Print this page
Sunday, 06 September 2020 15:57

ዋዜማውን በእውቀት!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
የምር ግን ይሄ “ጊዜው ይሮጣል…” የምንለው ነገር…አለ አይደል…ሳይንሱ ቢስቅብንም ‘እየሮጠ ያለ’ የሚያስመስለው የሆነ ነገርማ አለ፡፡ ይኸው ‘ሌላ ዓመት’ ደግሞ ሽው ብሎ ሊያልፍ ነው…‘ሽው፣ ሽው’ ሲያደርገን ከርሞ፡፡ የምር ግን…ሰኞ ይሆንና ሀሙስና ቅዳሜ ገና የደረሱ ሳይመስል እንደገና ሰኞ የሚሆነው በየትኛው ‘ካልኩሌሽን’ ነው? ብቻ…ያው  ጫፉ ላይ ደርሰናል፡፡ ሰላማዊ ሽግግር ያድርግልንማ! (እንትናዬ፣ በርዝደይ ኬኩ ላይ ያሉት ሻማዎች ስንት ደረሱ?)
ባለፈው የትንሳኤ በዓል ዋዜማ ቀናት በየገበያው የነበረው ‘ትርምስ’ ትዝ ይላችኋል? “እባካችሁ፣ የራሳችሁንም፣ የህብረተሰቡንም ደህንነት በጠበቀ መልኩ ተንቀሳቀሱ…” እየተባለም፣ “ህዝብ ከበዛባቸው ስፍራዎች ራሳችሁን አርቁ፣ የዛሬ መዘናጋት ነገ ችግር ያመጣል…” እየተባለም  ከማን ጋር እልህ እንደተጋባን እሱ ይወቀው እንጂ፣” በየገበያው ተዛዝለን ስንጋፋ ከረምን:: ይኸው እስከ አሁን ዋጋ እየከፈልን ነው..ከፍ ያለ ዋጋ፡፡
እናም… ምንም እንኳን ካለፉ ስህተቶች በመማር የሚጨበጨብልን ባንሆንም…የዛ ጊዜ ቸልተኝነት ሰሞኑንም የሚደገም ከሆነ ነገሮች እጅግ አስቸጋሪ ነው የሚሆኑት፡፡
ስሙኝማ…መቼም እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ዘንድሮ የዳያስፖራ ዘመዶቻችን እንደቀደሙት ዓመታት በብዛት ላይመጡ ይችላሉ፡፡ ብቻ በያሉበት ሰላሙንና ጤናውን ይስጣቸውማ! ከእኛም ዘንድ እንደ ፈረንጅ የሚያደርጋቸው የሀበሻ ‘እንቁጣጣሽን’…አለ አይደል… በ‘ፈረንጅ ሰፈር’ ለማክበር የሚሄዱ መአት ነበሩ፡፡ ዘንድሮ የውሀ መንገድ ብሎ ነገር የለም እንጂ! እኔ የምለው… ለበርገር ምን በዓል መጠበቅ ያስፈልጋል! ቂ…ቂ…ቂ…
“በነገራች ላይ እስካሁን የት፣ የት ሄደሃል?”
“ማለት…”
“ማለትማ ለጉብኝት፣ ለሽርሽር…”
“እዚህ በታች በኩል እስከ  ሦስት ቁጥር ማዞሪያ፣ ወደ ላይ ደግሞ እስከ ሱሉልታ መግቢያ…”
“አትቀልድ፣ እስካሁን የት፣ የት አገር ሄደሀል?”
“እናንተ የደላችሁ ሂዱ፡፡ እኔ አንድም አገር አልሄድኩም…”
“ምን! የትም አልሄደኩም ማለት ምን ማለት ነው?”
“የትም አልሄደኩም ማለት ነው…”
“ዱባይ እንኳን አልሄደክም!”
ይቺ…“ዱባይ እንኳን አልሄደክም!” የሚሏት ነገር ተደጋግማ የምትሰማ ነች:: ልክ እኮ ሰዉ በየአውቶብስ ፌርማታው አይደለም በትልቁ አውቶብስ፣ ‘ሀይገር ባስ’ በሚሉት ላይ “ዱባይ በመቀመጫ!” እየተባለ የሚሳፈር ነው የሚመስለው፡፡ እናላችሁ…ዱባይ የእኛ ሰው ‘ሆሊዴይ ዴስቲኔሽን’ ሆናለች፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ የዋዜማ ሰሞን አይደል…መቼም ዘንድሮም በወሰራ ዶሮና በግንባረ ነጭ  ጥቁር በግ ጭቅጭቅ ያለባቸው ቤቶች ካሉ ልዩ የቲቪ ፕሮግራሞች ይሠሩላቸውማ! 
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…“እንገማገም” የሚሏት ነገር በየቤቱ ገብታ ነበር፣ አይደል! አሁንም “ዘ ሴም ኦልድ ስቶሪ፣” ነው ወይስ ቢ.ፒ.አር. ተካሂዶባታል:: 
“እንድንወያይ እፈልጋለሁ፡፡”
“ብለሽ፣ ብለሽ ወር መሀል ላይ ገንዘብ አምጣ እንዳትዪኝ!”
“በቀደም ምሳ ከበላህ በኋላ በተናገርከኝ ነገር ላይ መገማገም እፈልጋለሁ፡፡”
“እየፈጩ ጥሬ! የመሥሪያ ቤቱ አላስቀምጥ ብሎኛል፣ እንገማግም የሚሏት ነገር ቤቴ ሰተት ብላ ገባች! እሺ…ቀጥይ፡፡”
“ስለ እኛ ነው የማወራው፣ ስለ መሥሪያ ቤት አይደለም፡፡”
“ጥሩ፣ እንገማገም፡፡ ይቅርታ፣ ገምግሚኝ::”
“በቀደም ምሳ ከበላህ በኋላ ደጋግመሽ ምስር የምታቀርቢልኝ ሆዴ ውስጥ አሸዋ ግርፍ ልትሠሪ ነው ባልከው ላይ እንድንገማገም እፈልጋለሁ፡፡ ምን ለማለት ፈልገህ ነው?”
ጉድ ፈላ! አንድ ሰሞን ‘ሽርርር’ የምትል የቀጠነች ሹሮ ሲባዛበት…አለ አይደል… “እንዴት ነው፣ ውሃውም የሚጠጣ፣ ሹሮውም የሚጠጣ፣” ሊላት ፈልጎ ከአፉ የመለሰው ትዝ ይለዋል፡፡  እናማ… የመከላከል አዋጩ ዘዴ ማጥቃት ነው ወደሚባለው ‘ስትራቴጂ’ ይዞራል፡፡ ግምገማ ከሆነ ሁሉ ነገር ‘አጄንዳ’ መሆን ይችላላ!
“አንቺ በቀደም በየቀኑ ቢራ የምታንቃርረው አንደኛውን ለምን ፋብሪካው ሄደህ በርሜሉ ስር አትቀመጥም ባልሽው ላይ መገማገም እፈልጋለሁ፡፡”
“ምን ያገናኘዋል! እኔ የምለው ሌላ፣ አንተ የምትለው ሌላ፡፡”
“ምንም ሌላ፣ ሌላ ብሎ ነገር የለም:: አንቺም ምስር ደጋግመሽ ሠራሽ፣ እኔም ቢራ ደጋግሜ ጠጣሁ…”  በቃ ግምገማ ነዋ! የራሱን ኑሮ እየኖር፣ ከሰው ብዙ ሳይቀላቀልና ሰው ላይም ሳይደርስ የተሰጠውን ሥራ በአግባቡ የሚሠራ ሰው እኮ… “ኩራተኛ ነው፣ ሰው ሰላም አይልም…” አይነት ግምገማ የሚደረግበት ዘመን እኮ ነው! ‘ቦተሊካችን እኮ ያላተራመሰው ነገር የለም፡፡ ይቺን ስሙኝማ…
የቀዶ ጥገና ሀኪም፣ ኢንጂነርና ፖለቲከኛ ስለ ሙያቸው እያወሩ ነበር፡፡ ቀዶ ጥገና ሀኪሙ እንዲህ አለ… “ሔዋን ከአዳም የጎድን አጥንት ነው የተሠራችው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የቀዶ ጥገና ጥበብ ማለት ነው፡፡”
ኢንጂነሩ ደግሞ እንዲህ አለ…“ትክክል፣ ግን ከዛ በፊት ሁሉም ነገር የተተራመሰ ነበር፡፡ የተስተካከለውም በኢንጂነሪንግ ሙያ ነው፡፡”
ይሄኔ ፖለቲከኛው ደረቱን ነፋ አድርጎ ምን ቢል ጥሩ ነው… “ታዲያ ትርምሱን የፈጠረው ማን መሰላችሁ!” አሪፍ አይደል! ብቻ ይህ ፖለቲከኛ የእኛው ጉድ እንዳይሆን!
አናላችሁ…አዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ ሆነን…አለ አይደል… “ፍሳሽ የጎርፍ ውሀ…” የማተራመሻ ሰበብ የሆኑትን ነገሮች ሁሉ ጥርግ አድርጎ እንዲወስደልን እንመኛለን:: ከሁሉም በላይ እርጋታውን ይስጠንማ! በምኑም፣ በምናምኑም፣ በተለይ ደግሞ በፖለቲካው፣ እርጋታ እየጠፋ ነው ደጋግመን እንደ ጅብ ችኩል ቀንድ እየነከስን ያለነው:: ሁለተኛ ማርሽ ለሚበቃው ቁልቁለት አምስተኛውን ማርሽ እስከ ጥግ እያስገባን ነው የምንረግጠውን መሬት ማየት እያቃተን መደነቃቀፍ የበዛው፡፡ ይቺን ስሙኛማ…
አንድ የአውቶብስ ሾፌርና አንድ የኃይማኖት ሰባኪ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት በር ላይ ቆመዋል፡፡ መጀመሪያ አውቶብስ ጠባቂው በር ላይ ደረሰና በሩ ላይ የነበረው ኃላፊ መልአክ እንዲህ ይለዋል፡፡
“እንኳን ደህና መጣህ፡፡ የአውቶብስ ሾፌር እንደሆንክ ይገባኛል፡፡ የቤት ጉዳይ የሚመለከተው እኔን ነው፡፡ ለአንተ በጣም ጥሩ ስፍራ አግኝቼልሀለሁ፡፡ እዛ ማዶ ጋራው ጫፍ ላይ ያለ የተንጣለለ ቤት ይታይሀል? የአንተ ነው፡፡”
ሰባኪው ይህን ሲሰማ ኮራ ማለት ጀመረ::  ለራሱም… “ለአውቶብስ ሾፌር ይህን የመሰለ ቤት ከተሰጠ እኔ የማገኘውማ ቤተ መንግሥት ይሆናል፣” ብሎ ያስባል፡፡ እናማ ወደ መንግሥተ ሰማያት በር ሲጠጋ ሀላፊው መልአክ ይቀበለዋል፤፡ “እንኳን ደህና መጣህ:: ሰባኪ እንደሆንክ ይገባኛል፡፡ እዛ ሸለቆ ውስጥ ያለችው ደሳሳ ጎጆ ትታይሀለች? የአንተ ነች፡፡”
ሰባኪው ብሽቅ ይላል፡፡ “እኔ ሰባኪ ነኝ፡፡ ህዝቡን ስለ ሀይማኖቱ ሳስተምር ኖሬያለሁ፡፡ የአውቶብስ ሾፌር የተንጣለለ ቤት እያገኘ ለእኔ እንዴት ደሳሳ ጎጆ ይሰጠኛል?” ሲል ይቃወማል፡፡ ይኸኔ ሀላፊው መልአክ ራሱን እየነቀነቀ ምን ቢለው ጥሩ ነው…
“አንተ ስትሰብከ አዳራሹ ውስጥ ያለ ሰው ሁሉ ያንቀላፋል፡፡ የአውቶብስ ሾፌሩ ሲያሽከርክር ግን አውቶብሱ ውስጥ ያለው ሰው ይጸልያል፡፡”
ሾፌሮች ሆይ… “ፍጥነት መንግሥተ ሰማያት ቪላ ካስገኘማ…” ብላችሁ ያለን ትርምስ አይበቃ ይመስል በላዩ እንዳትጨምሩብንማ! ከወራት በፊት የነበረው እንዳይደገም እባካችሁ፣ እባካችሁ ግብይታችን በእውቀት ይሁን!
መልካም የአዲስ ዓመት ዋዜማ ቀናት ይሁኑላችሁማ! ዋዜማውን በእውቀት!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 2003 times