Saturday, 21 July 2012 12:11

አሜሪካን አይዶል ዳኛ እያፈላለገ ነው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

በአሜሪካ ከሚታዩ የቲቪ ፕሮግራሞች በሁለገብ ስኬቱ ይታወቅ የነበረው አሜሪካን አይዶል በዳኞች መመናመንና በተመልካች ማነስ ሊዳከም እንደሚችል ቺካጎ ትሪቡን አስታወቀ፡፡ በወራት ግዜ ውስጥ 12ኛውን የውድድር ዘመን ለመጀመር በዝግጅት ላይ የሚገኘው የቴሌቭዥን ፕሮግራሙ ላለፉት ሁለት ተከታታይ በዳኝነት የሰሩለት እውቅ ድምፃውያኑ ጄኒፈር ሎፔዝና ስቲቨን ቴይለር ከዳኝነታቸው መገለላቸውን ከገለፁ በኋላ ለምትካቸው በከፍተኛ ሩጫ ላይ ይገኛል፡፡ የአሜሪካን አይዶልን በዳኝነት እንዲመሩ በርካታ እውቅ ድምፃውያንና አርቲስቶች እየተጠቆሙ ሲሆን የፕሮግራሙ ሃላፊዎች በተለይ በድምፃዊነቷ ዓለምአቀፍ ተምሳሌት ያላትን ማርያ ኬሪ ለመቅጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡

የ70ዓመቷ የሶል ንግስት አሪታ ፍራንክሊን እጅግ በማከብረው የአሜሪካን አይዶል ፕሮግራም ላይ በዳኝነት ብሰራ ደስ ይለኛል ብላ ለሲኤንኤን መናገሯም ትኩረት ስቧል፡፡የማርያ ኬሪ ባል የሆነውና የአሜሪካ ጎት ታለንት አስተዋዋቂ ሆኖ የሚሰራው ኒክ ካነን የአሜሪካን አይዶል ሃላፊዎች ባለቤቴን ለመቅጠር መፈለጋቸው ደስ ቢልም ክፍያዋን መቻላቸው ያጠራጥረኛል የሚል አስተያየት ሰጥቷል፡፡ ለጄኒፈር ሎፔዝ 20 ሚሊዮን ዶላር መክፈላቸውን እንደሚያውቅ የገለፀው ኒክ ካነን ማርያ ኬሪ እጥፍ ሊከፈላት ይገባልም እያለ ነው፡፡ ከወራት በፊት በተጠናቀቀው 11ኛው የአሜሪካን አይዶል በውድድሩ ታሪክ ዝቅተኛው ተመልካች መመዝገቡን ያስታወሰው ቺካጎ ትሪቡን በፕሮግራሙ ላይ በመስራችነት ከነበሩት የቀረው ማነጀሩና ፕሮዲውሰሩ ራንዲ ጃክሰን ብቻ መሆኑን ገልፆ በውድድሩ ላይ ዳኞች በቋሚነት አለመቀጠላቸው ለነበረው ስኬት ጋሬጣ ይሆናል ብሏል፡፡

 

 

 

 

Read 979 times Last modified on Saturday, 21 July 2012 12:18