Saturday, 12 September 2020 13:26

እንቁጣጣሽ

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(3 votes)

   እንኳን ከ2012 ዓ/ም ወደ 2013 ዓ/ም በሰላም አሸጋገራችሁ መጪው ዘመን ለመላውየኢትዮጵያ ህዝብ የሰላም፡ የጤና፡ የእድገት፤ የብልጽግና እንዲሆን የኢትዮጵያ የማህጸንና
ጽንስ ሐኪሞች ማህበር ይመኛል፡፡


             የኢትዮጵያ የጽንስና የማህፀን ሐኪሞች ማህበር ለመጪዉ 2013 አዲስ አመት እንኳን አደረሳችሁ ይላል። 2012 አ.ም የኮቪድ -19 ወረርሽኝ ወደ ዓለማችን እና ወደ ኢትዮጵያ የመጣበት አመት ነው።ይህ ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የጤና ቀውስ ሲያደርስ በሁሉም የሕይወት ዘርፎች ውስጥም ትልቅ ችግር አስከትሏል። የኮቪድ -19 ወረርሽኝ እ.ኤ.አ. ከ 2020 መጀመሪያ ጀምሮ በተለይ በጤና አጠባበቅ ሥርዓቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ ጫና አሳድሯል፣ ኢኮኖሚዎችን አስተጓጉሏል፣እንዲሁም በዓለም ዙሪያ በብዙ ሀገሮች ውስጥ ብዙ ማህበራዊ ክንዉኖች አስቁሟል።
የበሽታው ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ሰዎች የጤና አገልግሎቶችን መጠቀማቸዉ እንደቀነሰ የሚያረጋግጡ መረጃዎች እየታዩ ናቸው። በጤና ተቋማት ልጅ የሚወልዱ እናቶች ቁጥርም የመቀነስ አዝማሚያም ተስተውሏል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በወረርሽኙ ወቅት የቅድመ ወሊድ፣ የወሊድ እና የድኅረ ወሊድ አገልግሎቶች ተጠናክረው መቀጠላችው እና ያልታቀደ እርግዝናን ለመከላከል የእርግዝና መከላከያ መረጃዎች እና አገልግሎቶች መሰጠታቸው መቀጠሉን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው።ሰዎች የሚፈልጉትን የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ማግኘት መቻላቸው የእናቶችን ሞት ከመቀነሱም ባሻገር በጤናው ስርዓት ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ጫናዎችን ይቀንሳል። በተጨማሪም በዓለማችን ውስጥ በአደጋ ጊዜ በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት በዋነኛነት በሴቶችጤና ላይና ብሎም በዓለም አቀፍ የህዝብ ጤና ስጋት ሆኖ ቆይቷል።
የማህበረሰባችንን የስነተዋልዶጤና ለመጠበቅም የኢትዮጵያ የጽንስና የማህፀን ሐኪሞች ማህበርም ለአባላቱ በኮቪድ-19 እናበስነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶች ላይ የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ ነው።በኮቪድ -19 ወረርሽኝ ወቅት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል እና ለመቅረፍ የጤናው ዘርፍ እና ግለሰቦች ምን ማድረግ እንደሚችሉ አንዳንድ ቁልፍ መረጃዎችን እየሰጠ ይገኛል።
በዚህ ፈታኝ  ጊዜ የስነ-ተዋልዶ ጤና  አገልግሎቶችን በትጋት ለማህበረሰባችን  እያደረሳችሁ  ላላችሁ የጤና ባለሙያዎች ሁሉ በራሴ እና በኢትዮጵያ የጽንስና የማህፀን ሐኪሞች ማህበር ስም እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ።
ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ የማህበሩ አባላት የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶችን ለመስጠት ቁርጠኛ እንደሆኑ እያሳወቅን፤  ለምንወዳቸው እናቶቻችን እና ቤተሰቦቻችን ስንል እያንዳንዳችን ራሳችንን ከኮቪድ 19 እንድንጠብቅ አደራ እንላለን።
2013 ዓመተ ምህረት
የሰላም፣ የጤና እና የበረከት ዘመን ይሁንልን።
ዶ/ር መቅደስ ዳባ
የኢትዮጵያ ማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች ማህበር ፕሬዝዳንት

Read 10169 times