Saturday, 21 July 2012 11:07

ስልጣን (ነገር) ቢበዛ በአህያ አይጫንም!

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(0 votes)

ዲሞክራሲ በአኒሜሽን ይሰራልን!

አያችሁ ኢህአዴግ ተማርሮ “ሥልጣን ይዛችሁ እዩት” ብሎ ቢረግማቸው ወይም ቢመርቃቸው በብርሃን ፍጥነት ነበር “ባንዳፍ” የሚሉት፡፡ ከዛስ? “እንየዋ… ልቀቅልን!…” ይሉታል (ሥልጣኑን እኮ ነው) በዚህ የተነሳ ነው ምሬቱን እንኳን የማይገልፀው አሉ - አውራው ፓርቲያችን!! እናም ለዚህ ሁሉ ጣጣ ሁነኛው መፍትሄ

ምን መሰላችሁ?

የፖለቲካ አኒሜሽን ፊልሞችን

በብዛትና በጥራት

እያመረቱ መልቀቅ!!

ለስኬት የሚያነሳሱና የሚነሽጡ ራስን ማብልፀጊያ (Self development) መፃሕፍት ላይ ከምናገኛቸው አንኳር አንኳር ሃሳቦች መካከል visualization የሚለው ይጠቀሳል፡፡

ይሄ ፅንሰ ሃሳብ የምናልመውን ነገር እውን ለማድረግ ከሚያስችሉን መሳሪያዎች አንዱ ነው ይሉናል - የስኬት ሳይንስ ጠበብቶች፡፡

በእርግጥ እዚህ ደረጃ ጋ ከመድረሳችን በፊት ሌሎች የሚጠበቁብን ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ የህይወት ህልምና ግባችንን ለይተን እናውቀዋለን? ያሰብነውን ግብ ለማሳካት ፅናትና ቁርጠኝነት አለን? ግባችንን መቼ እንደምናሳካው እቅድ ነድፈናል ወዘተ--- ከዚህ በሁዋላ ነው visualization የሚመጣው፡፡

ነገሩ ይሄን ያህል እኮ ውስብስብ አይደለም፡፡ ለምሳሌ አንድ የምትወዱትን ነገር ወይም ሰው እስክታገኙት ድረስ ዘወትር በምናባችሁ ታስቡት ታሰላስሉት የለ----- በቃ እንዲሁ ማለት ነው፡፡ የምትፈልጉትን ነገር ከወትሮው በፍጥነት እጃችሁ ማስገባት የምትሹ ከሆነ በዓይነህሊናችሁ ሳሉት ---- ቅረፁት ----- ልክ እንዳገኛችሁ አድርጋችሁ ቁጠሩት - ይሉናል የስኬት ጠበብቶች፤ visualization የሚለውን ፅንሰ ሃሳብ ሲያብራሩ፡፡ የምትሹትን ነገር - የገንዘብ ነፃነት፣ ስኬት፣ ፍቅር፣ የስራ እርካታ፣ የሰመረ ትዳር ፣ ስልጣን፣ ወዘተ--- በእርግጠኝነት እውን ለማድረግ ከፈለጋችሁ በህሊናችሁ መቅረፅ - በምናባችሁ መሳል ይኖርባችሁዋል ሲሉም ይመክራሉ፡፡ ለምሳሌ አንገብጋቢ ፍላጐታችሁ  አውቶሞቢል ቢሆን ያንን የምትፈልጉትን አውቶሞቢል ከነቀለሙ፣ ከነሞዴሉ፣ በህሊናችሁ በመሳል ስታሽከረክሩት የሚሰማችሁን የእርካታ ስሜት በውስጣችሁ አጣጥሙት (የይምሰል ሳይሆን የምር) ይላሉ፡፡ ያኔ ያሻችሁት አውቶሞቢል ከች ይላል ወይም ከች የሚልበት ሁኔታ፣  እድል፣አጋጣሚ ይፈጠራል ባይ ናቸው - የስኬት ሳይንስ ጠበብቶቹ፡፡ ይሄ ነው የቪዥዋላይዜሽን ተዓምረኛ ምስጢር፡፡ ይሄ ነገር ለፖለቲካ ማለትም  የተመኙትን ስልጣን ለማግኘትም ይሰራ ይሆን? የሚል ጥያቄ ሊነሳ እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ባለሙያዎቹ እንደሚሉት ፖለቲካ --- ኢኮኖሚ---- ሳይንስ----- ፍቅር--- ሃብት---- ስኬት---- ወዘተ--- ያለአንዳች አድልዎ ለሁሉም ይሰራል፡፡ እውነቱ ይሄ ከሆነ ታዲያ ለምንድነው ተቃዋሚዎች በዚህ ዘዴ ተጠቅመው ስልጣን የማይይዙት? ልንል እንችላለን፡፡ (አይፈልጉ ይሆናላ) ልብ አድርጉ--- ስልጣንን ማሰብ፤ መመኘት፤ በዓይነህሊና መቅረፅ ----- አመፅ ወይም የጎዳና ላይ ነውጥ አይደለም፤ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ማፍረስ አሊያም በሃይል ስልጣን ለመያዝ መሞከርም አይደለም፡፡ ይልቁንም በሰላማዊ መንገድ ከራስ ጋር የመነጋገር--- የመታረቅ--- ህልምን እውን የማድረግ ዘዴ ነው - visualization፡፡ ሆኖም ለምን ፖለቲከኞች እስከዛሬ ለዓላማቸው አልተጠቀሙበትም ብትሉኝ ግን ምንም መልስ የለኝም፡፡

ለነገሩ ይሄን ፅንሰ ሃሳብ ለመነሻነት ተጠቀምኩበት እንጂ ዛሬ የምንጨዋወተው ስለአኒሜሽን ነው፡፡ በአኒሜሽን ፊልሞች በአሜሪካ ዝናው የናኘው ዋልት ዲዝኒ፤ 64 አካዳሚ አዋርድና 43 ኦስካር ተሸልሞዋል - አኒሜሽን ፊልሞችን በመስራት፡፡ አያስቀናም? አያችሁ ---- ከቀኑ አይቀር በእንዲህ እንዲህ ያሉት በጎ ነገሮች  ነው መቅናት (መልዕክቱ ለፊልም ባለሙያዎቻችን ነው) የጨዋታ አጀንዳዬ ግን ሌላ ነው፡፡ አኒሜሽንን እንድንጠቀም የፈለጉት በአጠቃላይ ለአገራዊ ጉዳዮች ነው፡፡ ምን አሰብኩ መሰላችሁ --- በኢቴቪ የሚሰብኩን ጋዜጠኞችና ካድሬዎች (የወል ስማቸው  ፕሮፓጋንዲስቶች እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ) ስለትራንስፎርሜሽን፣ ስለልማት፣ ስለኮብልስቶን ወዘተ---- የሚነግሩን ሁሉ አንዱም አልጥም  ብሎን የለ! (ራሳቸውም ቢጠየቁ ይጥማል አይሉም) ግን እኮ ጉዳዩ የሚጥም ባለመሆኑ አይደለም - ምናልባት ጠ/ሚኒስትሩ እንዳሉት በአቅም ማነስ ይሆናል እንጂ፡፡ መቼም በግድ ሊያሳምኑን ወይም ሊግቱን የሚሞክሩበት መንገድ አንጀት የሚያሳርር እንደሆነ ለናንተ አልነግራችሁም (እነሱን መሆን ነዋ!)

እናም ይሄንንና ሌሎች ተመሳሳይ ፈተናዎችና ችግሮችን ለመፍታት ነው አኒሜሽንን ያመጣሁት፡፡ ትንሽ ተደናገራችሁ እንዴ? ግዴለም በምሳሌ ስለማስደግፈው አሁኑኑ ግልጥልጥ ይልላችሁዋል፡፡ አያችሁ …ስለአብዮታዊ ዲሞክራሲ፣ ስለልማታዊ መንግስት፣ ስለኪራይ ሰብሳቢነት፣ ስለ1ለ5 --ወዘተ --- በካድሬዎችና በጋዜጠኞች ስንሰማ የኖርነው ፕሮፖጋንዳ ሁሉ አንጀታችን ላይ ጠብ አላለም፡፡ ይሄ ደግሞ ፖለቲካውን ወይም ኢህአዴግን እጀሰባራ (ሽባ) አድርጐታል፡፡ እናም የአኒሜሽን ፊልም ስትራቴጂው በዋናነት ይሄን ለመለወጥ ያለመ ነው፡፡

ባለራዕዩ አውራው ፓርቲያችን ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሳለፍ ምሎ ተገዝቶ የለ! (እኔ ብቻ ነኝ “የተቀባሁት” ማለቱን ግን ይተወን!) ይሄን ተልእኮውን ለማሳካት ደግሞ ቢያንስ የ30 ቢበዛ የ40 ዓመት (እንደሁኔታው ሊጨምር ይችላል) ሥልጣን ያስፈልገኛል ማለቱ ይታወቃል (ትዕዛዝ ነው ጥያቄ?) በጠባይ ይጠይቅ እንጂ እኛ አበሾች ሥልጣን ቋጣሪ አይደለንም፡፡ አይደለም የ40 ዓመት የ100 ዓመት ስልጣን ፈቅደንለት ሰርፕራይዝ ልናደርገው እንችላለን (ይቅርታ ለካስ ህገመንግስቱ አይፈቅድልንም) ለነገሩ ይሄ ሁሉ ዓመት ምን ያደርግለታል? (ስልጣን ቢበዛ በአህያ አይጫንም ይባላል እንዴ?)

ወደ ዋናው ቁም ነገር ስንመለስ ---- ኢህአዴግ ለምንድነው የ40 ዓመት ሥልጣኑን የፈለገው  የሚለው ጥያቄ በደንብ መመርመር ያለበት ይመስለናል (እንደህዝብ) የስልጣን ጥማት ነው ወይስ ግቡን ለማሳካት? ኢህአዴግ ይሄኔ “ተናገርኩ እኮ!” ሊለን ይችላል - “በደንፉ”፡፡ ግን ማን ሊያምነው! (ማን ነበረች ካላየሁ አላምንም ያለችው) እናም የተባለው ጊዜ ላይ ስንደርስ (ከ40 ዓመት በኋላ) ኢትዮጵያ ምን እንደምትመስል የሚያሳይ አኒሜሽን ፊልም እንዲሰራልን እንፈልጋለን (እስከዛው ማዝገሚያ ማለት ነው!) አኒሜሽኑ  መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ የምንሰለፍበትን ሂደት… ኪሳችንና መሶባችን ምን ያህል እንደሚሞላ፤ የኢኮኖሚው እድገት በስንት ፐርሰንት እንደሚመነደግ፤ የዜጐች የነፍስ ወከፍ ገቢ ምን ያህል እንደሚደርስ ወዘተ… በዝርዝር የሚያሳይና የሚነሽጥ ሲሆን ሁልጊዜ ማታ ማታ ከኢቴቪ ዜና ፊትና ኋላ ይቀርብልናል (ኢህአዴግም እኛም እንዳንረሳው)

አኒሜሽን የሚያስፈልገው ግን ይሄ ብቻ እንዳይመስላችሁ፡፡ እኛና ኢህአዴግን ያላስማሙንና በጥርጣሬ የምንመለከታቸው ጉዳዮች ሁሉ አኒሜሽን ፊልም ይፈልጋሉ (መተማመን ድሮ ቀረ!) ለምሳሌ ሲያወዛግበን ለቆየው የዋጋ ግሽበቱና የኑሮ ውድነቱ አኒሜሽን የግድ ነው፡፡ሰሞኑን የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ ለምክር ቤት አባላት ባቀረቡት ሪፖርት ላይ እንደገለፁት፤ እስካሁን ሪከርድ ይዞ የቆየው ባለሁለት ዲጂቱ የአገራችን የዋጋ ግሽበት (አሁን 25 በመቶ ላይ ነው) በሦስትና አራት ወራት ወደ አንድ አሃዝ ይወርዳል፡መንግሥታችን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትም (IMF) የዋጋ ግሽበቱ ወደ አንድ አሃዝ መውረዱ እንደማይቀር መተንበዩ ተጠቅሷል - በአምስትና ስድስት ወር ውስጥ፡፡

እኛ ግን የዋጋ ግሽበቱ በዚህ መጠን ሲቀንስና በኑሮአችን ላይ ለውጥ ሲያመጣ የሚያሳይ አኒሜሽን ፊልም ተሰርቶ ካልቀረበልን እንዲሁ በአፍ ብቻ አናምንም (IMFንም ቢሆን!) ለምን መሰላችሁ ---- ብዙ ጊዜ አምነን ብዙ ጊዜ ጉድ ሆነናላ! (የእድል ነገር!) ለነገሩ ኢህአዴግ እየለገመብን እኮ አይደለም በችግር የተተበተበነው፡፡ የማያዋጣ ስትራቴጂ እየተከተለ እንጂ! (በዚያ ላይ የሰው ምክር አለርጂክ ነው!)

ለምሳሌ የስኳር እጥረትንና ውድነትን ለመቅረፍ ምን ያልፈነቀለው ድንጋይ አለ? (ኮብልስቶንን ጨምሮ) ስኳር ከመቸርቸርና ከማከፋፈል ጐን ለጐን አንድ ሳይሆን ብዙ የስኳር ፋብሪካዎች ባለቤት እንደሚያደርገን በወኔ ተሞልቶ ነግሮን ነበር (ወኔ ስኳር አይሆንም) ግን ይኸው ስንት ዓመታችን? ምንም ነገር የለም፡፡ ለነገሩ አንድ ቀን መሰራቱማ አይቀርም፡፡ አሁን ጥያቄው እስከዚያው ምን ይደረግ ነው፡፡ መፍትሄው ቀላል ነው፡፡ የስኳር ፋብሪካ በአኒሜሽን ሰርቶ በኢቴቪ ማስተላለፍ! አያችሁ በየቦታው ይገነባሉ የተባሉትን የስኳር ፋብሪካዎች የምርት አቅም፣ የሠራተኞች ብዛት፣ የጥራት ደረጃ፣ የስኳር አይነት (ለአገር ውስጥና ለኤክስፖርት) ወዘተ… ያካተተ አኒሜሽን ቢሰራልን እኮ ለጊዜው እንረጋጋለን፡፡ አኒሜሽኑ ታዲያ ደረጃውን የጠበቀ ሊሆን ይገባል (በስንቱ እንበደል?) አያችሁ… ለዓመታት የናፈቀንን የስኳር ፋብሪካ በአኒሜሽን መልክ ስናይ አንድ አንድ ኩንታል ስኳር እቤታችን የገባልን ስለሚመስለን እጥረትና ችግር ደህና ሰንብት እንላለን - በእውናችን ሳይሆን በምናባችን (አንዳንዴ እኮ ከእውን ስኳር የምናብ ስኳር ይበልጣል!) ለኢህአዴግም ቢሆን ጊዜ መግዣ ይሆነዋል፡፡ “እንዲህም ሆኖ ካልተሳካለትስ?” የሚሉ ጨለምተኞች አይጠፉም፡ እውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደር ይባል የለ! እውነቱን ይናገራ! - አልሆነልኝም ብሎ፡፡

አሁን ደግሞ ወደ ኮብልስቶን አኒሜሽን እንግባ፡ ዜጐች በዲግሪና በማስተርስ ከተመረቁ በኋላ በኮብልስቶንና በግብርና መሰማራታቸውን በመንቀፍ ኢህአዴግንና የትምህርት ሥርዓቱን የሚተቹ ወገኖች ተበራክተዋል (ስልጣን የያዘ ፓርቲ ምሳር ይበዛዋል እንዲሉ!) እኒህ ወገኖች ግን  አንድ ያልገባቸው ነገር አለ፡፡ ኢህአዴግ እቺንም የሥራ እድል (ኮብልስቶንን) ለመፍጠር እኮ ስንት ፍዳውን በልቷል፡፡

የሆኖ ሆኖ ይሄንን ትችትና ነቀፋ ለመከላከልም ብቸኛው መፍትሄ አኒሜሽን ፊልም ነው (ካድሬዎችንማ!) እናላችሁ…ባለዲግሪና ባለማስተርሱ ወጣት ኮብልስቶን አንጥፎ… በበሬ አርሶ… ከተማ አፅድቶ… በአጠቃላይ ከአእምሮ ስራ ወደ ጉልበት ስራ ገብቶ ለራሱም ሆነ ለአገሩ የሚያስገኘውን ለውጥና ላቅ ያለ ጥቅም የሚያሳይ አኒሜሽን ሰርቶ በኢቴቪ ማቅረብ ነው መፍትሄው (በተጨባጭ ማሳየት ከባድ ነዋ!)

የኢትዮጵያን እድገትና የተረጋጋ ኢኮኖሚ ለመቀበል የሚተናነቃቸው አንዳንድ የኒዮሊበራል ተላላኪዎች፤ ኢህአዴግ ህዝቡን በቀን ሦስቴ አበላለሁ ብሎ በቀን አንዴም እንዳይበላ አደረገው እያሉ… ወሬ ሲያናፍሱ ይሰማሉ(እኛ ራበን አልን እንዴ!) እነዚህን ተላላኪዎች አፋቸውን ለማዘጋት ህዝቡ በቀን ሦስቴ ሳይሆን አራቴ (መክሰስን ጨምሮ) እየበላ እንደሆነ የሚያሳይ ምርጥ የጥጋብና የመትረፍረፍ አኒሜሽን መስራት ያስፈልጋል - ለኒዮሊበራል ተላላኪዎች ብቻ ሳይሆን ለእኛም ጭምር፡፡ በእርግጥ ኢህአዴግ በቀን ሦስቴ አበላችኋለሁ ብሎ ቃል የገባው የዛሬ 20 ዓመት ገደማ ነበር (ባለማወቅ ነው!)

አሁን ሳስበው ግን…ምናልባት በቀን ሦስቴ የመብላቱ ነገር የሚሳካልን አገራችን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ስትሰለፍ ይመስለኛል፡፡ (ከ30 እና 40… 50… 60 ዓመታት በኋላ ያውም በኢህአዴግ ብርታትና ትጋት ብቻ!) ለዚያ እኮ ነው በቀን ሦስቴ አማርጠን ስንበላ የሚያሳይ ደረጃውን የጠበቀ አኒሜሽን ፊልም መኮምኮም የሚያስፈልገን፡፡

አያችሁ አንዳንድ ጊዜ እኮ በአውራው ፓርቲም ቢሆን መፍረድ ያስቸግራል፡፡ ለምን መሰላችሁ… አንዳንድ ነገሮችን በፕሮፓጋንዳ እንጂ በተግባር ማሳየት ከባድ ነው፡ለዚህ እኮ ነው በአኒሜሽን ቴክኒክ መጠቀም ያስፈለገው፡ለምሳሌ ኢህአዴግ ኢኮኖሚው 11 በመቶ እየተመነደገ ነው ቢልም አንዳንድ ጨለምተኞችና ሟርተኞች አልተቀበሉትም - ህዝቡ ኪስ ወይም ሌማቱ ውስጥ ለውጥ የለም በሚል፡፡ ይሄንን በፕሮፓጋንዳ ለማሳመን መጣር ከንቱ ልፋት ነው (ካድሬዎች ብለው ብለው አቅቶዋቸዋል) ስለዚህ የኢኮኖሚ እድገቱንና ለአገርና ለህዝቡ ያቀዳጀውን ውጤት በአኒሜሽን ሰርቶ ለህዝቡ ማሳየት!! ያኔ የኢኮኖሚውን እድገት “ፌክ” ነው እያለ ሲቃወምና ሲተች የነበረ ሁሉ ኩም ይልልናል፡፡ አያችሁ… አኒሜሽኑ 11 በመቶ እድገቱን በፕሮፓጋንዳ ሳይሆን በተጨባጭ የሚያሳይ ይሆናል - ኢንዱስትሪዎች ሲስፋፉ፤ ፋብሪካዎች እንደ አሸን ሲፈሉ፤ ሠራተኛው በደሞዝ ጭማሪ ሲንበሸበሽ ወዘተ… ዜጐች የተንደላቀቀ ኑሮ ሲመሩ ያሳየናል፡፡ እናም በገሃዱ ዓለም ያጣነውን በአኒሜሽን እናገኛለን ማለት ነው (ኑሮ በዘዴ ይሏል ይሄ ነው!)

ወደ ፖለቲካውም ስንመጣ አኒሜሽን ብዙ ችግሮቻችንን ይፈታልናል ተብሎ ይታመናል፡፡ በተለይ በአሁኑ ሰዓት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኢህአዴግን እያማረሩ አይደል… የፖለቲካ ምህዳሩ ጠበበ… ሰብአዊ መብቶች ተጣሱ… ህገ መንግስቱ አልተከበረም… የፕሬስ ነፃነት አደጋ ላይ ነው… ወዘተ በተደጋጋሚ ሲናገሩ፣ መግለጫ ሲያወጡ… ሲያወግዙ እየተሰማ ነው፡፡ በእርግጥ በባዶ ሜዳ አይደለም - ማስረጃ ያቀርባሉ (ኢህአዴግ ባይቀበለውም) አባላቶች ታሰሩ… ተዋከቡ… ተገደሉ… እያሉ፡፡ በሽብርተኝነት ስም ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች እየታሰሩ ነው በማለትም የፍትህ ተቋማት ነፃ አይደሉም ብለዋል፡፡

እንግዲህ ገዢው ፓርቲ ይሄንን ጉዳይ የግድ ማስተባበል ወይም አምኖ መቀበል አለበት አይደል! በእርግጥ በየጊዜው ለማስተባበል ሞክሯል (ባይሳካለትም!) ተቃዋሚዎቹ የፖለቲካ ምህዳሩ ጠበበ ሲሉ ጠ/ሚኒስትሩ ምን አሉ? “የጠበበ ምህዳር የለም!” ግን ተቃዋሚዎች አመኗቸው? በፍፁም! አያችሁልኝ… ገዢ ፓርቲ የመሆንን ጣጣ! (ላለመታመን የተጋለጠ ነው) ወላጆች ልጆቻቸው ሲያማርሯቸው ምን ይላሉ መሰላችሁ? “ወልደህ እየው!” ኢህአዴግም እንዲህ ሊል ትንሽ ነው የቀረው - ተቃዋሚዎቹን! ከምሬ እኮ ነው… እየፈራ ነው እንጂ “ሥልጣን ይዛችሁ እዩት” ለማለት ይፈልግ ነበር፡፡  ግን ተቃዋሚዎች እንኳን እቺን አግኝተው እንደውም እንደው ናቸው፡፡ አያችሁ ኢህአዴግ ተማርሮ “ሥልጣን ይዛችሁ እዩት” ብሎ ቢረግማቸው ወይም ቢመርቃቸው በብርሃን ፍጥነት ነበር “ባንዳፍ” የሚሉት፡፡ ከዛስ? “እንየዋ… ልቀቅልን!…” ይሉታል (ሥልጣኑን እኮ ነው) በዚህ የተነሳ ነው ምሬቱን እንኳን የማይገልፀው አሉ - አውራው ፓርቲያችን!! እናም ለዚህ ሁሉ ጣጣ ሁነኛው መፍትሄ ምን መሰላችሁ? የፖለቲካ አኒሜሽን ፊልሞችን በብዛትና በጥራት እያመረቱ መልቀቅ!!

ሃቁን ለመናገር በፖለቲካው ዘርፍ ያሉ አያሌ ችግሮቻችንን ለመፍታት በርካታ አኒሜሽን ፊልሞች ያስፈልጉናል፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩ እንደ አገር መስፋቱን… ዲሞክራሲ እያበበና እየጐመራ መሆኑን… ሰብአዊ መብት ሙሉ በሙሉ መከበሩን… ተቃዋሚዎች እንዳሻቸው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን… አንድም የታሰረ፣ የተዋከበ፣ የተገደለ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል እንደሌለ… ወዘተ ወዘተ… እነዚህን ሁሉ ኢህአዴግ በአኒሜሽን ሰርቶ ማቅረብ ይጠበቅበታል (በእውንማ አይሞከርም!)

የአኒሜሽን ጥቅሙ ምን መሰላችሁ? በመሬት ላይ ያለው እውነታ ከፊልሙ ፍፁም ተቃራኒ ቢሆንም… ማንም የሚቃወም የለም! ለምን አትሉም… በመልካምና በጐ ነገሮች የተሞላ ስለሆነ ዜጐች (ተቃዋሚዎችን ጨምሮ) ዛሬ ባይሆንም ወደፊት (ቀን አልተቆረጠለትም) እውን ይሆናል በሚል ተስፋ (ያለ ያህል በመቁጠር) አኒሜሽኑን ይኮመኩሙታል! (ምርጫ የለማ!)

አያችሁ የአኒሜሽን ባህል እየተለመደ ሲመጣ (መለመዱ አይቀርም) በእውን አልሳካ ያለንን ነገር ሁሉ… በፊልም እየሰራን ዓለማችንን እንቀጭበታለን፡፡ የሞቀ ትዳር፣ ከፍተኛ ሥልጣን፣ የተቀማጠለ ኑሮ፣ ከፍተኛ ትምህርት፣ የላቀ ስኬትና ብልፅግና ወዘተ… በአኒሜሽን እየሰራን እንኮመኩማለን፡፡

አንድ ቀን የምር እስኪሳካ በአኒሜሽን እንፅናናለን፡፡ በአኒሜሽን እንበላለን፡፡ በአኒሜሽን እንጠጣለን፡፡ በአኒሜሽን እንጠግባለን፡፡

በአኒሜሽን እንዝናናናለን፡፡ በአኒሜሽን እንማራለን፡ በአኒሜሽን እንበለጽጋለን፡፡ በአኒሜሽን እንደግፋለን፡፡ በአኒሜሽን እንቃወማለን፡፡  በአኒሜሽን ህገ መንግሥታዊ መብቶቻችንን እናስከብራለን…በገሃዱ ዓለም ያጣነውን በአኒሜሽን እናገኛለን፡፡ የአኒሜሽን ህይወት እናጣጥማለን (ይሄንንስ ማን አየበት!) ሃሳቤን ነግሬአችሁ ልሰናበት --- ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሰላማዊ መንገድ (በምርጫ ማለት ነው) ስልጣን ይዘው ሲያስተዳድሩን የሚያሳይ አኒሜሽን ለማሰራት ኢህአዴግን ስፖንሰር ልጠይቅ አስቤአለሁ፡፡ (እርግጠኛ ነኝ እምቢ አይለኝም!)

 

 

Read 3956 times Last modified on Saturday, 21 July 2012 11:12