Saturday, 29 August 2020 13:07

"ምንድነው ነው የምትፈልጉት?!"

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)


              እንዴት ሰነበታችሁሳ!
አዲሱም ዓመት እየተቃረበ ነው፡፡ መልካም የመዳረሻ ቀናት ይሁንልንማ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ! አንድዬ!
አንድዬ፡— ማን ልበል?
ምስኪኑ ሀበሻ፡— እኔ ነኝ አንድዬ፡፡
አንድዬ፡— እኮ አንተ ማነህ? ስም የለህም እንዴ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡— ምስኪኑ ሀበሻ ነኛ አንድዬ:: እንደው ሀጢአታችን ምን ያህል ቢበረታ ነው እንዲህ የረሳኸኝ፣ አንድዬ?
አንድዬ፡— ምነው አስገረመህ፣ እንደውም ቆይቻለሁ፡፡ እናንተ ከረሳችሁኝ ይኸው ስንት ዘመን ሆነ አይደለም እንዴ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ እኛማ አንተን እንዴት አድርገን ነው የምንረሳው! ማንስ አለንና!  ስንበደል፣ ሲከፋን፣ ሆድ ሲብሰን ወደ አንተ  አይደለም እንዴ የምንጮኸው!
አንድዬ፡— እኮ፣ የእኔ መኖር ትዝ የሚላችሁ ሲቸግራችሁ፣ አቤት ማለት ስትፈልጉ ነው፡፡ የጠገባችሁ ጊዜማ አንዳንዴ መች ትዝ እላችሁና! ድንገት ትዝ ካልኳችሁም እኔ ላይ… ምን ነበር የምትሉት… አዎ እኔ ላይ የመሬት ወረራ አድርጋችሁ ከይዞታዬ…
ምስኪኑ ሀበሻ፡— ኸረ አንድዬ! ኸረ አንድዬ እንደእሱ ስትል በጣም ነው የሚከፋን፡፡
አንድዬ፡— ታዲያ ምን አለበት! እንደውም አቤት ማለታችሁ ስለማይቀር በሰበቡ ትዝ እላችኋለሁ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እኛ እኮ በጸሎት ዓለም ቁንጮ ላይ ነን፡፡ ምድረ ፈረንጅ ሳይቀር አምኗል፡፡
አንድዬ፡— በቃ ለእናንተ ሁሉ ነገር ትክክል የሚሆነው ፈረንጅ የምትሉት በተናገረው ጊዜ ብቻ ነው፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡— እንደሱ ለማለት ሳይሆን…
አንድዬ፡— ግዴለም፣ ግዴለም፣ እሺ ዛሬ ደግሞ ምን እግር ጣለህ?…
ምስኪኑ ሀበሻ፡— ኸረ አንድዬ እኔ ወዳንተ የምመጣው እግር ጥሎኝ ብቻ አይደለም!
አንድዬ፡— ጥሩ እሺ፤ በል ቶሎ ስጠኝና ወደመጣህበት…
ምስኪኑ ሀበሻ፡— ምኑን  አንድዬ! ምኑን ነው የምሰጥህ!
አንድዬ፡— የአዲስ ዓመት ስጦታ ልትሰጠኝ አይደለም እንዴ የመጣኸው?
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ ምንስ ግራ ቢገባን፣ ምንስ ብንዳፈር--- እንደው መላ ሁሉ ቢጠፋን ለአንተ ስጦታ ልናመጣ! አንድዬ እንደውም ከምንጊዜም በላይ የአንተን ስጦታ የምንፈልግበት ጊዜ ነው፡፡
አንድዬ፡— እሺ አሁን ደግሞ ምን ላድርግላችሁ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡— ባርከን አንድዬ! የእስከዛሬው ይበቃችኋል፣ እስቲ እናንተም እንደ ሌላው ህዝብ ይለፍላችሁ በልና አንድ ጊዜ ቡራኬህን አውርድልን፡፡
አንድዬ፡— እኮ እስከ ዛሬ ድረስ ረግሜያችሁ ነው የኖርኩት ማለት ነው! እንደው እኔን የምትከሱበት ብታጡ በዚህ መጣችሁ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ ክስ አይደለም:: ምን እናድርግ አንድዬ! ሁሉም ነገር ተደባልቆብናል፡፡ እንደኛ ግራ የገባው ህዝብ ዓለም ላይ ያለ አይመስልም፡፡
አንድዬ፡— ሌላው ደግሞ እንደ እናንተ ግራ የሚያጋባ ህዝብ የለም እያላችሁ ነው:: ምን እንደምትፈልጉ፣ ምን እንደማትፈልጉ፣ አይደለም ሌላው ራሳችሁ አታውቁትም፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡— ሰላም፣ አንድዬ፣ ሰላም ነው የምንፈልገው፡፡ እየራበን፣ እየጠማን ያለው ሰላም ነው፡፡
አንድዬ፡— አነጋገርህ ሁሉ ተለውጧል፡፡ ገጣሚ ሆንክ እንዴ!?
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ!
አንድዬ፡— ተወው ግዴለም፣ እሱን ሌላ ጊዜ ታወራኛለህ፡፡ እርግማን ስለምትለው ነገር እኔ እናንተን የምረግምበት ምክንያት የለኝም፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ ማለት…
አንድዬ፡— ቆይ አስጨርሰኛ፡፡ ለዚህ ነው እኮ አንድም ነገር ብዙ ጊዜ የማይሳካላችሁ:: በጣም ችኩሎች ናችሁ፡፡ አንዲት ነገር ጫፏን የያዛችሁ እንደሁ ግራ፣ ቀኙን እንደ መመርመር ዘላችሁ ትገቡበትና በኋላ መውጫው ያጥራችኋል፡፡ ዋሸሁ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡— ኸረ ምን በወጣህ አንድዬ! በደንብ ነው ያየኸን፡፡
አንድዬ፡— ጎሽ፣ እንዲህ ነገር ስትሰሙ ጥሩ:: ሌላው ሲያደርግ የምታዩት ሁሉ እናንተ ላይ ያምር ይመስል ከዚህ ቦታ የወሰደንው፣ ከእነ እከሌ ልምድ ያገኘነው ስትሉ እኔ ሳቅ ይከጅለኝና በእነኚህ ምስኪኖቼ ላይማ አልስቅባቸውም ብዬ እተዋወለሁ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡— ኸረ ከሳቅ በላይም ይገባናል፡፡
አንድዬ፡— ቆይ፣ ንገረኝ እስቲ፡፡ ለምንድነው ራሳችሁን መሆን ያቃታችሁ? እናንተው አይደላችሁ እንዴ የሰው ወርቅ አያደምቅ የምትሉት!
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እውነትህን ነው:: ይሄ ሁሉ ችግር እኮ የሚፈራረቅብን ራሳችንን መሆን አቅቶን ነው፡፡
አንድዬ፡— እኮ እሱን እኮ ነው አስረዳኝ የምልህ፡፡ ራሳችሁን መሆን ያቃታችሁ ለምንድን ነው?
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ…እ…እ…
አንድዬ፡— ጭራሽ ለመናገርም ፈራህ እንዴ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡— እንደሱ ሳይሆን… በየጓዳችን የምንሾካሾከውን ልንገርህ? 
አንድዬ፡— ቀድሜ ንገረኝ ያልኩህ እኔው አይደለሁ እንዴ! መልሰህ ፈቃዴን ትጠይቃለህ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡— እንዳትቆጣ ብዬ ነው፡፡
አንድዬ፡— ወይ ጣጣ…
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ ግዴለህም…አትማረርብን፡፡ እኛማ የምንለው ይሄ ሁሉ መከራ የበዛብን ባ…ባ…
አንድዬ፡— ትቼህ መሄዴ ነው፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡— ባንተ እርግማን ነው እያልን ነው፡፡ 
አንድዬ፡— ጉድ እኮ ነው…ስማ፣ ለምን ራሳችሁን ታታልላላችሁ፡፡ አሁንም ደግማችሁ፣ ደጋግማችሁ ስሙኝ፡፡  እርግማን የሚባል ነገር ካለ እዛው ምድር ላይ ራሳችሁ በራሳችሁ ላይ ያመጣችሁት ነው:: እኔን አታነካኩኝ፡፡ ሁልጊዜ ግራ የሚገባኝ እኮ ለሁሉም ነገር ሰበብ ፈላጊ ሆናችሁ እስከመቼ  ድረስ ነው የምትዘልቁት!
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አን…
አንድዬ፡— ሁልጊዜም  ሰበብ ነው፣ ሁልጊዜም የእናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝ፡፡ በእናንተ ቤት እናንተ መቼም አትሳሳቱም፣  እናንተ መቼም ቢሆን አታጠፉም፡፡  ሁሉም ክፉ የምትሉት ነገር  ከውጪ የሚመጣባችሁ ነው፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ ከውጪ እኮ ብዙ ደህንነታችንን የማይፈልጉ አሉ:: ዘንድሮም ነገር ሲያባብሱብን የከረሙት እነሱ ናቸው እኮ!
አንድዬ፡— እሱን መች ካድኩ፡፡ አሁን ከውጪ ክፉ የሚመኙላችሁ የሉም አልኩ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አላልክም አንድዬ፣ አላልክም፡፡ አንድዬ ግራ ቢገባን እኮ ነው፡፡
አንድዬ፡— ግራ ባይገባችሁ ነበር የሚገርመኝ:: ግራ ተጋብታችሁ እኔን ሳይቀር ግራ የምታጋቡ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ዛሬ በጣም ተቆጣህ፡፡
አንድዬ፡— እሱን ተወውና ምንድነው  የምትፈልጉት! ምን ይሁን ነው የምትሉት!
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ፣ አሁንማ ከምንም በላይ የምንፈልገው ሰላም ነው፡፡
አንድዬ፡— በል እኔንም አታድክመኝ:: ሰላማችሁን ያጠፋችሁት ራሳችሁ ናችሁ፡፡ እዛው ፈልጉት፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ…
አንድዬ፡— ነገርኩህ ሰላምን እዛው ፈልጉት:: ቢያንስ ስትሞክሩ አሳዩኝና በጎደለ ሙላልን በሉ፡፡ ያን ጊዜ እንነጋገራለን፡፡ ደግሞ እርግማን የምትሉት እኔን ስለማይመለከት እዛው ተፈታተሹ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ…
አንድዬ፡— ጨርሻለሁ፣ በሰላም ግባ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አሜን አንድዬ! አሜን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1851 times