Thursday, 10 September 2020 00:00

በአፍሪካ ጥቅል የኮሮና ስርጭት መቀነስ ማሳየቱ ተነገረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

     በመላው አለም የተጠቂዎች ቁጥር ከ26.3 ሚሊዮን፣ የሟቾች ቁጥር ከ870 ሺህ አልፏል

           በአፍሪካ ጥቅል የኮሮና ስርጭትና የማጥቃት መጠን ባለፈው አንድ ሳምንት በተወሰነ መልኩ መቀነስ ማሳየቱንና በአህጉሪቱ በቫይረሱ ከተጠቁት ሰዎች መካከል 80 በመቶ ያህሉ በማገገም ላይ እንደሆኑ የአፍሪካ የበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ማዕከል ባለፈው ሃሙስ ባወጣው መግለጫ ማስታወቁን አናዶሉ ኤጀንሲ ዘግቧል፡፡
በአህጉሪቱ ጥቅል የቫይረሱ ስርጭት መጠን በሳምንቱ ቅናሽ ቢያሳይም አፍሪካ ቫይረሱን አሸነፈችው ማለት እንደማይቻልና ገና ብዙ መስራት እንደሚገባ ማዕከሉ ማስታወቁን የጠቆመው ዘገባው፣ በአንጻሩ ደግሞ ስርጭቱ በምስራቅ አፍሪካ የ2.4፣ በሰሜን አፍሪካ ደግሞ የ7.5 በመቶ መጨመር ማሳየቱን የጠቆመው ዘገባው፤ በአፍሪካ የአዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ባለፈው አንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ በ14 በመቶ ያህል መቀነስ ማሳየቱንም አክሎ ገልጧል፡፡
ኮሮና ቫይረስ እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ ድረስ በአፍሪካ ከ1.267 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ማጥቃቱን፣ የሟቾች ቁጥር ከ30 ሺህ ማለፉንና ያገገሙት ሰዎች ቁጥርም ከ1 ሚሊዮን ማለፉንም ዘገባው አመልክቷል፡፡ በመላው አፍሪካ ከ11.8 ሚሊዮን በላይ በሚሆኑ ሰዎች ላይ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ መደረጉንና ከዚህ ውስጥም 10.7 በመቶ ያህሉ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ያስታወቀው የአፍሪካ የበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ማዕከል፤በአህጉሪቱ በቫይረሱ ከተጠቁ ሰዎች 70 በመቶ ያህሉ በ5 አገራት ውስጥ እንደሚገኙና አገራቱም ደቡብ አፍሪካ፣ ግብጽ፣ ሞሮኮ፣ ናይጀሪያና ኢትዮጵያ መሆናቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
ወደ አለማቀፍ መረጃዎች ስንሄድ ደግሞ፤ ኮሮና ቫይረስ እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ ድረስ በመላው አለም ከ26.29 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ማጥቃቱንና ወደ 870 ሺህ ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን የጠቆመው የወርልዶሜትር ድረገጽ መረጃ፣ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከ18.6 ሚሊዮን በላይ መድረሱን አስታውቋል፡፡ አሜሪካ በ6.3 ሚሊዮን ተጠቂዎቸና ከ190 ሺህ በለይ ሟቾች ከአለማችን አገራት ቀዳሚነቱን ይዛ የቀጠለች ሲሆን ብራዚል በበኩሏ፤ ከ4 ሚሊዮን በላይ ተጠቂዎችና በ124 ሺህ ያህል ሟቾች በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
ከ3.9 ቢሊዮን በላይ ሰዎች ተጠቅተውባትና 68 ሺህ ሰዎች ሞተውባት በሶስተኛ ደረጃ ላይ በምትገኘው ህንድ ባለፈው ረቡዕ ብቻ 83 ሺህ 883 የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች መገኘታቸውንና ይህም አገሪቱን ከአለማችን አገራት መካከል በአንድ ቀን ከፍተኛውን የተጠቂዎች ቁጥር የመዘገበች አገር እንዳደረጋት ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ፤ ህንድ ባለፈው ረቡዕ ብቻ ከ11.7 ሚሊዮን በላይ በሚሆኑ ሰዎች ላይ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ማድረጓንና ይህም በአለማችን በአንድ ቀን የተደረገ ከፍተኛው የምርመራ ቁጥር መሆኑን የአገሪቱ የጤና ሚኒስትር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ በመጪው ህዳር ወር መጀመሪያ ለዜጎቿ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ለመስጠት ማቀዷን ከሰሞኑ ይፋ ያደረገቺው አሜሪካ፣ ለኮሮና ቫይረስ ክትባትና መድሃኒት ለማምረትና በቀጣይም በፍትሃዊነት ለማሰራጨት የሚደረገውን ጥረት በጋራ ለማሳካት በአለም የጤና ድርጅት አስተባባሪነት በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘውና ከ150 በላይ አገራት በአባልነት የተካተቱበት አለማቀፍ ጥምረት ውስጥ እንደማትሳተፍ ከሰሞኑ ማስታወቋን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እስከመጪው አመት በመላው አለም የሚገኙ 47 ሚሊዮን ያህል ሴቶችንና ልጃገረዶችን ለድህነት ሊዳርግ እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ ማስጠንቀቁን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ የአለም የኢኮኖሚ ፎረም በበኩሉ፤ በመላው አለም ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ህጻናት በኮሮና ወረረሽኝ ሳቢያ ከትምህርት ገበታቸው ውጭ መሆናቸውን፣ 370 ሚሊዮን ያህል ህጻናት የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር እንደተቋረጠባቸው እንዲሁም 80 ሚሊዮን ያህል ህጻናት በክትባት አለማግኘት ሳቢያ ለተለያዩ በሽታዎች ሊዳረጉ እንደሚችሉ ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
በኮሮና ሳቢያ ባለፉት 6 ወራት 133 ሚሊዮን ዶላር ያህል ኪሳራ የደረሰበት ኬንያን ኤርዌይስ፤ የአለማችን የጤና ሰራተኞች በኮሮና ወረርሽኝ ትግል ውስጥ እየከፈሉት ላለው መስዋዕትነት እውቅናና ምስጋና ለመስጠት በማሰብ ከመጪው ወር ጀምሮ በመላው አለም አገልግሎቱን ለሚጠቀሙ የጤና ሰራተኞች፣ ከመደበኛው ዋጋ በግማሽ ቀንሶ አገልግሎት እንደሚሰጥ ከሰሞኑ ይፋ ማድረጉ ተዘግቧል፡፡

Read 3674 times