Wednesday, 09 September 2020 00:00

ኦክስፎርድ ለ5ኛ ጊዜ የአለማችን ምርጥ ዩኒቨርሲቲ ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የአለማችንን ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ መስፈርቶች እያወዳደረ በየአመቱ ይፋ የሚያደርገው ታይምስ ሃየር ኢጁኬሽን የተባለው አለማቀፍ ተቋም፣ ከሰሞኑም የዘንድሮውን ሪፖርት ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ላለፉት አራት ተከታታይ አመታት የአለማችን ምርጥ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ የዘለቀው የእንግሊዙ ኦክስፎርድ ዘንድሮም ክብሩን አስጠብቋል፡፡
በዘንድሮው የአለማችን ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ዝርዝር ውስጥ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ የያዙት ሁሉም የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ስታንፎርድ፣ ሃርቫርድ፣ ካሊፎርኒያ ኢንስቲቲዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ እና ማሳቹሴትስ ኢንስቲቲዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ ናቸው፡፡ የእንግሊዙ ካብምሪጅ ጣልቃ ገብቶ የ6ኛነት ደረጃ ቢይዝም፣ እስከ 10ኛ ያለውን ስፍራ የያዙትም የአሜሪካዎቹ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ፣ የል ዩኒቨርሲቲ፣ ፕሪንሲተን ዩኒቨርሲቲ እና ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቺካጎ ናቸው::
በአለማቀፉ የምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ዝርዝር ውስጥ የ155ኛ ደረጃን የያዘው የደቡብ አፍሪካው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኬፕታውን፣ ከአፍሪካ በ1ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን፣ ደቡብ አፍሪካ በድምሩ 11 ዩኒቨርሲቲዎችን በዝርዝሩ ውስጥ ለማስፈር ችላለች፡፡
በ2021 የአለማችን ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ዝርዝር ውስጥ እስከ 500 ባለው ደረጃ ውስጥ ከተካተቱ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ደግሞ የግብጾቹ አስዋን እና ማንሶራ፣ የናይጀሪያው ዩኒቨርሲሲ ኦፍ ኢባዳንና የኡጋንዳ ማካሬሬ ዩኒቨርሲቲ እንደሚገኙበት ተነግሯል፡፡ በዝርዝሩ ውስጥ በ20ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የቻይናው ሲንጉዋ ዩኒቨርሲቲ እስከ 20 ባለው ደረጃ ውስጥ የገባ የመጀመሪያው የእስያ ዩኒቨርሲቲ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ታይምስ ሃየር ኢጁኬሽን የተባለው አለማቀፍ ተቋም በ93 የአለማችን አገራት ውስጥ የሚገኙ 1ሺህ 527 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የተለያዩ መስፈርቶችን ተጠቅሞ በመገምገም ባወጣው የአለማችን ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ዝርዝር ውስጥ 141 ዩኒቨርሲቲዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተካትተውበታል፡፡

Read 2655 times