Wednesday, 26 August 2020 17:46

በአዶኒስ ዜና እረፍት አዝነናል!

Written by 
Rate this item
(5 votes)

በርካቶች አዶኒስ በሚለው የብዕር ስሙ ነው የሚያውቁት፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተወዳጅ የነበረው ;ገመና; ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ደራሲ ነበር - አድነው ወንድይራድ፡፡ #መለከት; የተሰኘው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማም ደራሲ ነበር፡፡
አዶኒስ በ1996 ዓ.ም  #የአና ማስታወሻ;ን በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በየሳምንቱ ተርጉሞ በማቅረብም ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፈ ሲሆን  በኋላም በመጽሐፍ አሳትሞ ለተደራሲያን አቅርቦታል፡፡ ወደ ተውኔትም ተለውጦ ለመድረክ በቅቷል፡፡ በመቀጠልም የአዶልፍ ኤክማንን ታሪክ በአዲስ አድማስ እየተረጎመ ለአንባቢያን ሲያደርስ የቆየ ሲሆን በተመሳሳይ ይሄንንም በመጽሐፍ ማሳተሙ ይታወቃል፡፡
    
       
አዶኒስ ከነዚህ ሥራዎቹ በተጨማሪ የሕጻናት መዝሙሮችና የበርካታ ፊልሞች፤ እንዲሁም የሌሎች የኪነ ጥበብ ሥራዎች ደራሲና ተርጓሚ ነው።
ብዙ ጊዜ በሚዲያ የመቅረብና በአደባባይ የመታየት ፍላጎት ያልነበረው አዶኒስ፤ በሙያው አርክቴክት ሲሆን በዚህም መስክ የበርካታ ሕንፃዎችን ዲዛይን እንደሰራ ይነገርለታል።
አዶኒስ ባደረበት ህመም ህክምና ሲከታተል ቆይቶ ህይወቱ ማለፉ ነው የተነገረው፡፡ አዶኒስ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነበር፡፡   
አዲስ አድማስ ጋዜጣ፤ በተወዳጁ ደራሲና ተርጓሚ አዱኒስ፣ ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለጸ ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጆቹና ለአድናቂዎቹ መጽናናትን ይመኛል፡፡
***
በአዲስ አድማስ ጋዜጣ በየሳምንቱ #የአና ማስታወሻ; መግቢያ የነበረውን ጽሁፍ ለትውስታ ያህል እነሆ፡-
#የአና ማስታወሻ - አንዲት አይሁድ ልጃገረድ ከተደበቀችበት ጣሪያ ሥር ያሰማችው ሰብአዊ ዋይታ ብቻ አይደለም፡፡ የአና ማስታወሻ-እያንዳንዱ የ20ኛው ክፍለ ዘመን አዕምሮ ከየነበረበት የኑሮ ስርቻ ተወትፎ ሲያሰማው የነበረው ድምጽ አልባ ኡኡታ ነው፡፡ የአና ማስታወሻ - ሌሎች በፈጠሩበት አውላላ የሕይወት በረሃ መሃል ተጥሎ አቅጣጫው ጠፍቶት ብቻውን ይንቀዋለል ዘንድ የተገደደው የእያንዳንዱ የህይወት ስደተኛ የድረሱልኝ ዕሪታ ነው፡፡ የአና ማስታወሻ - ችምችም እያለ በመጣው የሕይወት ቁጥቋጦ ተውጦ በቁሙ እያለ መታየት የተሳነውና ዳግም ለመታየት ሰማይ እየቧጠጠ ያለው እያንዳንዱ የዘመናችን ሰው የሚያንቋርረው የጣዕር ኤሎሄ ነው፡፡;








Read 5831 times