Sunday, 06 September 2020 00:00

በአዲሱ ዓመትስ ምን እንጠብቅ?

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

  በየዓመቱ ሐምሌ 1 ቀን የሚጀምረው የኢትዮጵያ መንግሥት የባጀት ዓመት የሚያልቀው ወይም የሚዘጋው በየዓመቱ ሰኔ 30 ቀን ነው፡፡ ሲቆጠብ የከረመው ገንዘብ ተጣድፎ ሰኔ ላይ ነው ወደ ሥራ የሚገባው፡፡ ሹማምንቱ የቢሯቸውን ወንበር የሚቀይሩት፣ ‹‹መሐረብ›› ሳይቀር የሚገዙት በሰኔ ነው፡፡ ሐምሌ የአዲሱ ዓመት የባጀት መጀመሪያ ነው ቢባልም፣ ሥራ የሚጀመረው መስከረም ላይ ነው፡፡ ሐምሌና ነሐሴ ደመወዝ ከመክፈል ያለፈ የሚጠቀስ ሥራ የሚሰራባቸው አይመስሉም፡፡
አሁን አሁን በሀገራችን ፖለቲካ፣ የበጀት መዝጋትና መክፈት የሚመስሉ ሥራዎች እየተሠሩ ነው የሚያሰኙ ተግባራት እየተፈጸሙበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ አምና ሰኔ ወር 2011 ዓ ም የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር (ፕሬዚዳንት) ዶ/ር አምባቸው መኮንንና ሁለቱ የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፤- አቃቤ ሕጉ አቶ ምግባሩ ከበደና የከልሉ ርዕሰ መስተዳድር አማካሪ አቶ አዘዝ ዋሴ ባሕር ዳር ላይ ተገደሉ:: አዲስ አበባ ላይ ደግሞ ብዙም የሰዓት ልዩነት ባልታየበት ሁኔታ፤ በኢትዮጵያ ጦር ከፍተኛውን ሥልጣን የያዙት ኤታማዦር ሹሙ ጀኔራል ሰዐረ መኮንንና ሜጀር ጀኔራል ገዛኢ አበራ ተገደሉ፡፡ አዲስ አበባንና ባሕር ዳርን የመሳሰለው የሞት ድግስ እንዴት ቀድሞ ሳይደረስበት ቀረ? የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም፡፡ ዛሬም ይህ ጥያቄ፤ ከአሳምነው ጽጌ ጋር ሞቷል ለማለት ይከብዳል፡፡
በ2011 ዓ.ም የገጠመውን ችግር ይፈታልኛል ብሎ ያሰበው የሳይንስና  የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ፣ በ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን መጀመሪያ ላይ የየዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ምንም አይነት ረብሻ ላለመቀስቀስ ውል ገብተው እንዲመጡ ቢያደርግም፣ ትምህርት ማቆሙንም ሆነ መገዳደሉን ሊያስቀረው አልቻለም፡፡ ለሕይወታቸው የሰጉ የደምቢ ደሎ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጠለፋና አድራሻ መጥፋት፣ ዛሬም የተማሪዎችን ወላጆች ብቻ ሳይሆን አገርንም እያስጨነቀ ያለ ችግር መሆኑ ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ከተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን እያደረጉት ያለው ዘር ተኮር ቅስቀሳ ለምን ችላ ተባለ የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ ለዚህ በሰጡት ምላሽም፤ የውጭ አገር ዜግነት ይዘው ተገቢ ያልሆነ ሥራ የሚሰሩ እንዳሉ ጠቅሰው፤ ከአድራጎታቸው እንዲቆጠቡም አሳሰቡ፡፡ ነገሩ ለእኔ ነው ብሎ ያመነው አክቲቪስቱ ጀዋር ሞሐመድ፤ በጥቂት ቀናት ውስጥ የሚፈልገውን አጋጣሚ አገኘ፡፡ #የተሰጠኝ የጥበቃ ኃይል እየተነሳ ነው፤ ለሕይወቴ እሰጋለሁ; (ተከብቤአለሁ!) የሚል መልእክት ለደጋፊዎቹ አስተላለፈ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥም ብዙ ወጣቶቹ  ከቤቱ አካባቢ የደረሱ ሲሆን በክልል የሚገኙ ደጋፊዎቹ መንገድ በመዝጋት ተቃውሟቸውን አሰሙ:: አቶ ታየ ደንደና በቅርብ በሰጡት መግለጫ እንዳሳወቁት፤ አቶ ጀዋር ነገሩ መለወጡንና ሁኔታው መረጋጋቱን እንዲገልጽና ደጋፊዎቹን እንዲያረጋጋ ተጠይቆ፣ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ተከታዮቹ በሁለተኛው ቀን የጥፋት እጃቸውን አነሱ፡፡ ምንም መከላከያ በሌላቸው ንጹሐን ላይ የመከራ መአቱን አወረዱት፡፡ ሰዎች እንደ ከብት ታረዱ፡፡ ዶዶላ ላይ የእናት ጡት ተቆረጠ፡፡ ጎባ ላይ ያለ ምንም መጨነቅ በአደባባይ ‹‹ ከአማራ ጋር አትገበያዩ›› የሚል ቅስቀሳ ተካሄደ:: እነ ጀዋር ኃይላቸው ቀላል አለመሆኑን ለመንግሥት አሳዩ ተባለ፡፡ በዚህ  የሁለት ዝሆኖች ፉክክር፤ 97 ሰዎች ሕይወታቸውን አጡ፡፡ ይህን የሟች ቁጥር መንግሥት በቅርቡ ማሳወቁ አይዘነጋም፡፡
ዓለምን ያንቀጠቀጠው ኮቪድ 19 መጋቢት መጀመሪያ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ገባ፡፡ የፖለቲካ ውዝግቡ ረግቦ፣ ሁሉም አገርን በመታደግ ላይ ያተኩራል ተብሎ ሲጠበቅ እንደገና አቧረው ጤሰ፡፡ መንግሥት በሽታውን ለመከላከል አስቸኳይ አዋጅ አወጀ፡፡ በሽታው መቼ በቁጥጥር ሥር እንደሚውል ስለማይታወቅ፣ በበሽታው የመተላለፊያ መንገድ የተነሳ ምርጫ ማካሄድ ስለማይቻል፣ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት፣ ሕገ መንግሥታዊነቱ ስለሚያበቃ  በሚል፣ የመንግሥቱን እድሜ ለማራዘም የሕግ ማሻሻያ አስፈለገው፡፡ ወደ ሕገ መንግሥት ትርጉም ገብቶ፣ ኮሮና በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ በዘጠኝ ወር ውስጥ አገር አቀፍ ምርጫ እንዲካሄድ በምክር ቤት አስወሰነ፡፡ ተቃዋሚዎቹ በተለይም እነ ጃዋር ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ገዥው ፓርቲ ሥልጣን እንደሌለው፣ መንግሥቱ ሕገ ወጥ መሆኑንና ጦሩም ሊታዘዘው እንደማይገባ ቀሰቀሱ፡፡ ኢትዮጵያ መንግሥት አልባ አገር ትሆናለችም ተባለ:: የሽግግር ወይም የባለ አደራ መንግሥት እንዲቋቋም ተጠየቀ፡፡ መንግስት፤ ቃል በቃል ባይሆንም፣ "ቀልዳችሁን አቁሙ" ብሎ ተቆጣ፡፡
ሰኔ እንደተለመደው ጊዜውን ጠብቆ መጣ፡፡ መምጣቱን የሚጠብቁ አካላት ተወዳጁን አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን፣ ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም አስገደሉ፡፡ ይህ ግድያ መፈጸሙን እንደሰሙ ወደ ተሰጣቸው ግዳጅ እንዲገቡ የተዘጋጁት ቡድኖች፤ሜንጫ፣ ገጀራና ሌላውንም ድምጽ አልባ መሣሪያ ይዘው፣ ከቦታ ወደ ቦታ የሚያንቀሳቅሳቸው መኪና መድበው፤ ዘርና ሃይማኖት እየለዩ በስም እየጠሩ፣ ሰው ለመግደልና ንብረት ለማውደም ተሰማሩ፡፡ በዝዋይ፣ በሻሸመኔ፣ በአርሲ ነገሌ፣ በአጋርፋ፣ በድሬ ዳዋና በሌሎችም ቦታዎች ብዙ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደሉ፡፡ በቢሊዮን የሚገመት ንብረት ወደመ፡፡ ባሁኑ ጊዜ የማቋቋም ሥራ እየተሠራ ቢሆንም፣ የተሰበረን ኅሊና ለማከም ግን ብዙ ጊዜ መጠየቁን መገንዘብ አያዳግትም፡፡
ጥቅምት 2012 ክፉ ክስተት የታየበት ወር ቢሆንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የመጀመሪያው የኖቤል ተሸላሚ ኢትዮጵያዊ  የሆኑበትም ታሪካዊ ወር ነበር:: በብዙ የሀገራችን አካባቢዎች የደስታ መግለጫ ሰልፎች ተደረጉ፡፡
ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ሳተላይት ማምጠቋ፣ የዚያድ ባሬ ወራሪ ጦር የተደመሰሰበት የካራ ማራ ድል ለመጀመሪያ ጊዜ ታስቦ መዋሉ፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እራሱን ነጻ አድርጎ የዜጎችን ሰብአዊ መብት ለማስጠበቅ በጽናት መቆሙ፣ የዚህ ዓመት ትሩፋቶች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ሌላው ትሩፋት የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ነው፡፡ የዓለም ባንክንና የአሜሪካንን መንግሥት በታዛቢነት ተቀበሎ ለድርድር ወደ አሜሪካ የተጓዘው የኢትዮጵያ መንግሥት፤ሁለቱ መንገድ ሲለቁ ወንበሩን ለቆላቸው በመውጣት ሃፍረታቸውን አከናንቧቸዋል፡፡ "ከእኛ ጋር ሳትስማሙ የሕዳሴውን ግድብ አትሞሉም" እያሉ ሲዝቱ የነበሩትን ግብጽና ሱዳን፣ በራሱ ጊዜ ውኃውን ሞልቶ፣ ሥልጣኑ የእሱ እንጂ የእነሱ አለመሆኑን በአደባባይ አሳይቷቸዋል፡፡ ዐቢይ ለአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ያሳዩት ‹‹ብቀጥንም ጠጅ ነኝ›› ተግባራዊ መልስ ‹‹አበጁ›› የሚያሰኝ የዚህ አመት ተግባር ነው፡፡ ነገሩ የሆነው እንዲህ ነበር፡፡ ማይክ ፖምፒዮ አዲስ አበባ መጥተው በነበሩበት ጊዜ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ ተቀብለው ወደ ቢሯቸው ይሄዳሉ፡፡ እሳቸውን ለመቀበል ከቢሯቸው የወጡት ጠ/ሚኒስትሩ፤ቢጠብቁ ቢጠበቁ ማይክ ፖምፒዮ ከመኪናቸው አይወርዱም:: መኪናቸው ውስጥ ሆነው ፎቶ አንሺ  የሚጠብቁትን ሰውዬ እደጅ ትተዋቸው ዐቢይ ወደ ቢሯቸው ተመለሱ፡፡  ፖምፒዮን ያነጋገሯቸው ውቃቤያቸውን ከገፈፏቸው በኋላ ነበር፡፡
ከሕወሐት በስተቀር የኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች አንድ ሆነው የብልጸግናን ፓርቲ የመሠረቱት በዚህ ዓመት ነው፡፡ የሕወሓትን የሴራ መንገድ እንደሚከተሉ፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልሽ አብዲሳ፤በኦሮምኛ መናገራቸውን የሰማነው ዘንድሮ ነው፡፡ ደጉ ነገር፤ ምስጢሩ መውጣቱ ነው፡፡ ለሕወሓት ያልበጀ መንገድ፣ ለኦሮሞ ብልጽግና እንደማይበጅ የሚገነዘቡበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ተስፋ አለኝ፡፡
ዶ/ር ዐቢይ ‹‹የከረመ ብሶት የፈጠረው ግንፍልተኝነት ነው›› ሲሉት የነበረው ብሶት፤ ደሃ አርሶ አርሶ አደሮችን ለማፈናቀል፣ አስራ ስምንት ባንኮችን ለመዝረፍ፣ ሰዎች በገዛ መንደራቸው ታስረው እንዲደበደቡ፣#ማነው ባለ ተራ; እየተባሉ ለመገደል፣ በዘራቸው ወይም በሃይማኖታችው እየተለዩ የጥቃት ሰለባ ለመሆን ወዘተ--ዜጎችን ዳርጓል፡፡ በአዲሱ ዓመትስ (በ2013) የሚጠብቀን ምን ይሆን?
‹‹የንጋት›› ሰዎች፤ ይህ ቀን እንደሚለወጥ ቢነግሩንም፣ እነሱ ራሳቸው ፊታቸውን ወደ ጨለማው ሲያዞሩ እያየን ነው፡፡ መግባባትና መደማመጥ ርቋቸው፣ እርስ በርስ ሲካሰሱ እየታዘብን ነው፡፡ የፖለቲካ ችግርን በድርድር መፍታት እንደ ሰማይ ርቆ፣ አንዱ በሌላው ላይ የፕሮፓጋንዳ ጦር ሲሰብቅ ከርሟል፡፡ ሕወሓትና ማዕከላዊ መንግሥት ለዚህ ጥሩ ምስክሮች ናቸው፡፡
በጥያቄ እንጨርስ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን መንግሥት፣ በመጪው አዲስ ዓመት የምናገኘው የት ነው? ምን ያሰበልን ነገር አለ? መንግሥትን ለማንበርከክ፣ ሕዝብን ለመከራ መዳረግን ስልታቸው አድርገው የመረጡ የፖለቲካ ኃይሎች፣ እጃቸው ላይ ምን ይዘዋል? በእርግጠኝነት መገመት ያዳግታል፡፡ እኛ ግን መልካሙን እንመኝ፡፡
 አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የፍቅርና የጤና ይሁንልን!!

Read 1305 times Last modified on Sunday, 06 September 2020 16:13