Saturday, 29 August 2020 10:43

ኢዜማ በአዲስ አበባ ህገወጥ የመሬት ወረራ መካሄዱን በምርመራ አረጋግጫለሁ አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(12 votes)

   ኢዜማ በአዲስ አበባ ህገወጥ የመሬት ወረራና እጣ ላልደረሳቸው የኮንዶሚኒየም ቤት እደላ መካሄዱን በምርመራ ማረጋገጡን ያስታወቀ ሲሆን ትላንት በጉዳይ ዙሪያ ለጋዜጠኞች ሊሠጥ የነበረው መግለጫም በፖሊስ ተከልክሏል፡፡
ኢዜማ ከህብረተሰቡ የቀረቡለትን ጥቆማዎች መነሻ በማድረግ ኮሚቴ አቋቁሞ በከተማዋ የመሬት ወረራ ጉዳዮችን ማጣራቱንና በከተማዋ መጠነ ሰፊ የመሬት ወረራ መካሄዱን ህገወጥ የኮንዶሚኒየም ቤቶች እደላ መፈፀሙን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
ምርመራውን ለማካሄድ ገፊ ምክንያት የሆነው ከህብረተሰቡ፣ የሚቀርቡ ቅሬታዎችና አቤቱታዎች መሆናቸውን ለአዲስ አድማስ የገለፁት የኢዜማ አመራርና የጥናት ኮሚቴው አባል አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ፤ የኢዜማ ስራ አስፈፃሚም በጉዳዩ ላይ በትኩረት ከመከረ በኋላ ምርመራ ለማካሄድ በመወሰን 4 አባላት ያሉት መርማሪ ኮሚቴ ማቋቋሙን አስረድተዋል:: ከሰኔ አጋማሽ ጀምሮም ኮሚቴው ኢዜማ ያለውን መዋቅር ጭምር በመጠቀም የህብረተሰቡን ጥቆማ እየተቀበለ የምርመራ መስፈርቶችን ባሟላ መልኩ ማጣራት ማድረጉን አመልክቷል፡፡
በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ2ሺህ በላይ የስልክ ጥቆማዎች ለኮሚቴው መቅረባቸውን፤ ከእነዚህም መካከል 25 ያህል ቦታዎች ላይ ኮሚቴው ተንቀሳቅሶ የማጣራት ሥራ ማከናወኑንና በእርግጥም ድርጊቶቹ ተፈጽመው መገኘታቸውን መረጋገጡ ተገልጿል፡፡
ምርመራው የመንግስት አካላትን ምላሽ ያካተተ እንዲሆን ፓርቲው ከመንግስት መረጃ ይሰጠው ዘንድ ለከንቲባ ጽ/ቤት፣ ለቤቶች ልማትና ለመሬት አስተዳደር በደብዳቤ ጥያቄ ማቅረቡን ነገር ግን የሚመለከታቸው አካላት ደብዳቤውን ለመቀበል ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል ብለዋል- አቶ ዋሲሁን፡፡
የጥናቱን ግኝቶችም ጨምር ለከንቲባ ጽ/ቤት አስገብቶ የነበረ ቢሆንም ምላሽ አለማግኘቱን ነው ያመለከተው፡፡  ፓርቲው በቀጣይ በተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎች የተደገፈውን የምርመራ ሪፖርቱን ለመገናኛ ብዙሃን ይፋ እንደሚያደርግ የጠቆሙት አቶ ዋሲሁን በህገ ወጥ መንገድ በከተማዋ ስፋት ያለው የመሬት ወረራ መካሄዱን፣ የግለሰብ ቤቶች መቀማታቸው እንዲሁም ህገ ወጥ የኮንዶሚኒየም ቤት ማስተላለፍ ተግባራት መከናወናቸውን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡
ለአረንጓዴ ልማት፣ ለመዝናኛ፣ ለጤና ጣቢያ እና ለሎች መሠረተ ልማት የተከለሉ ቦታዎች በህገወጦች ተወርረው መገኘቱም ተመልክቷል::
ኢዜማ የጥናት ውጤቱን መነሻ በማድረግ ለጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ ለፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ለህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋማት የይጣራ አቤቱታ እንደሚያስገባ ለአዲስ አድማስ የጠቆሙት አቶ ዋሲሁን ከዚህ በተጨማሪም በዚህ የመሬት ወረራ እና የኮንዶምኒየም ቤቶች ጉዳይ ህዝባዊ ንቅናቄዎች ለማድረግ መታቀዱንም አስታውቀዋል፡፡
በቀጣይ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋርም በኢዜማ የምርመራ ውጤት ግኝቶች እና በከተማዋ ባለው የመሬት ወረራና የኮንደሚኒየም አስተዳደር ጉዳዩ የፓናል ውይይት ለማካሄድ መታቀዱንም አቶ ዋሲሁን አስረድተዋል፡፡  
ኢዜማ ይህን የጥናት ውጤቱን የተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ትናንት በራስ ሆቴል አዘጋጅቶ የነበረ ቢሆንም ፍቃድ የለውም በሚል በፖሊስ ተከልክሏል፡፡ መግለጫው የሚሰጥበት ቀንም ወደ ሰኞ ነሐሴ 25 ቀን 2012 መሸጋገሩን የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ክፍል አስታውቋል፡፡ ስለሚሰጠው መግለጫም ቀደም ብሎ የሠላም ሚኒስቴር እንዲያውቀው ተደርጐ እንደነበርና ወደ ሰኞ የተሸጋገረውን መግለጫም እንዲያውቁት ለሠላም ሚኒስቴር እና ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ትናንት ደብዳቤ መፃፉን ፓርቲው አስታውቋል፡፡


Read 14297 times