Wednesday, 02 September 2020 00:00

“ሂዩመን ሄር” - ከናይጄሪያ እስከ ኢትዮጵያ!”

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

  የጣሊያን ወይስ የህንድ? የኮሎምቢያ ወይስ የበርማ?
                             
              ፀጉሬ እንደልብሴ ነው ትላለች - ኦላይንካ:: በየቀኑ ልብስ ስትቀይር፣ ፀጉሯንም ትለወጣለች:: የትናንት ፀጉሯን፣ ዛሬ አትደግመውም፡፡ የዛሬውን፣ ነገ ደግማ አታደርገውም፡፡ የተለያየ የፀጉር አይነት፣ በየእለቱ እየለዋወጠች ወሩን ሙሉ ታጌጣለች ይላል - ዘኢኮኖሚስት መጽሔት፡፡
ቀኑ ብርዳማ ከሆነ፣ …የተዘናፈለ ረዥም ፀጉር ይኖራታል፡፡ ለሞቃት የበጋ ቀናት ደግሞ፣ አንገትን የማይሸፍኑ፣ ከጆሮ ግንድ የማይሻገሩ፣ አጠር አጠር ያሉ የፀጉር አይነቶችን እያማረጠች ትዋባለች - ኦላይንካ::
እያጌጠች፤ እየተዋበች እንደሆነ አትጠራጠርም፡፡ ነገር ግን፤ ለሌሎችም ሴቶች አርአያ ለመሆን ነው ጥረቷ፡፡ እሷን አይተው፣ የፀጉር ቅያሪ አብዝተው እንዲመኙ ትፈልጋለች - እንደ ልብስ ቅያሪ፡፡ ተመኝተው እንዲቀሩ አይደለም፡፡ የፀጉር ቅያሪ እንዲገዙ ነው፡፡ አንድ ሁለቴ ብቻ አይደለም:: አዘውትረው ፀጉር የመግዛትና ፀጉር እየለዋወጡ የማጌጥ ልምድ እንዲኖራቸው ትመኛለች፡፡
ለምን? በዊግ መቆንጀትን ትወዳለች:: ግን፣ እንጀራዋም ነው፡፡ ቅያሪ ፀጉር ወይም ዊግ መሸጥና ሴቶችን በዊግ ማቆንጀት ነው ስራዋ፡፡ ከዓመት ዓመትም፣ ገበያዋ እየደራ ነው፡፡ ዋጋው ቀላል ባይሆንም፣ አዘውትረው በዊግ የሚያጌጡ፣ ቅያሪ ፀጉር የሚገዙ ሴቶች በርክተዋል፡፡
በጣም ርካሹ፣ 60 ዶላር አካባቢ ነው - ወደ 2000 ብር ገደማ፡፡ በኮንትሮባንድ የሚገባ “ፌክ ፀጉር” በዝቷላ፡፡ ግን እንደጥራቱና እንደውበቱ፣ ዋጋው ይወደዳል፡፡ ኦላይንካ፣ 800 ዶላር የሚያወጣ ፀጉርም ትሸጣለች፡፡ በተለይ፣ የኮሎምቢያ ሂዩመን ሄር የፀጉሮች ሁሉ ቁንጮ ነው ትላለች ኦላይንካ፡፡ ለአንድ የፀጉር ቅያሬ፣ 30ሺ ብር ገደማ መሆኑ ነው:: ይሄ የናይጀሪያ ቢሆንም፤ በኢትዮጵያም “ሂዩማን ሄር” ተብሎ ለገበያ የሚቀርበው፣ ከ7000 ብር ጀምሮ፣ እስከ 20ሺ እና ከዚያ በላይ ሆኗል፡፡ “እዚህ ገዝቼ አላውቅም፤ ጓደኞቼ ከውጭ ይልኩልኛል” ብለው የሚናገሩም የቅያሪ ፀጉር ተጠቃሚዎችም አሉ፡፡
በእርግጥ፣ በዊግ ማጌጥን የሚያንቋሽሹ፣ “ለምዕራባውያን አስተሳሰብ ምርኮኛ መሆን ነው” ብለው የሚያወግዙ፣ “አክቲቪስቶች” ጥቂት አይደሉም፡፡
“ባለ ዊጐች፣ ፈረንጅ አምላኪዎች ናቸው” እያሉ ከመስበክ አልቦዘኑም፡፡
ነገር ግን፤ በቅያሪ ፀጉር ማጌጥ እየተስፋፋም እየተዘወተረም ነው፡፡ የፀጉር ገበያም ደርቷል፡፡ በዓይነትና በብዛት፣ ጨምሯል፡፡ ፋብሪካ ሰራሽ “ሲንቴቲክ” ፀጉር፣ እንዲሁም ውቅያኖስ ተሻጋሪ “ሂዩመን ሄር”፣ ከአህጉር አህጉር እየተጓጓዘ ነው:: ከህንድ ቤተመቅደሶች የሚሰበሰብ ዘለላ ዘለላ “ሉጫ” ጥቁር ፀጉር፣ ከባንግላዲሽና ከበርማ ቤት ለቤት ከማበጠሪያ የሚለቀም “ተረፈ ፀጉር”ም ገበያውን ያሟሙቃል:: የፈረስ ጋማ እና ጭራ የተቀላቀበለበትም ጭምር፣…አልቀረም፡፡ በአጠቃላይ፣ የፀጉር ገበያ፣ አለምን አዳርሷል፡፡ በአፍሪካ ደግሞ ተጧጡፏል፡፡
ከኢትዮጵያ እስከ ቤኒን፣ ከደቡብ ሱዳን እስከ ደቡብ አፍሪካ፣ ገበያው ሰፍቷል፡፡ ናይጀሪያማ፣ የፀጉር ገበያ መዲና እየሆነች ነው ማለት ይቻላል:: የማጌጥና የመቆንጀት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ ከፍ ብሎ፣ በልጦ የመታየት፣ የጉራና የክብር ጉዳይ እየሆነም ይመስላል፡፡ ለማንኛውም ሸመታው ጨምሯል፡፡ ሻጮችም ገበያቸውን ለማዳመቅ አልሰነፉም፡፡
“የብራዚልን ፀጉር፣ ከወዛምነቱ መበርከቱ” እያሉ ያዳንቃሉ - ዊግ አሻሻጮች::
ይበረክታል የሚሉት፤ ለረዥም ጊዜ ያገለግላል ለማለት ነው፡፡ “የቬትናም ፀጉር፣ ከአረማመድ ጋር ከፍ ዝቅ፣ ልምጥ ዞርጋ ሲል ማማሩ!” እያሉም ያስተዋውቃሉ፡፡ “የሞንጐሊያ ፀጉር፣ ስራ አይፈጅም፤ ራሱ “ከርል” ይፈጥራል” በማለት ያዋድዳሉ:: ”የጣሊያን ምርጥ ፀጉር፣ ሽታ የማያመጣ የቅንጦት ፀጉር አስመጥተናል!” እያሉ ገዢዎችን መማረክም ተለምዷል፡፡  
ዘኢኮኖሚስት መጽሔት እንደዘገበው ግን፣ ወደ አፍሪካ አገራት የሚጐርፈው ፀጉር፣ በአብዛኛው ከቻይና የሚመጣ ነው፡፡
ከየአገሩ የሚሰበሰበው የፀጉር አይነት፣ ገሚሱ፣ ቻይናን ሳይረግጥ አያልፍም:: ታጥቦና ተበጥሮ፣ በአይነትና በርዝመት ተለቅሞ፣ ቀለም ጠግቦ፣ “ከርል” ተሰርቶ (ተፈሽኖ)፣ በእሽግ በእሽግ ይዘጋጃል፡፡ ይሄ ሁሉ ስራ የሚከናወነው እና ለገበያ የሚሰናዳው፤ እናም፣ ወደ አፍሪካ አገራት የሚሰራጨው፣ በቻይና ፋብሪካዎች እንደሆነ ዘኢኮኖሚስት ይገልፃል፡፡
ከቻይናዊት ራስ ቅል ላይ ተላጭቶ የተዘጋጀ ፀጉር፤ የፔሩ ወይም የኮሎምቢያ ፀጉር ተብሎ ሊታሸግ ይችላል፡፡ የሰው ፀጉር፣ ከፈረስ ጋማ እና ከፍየል ፂም ጋር ተቀላቅሎም ይታሸጋል - በርከትከት እንዲል፡፡
ሕንድ፣ ከየአገሩ ወርቅ በመግዛትና በማጌጥ እጅግ የመታወቋ ያህል፤ ናይጀሪያም፣ በዓለም ገበያ ውስጥ፣ ከየአገሩ ፀጉር በመግዛት (“በፀጉር ኢምፖርት”) ስመገናና ሆናለች፡፡
ከ3.6 ሚሊዮን ኪሎ ግራም ይበልጣል - የናይጀሪያ አመታዊ የፀጉር “ኢምፖርት”:: ከፊሉ የሰው ፀጉር ነው፡፡ ከፊሉ የእንስሳት ወይም የፋብሪካ ፀጉር ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ፀጉር፣ የሰው ፀጉር ከሆነ ግን፣ እስከወገብ ድረስ የሚዘናፈል የ20 ሚሊዮን ሴቶች ፀጉር እንደማለት ነው፡፡
ገበያው ሲሟሟቅ፣ ፀጉር የሚሸምት ሲበዛ፣ ከዚሁ ጐን ለጐን፣ በፀጉር “ኤክስፖርት” ተፎካካሪ ለመሆንና ለማሸነፍ የሚሟሟቱ አገራት መምጣታቸው አይገርምም፡፡ በርማ (በዛሬ መጠሪያዋ ማይነማር የተሰኘችው አገር)፣ ከእነዚህ አገራት መካከል አንዷ ናት፡፡
በ10 ዓመት ውስጥ፣ የበርማ የፀጉር ኤክስፖርት ወደ አራት እጥፍ አድጓል:: አሁን፣ ከዓለም 4ኛ ሆናለች በፀጉር ኤክስፖርት፡፡ ድሮ ያልነበሩ የስራ አይነቶችም ተፈጥረዋል፡፡ የፀጉር “ቁራሌዎች” ቤት ለቤት ይዞራሉ፡፡
የፀጉር መግዣ ሱቆችም ተፈጥረዋል ይሄ ለሚስተር ሊን የኑሮ መተዳደሪያ ነው፡፡
የሴቶችን ፀጉር መላጨትና ፀጉር መግዛት ነው - የእለት እንጀራው፡፡ የአገር ኢኮኖሚ እያደገ ይሁን ወይም እያሽቆለቆለ ይሁን፣ ለይቶ ለማወቅ ለሚስተር ሊን ከባድ አይደለም፡፡
ኢኮኖሚ ሲያሽቆለቁል፣ ኑሮ ሲከብድ፣ ወደ ፀጉር ሱቅ የሚመጡ ሴቶች ይበራከታሉ - ፀጉራቸውን ለመሸጥ፡፡ ከነጋ፣ አስር ሴቶችን እንደላጨ ይናገራል - ሊን፡፡ ኑሮ ከብዷል ማለት ነው፡፡ በርካታ ሴቶች፣ ፀጉራቸውን በ18 ዶላር ሸጠው ይሄዳሉ፡፡ ወደ 700 ብር ገደማ መሆኑ ነው፡፡
ታዲያ፣ የፀጉር ኤክስፖርት ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ እንደ “ቁራሌው”፣ ቤት ለቤት እየዞሩ፣ ከሴቶች ማበጠሪያ ላይ፣ ፀጉር መሰብሰብ፣ በበርማ አገር የብዙ ሰዎች መተዳደሪያ ሆኗል፡፡ ከማበጠሪያና ከየቦታው የተቃረመው ፀጉር ተሰብስቦ ይከማቻል:: የተወታተበውንና የተድበለበለውን የፀጉር እራፊ፣ ማፍታታትና አንድ በአንድ እየነቀሱ መልቀም፣ ከተባይ ማጽዳት፣ ሽበት ካለም ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ ይሄን የሚሰሩ፣ በቀን 1 ዶላር ከ20 ሳንቲም ይከፈላቸዋል - 40 ብር አካባቢ፡፡
የተቃረመው ተረፈ ፀጉር፣ ከህንድ እና ከባንግላዲሽ ተሰብስቦ ወደ በርማ ይሄዳል፡፡ እዚያ ተበጥሮና ተለቅሞ ወደ ቻይና ይሻገራል:: እዚያም በቻይና አገር ፋብሪካዎች ውስጥ ተስተካክሎና ታሽጐ፣ ወደነ ኢትዮጵያ፣ ወደነ ናይጀሪያ ይጓጓዛል፡፡ አጃኢብ ነው፡፡  

Read 1782 times