Monday, 07 September 2020 00:00

የዘረኝነት ማርከሻ 2 መፍትሔዎች!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

       • ዘረኝነትንና መዘዞቹን የምናወግዝበት “ቋንቋ” ጠፍቶብናል፡፡
        • “ሰዎችን እንደራስህ ውደድ” የሚለው ፈሊጥ መፍትሔ ይሆናል?
             
            አገራችን ለይቶላት አለመፍረሷ፣ የሚሊዮኖች ሕይወት አለመርገፉ፣ “ተመስገን” ያስብላል -የዘንድሮው ከባድ ዓመትና የኢትዮጵያ የፈተና ብዛትኮ፣ ያደነዝዛል፡፡
ከቋንቋም ለቁጥርም ይቸግራል፡፡ አንድ ሁለት እያሉ ቢለኩት ቢቆጥሩት፣ ይጀምሩታል እንጂ አይዘልቁትም፡፡
የብዙ ሰዎች ሕይወት ተቀጥፏል፡፡ አካል ጐድሏል፡፡ እልፍ በእልፍ፣ ከኑሯቸው ተነቅለው ተሰደዋል፡፡ መጠለያ መተዳደሪያቸው ተቃጥሎ፣ ትቢያ ላይ ቀርተዋል፡፡
ኢንቨስትመንት እየወደመ፣ በአመታት ጥረትና ድካም የተጠራቀመ የስራ ፍሬ፣ እንደዘበት አመድ ሆኗል፡፡ እልፍ ሰዎች፣ እንደገና ወደ ስራ አጥነት ወርደዋል፡፡ እንደ ብዙ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን፣ የኑሮ ተስፋ ርቋቸው፣ ቀኑ ጨልሞባቸዋል፡፡ ስንት ድርጅት፣ ስንት ሱቅና መኪና፣ እንደዋዛ እየጋየ፣ እንዴ አይጨልምባቸውም? እልፍ ሰዎች መተዳደሪያ አጥተው፣ ኑሯቸው ጽልመት ቢያጠላበት፣ ምን ይገርማል?
በየቦታው ዓመጽና ሁከት እየተራባ፣ በየአቅጣጫው መንገድ እየተዘጋ፣ አምርቶ የመነገድ፣ ሰርቶ የመኖር፣ ወጥቶም የመግባት መንቀሳቀሻ ሲጠፋ፣ ወዴት ይኬዳል? በመላ አገሪቱ፣ ሰላም ሲደፈርስ፣ ኑሮም ይባስኑ ሲናጋና ሲፍረከረክ፣ እንዳለፉት ዓመታት ዘንድሮም አይተናል፡፡ ግን፣ ለወደፊትም መዘዝ ያመጣል፤ ለሚቀጥለው አመትም ጦስ ይሆናል፡፡
የእለት ተእለቱ ጥፋትና መከራ እጅግ አሳዛኝ ነው፡፡ ግን ደግሞ፣ የዛሬ ጥፋት፣ ለነገና ለተነገወዲያ፣ በገፍ እየጐተተ የሚያመጣብን እዳ ይብሳል፡፡ እያንዳንዱ የጥፋት አዙሪት፣ በእለቱ ሕይወትን የመቀጠፉና ኑሮን የማውደሙ ያህል፤ የነገ አለኝታችንንም ይሸረሽራል፡፡
ውስጣዊ የሰውነት መንፈሳችንን ያጠወልግብናል፡፡ መሰረታዊ የአገርነት አቅማችንን ያመክንብናል፡፡
ዛሬ በሚፈፀም ጥፋት ሳቢያ፣ ዋና ዋና ነገሮቻችን በተሸረሸሩ ቁጥር፣ ነገ ከነገ ወዲያ፣ እጅግ ለከፋ የጥፋት ዙር እንመቻቻለን እንዴት በሉ፡፡
“አሳፋሪ ንግግር”፣ “አስነዋሪ ተግባር” ተብለው ሲወገዙ የነበሩ በርካታ አስፀያፊ ነገሮች፣ ከቀን ወደ ቀን፣ እየተዘወተሩና እየተለመዱ አልመጡም እንዴ? ዘረኝነትና ጭፍንነት፣ ክፋትና ጭካኔ፣ እየተባባሱ፣ ይበልጥ አፍጥጠው አግጥጠው አደባባይ አልወጡም እንዴ?
“የእገሌና የእከሌ ብሔረሰብ” እያሉ በዘር መቧደን፣ ሃላል ሆኗልኮ፡፡ “የእንትና የእንቶኔ ሃይማኖት” እያሉ በተከታይነት መንጋጋት፣ በጣም ተለምዷልኮ፡፡ “ሃብታምና ድሃ” እያሉ በማገዶነት ወይም በምቀኝነት መፋጀት፣…ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረከተና እየተባባሰ አልመጣም እንዴ? አዎ፤ ጭፍንነትም ዘረኝነትም፣ ከዙር ወደ ዙር፣ ከጥፋት ወደ ጥፋት፣ እየጦዙ እንጂ እየበረዱ አይደሉም፡፡
አስፈሪው ነገር፣ ይህን ሁሉ ጥፋት በእውን እያየንም፣ ጥፋትን መግታትና ዘረኝነትን መከላከል አልቻልንም፡፡ ከነአካቴው፣ ለወሬ አስቸጋሪ ሆኖብናል፡፡ የየእለቱን የጥፋት ክስተት በቅጡ ለመገንዘብ የሚያስችል የአስተሳሰብ አቅም አጥተናል፡፡ ከእውቀት ርቀናል፡፡  
በተቃና መንገድ አስበን፣ በትክክል የምንገልጽበት ቋንቋ የጠፋብንም፣ በዚህ ምክንያት ነው፡፡
ወይ በድፍኑ፣ “የሰው ሕይወት አልፏል፤ ንብረት ወድሟል” እንላለን፡፡ ከዚህ ውጭ፣ በግልጽ ዘርዝረንና ተንትነን መናገር ተስኖን በዝምታ እንዋጣለን፡፡
ወይም ደግሞ፣ በግልጽ የተናገርን እየመሰለን፣ ወደ አስቀያሚው የዘረኝነት ረግረግ፣ ዘልለን እንገባበታለን፡፡  በዝርዝር ለመናገር ስንሞክር፣ ለተጨማሪ የጥፋት ዙር፣ ተጨማሪ ቅስቀሳ እየጠነሰስንና እያማሰልን፣ ወደባሰ የዘረኝነት ማጥ እንዘፈቃለን፡፡ እንዴት? “ግድያ ፈፃሚዎች የእከሌ ብሔረሰብ”፣ “ንብረት ዘራፊዎች፣ የእገሌ ሃይማኖት”፣ “አፈናቃይ የእንትን ጐሳ”፣ “መንገድ የዘጉና ያቃጠሉ የእንቶኔ ብሔረሰብ”…እያሉ የጭፍንነትና የዘረኝነት አስተሳሰብን የሚሰብኩ አሉ፡፡ ማለትም፣ ዘረኝነትን የተቃወሙ እየመሰላቸው ወይም እያስመሰሉ፣ ዘረኝነትን ያግለበልባሉ፡፡ ዘረኝነትን ለመከላከል የሚያስችል “ቋንቋ” የላቸውም፡፡ ወይም እንዲኖር አይፈልጉም፡፡
“የሞተው የእከሌ ሃይማኖት ተከታይ”፣ “የተፈናቀለው፣ የተዘረፈውና ንብረት የተቃጠለበት የእከሌና የእገሌ ብሔረሰብ” እያሉ በጭፍንና በጅምላ ከመጮህ ውጭ፣ ሌላ “ቋንቋ” አይመጣላቸውም፡፡ እውነታን አጥርተው መገንዘብና በትክክል መግለጽ ማይቻል ይመስላቸዋል፡፡ ወይም ያስመስላሉ፡፡
ለእውነት የታመነ “ቋንቋ” - የዘረኝነት ማርከሻ!
እውነታው ግን፣ አይናችንን ካልጨፈንን በቀር፣ ፍንትው ብሎ ይታያል፡፡ የሚያለማ ወይም የሚያጠፋ “አቶ ብሔር” የለም፡፡ እስከዛሬ አልነበረም፡፡ ወደፊትም አይኖርም፡፡
ወንጀል የምትፈጽም ወይም የማትፈጽም፣ “ወ/ሮ ብሔረሰብ” የለችም፡፡ ተከሳሽ ወይም ከሳሽ ሆኖ ወደ ፍ/ቤት የሚቀርብ “ወጣት ብሔር”፣ ወይም “ጐልማሳ” ብሔረሰብ”፣ እስከዛሬ ኖሮ አያውቅም፤ ለወደፊትም ሊኖር አይችልም፡፡
አልሚም አጥፊም፣ …”ይሄ፣ ይሄ፣ ይህች፣ ይህች” ተብለው በግል ሊጠቀሱ የሚችሉ ሰዎች ናቸው፡፡ አንድም ሁለትም፣ መቶም ሁለት መቶም፣ ሊሆን ይችላል - የአጥፊዎች ቁጥር፡፡ ግን እያንዳንዳቸው፣ ራሳቸውን ወክለው ነው ወንጀል የሚፈጽሙት፣ በጥፋት ድርጊትም የሚሳተፉት፡፡ “ብሔር ብሔረሰብ” የተሰኘ አንዳች ፍጡር፣ ጥፋት ሲፈጽም ታይቶ አይታወቅም፡፡
መስራትና ማምረትም እንደዚያው ነው፡፡  ብሔር ብሔረሰብ፣ አያርስም፣ አይኮተኩትም:: ብሔር ብሔረሰብ ህንፃ አይሰራም፤ ድልድይ ወይም ግድብ አይገነባም፡፡ ብሔር ብሔረሰቦች፣ “ይሰራሉ፣ ይገነባሉ” የምትሉ ከሆነ፣ “የአቶ ብሔር መኖሪያ ቤት”፣ “የወ/ሮ ብሔረሰብ ህንፃ” አሳዩን፡፡
ቁጥራቸው ይብዛም ይነስም፣ “ይሄ፣ ይሄ፣ ይህች፣ ይህች” ተብለው ሊጠቀሱ የሚችሉ ሰዎች ናቸው፣ አልሚና ገንቢ፡፡ ቦንድ በመግዛት ለግድብ ግንባታ የሚሳተፉት፣ ገንዘብ አጠራቅመው ባጃጅ የሚገዙት፣ ማሳቸውን አርሰው የሚዘሩት እነማን ናቸው? በግል ሊዘረዘሩ የሚችሉ ሰዎች ናቸው፡፡
ምናለፋችሁ! የሰው ህልውናና ማንነት፣ የግል ህልውናና የግል ማንነት ነው፡፡ የዳኝነት መንገዳችንም፣ ለዚህ እውነታ የታመነ መሆን ይገባዋል፡፡ እያንዳንዱ ሰው፣ ለክፉም ለደጉም፣ ለጥፋትም ለልማትም፣ እንደየግል ተግባሩ፣ እንደየግል ባሕርይው፣ እንደየግል ድርሻውና ተሳትፎው፣ ልንዳኛት፣ ልንዳኘው ይገባናል፡፡ የሰው ማንነት፣ “የግል ማንነት” ነውና፡፡
“የብሔር የብሔረሰብ፣ የሃይማኖት ወይም የሰፈር ማንነት” ብሎ ነገር የለም፡፡ የጋርዮሽ አስተዋይነት ወይም የጋርዮሽ ጭፍንነት የለም - የጋራ አእምሮ ስለሌለ፡፡
የጋርዮሽ እውቀትና የጋርዮሽ ሞኝነትም የለም፡፡ የጋርዮሽ ዲግሪ ወይም ዶክትሬት የለም፡፡ ብቃትና መናኛነት፣ ጠንካራ ሰብዕናና ወራዳነት፣ አልሚነትና አጥፊነት፣ ቀናነትና ክፋትም እንዲሁ የጋርዮሽ የለም፡፡
እውነታው የዚህን ያህል የጠራ የነጠረ ነው - የማያሻማ፡፡
ከዚህ እውነታ ለማምለጥና ለመሸሽ ግን፣ “የጋራ ማንነት” የሚል ፈሊጥ በየአቅጣጫው ይፈለፈላል፡፡ ከእውነታ ማምለጥ ለምን?
የሰዎችን የግል ብቃትና ውጤት በግድ ለመጋራት የሚመኙ ቀማኞች፣ “የጋራ ማንነት” እያሉ ይጮሃሉ፡፡
የግል ጥፋትንና የግል ኃላፊነትን ለሌላ ሰው አጋርተው ለማሸከም የሚመኙ ወንጀለኞችም፣ “የጋራ ማንነት”፣ “የብሔር ማንነት” እያሉ ያነበንባሉ፡፡ “ብሔር ብሔረሰብ” እያሉ፣ በዘረኝነት ይቧደናሉ፤ ያቧድናሉ፡፡ ወይም በሃይማኖት ተከታታይነት፣ በጭፍን መንጋ እየፈጠሩ ይንጋጋሉ፤ ያንጋጋሉ፡፡ ጥፋትን ይቆሰቁሳሉ፡፡ በድርጊትም ይሳተፋሉ፡፡
በአጭሩ፣ ሁለት እውነታዎችን አጥርቶና አንጥሮ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
አንደኛ ነገር፤ የሰው ማንነት የግል ማንነት በመሆኑ፣ የግል ሃላፊነት ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብና ትክክለኛ የስነምግባር መርህ ያስፈልገናል፡፡ ሌላ የዳኝነት መንገድ መኖር የለበትም፡፡
በግል ራስህን፣ በግል ራስሽን፣ እንዲሁም በግል ሌሎች ሰዎችን ለመዳኘት፣ ትክክለኛውን የስነምግባር መርህን መታጠቅ አለብን፡፡ ሁልጊዜ!
ሁለተኛ ነገር፤ ከግል ሃላፊነት ለማምለጥ የሚመኙ ወንጀለኞች “የጋራ ማንነት” የሚለውን ማመካኛ ፈሊጥ ይጠቀማሉ፡፡ በብሔር ብሔረሰብ፣ በዘረኝነት ወይም በሃይማኖት ተከታይነት እና በሌሎች ሰበቦች፣ በጭፍን ይቧደናሉ፡፡ እዚህም ላይ፣ ለእውነታ መታመን ነው መድሃኒቱ፡፡ የሰው ማንነት፣ “የግል ማንነት” እንደሆነ፣ ለአፍታም መዘንጋት አይኖርብንም፡፡
እነዚህ ሁለት ቁምነገሮችን በቅጡ ካልጨበጥን በቀር፤ ተስፋ አይኖረንም:: የዘረኝነት ጥፋቶችን መግታትና መከላከል ይቅርና፣ የጥፋቶቹን ምንነት በወጉ ማሰብ ይሳነናል፤ የምንገልጽበት ቋንቋም ያጥረናል፡፡
የዘረኝነት ማርከሻ “ቋንቋ”፣ ወዴት ጠፋብን?
“ለዝርፊያ የተቧደኑ 10 ሰዎች፣ ዘበኛ ገድለው መጋዘኑን በዘበዙ” ብለን መግለጽኮ አያቅተንም:: ቋንቋ አያጥረንም፡፡ ታዲያ፣ “ብሔር ብሔረሰብ በሚል የተቧደኑ 100 ሰዎች፣ ግድያ ፈፀሙ፣ ንብረት አወደሙ” ብለን መግለጽ ለምን አቃተን? ሁለቱን ቁምነገሮች በውል አሟልተን አገናዝበናል ወይ የሚል ነው ጥያቄው፡፡
1/ የሰው ማንነት የግል ማንነት እንደሆነ በቅጡ ተገንዝበናል ወይ?
2/ እያንዳንዱን ሰው የምንዳኝበት ትክክለኛ የስነምግባር መርህን ጨብጠናል ወይ? እነዚህ ናቸው ሁለቱ ቁምነገሮች፡፡ እነዚሁ ናቸው የዘረኝነት ማርከሻዎች፡፡ እንዴት?
“ለቅሚያ የተቧደኑ 10 ሰዎች፣ ዘበኛ ገድለው ዘረፉ” የሚል መረጃ ስንናገር ወይም ስንሰማ፣ ሁለት ዋና ዋና ቁምነገሮች ግልጽ ናቸው ትክክለኛ የስነምግባር መርህ እና የግል ማንነት ናቸው ቁምነገሮቹ፡፡
አንደኛ በሉ፡፡ የተቧደኑበት ጉዳይ፣ አስነዋሪና አደገኛ ነው፡፡ መነሻቸውና ውጥን ሃሳባቸው፣ ከሥረመሰረቱ፣ የስነምግባር ምሰሶዎችን የሚንድ ነው፡፡ “የሰውን ንብረት አትመኝ፣ ሰርተህ ጥረህ ንብረት አፍራ” የሚሉ መርሆች ከፈረሱ፣ ህልውና ይከስራል፣ ስብዕና ይረክሳል፡፡ የሰው ንብረት ላይ ማሰፍሰፍና መዝረፍ፣ ሐራም ካልሆነ፣ ሐላል ከተለቀቀ፣ ሰው ከነክብሩ ህልውናውን ማለምለም አይችልም - ወደ አውሬነት ይወርዳልና፡፡
ለቅምያ ተቧድነው፣ በዚያው ይቀራሉ?  አስነዋሪ ሃሳባውንና ውጥናቸውን፣ ወደ አስነዋሪ የበደልና የግፍ ድርጊት ያደርሱታል፣ የክፋትና የወንጀል ተግባር ይፈጽማሉ፡፡ ገድለው ይዘርፋሉ፡፡
“አትስረቅ፣ አትግደል” የሚሉ የስነምግባር ምሰሶዎችንና የህግ መሠረታዊ መርሆችን በማፍረስ ወደ አውሬነት ይወርዳሉ፡፡
ሁለተኛ በሉ፡፡ ትክክለኛ መርህ አስፈላጊ የመሆኑ ያህል፤ “የስነምግባርና የሕግ ዳኝነት”፣ በማን እና በማን ላይ ማነጣጠር እንደሚገባውም ግልጽ ነው፡፡ ትክክለኛ የስነምግባርና የሕግ ዳኝነት፣ ጭፍን የጅምላ ፍረጃ አይደለም፡፡ የግል ማንነትንና የግል ኃላፊነትን በጽናት ያገናዘበ ነው - ትክክለኛ የስነምግባር መርህ፡፡
“የግል ማንነትና የግል ኃላፊነት”፣ እጅግ የረቀቀ የሩቅ ሚስጥር አይደለም፡፡ ወንጀል የፈፀሙ ሰዎች …በግል ማን ማን እንደሆኑ ተጣርቶ፣…”ይሄ፣ ይሄ፣ ይህች፣ ይህች” በሚል በግል ማንነታቸው ተለይቶ መታወቅ እንዳለበት ግልጽ አይደለም? ግልፅ ነው፡፡ እያንዳንዱን ሰው፣ እንደተግባሩና እንደባህርይው ልንዳኘው ይገባልና፡፡
“በሰፈር በመንደር፣ በብሔር ብሔረሰብ፣ ወይም በሃይማኖት፣… የተቧደኑ 20 ወጣቶች፣ መንገድ ዘግተው መኪና አቃጠሉ፤ ሾፌሩን በስለት ወጉ”  የሚል መረጃ ስንናገርና ስንሰማም፣ ግልጽ መልዕክት አለው፡፡
አንደኛ ነገር፣ የተቧደኑበት ጉዳይ፣ አስነዋሪ ነው፡፡ ሰውን መቅረብ ወይም መራቅ፣ ሰውን ማመስገን ወይም መንቀፍ የሚገባን፣ የዚህ ሰፈር ወይም የዚያ ሰፈር በሚል አይደለም፡፡ በስነምግባር መርህ መሆን አለበት - ዳኝነታችን:: እያንዳንዱን ሰው በግል ኃላፊነቱ፣ ነው ልንዳኘው የሚገባን፡፡ ማለትም፣ በግል ተግባሩና በግል ባህርይው፣ በግል ተሳትፎውና በግል ድርሻው ልክ ነው መዳኘት የሚገባን፡፡
ከዚህ በተቃራኒ፣ የስነምግባር መርህን ወዲያ አሽቀንጥረን፣ የግል ኃላፊነትን አስክደን፣…”በሰፈር በመንደር፣ በብሔር ብሔረሰብ ወይም በሃይማኖት ተከታይነት” ሰበብ መቧደን አስነዋሪ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡
በአስነዋሪ መንገድ ተቧድነው፣ ንብረት አጥፍተዋል፤ ሰውን አጥቅተዋል፡፡ የወንጀል ድርጊት ፈጽመዋል፡፡ ሁለተኛው ቁምነገር እዚህ ላይ ነው፡፡
የድርጊቱ ተጠያቂዎች፣ በደፈናውና በጅምላ፣ “የሰፈሩ ነዋሪዎች”፣ “የዚያ ሰፈር ወጣቶች”፣ “የዚያ ብሔር ብሔረሰብ ተወላጆች”፣ “የዚህ ወይም የዚያ ሃይማኖት ተከታዮች” ሊሆኑ አይችሉም፡፡ “የጋርዮች አእምሮ”ም ሆነ “የጋርዮሽ ማንነት” ፈጽሞ ሊኖር አይችልምና፡፡
የወንጀል ድርጊት ተጠያቂዎች፣ ሁለት ሆኑ ሃያ፣ ሁለት ሺ ሆኑ ሃያ ሺ፣ እነዚሁ ብቻ ናቸው ተጠያቂዎቹ - በየግላቸው እንደየነወራቸውና እንደየወንጀላቸው መጠን፣ እንደየግል ተሳትፏቸው፡፡
በዚህ መንገድ፣ እያንዳንዱን ጥፋት በትክክልና በአግባቡ መግለጽ ያቃተን ለምንድ ነው? ጠንካራ የስነምግባር መርህንና የግል ተጠያቂነትን በጽናት አለመጨበጣችን ነው - ችግሩ፡፡
“በብሔረሰብ መቧደንና መደራጀት” ነውር ካልሆነ፤ ዘረኝነትን መከላከል አይቻልም፡፡
“ለንጥቂያ መቧደን”፣ እንደ አፀያፊ ነውር ባይቆጠር፣ ምን እንደሚፈጠር ይታያችሁ:: “ለንጥቂያ መቧደን”ን፣ “ነባር አኩሪ ባህል”፣ ወይም “ዘመነኛ የማህበራዊ ማንነት ግንባታ” እያልን የምናዳንቅ ጉዳይ ቢሆን አስቡት፡፡ ደግነቱ፣ ገና ወደዚህ የአውሬነት አዘቅት አልወረድንም:: ወደ አዘቅቱ እየተንሸራተትን ቢሆንም፣ ገና አልተዘፈቅንበትም፡፡ አለበለዚያማ፣ ለንጥቂያ የምናቧድን ፊታውራሪዎች፣ የቅሚያ ጠበቆችና የዝርፊያ አጨብጫቢዎች ሆነን እናርፈው ነበር::
ለንጥቂያ መቧደን ተስፋፍቶ ከተላመድነው፣ ለወሬ ይቸግረናል፡፡ ለነቀፋም ይከብደናል:: ትችት ሆነ ውግዘት ከተሰነዘረበት፣ እጅግ ሲከነክነን ሲቆረቁረን አስቡት፡፡ ጥቃት የተፈፀመብን ያህል ሲያንገበግበን ይታያችሁ፡፡ “ይሄ ሊሆን አይችልም” ብትሉ አይገርመኝም:: ንጥቂያና የዝርፊያ ተቆርቋሪ ከሆንንማ ምን ቀረን! ያስብላል፡፡
“In Defense of looting” በሚል ርዕስ የሚታተም መጽሐፍ ይመጣል ብለን ለመገመት ቢያስቸግረንም፣ አይገርምም፡፡ ነገር ግን፣ በእውን ታትሟል፡፡ ለዚህ የጥፋት የቁልቁለት አቅጣጫ፣ ትንሽ መንገድ ከሰጠን፣ የስነምግባር ምሰሶ ይፍረከረካል፡፡ ዝርፊያ የሚከላከል ቋንቋ ያጥረናል፡፡ “ለንጥቂያ የተቧደኑ 10 ሰዎች፣ አውቶቡስ አስቁመው፣ መንገደኞችን ዘረፉ” ብለን መግለጽ የምንችልበት ቋንቋ ይጠፋብናል::
በሰው ንብረት ላይ አታሰፍስፍ፣ ሰርተህ በልጽግ፣ አትስረቅ የሚሉ የስነምግባር መርሆዎችን ከሸረሸርናቸው፣ በምን አፋችን እንናገራለን? ከዚህ ጥፋት መዳን ከፈለግን፣ የስነምግባር መርሆዎችን ማጽናት ነው የሚበጀን፡፡ እስካሁን የፈረሱብንን የስነምግባር ምሰሶዎች መልሰን መገንባት ነው የሚሻለን፡፡
“ለንጥቂያ መቧደን”፣ …ዛሬም አስፀያፊ ነውርነቱ ገና ባይደበዝዝም፤ “በብሔር ብሔረሰብ መቧደን” ወይም “በሃይማኖት መቧደን” ግን ተለምዷል፡፡
በዚህም ምክንያት ዘረኝነትን የምንከላከልበት አቅማችን ሟሽሿል፡፡ የዘረኝነት መዘዞችንና ጥፋቶችን በግልጽ የመዘገብ፣ እንዲሁም በትክክል የመግለጽ ቋንቋ ጠፍቶብናል፡፡
“በብሔረሰብ የተቧደኑ ሃያ ወጣቶች፣ የዝርፊያና የግድያ ወንጀል ፈፀሙ” ብለን፣ ዘረኝነትን የማውገዝ፣ ወንጀልን የመቃወም አቅማችን ምንኛ እንደተመናመነ አስተውሉ፡፡ አሃ፣
በዘር የመቧደንና የመደራጀት በሽታ፣ እንደመልካም ነገር ተስፋፍቷልኮ፡፡  የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ ተንሰራፍቷልኮ፡፡
ይህንን የጥፋት መንገድ ለመግራትና ለመግታት በጽናት መትጋት፣ የእያንዳንዱ ሰው ኃላፊነት ነው፡፡ ግን በቂ አይደለም፡፡ ዘረኝነትን ለማስወገድና በትክክለኛ አስተሳሰብ ለመተካት በአስተዋይነት መጣር፣ ከዋና ዋና ቅዱስ ተግባራት መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህንን መገንዘብ ይገባናል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡
የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ በተስፋፋ ቁጥር የግል ማንነትንና የግል ኃላፊነትን አጣጥሎ ማራከስና ማዋረድ በርክቷል፡፡ በማንነት ቀውስ መዳከር ተለምዷል፡፡ ከግል ኃላፊነት ለማምለጥም “የጋራ ማንነት” በሚል ስበብ የግል ስብዕና ላሽቋል፡፡  ከዚህ አስቀያሚ የዘረኝነት ረግረግ ለመላቀቅ መትጋት ይኖርብናል፡፡
“የጋራ ማንነት” የተሰኘውን የዘረኝነት በሽታ ለማስወገድ መትጋት በቂ አይደለም፡፡ በምትኩም፣ የግል ማንነትን አቃንቶ የመገንባት ብርታት ሊኖረን ይገባል፡፡ የግል ኃላፊነትን የመጨበጥ ጽናትንም ማዳበር አለብን፡፡
በአጭሩ፤ እያንዳንዳችን፣ ራሳችንንም፣ ሌላውንም ሰው፣ በግል የምንዳኝበት ትክክለኛ የስነምግባር መርህ የግድ ያስፈልገናል፡፡ በሰፈርና በመንደር፣ በብሔረሰብ ወይም በሃይማኖት ታርጋ መሆን የለበትም - ዳኝነታችን፡፡ ሰው የመሆን ክብርን የምንጐናፀፈውና ህልውናችንን የምናለመልመው፣ ትክክለኛ የስነምግባር መርህ ሲኖረን ብቻ ነው፡፡
የተቀደሰ የፍትህ እና የፍቅር መንፈስ የሚሰፍነውም፤ በዚሁ መንገድ ብቻ ነው:: አገራችን የአንድነትና የቅንነት አገርነቷ የሚደምቅልንም በሌላ መንገድ አይደለም፡፡ ራሳችንን በግል ለመዳኘት፣ ትክክለኛ የስነምግባር መርህ ሊኖረን ይገባል፡፡ በዚሁ ትክክለኛ የስነምግባር መርህ አማካኝነትም፣ ሌሎችን ሰዎች በግል መዳኘት ይኖርብናል፡፡ በዘር ወይም በሰፈር አይደለም፡፡ ለራስም ለሌላም ሰው፣ የዳኝነት መርሃችን፣ ልዩነት የለውም፡፡ የዳኝነት መርሃችን፣ ትክክለኛው የስነምግባር መርህ ብቻ መሆን አለበት፡፡
“ሌሎችን ሰዎች እንደራስህ ውደድ”  የሚለው አባባል፣ እጅግ የተቀደሰ ትርጉም የሚኖረው፣ ከዚህ አንፃር ነው፡፡ በፍትህና በፍቅር አምሮ የተገነባ የአገር አንድነትና የሰው ህብረት የሚፈጠረውም፣ የግል ማንነትን ባገናዘበና እጅግ የተቀደሰ ትክከለኛ የስነምግባር መርህ አማካኝነት ብቻ ነው፡፡    


Read 8392 times