Tuesday, 25 August 2020 06:09

የአጭር አጭር ልብወለድ

Written by  ከአንለይ ጥላሁን ምትኩ
Rate this item
(4 votes)

 ፍርሃትን ፈራሁት!
              

                በግቢዬ የተከልኩትን ሽንኩርት እየኮተኮትኩ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ያድጋል የሚል እምነት አልነበረኝም፡፡ ዛሬ ላይ ሆኜ ዘሩን ስተክል የነበረኝን ፍርሃት ሳስታውሰው ስጋት ይደቀንብኛል፡፡ በትክክል አድጎ ያፈራ ይሆን!? እላለሁ፡፡ ያም ሆኖ እየኮተኮትኩ ነው፡፡ ስራዬን አላቋረጥኩም፡፡ ሰውን ሰው ያደረገው ስራው ነው -- አባባልን በአዕምሮዬ አሰላስላለሁ፡፡
በእርግጥ ትላትል ይበላው ይሆን...? ዶሮዎች ይፈልሱት ይሆን...? ቀጭጮ ሳያፈራ ይቀር ይሆን...? አይነት ሀሳቦች ይተረማመሱብኛል፡፡ አንዳንዴም ዘርና እምነት አንድ ናቸው፤ ሁለቱም በተስፋ ላይ ይፀናሉ - እላለሁ፡፡ ክረምትስ ቢሆን በየዓመቱ እንደሚከሰት ማመንን እንጂ ስራን አይጠይቅም -- እላለሁ፡፡
አሁን አሁን ...ፍርሃቴን እፈራዋለሁ:: የጫማዬን ተረከዝ መጣመም ስመለከት የእግሬ መጣመም እጅጉን ጎልቶ ይታየኛል:: ዛሬ ላይ ቆሜ እርጅናዬ ድቅን ይልብኛል፡፡ ሆሆ...ሰላሳን እንኳ ሳልዘል እንዴት እርጅና ያሳስበኛል? የጤናም አይደል፡፡
አላልኩም... ይኸው የጣቴ መድማት ባይጠዘጥዘኝ፣ የእርጅና ፀፀት  ይበላኝ ነበር::
መኮትኮት፤ የህሊናዬን ማሳ ማረም፣ ማልማት የክረምት ጨለማ ቢሆንብኝም የሽንኩርቱን ያህል አላሳሰበኝም፡፡ በርግጥ የፍርሀት ምንጩ  በርካታ ነው፡፡ ህይወት ፍርሃት ውስጥ ወድቃለች፡፡ ይህን ለመቋቋም ይመስላል፣ የሰው ልጅ በተለያዩ የዕውቀት ዘርፎች አማካኝነት ፍርሃቱን ይደብቃል፤ ሀይል እንደተላበሰ ያምናል -- ተሰግስጓል:: ሆኖም ሞትን የሚያህል ጠላቱን እንኳ ማሸነፍ የቻለ ቢመስለውም እውነታው ግን ለየቅል ነው፡፡
እናንተዬ፤ ፍርሃት ፍርሃትን ይወልዳል-- ለካ!  እኔን ጉድ ያደረገኝ ይኸው ነው፡፡ የሆነ ነገር ትዝ ሲለኝ አስከትሎ የሚመጣው ፍርሃትን ነው፡፡ ምናልባትም እልባት የሚያገኘው ከውጣ ውረድ በሚገኝ የጠነነ ልምድ ይመስለኛል፡፡ ለነገሩ ኑሮ የዛሬን ብቃት እንጂ የነገን ተስፋ ከመጤፍ የሚቆጥር አይመስልም፤ ችግር ሲውል ሲያድር ይገነግናል፡፡ አይበለውና ...አሁን ስኮተኩት እባብ ከመሬት ውስጥ ከአፈር ጋር ተመሳስሎ ብቅ ቢል ምን አደርጋለሁ? ...እ... እጮኸለሁ፣ እሮጣለሁ ወይም እገለዋለሁ:: እፍፍፍፍፍ .....ምን ሆኜ ነው ግን የምጨነቀው..... ፀጥ ብዬ አልኮተኩትም!   እንሽላሊቱንም፣ ቴንዜሉንም ባየሁ ቁጥር “ስም አይጠሩ” የመጣ እየመሰለኝ እበረግጋለሁ፤ እቁነጠነጣለሁ፡፡ አንዳንዴ ዙሪያ ገባውን እቃኛለሁ፡፡ ፍርሃት መገኛው የት ነው --- ቢባል፤  እኔው  እራሴ ነኝ፡፡
ሳሳዝን!...  ሽንኩርቴን ነቀልኩት፡፡ ፈሪ ድሮስ ምን ሊረባ!!..
ከአዘጋጁ፦ ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 2482 times