Print this page
Saturday, 12 September 2020 13:19

“ሹመቱን እንደ ትልቅ ሀገርን የማገልገል እድል እቆጥረዋለሁ”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

 የኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲቲዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት አንጋፋው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ” ሹመቱን እንደ ትልቅ ሀገርን የማገልገል እድል እቆጥረዋለሁ ሀገርን የማገልገል ትልቅ እድል ነው ያገኘሁት” ብለዋል፡፡
በጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በተሰጣቸው የም/ዳይሬክተርነት ሹመት ዙሪያ  አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው ፕ/ር በየነ፤ “እኔ የጥናትና ምርምር ሰው ነኝ፣ የተሰጠኝ ቦታም ጥናትና ምርምር የሚሠራበት በመሆኑ ከማራምደው የፖለቲካ አቋም ጋር አይጋጭብኝም” ብለዋል፡፡  “ፓርቲያችንም እድል ቢያገኝ ለሀገር ነው የሚሠራው፤ እኔም ባገኘሁት እድል ሃሳቤን ለሀገር ጠቃሚ በሚሆን መልክ የማቅረብ እድል ማግኘቴ መልካም አጋጣሚ ነው” ነው ያሉት -ፕ/ሩ፡፡
“ሀሳባችንን ይዘን ወደ ግብአተ መሬት ከመውረዳችን በፊት ለሀገር የሚጠቅም ሃሳብ እንድናዋጣ መደረጉ ትልቅ ጉዳይ ነው” ያሉት ፕ/ር በየነ፤ ድሮውንም ሲሆን ለሀገራችን አስተዋጽኦ ማድረጊያ ቀዳዳ አጥተን ነበር የተቸገርነው፤ አሁን ደግሞ እድሉ ሲገኝ በሚገባ መጠቀም ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ሹመቱን ሲሠጧቸው፤ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ መሆናቸውን ከግምት አስገብተው መሆኑን ለአዲስ አድማስ ያስረዱት ፕ/ር በየነ፤ የሰጡኝም ቦታ ለሀገሬ መልካም አስተዋጽኦ ማድረግ የምችልበት ቦታ ነው ብለዋል፡፡
እኔ ሹመቱን እንድቀበል የሳበኝ የጥናት ማዕከል መሆኑ ነው ያሉት ፕ/ር በየነ፤ ይህም ምሁራዊ አበርክቶ እንዳደርግ ይጠቅመኛል፤ ተቋሙም ትልቅ መሆኑን ተረድቻለሁ” ብለዋል።
በፓርቲያቸው በኩል የሚያደርጉት እንቅስቃሴና የፖለቲካ አቋም የማይለወጥ መሆኑን ያስገነዘቡት ፕ/ር በየነ፤ ሹመቱም ይህን አቋሜን በጠበቀ መልኩ የተሰጠ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡  “ዝም ብሎ በተቃዋሚ ስም ግራና ቀኝ መወራወር የትም አያደርስም፤ እንዲህ ያሉ እድሎች ሲገኙ ጠጋ ብሎ አጋጣሚውን መጠቀም ተገቢ ነው” ብለዋል፡፡
አንጋፋው ፖለቲከኛ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ፤ በአሁኑ ወቅት የብሔራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን አባል እንዲሁም ግዙፍ የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዘዋወር የተቋቋመው ኮሚቴም አባል እንደሆኑ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል። በኢህአዴግ የሽግግር ዘመን የትምህርት ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር በመሆን ተሾመው እንደነበር አይዘነጋም፡፡  

Read 9931 times