Print this page
Saturday, 12 September 2020 14:51

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by  (ዮናስ አንገሶም ኪዳኔ)
Rate this item
(3 votes)

   ለአዲስ አበባ
            
“ወይ ኣዲስ ኣበባ!
ወይ ኣራዳ ሆይ!
ከተማም እንደሰው…” ይጀግናል ወይ?
ኣገሩን በሙሉ ፍርሃት ሲሸብብው፣
በርጥባን ሲደለል የዋህ ያገሬ ሰው፤
ታጥቀው የገጠሙሽ ኣይተዋል ልክሽን፣
ዛሬ ሊታይ ነገር መጥበብ እንደፋሽን።
ወይ ኣዲስ ኣበባ፣ ወይ ኣራዳ ውዴ፣
ላገር ልጆች ከፍለሽ፣
ለዘር ሲዋከቡ ግራ ገባሽ እንዴ?
---
እኮ እንዴት ይረሳል?
ትኩሳትሽ ሰፍቶ ጫፍ ኣገር ይደርሳል፤
ውሃሽ ጠበል ሆኖ ት’ቢት ይፈውሳል፤
መርካቶ፣ ልደታ፣ ፈረንሳይ፣ ካዛንቺስ
በወኔ፣ ባላማ ኣትታሚም ኣንቺስ።
---
ኣገር! ኣገር! ነበር ያንቺማ ዝማሬ፣
ኣዲስ ቅኝት ገኖ ኣፈዘዘሽ ዛሬ፤
እሴትና መርህ ጭራሽ ያልገባቸው፣
“ኣንቀላፋች” ብለው ሊንቁሽ ዳዳቸው።
---
የት ነበሩ እነሱ?
ልጆችሽ ለጥይት
ድንጋዩን ሲያነሱ፤
ጎማ ሲያቃጥሉ፣
እንደዘረኛ ልብ ኣስፓልቶች ሲከስሉ።
“አንመካም በጉልበታችን
እግዚአብሄር ነው የኛ ሃይላችን”
መስቀል ኣደባባይ ባንድነት ሲዘመር፣
ብላቴና ወድቆ የእናት ልብ ሲሰበር።
የት ነበሩ እነሱ?
በዘጠና ሰባት የከተሜ ትግል፣
ሽማግሌ ዝናብ ወርዶ ሲገላግል፤
የፌደራል ህንፃ
ጉልበት ሰራተኞች፣
ድንጋይ እየጣሉ፣ ፌደራል ሲደቁ፣
“በርቱ!” ባይ ያገኙት
የተግባረ–’ድ ልጆች ኣይተው ሲደነቁ፤
የታክሲ፣ ያውቶብስ፣ ሹፌር ሲተባበር፣
መስታወት ሲሰበር፣
ደም–እንባ ሲገበር፤
ጎረቤት የት ነበር?
ባለ–ኣገር የት ነበር?
–––
በርግጥ ቅን ነሽ እንጂ ፍፁም ኣይደለሽም፣
ኣንቺም ዘረኛ ኣለሽ፣ ኣንቺም ኣለሽ ቀሽም፤
የባህር ኣድናቂ መልካም ኣደረገ፣
ምንጩን ማደፍረስ ግን ለምን ኣስፈለገ?
–––
“ወይ ኣዲስ ኣበባ
ወይ ኣራዳ ሆይ
ኣገርም እንደ ሰው…” ያንቀላፋል ወይ።
–––
ሰኔ ኣንድ ልደታ ብትፈትን፣ ብትጨንቅም፣
ሸገር ኣዋቂ ናት!!
ልክ እንደ ህፃናት፣
ለጠብ በቀጠሮ፣ ሰላሳ ኣ’ጠብቅም።

Read 28382 times