው፡፡
ይህን የታሪክ ክስተት እየሰሙ ያደጉት ለማ ጉያም፤ አውሮፕላኑ የሕይወታቸው ምዕራፍና የእድላቸው ምልክት እንደሆናቸው ያስታውሳሉ፡፡ ሠዓሊ ለማ እንዳጫወቱኝ፤ ቀደም ሲልም  ተገጣጥሞ የሚበርር የአውሮፕላን ዕቃ በባቡር ተጭኖና ከፈረንሳይ ጂቡቲ፤ ከጂቡቲ አዲስ አበባ ገብቶ ነበር፡፡ ነገር ግን  አዲስ አበባ ውስጥ ሳይከፈትና ተገጣጥሞ ሳይበርር ወደመጣበት ተመልሷል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ቀሳውስቱና መሳፍንቱ “የእግዚአብሔርን መዓት ሊያመጣብን ይችላል” ብለው እንዳይከፈት ስለተቃወሙ ነው፡፡ እናም ዶሎ ያረፈው አውሮፕላን ከፈረንሳይ ዕቃው (ቦዲው) መጥቶ የተገጣጠመው ጂቡቲ ውስጥ ነው፡፡ ነሐሴ 12 ቀን 1921 ከቀኑ 7 ሰዓት ሲሆን ደመናው እየተገፈፈና ሰማዩም እየጠራ ቀኑ ብሩህ በመሆኑ አውሮፕላኑ ተነሥቶ  አዲስ አበባ ገፈርሳ ላይ ሲያርፍ፣ የተሰለፈው ሕዝብ  በስስት ስሜትና በብርቅዬነት መልክ እያየ በእልልታና በጭብጨባ ይቀበለዋል፡፡
የሠዓሊው ምስል (ፖርትሬት) በቆዳ የአሣሣል ጥበብ

ለማ ጉያ በልጅነታቸው በዶሎ የገጠር መንደር ውስጥ የቤተሰቦቻቸውን ከብቶች ሲጠብቁ ዐፈሩን፤ ዐመዱን፤ ጠጠሩን እየሰበሰቡና እያድቦለቦሉ ዱላ የያዙ እረኞችን መሥራት ይለማመዳሉ፡፡ የሰው ሥዕል ግድግዳ ላይ መሣል ይጀምራሉ፡፡ በጣሊያን ወረራ ጊዜ ከከተማ ወደ ገጠር ማለት ወደ ዶሎ ሰዎች  ይመጡ ስለነበር የእነርሱን የአለባበስ ሁኔታ ያያሉ፡፡ በተጨማሪም ሰዎች ከቡልጋ፤ ከምንጃርና ከመንዝ ወደ ዶሎ የሚመጡ ባላገሮች ነበሩ፡፡ እርሳቸው ይኖሩበት የነበረውም ቦታ  የቡልጋ ባላባት ርስትና ጉልት  ነበር፡፡ የሠዓሊ ለማ ጉያ ወላጅ እናት ወይዘሮ ማሬ ጎበና የተወለዱት ለገዳዴ አብቹ በተባለ ቦታ ነው፡፡ የአባታቸው አባት አያታቸው  አቶ ገመዳ ኮርሜ  ደግሞ ከሰላሌ ወደ ዶሎ የመጡ ሰው ናቸው፡፡ ወላጅ እናታቸው ወይዘሮ ማሬ ጎበና የእጅ ሥራ ዐዋቂና ባለሙያ ነበሩ፡፡ ሸክላ፤ ጋን፤ እንስራ፤ ጀበና ምጣድ ይሠራሉ፡፡ በግድግዳ ላይ ሥዕል ይሥላሉ፡፡ ለማም ሁልጊዜ የእናታቸውን ሥራ አትኩረው ይመለከታሉ፡፡ እናት የሸክላ  ዕቃዎችን ከመሥራትና ልዩ ልዩ ሥዕሎችን ከመሣል አልፈው ስፌትም ይሰፋሉ፤ ሥጋው ተበልቶ አጥንቱ የሚቀመጥበት ገበቴ  ይሠራሉ:: ሁሉ ነገር ሥርዓት እንዲይዝ ያደርጋሉ:: በዚያ  ዘመን  ባቡር፤ መኪና አልነበረምና የሸክላ ምርታቸውን ከለገዳዴ በአጋሰስና በአህያ  ጭነው ወደ አድኣ እያመጡ ይሸጡ ነበር፡፡ የእናታቸው ወንድም ኦርዶፋ ጎበናም እንዲሁ  በዘመኑ የልብስ ስፌት መኪና ሳይኖር ልብስ በመርፌ ይሰፉና ሞፈር፤ ቀንበር፤ድግር ለገበሬዎች ያበጁ ነበር፡፡ ቤተሰባቸው ሁሉ ጥበበኛ ነበር ማለት ነው፡፡ ሠዓሊ ለማ ጉያ እንደሚያስታውሱት፤ በልጅነታቸው  የከብት እረኛ በነበሩ ጊዜ በአካባቢያቸው ሞጃ ከተባለ ቦታ የረር ወንዝ ላይ ባቢቾብ የተባለ ሩሲያዊ በውኃ ኃይል የሚንቀሳቀስ የእኽል ወፍጮ  ሠርቶ ስለነበር ወደ ደንጋይ ቋት የገባውን ጥሬ እኽል በአንዴ ዱቄት አድርጎት  ሲመለከቱት ይገረሙ ነበር፡፡
ያኔ መኪናም፤ የመኪና መንገድም ስላልነበረ በተለይ በክረምት ወቅት  ሁሉ ነገር በእንስሳና በሰው ጉልበት  በከባድ ጭቃ ውስጥ ከቦታ ወደ ቦታ  ይንቀሳቀስ ነበር፡፡ በዚህ ረገድ ጣሊያኖች በ1928  በመኪና ቢሾፍቱ ገልቻ ወንዝ  አካባቢ ሲንቀሳቀሱ ጭቃ ይዟቸው ስለተገኙ በሕዝብ  ተገድለዋል፡፡ ሠዓሊ ለማ ጉያ ሞፈርና ቀንበራቸውን ሰቅለው ደብረ ዘይት (ቢሾፍቱ) ዓፄ ልብነ ድንግል ተብሎ ይታወቅ ወደነበረውና ዛሬ ስሙ ወደተቀየረው ዘመናዊ ትምህርት ቤት የገቡት በ17 ዓመታቸው ነው፡፡ ሀ ብለው ፊደል ከቆጠሩ በኋላ በ1943 ዓ.ም 7ኛን ክፍል ጨርሰው ናዝሬት ዓፄ ገላውዴዎስ (ዛሬ ስሙ ወደተቀየረው) ትምህርት ቤት ይገባሉ፡፡ እዚያም በመምርነት ሠልጥነው በ70 ብር ደመወዝ ይቀጠራሉ፡፡ ወዲያው ሥራውን አልፈልግም ብለው ይተውታል፡፡
ስለ አውሮፕላን ነገር በልጅነታቸው የሰሙትና በኋላ  በቢሾፍቱ ሰማይ ላይ ሲበር የሚያዩት የአየር ኃይል ጀት መንፈሳቸውን ስለማረከው የተለየና ያማረ የአውሮፕላን  ሞዴል ቅርፅ ሠርተው ግርማዊ ጃንሆይ ለሽርሽር ወደ ቢሾፍቱ በሚመጡበት ዕለት ለማበርከት ስለፈለጉ ቀን ይጠባበቁ ጀመር፡፡ ከዕለታት በአንዱ ግርማዊ ጃንሆይ ለጉብኝትና ለሽርሽር ቢሾፍቱ አየር ኃይል ሲደርሱ፣ ለማ ልክ እንደ ወታደር ቀጥ ብለው በመቆም ለንጉሡ የክብር ሰላምታ ይሰጣሉ፡፡ ንጉሡም «ምን ትፈልጋለህ?» ብለው ይጠይቋቸዋል፡፡ «ግርማዊ ሆይ፤ አየር ኃይል ያስገቡኝ» ይላሉ፡፡ ያኔ ንጉሡ፤  ግራዝማች ሣህሉ ድፋየን ጠርተው  «በል በአስቸኳይ ለጂኒናር አሰፋ አያና ንገርና ይንን ልጅ ያስገባው» ብለው መመሪያ ይሰጣሉ:: 60 ብርም ለለማ ጉያ ይሰጡዋቸዋል፡፡ ለማም በ60 ብሯ አንዲት ላም ገዝተው ለዘመዶቻቸው ይሰጣሉ፡፡ በጃንሆይ ብር የተገዛ ከብት ደግሞ በዘመኑ አይሰረቅም ነበር፡፡ በጃንሆይ ብር የተገዛች የጃንሆይ ላም ናት ከተባለ ማን አባቱ ነክቶ? የትስ ሊገባ? ሌሎች ከብቶች ሲሰረቁ የለማ ጉያ ላም ግን  በሰላም ኖራለች፡፡
ወጣቱ ለማ ጉያ  በጀኔራል አሰፋ አያና ትእዛዝ ወደ አየር ኃይል ገብተው የመካኒክነት ሙያ (አውሮፕላን የመፍታትና የመግጠም ትምህርት) ይማራሉ፡፡ ማታ ማታ ደግሞ በእንግሊዝ መምህራን፣ እንግሊዝኛ የመማር እድል ያገኛሉ፡፡ ከሁለት ዓመት ጥናት በኋላም በመካኒክነት ይመረቃሉ፡፡ እርሳቸው ግን አብራሪ እንጂ መካኒክ መሆን አልፈለጉም ነበርና “ለምን መካኒክ ሆንኩ? ለምን አብራሪ አልሆንኩም? የላኩኝ እኮ ንጉሡ ናቸው”  ብለው  ለኃላፊዎች ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ በወቅቱ አብራሪ መኮንኖች ይሄዱ የነበሩት በመኪና ሲሆን ለማ ግን በእግራቸው ይመላለሱ ስለነበር በዚህም ተናድደዋል፡፡ ይህንኑ ምክንያት አድርገው  አሰፋ ከተባለ የድሬ ሰው ጋር ይጠፋሉ፡፡ አቶ ጉያም እሳት ለብሰውና እሳት ጎርሰው «ከዛሬ ጀምሮ ልጄ አይደለህም፡፡ ኃይለ ሥላሴ ራሳቸው አስገብተውህ  እንደዚህ ማድረግ አልነበረብህም፡፡ የጠፋኸው እኔን ልታስገድለኝ ነው ? የንጉሡን ትእዛዝ ጥሰህ ሽፍታ ልትሆን ነው እንዴ?” ብለው  ቢቆጡዋቸው  እሺ ብለው ወደ አየር ኃይል ይመለሳሉ፡፡ ነገር ግን ኃላፊዎቹ “አንዴ ጥለህ ሄደሃልና አናስገባህም” ይሏቸዋል፡፡
ወጣቱ መካኒክም ብልህ ስለሆኑ «እስከ አሁን የጠፋሁት አባቴ ታሞብኝ ስለነበረ ነው፡፡ እምቢ ካላችሁ ለግርማዊ ጃንሆይ ሄጄ እነግራቸዋለሁ» ሲሉ የአየር ኃይል ኃላፊዎችም ተደናግጠው  “ይኸማ  አይሆንም»  ብለው ያስገቧቸዋል፡፡ ደመወዛቸውም 40 ብር ነበር፡፡ በጊዜው ይህ ብር ተዝቆ አያልቅም ነበር፡፡ ሠዓሊው እንደሚሉት፤ ያኔ ከደብረ ዘይት ወደ ናዝሬት  ይወርዱና በ25 ሳንቲም ሥጋ ወጥ በልተው፣ 1ብር ባልሞላ ቀኑን ሙሉ ተዝናንተው ወደ ትንሺቱ የአየር ኃይል መንደር ይመለሱ ነበር፡፡
ለማ በመካኒክነት ደብረ ዘይት ከሠሩ በኋላ ወደ ጂጂጋ ተልከዋል፡፡ ጂጂጋ ደግሞ ሌሊት ሌሊት ጊንጥ እየነደፈች ሰው ትገድል ስለነበር  ሞኝሽን ፈልጊ ብለው አውሮፕላን ውስጥ እየገቡ ያድሩ ነበር፡፡ ያኔ ነዳጅ ወደ አውሮፕላን ይሞላ የነበረው በበርሜል በሰው ኃይል ተቀድቶና ተሞልቶ ፤እንደገና በፓምፕ እየተገፋ ነበር፡፡ በመካኒክነት ሲያገለግሉ የቆዩት ለማ ጉያ፤እ.ኤ.አ በ1952 በአየር ኃይል አርማሜንት ክፍል ለአምስት ዓመት ኮርስ (ሥልጠና) ወስደው ተመርቀዋል፡፡ ትምህርቱ በጦር መሣሪያ ኃይል ጠላትን እንዴት መከላከል፤ ማጥቃትና ማሸነፍ እንደሚቻል፤ እንዴት ጥይቱን፤ረሹን ገዝተው እንደሚሠሩ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ነው፡፡ ተመድበው የሚሰሩት በስዊድን ቢ-17 ቦምብ ጣይ አውሮፕላን ላይ ነበር፡፡ አሥመራን ከጥቃት ለመከላከል በደቀ መሐሪ 40 ኪሎ ሜትር ላይ ልምምድ ያደርጉ ነበር፡፡ በ1966 ዓ.ም ደብረ ዘይት ላይ «ያለምንም ደም--» ብለው የተነሡትና የመጀመሪያውን ደርግ ያቋቋሙት ሠዓሊ ለማን ጨምሮ የአየር ኃይል መኮንኖች ናቸው፡፡ በወታደራዊ ማዕረግ ከታች ጀምረው እስከ ሻምበልነት ማዕረግ የደረሱት ለማ ጉያ፤ በ40 ደራስያን የተጻፈ የኮሙኒስት መጽሐፍ ለወጣት መኮንኖች ስላሠራጩ  “ኮሙኒስት ነህ” ተብለው ተወንጅለው ታሥረው ነበር፡፡               
(ይቀጥላል)

Read 684 times