Tuesday, 25 August 2020 06:05

አዲሱ የደራሲ አለማየሁ ገላጋይ የምናብ ልጅ!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(4 votes)

 ደራስያን ተፈጥሮ የሰጠቻቸውን ወንበር ካልናቁ፣ …መቅረዛቸው በንባብ ዘይት ጢም ካለች፣ ምናባቸው የሚለጠጥበትን አድማስ በገበያና ቁሳቁስ ካልደፈኑ… ነበልባላቸው ወደ ግግር ፍም፣ የነፍሳቸው ዳንስ በሰማይና በምድር ወሰን አልባ ኮከብ በመሆናቸው እርሻቸውም የቀለዘና ባለ ፍሬ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡
የእንባና ሳቅ እንጎቻ፣ የብልጽግና ካባና የድህነት ድሪቶ፣ የሰላም እልፍኝና የጦርነት ዐውድማ ለደራሲው የፈጠራ ዝርግፍ ጌጦች ናቸው፡፡ እያለቀሰ መክነፍ-እየሳቀ-መገተርም ይችላል፡፡ በሲዖልና በገነት መካከል በተከላቸው ዛፎች ላይ የሚደንሱ ንቦች ‹የሚወዛወዙትን ቢራቢሮዎች ብቻ ሳይሆን፣ በብርሃን መሃል ተጠብሰው የሚሞቱትን የሳት ራቶች ድምጽ የሚሰማበት ጆሮም አለው፡፡
ዛሬ መጽሐፉን የምዳስስለት ደራሲ አለማየሁ ገላጋይም በሀገራችን ሥነጽሑፍ፣ እሾህ በወረሰው ሁዳድ ውስጥ እጅ ሳይሰጥ፣ ባንዲራውን ሳያስነካ፣ ገበያ መሃል በወላዋይነት ሳይዳክር፣ እንደ እንግሊዙ ጸሐፌ ተውኔት ጆርጅ በርናንድ ሾ ራሱን ለኩሶ፣ በጥበቡ ሰፈር ድንኳን ውስጥ የነደደ ቸር ነው፡፡ የዛሬ አስራ ሶስት አመት ገደማ "አጥቢያ" የተሰኘች ልቦለድ መጽሐፍ ይዞ ብቅ ሲል ብዙዎቻችን "የት ጉድጓድ ውስጥ ነበረ?"  ብለን ጠይቀናል፡፡በርግጥም ‹‹አጥቢያ›› የአራት ኪሎ ዐይኖች የተገጠሙላት፣ መጻኢውን የሕይወት እንዝርት ልቃቂት በምልዐት የምትተረትር ነበረች፡፡
ዛሬ ደግሞ አለማየሁ ‹ሀሰተኛው በእምነት ስም› ብሎ ሲመጣ እንደ ትናንቱ በዓይን የሚታይ፣ በጆሮ የሚደመጥ፣ ተጨባጭና ዕውናዊ ዐለም ይዞ አልመጣም፡፡ ይልቅስ ረቂቁን ዐለም እየፈተሸ፣ መንኩራኩሩን እያመጠቀ፣ ምናባዊውን ዐለም ለመዳሰስ ሞክሯል፡፡ ይህ ደግሞ ዕድገትም፣ ልዕቀትም ይመስለኛል፡፡ ይህ መጽሐፍ ከቀደመው ሥራው ከ ‹‹ታል በእውነት ስም››ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው፡፡ እንዲያውም በርካታ ገጸ ባሕርያት ወደዚህኛው መጽሐፍ ተሻግረዋል:: ለምሳሌ አልዐዛር፣ ነጸብራቅ፣ ረድ ሰርዌ፣ ሲፈን ወዘተ-- ይጠቀሳሉ፡፡
መጽሐፉ ሁለት ዐለማትን፣ ሰማያዊና ምድራዊ፣ አሁንና ወደፊትን፣ ውስንነትና ዘላለማዊነትን፤ ሁለት ስነምህዳር፣ ሁለት ማህበራዊ፣ ሁለት ባህላዊ  መዋቅሮችን፣ የሚያሳይ ነው፡፡ በዚህም መካከል የግጭቶችና ስምምነቶች ነጸብራቆች መጽሐፉን በብርሃንና በጭጋግ ሞልቶት እናያለን፡፡ የመጀመሪያውና በአንደኛ መደብ የሚተርከው ገጸ ባህርይ ሕይወት የሚያሳየን የሕይወትን ዝብርቅርቆሽ፣ የሕይወትን ወለፈንዴነትና በሁለት ዐለም መንጠልጠል የፈጠረበትን ቀውስ ነው:: ታሪኩ ሲጀምር መግቢያ ያደረገው የጠቢቡን ሰለሞን "መክብብ" የፍልስፍና ጽሑፍ ነው፡፡ ጭብጡም የሕይወትን ከንቱነት የሚያሳይ ነው፡፡ የነገረ መለኮት ምሁራን ይህን መጽሐፍ  "ንጉስ ሰለሞን ጤናማ መንፈሳዊ ሰው በነበረ ጊዜና ችግር ውስጥ ገብቶ መንገድ በሳተ ወቅት የጻፈው ነው" በማለት ለሁለት ይከፍሉታል፡፡ ሰለሞን ወለፈንዴያዊ ሃሳቦቹን የጻፈው በእምነት ዳንዳ ላይ ሰማያዊ ክብር እያየ ሳይሆን በተስፋ መቁረጥ ጭጋግ ውስጥ ሆኖ ሲዝል፣ የዘላለሙ አድማስ ተጋርዶበት ነበር ይባላል፡፡
 አለማየሁ ገላጋይም ወደ ራሱ የፍልስፍና አቅጣጫ ወይም የገጸባሕርያቱ ሕይወት ወደሚወክለው አቅጣጫ የሚወስደውን ሰረገላ  የመረጠ ይመስላል፡፡ ስለዚህ የኔም ዳሰሳ የሚያተኩረው ደራሲው በመረጠበት መንገድ በቀደደው ቦይ፣ በዘረጋው ሃዲድ ላይ  ነው፡፡ ታሪኩን አሃዱ ያለበት የሰለሞን የፍልስፍናም መጽሐፍ ገጽ 9 ላይ እንዲህ ሰፍሯል፤-
"የሰው ልጅ በከንቱነት ተፈጥሯልና…ከተፈጠረም በኋላ እንዳልተፈጠረ ሆኗልና …በአፍንጫችን ያለ ትንፋሻችንም እንደ ጢስ ነውና… ሰውነታችንም እንደ ምጣድ ብልጭልጭታ ናትና…"
ለመጽሐፉ አጠቃላይ ሀሳብ አለማየሁ ልብ ላይ የወደቀው የጠቢቡ ሰለሞን ጥሬ ዘር ይህ ነው፡፡ ይህ ዘር በውስጡ ተብላልቶና በስሎ የተቀጠፈው ፍሬ ደግሞ ‹‹ሐሰተኛው በእውነት ስም›› ብሎ በፈጠረው ዐለም ውስጥ ያለውን  የሕይወት ዝብርቅርቅ፣ ሕልምና ቅዠት፣ እውነታና ትንቢት አደባባይ አውጥቶታል፡፡ ደራሲው፤ ሰማያዊና ምድራዊ፣ ተጨባጭና ረቂቅን ሲያነጽር - በዋናነት ታሪኩ ውስጥ ዐምድ ሊባል የሚችለውን ገጸ ባህርይ፣ ረድ ሠርዌን፣ የሳለበትንና የሚያምንበትን የሐሰተኛው መሲህ መገለጥ ጉዳይ መሰረት አድርጎ ነው፡፡ እናም ረድ ሠርዌን በተለያዩ ግጭቶችና ሕልሞች ፈትኖ በታሪኩ ውስጥ እንደ ባንዲራ አውለብልቦታል፡፡ ጉዳዩም ከዘላለም ጋር የሚያያዝና የሩቅ ግብ ያለው ስለሆነ ብዙ ዋትቷል፤ አንባቢውንም ቀልቡን ወስዷል፡፡
በአጠቃላይ መጽሐፍዋ ዘላለምን የምትፈልግ ትንሽ ባዛኝ መንኩራኩር ትመስላለች፡፡ ታሪኩ ውስጥ በረዥሙ ቁመናው በየአጋጣሚው ብቅ የሚለው ሐሰተኛው መሲህ ነው፡፡ እንደ ረድ ሠርዌ አባባል፤ ሐሰተኛው መሲህ መልክና ቁመናው ለየት ያለ ነው፡፡ ቁመተ ቀውላላ፣ አንገተ ሰላላ፣ ጭንቅላተ ሞላላ፣ቀኝ ዐይኑ የተኮላሸች ግራ ዐይኑ የተቅላላች ናት:: ከሐሰተኛው ክርስቶስ መገለጥ ጋር ይኖራል ተብሎ የሚገመተው ‹‹የአርማጌዶን ጦርነት››ን አልፎ አልፎ በስሱ ጠቅሶታል:: ሐሰተኛው መሲህ ግን በተራኪው ገጸ ባህርይ ሕይወትና አንደበት፣ ሕሊናና ሕልም ብቅ እያለ የምናየው አንዳች ትንቢታዊ ክስተት ሆኖ ተስሏል፡፡
አውራው ገጸ ባሕርይ ዋና ስራው ጋዜጠኛ ይሁን እንጂ በትርፍ ሰዐቱ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የፍልስፍና ትምህርት ያስተምራል፡፡ ይሁን እንጂ ይኸው የፍልስፍና መምህር ረድ ሠርዌ ባሰረጸበት የትንቢት ቀጠሮና የእምነት መንጠቆ ተይዞ መፈናፈኛ ሲያጣ እናየዋለን፡፡ ለኑሮው ደንታ ቢስ፣ ስለ ነገ የማይገድደው፣ ለቅንጦትና ክብር ደንታ ቢስ ሆኖ እናየዋለን:: ምናልባትም እንደ ግሪኩ ፈላስፋ ዴዎጋን፤ ለውሃ መጠጫ የያዛትንም ጥሎ በእጁ እፍኝ የሚታጣበት ግድ የለሽነት ይታይበታል፡፡ከረድ ሰርዌ ጋር ተጋርቶ የሚበላውን ስናይ፣ ሰውዬው ለምንም አይመለስም ማለታችን አይቀርም፡፡ ብዙ ወዳጆቹንም ግራ ሲያጋባ የምናየው በዚህ ነው፡፡ በማይመጥነው ሕይወት፣ በማይመጥነው ድንኳን ቁጢጥ ብሎ መገኘቱ!!
ሌላኛው የሕይወት ንጽጽር፣ በመጽሐፉ ክፍል አንድና ሁለት፣ የሚታየው የሕይወት አጽናፍ ነው፡፡ በአንድ በኩል፤ ፉክክር ምድጃ ስር የተወዘተ፣ በጥድፊያና ግብግብ የነደደ የአዲስ አበባ አንድ መንደር፣ እነ ናትራንን የመሰሉ እሳት የላሱ አራዳዎችን ታቅፋ ስትደንስ፣ በሌላ በኩል፤ ዐይነምሳ የተባለችው የገጠር ቀበሌ፣ ቡልቡላን የመሰለች ቅንና ቸር ሴት ይዛ፣ ሌሎችን እሹሩሩ በሚል ልብ ሆና፣ ካብ ለካብ ትታያለች፡፡ የሸገርዋ ናትራን፤ ‹‹ሴሽ አለህ?›› እያለች ወደ ቤቱ ዘው ስትልና፣ የዐይነምሳዋ ቡልቡላ እርጎና ዳቦ ይዛ ስትመጣለት አስተውሏል፡፡ ቡራቡሬ ዐለም!!
ናትራን አውሬ አይደለችም፤ ልቧ በጨካኞች የተነከሰ፣ የማይታይ ጠባሳዋን ደብቃ የምትኖር፣ ልቧ እንደፈቀዳት እንድትኖር ሕይወት ያስተማረቻት፤ ልጓሟን ያላላች ምስኪን ናት፡፡ አንዳንዴም ቁስሏ ሲነካባት እዬዬ የምትል፤ ‹‹እያነቡ እስክስታን›› ማሳያ ናት፡፡ በዚያች የቀበጠች የጦፈች ሰፈር፣ ጥድፊያ በነገሰባት ቀበሌ፣ ለሕይወቷ ምሽግ የሰራች ወታደር ነች፡፡
ገራሟ  ቡልቡላ ገጠር ተደብቆ፣ በጮሌዎች ያልተነከሰ ድንግል ልብ፣ፍቅር ፍቅር የሚሸትት ነፍስ ያላት፣ ኦሮምኛ ተናጋሪ፣ ቤት አከራይ፣ ቸር፣ ነች፡፡ ፍቅሯን ከጋሽ ቢራራ ጋር ለመጨረስ ዐይናፋርነቷ በልምጭ የሚገርፋት ምስኪን ናት፡፡ በዐረንጓዴው ዐለም፣ በተረጋጋው የሕይወት ጅረት የምትፈስስ፣ መጠላለፍና ማስመሰልን የምትጸየፍ፤ ማታለል ባልገነነበት ዐለምና መንደር ትኖራለች፡፡ ጋሽ ቢራራ የገጠር ትምህርት ቤት አትክልተኛ ግን ደግሞ “መምህር ነኝ" የሚልና መምህር ተብሎ ሲጠራ ደስ የሚለው ገራገር ዐይነት ሰው!
የአላዘር ሕይወት በዚህ አረንጓዴ ዐለም፣ በዚህ በሰከነ መንፈስ፣ በዚህ ገርነት በገነነበት ዐለም፣ ነፍሱ ጨርቁን ጥላ አብዳ ነበር:: ጥሬዋ ሕይወት ያለችው እዚያ ነበር፡፡ ፈላስፋው ሔነሪ ዴቪድ ቶሩ እንደሚለው፤ ከተሜነት የሸረኝነት ማዕከልና የፉክክር መንበር ነው፡፡ ‹‹ዋልደን›› የተባለውን ድንቅ ጽሑፉን የፃፈው፣ ሶስት ዶላር በማይሞላ ወጪ፣ የገዳም ያሕል ኑሮ የኖረውን አልዐዛር ዐይነት ስሜት ተሰምቶት ነበር፡፡ ሀርቫርድ ተመርቆ እዚያ ገጠር ከገባ፣ አልዐዛር እንዴት የፍልስፍና መምህርና ጋዜጠኛ ሆኖ አይነምሳ ገባ አይባልም!
አይነምሳ ቅንብቢት፣ አይነምሳና አዲስ አበባ፣ የገነትና ሲዖል ያህል ናቸው፡፡ እንደ ተርጓሚዎቹ ሩቅና ሩቅ፣ ምስራቅና ምዕራብ!... ናትራንና ቡልቡላ፤ ነፀብራቅና ቡልቡላ፤ ጋሽ ቢራራና የከተሜው ሰዎች:: ዓይነምሳ ቀዝቃዛ ምድር ናት፡፡ ነጭ ችፍርግ፣ ነጭ ቅጠል፣ ነጭ ግንድ፣ ነጭ ፍሬ ያላቸው ብዙ ተክሎች ሠርመዴን ያፈረሰ ቄስ አስመለዋታል፤ ይላል፡፡ (ገጽ 185)
ቋንቋዋ አፋን ኦሮሞ ነው፡፡ “ኬሱማ” እንግዳ ማለት ነው፡፡ “በሲሳ” መምህር!... “በሲሳ አዲስ አበባ” የአዲስ አበባው መምህር ነው፡፡ ደርጌሳ ጐረምሳ ማለት ነው፡፡ “ኢልማ አዲስ አበባ” ቢባል የአዲስ አበባ ልጅ ነው:: ቁመናውን ለማሣየት “ኤልማ ወለጋ” ብለውታል፤ ጋሽ ቢራራ፡፡ ባብዛኛው የወለጋ ልጆች ቁመታቸው ዘለግ ያለ ስለሆነ፡፡
መጽሐፉ እንደ ቀሰም ጠቅልሎ ልቃቂቱ የሚተረትበት ሀሣብ፣ የሐሰተኛው መሲህ ጉዳይ ይሁን እንጂ ሌሎችም ንዑሳን ጭብጦች አሉት፡፡ በርካታ ማህበራዊ፣ ባህላዊና ትውፊታዊ ስነ-ልቦናዊ በሮችን ያንኳኳል፡፡ የሐሰተኛው መሲህ ጉዳይ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ የተሰሎንቄ አማኞች የምፅዓት ቀንን ተቀምጦ መጠበቅ ያስከተለው ሥጋት፣ ሃዋርያው ጳውሎስን ሁለተኛን መልዕክት እንዲፅፍ አስገድዶታል የሚል ነገረ መለኮታዊ ሀሳብ አለ፡፡ ስለዚህም ክርስቶስ ወዲያው ይመጣል ብለው ምድራዊውን ሕይወት ንቀውና ችላ ብለው የተቀመጡትን ሰዎች “ጊዜው ገና ነው” በማለት ከሰጣቸው ምክንያቶች አንዱ ‹‹የሐሰተኛው ክርስቶስ›› ቤተ መቅደሱ ውስጥ ሳይገባ ሐሰተኛው ያለመገለጡን ነው፡፡ ያ ሣይሆን ሀሰተኛው መሲህ ሣይገለጥ፣ እውነተኛው አይመጣም፤ በሚል ስለ ሀሰተኛው ክርስቶስ ፍንጭ ይሰጣል፡፡ ሌላኛው ሃዋርያው ዮሐንስ፣ በፍጥሞ ደሴት በእሥር ሆኖ በፃፈው የራዕይ መጽሐፍ፣ ምዕራፍ አሥራ ሦስት ላይ “አውሬው” ተብሎ የተጠቀሰውን እንደ መነሻ መውሰድ ይቻላል፡፡
ይሁንና “ሐሰተኛው” በሚለው የአለማየሁ መጽሐፍ ላይ ግን ስለ ፈረንጁ መሲህና ስለ ኢትዮጵያዊው መሲህ ውድድር የታዩ ሀሣቦችና ምልክታዎች አሉ:: ኢትዮጽያ ውስጥ “እኔ ክርስቶስ ነኝ” ብሎ የተነሣውን ሰው በዘመኑ የነበሩት ንጉሥ፣ አንገቱን አሥቆርጠው እንዳሰናበቱት ያስነብባል:: ይሁንና ኢትዮጵያዊ ክርስቶስ የመመኘቱ ጉዳይም ወደ ብዙ ስነ ልቦናዊ ዝብርቅርቅ ይወስደናል፡፡ ”ጥቁር  መሲህ  መፈለግ  የንግስት ሳባን ከሰለሞን ጋር መዋለድ፤ ቀዳማዊ ምኒልክን በእስራኤል ንጉሥ መንገሱን ያለመቀበል፣ የኛን ዘመን ገናናነት አሳንሶታል የሚል ቁጭት ሣይቀር ተወርቶበታል:: በዘመኑ የነበረችው ኢትዮጵያ፣ ንጉሥ ከእስራኤል ሊነግሥላት ይገባ ነበርን? የሚል ጥያቄ አለ፡፡ ታላቅነታችንን እንስቷ ንግሥታችን አሣንሳለች የሚል እንባም አለ:: ወደ መጽሐፉ ሲኬድ ደግሞ “እስራኤል የተመረጠ ነው” የሚል ግጭቱ እሣት ይተፋል፡፡ እሣቱ ታሪኩን ያሞቀዋል፤ ፍሙን ይጋግረዋል፤ ትልልቅ ሀሳቦች ቁጭትና ሕልሞች… የሚያስተጋቡ ስላቆች፤ የጠነኑ ፍልሚያዎች  አሉበት፡፡
የረድ ሠርዌ እምነት ሥጋን በመጨቆን መንፈስን እንደ ጧፍ መለኮስ ነው፡፡ በፆም በፀሎት መትጋት ወይ ደግሞ መጽሐፉ ውስጥ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከሐሰተኛው መሲህ ትይዩ ብቅ የሚል ነው፡፡ ረድ ሠርዌ በሕይወት ድንግዝግዝ አካባቢ ዐይኖቹ ሲጠፉ እንደ እግሊዛዊው ባለቅኔ ጆን ሚልተን፣ ከእግዚአብሔር ጋር መነታረከ አልዳዳውም፡፡ ይልቅስ እንደ ጽድቅ ማጠራቀሚያ ሪቅ አድርጎ ተቀበለው፡፡ በእርሱ ቤት ዐይን ካላየ ሀጢአት የለማ!
በዚህ ዐይነት ስጋን መጨቆን በተለያዩ ሀይማኖችና ሃይማኖት ነክ ፍልስፍናዎች ውስጥ አለ፡፡ በ150 ዐም ጀምሯል ከሚባለውና አንዳንዶች ስምዖን ማገስ ከተባለ ሰው ጋር ይያያዛል ከሚሉት የኖስቲሲዝም ፍልስፍና ጋር የሚዛመዱ ነገሮች አሉበት፡፡ ትምህርቱ ሁለት መልኮች ያሉት፣ መንፈስን ከመልካም፣ ክፉን ከቁስ ጋር የሚያያይዝ  ነበረ፡፡ይህ ትምህርት ስጋን በመጨቆን የሚያምን ስለነበር፣ ለምናኔም የራሱ ድርሻ ነበረው፡፡ ይህን በተመለከተ በተስፋ የአይሁድ፣ የክርስትና፣ የእስልምና እንዲሁም የቡድሃና ሒንዱ እምነት ተከታዮች በዚህ መርህ ውስጥ እንደሚካተቱ ፒተር ኮሌ የተባሉ ተመራማሪ “Religious experiences” በሚል መጽሐፋቸው ስለ ሃይማኖታዊ ልምምዶች ይነግሩናል:: “mysticism” ማለትም እነዚህን ሁሉ ስርዐቶችና ተቀባይነት ያገኙ ልማዶችን የሚጠቀልል ነው፡፡ ታዲያ እነዚህ ልማዶች እንደየ ዐውዱና ባህሉ ይለያያሉ የሚሉና ሁሉም ተመሣሣይን አንድ ናቸው የሚሉ ወገኖች እንዳሉ ያስረግጣሉ፡፡ እንደ ረድ ሠርዌ በግል የሚለማመድና የአልዛቤል (የረድ ሠርዌ ፍለጋ እግሯን ያቀጠናት የሴሰኝነት ተምሳሌት ሴት) በኋላ አልአዛር ያገኛቸው ቡድን ዐይነቱ ልምምድ ለየቅል ነው ይላሉ፡፡ ይህንንም Introtive እና Extrotive ብለው ያቧድኑታል፡፡ እንደ ካትዝ አርጊዩ ያሉት ተመራማሪዎች ደግሞ ድንበር ሊበጅለትም አይችልም ይላሉ፡፡ ዋናው ነገር ግን ዞሮ ዞሮ የነፍስን ልዕልናና ውበት ለመጠበቅ የሥጋን ውበት ሃይል የመገሠሥ ፍላጐት ናቸው:: ስለዚህም ገዳማዊት ሕይወትና የፆምና የፀሎት ትጋት ግብ፣ ጽድቅን ፍለጋ የመባተት ውጤቶች ናቸው፡፡
ለዚህ ነው ረድ ሠርዌ  “Sick Souls” በሚል በአንድ ነፍስ ሁለትነት ውስጥ የሚሠቃየውን አልዐዛርን የዚሁ መቃተት ተጋብቶበት፣ የምድሩንና የሰማዩን፣ ትንቢቱንና ተጨባጭ አለምን የሚያናውጠው፡፡ ዐለም አቀፍ ዝናን  የተጐናፀፈው ደራሲ ጆን ቡንያን በዚሁ ምጥ ውስጥ ሆኖ "-- and now I was sorry that God had made me a man” ያለው፣ ሰው ከመሆን ይልቅ አውሬ \አሳ መሆንን የመረጠበት ምክንያትም ይኸው የሀጢአት መዘዝን መሸሽ ነበር፡፡ ስለዚህም “The beasts, the hinds, fishes etc…, I blessed their condition, for they had not a sinful nature!” ይላል፡፡ ይህ ሰው እንግሊዝ ውስጥ የታወቀ ሰባኪም እንደነበር ይታወቃል፡፡… ረድ ሠርዌም የቤተክህነት ሰው ነው፡፡ ግዕዙን አቀላጥፎ የሚናገር፣ ገድላትና ድርሳናትን አላምጦ የዋጠ፣ በቃሉ የሚያነበንብ፡፡
የአለማየሁ ገለጋይ አዲሱ መጽሐፍ፤ መንፈሳዊና ቁሳዊ፣ የሚታዩና የማይታዩ ዐለማት ቀለም የተሞላ፤ የሰውን ልጅ ሕይወት ግራ አጋቢ ትልም የሚከተል፣የሚጠይቅ፣ የሚፈለቅቅ፣ የሚፈትል ሸማውን ሰማይ ላይ ዘርግቶ ዐለምን የሚያጨግግ ዐይነት ነው፡፡ ዘውጉም ባህላዊ ድህረ ዘመናይነት የሚባለውን የቀየጠ፤ በታሪክ  አወቃቀሩን በድርጊት  አከዋወን በገፀ ባህሪያት ወጥነት ዘመናዊነት ዘውግ የታከከውን ዝንቅ ነው:: ስለዚህ ባብዛኛው የታሪክ መዋቅር ባሪያ የሆነው የሀገራችን አንባቢ እንደ “Stream of consciousness” ብዥታ በመፍጠር ዱካ በመሰወር ብዙ አያባትተውም፡፡ ምስቅልቅ እንዳለው የድህረ ዘመናይነት ስነ ጽሑፍ “ይቅርብኝም!” አያሠኘውም፡፡ እያንዳንዱ የታሪክ አፀቅ መምታታት፣ ወደ ፊት ወደ ኋላ ስለማያሰኘው፣ ነገሩን እያጣጣመም ሆነ እየተፈላሰፈ፤እሳት እየጋጠም ጭምር መጽሐፉን ያጠናቅቀዋል ብዬ አምናለሁ፡፡
ከተጨባጭ ወደ ረቂቅ ሀሣቦች የገባው ደራሲም፣ የሰው ልጆችን ሕይወት ከዘወትራዊ ምልከታና አተያይ ከፍ አድርጐ በጥበብ ማማ ላይ የሠቀለው የአዳም ልጅን ሁለንተናዊ ከፍታና ነፍሱ ላይ የተሠነቀረውን መንቁር ህመምና ጥዝጣዜ ለማስታወስ ይመሥለኛል፡፡ መጽሐፉ ውስጥ “አለማየሁ ገላጋይ ራሱን አጠፋ!” የሚለውን ሟርት በልቤ ብረግመውም፣ ዘውጉ በፈቀደለት መንገድ ሄዶ መናገሩን መውቀስ አይቻለኝም:: ብቻ አይሁንበት እላለሁ፡፡ ይህ ግን የሰው ልጆች በሕይወት መሸነፍን ማምለጫ ሽንቁር መሆኑን ማሣያ በመሆኑ፣ አንባቢያን በዚያው በድህረ ዘመናይነቱ የአፃፃፍ ይትባሀል ውስጥ የሚያዩት ይመሥለኛል፡፡
የዛሬ አሥራ ሦስት ዐመት፣ በስነ ልቦናዊ ውጥረት ውስጥ ችቦ የለኮሰችውን “አጥቢያ” እንካችሁ ያለን ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ፤ ዘንድሮ ደግሞ በፍልስፍናና በእምነት ፍተሻ ፍቅር ቀብጣ፣ ጨርቋን የጣለችውን “ሐሰተኛው በእውነት ስም›› መጽሐፈ ማበርከቱ እሰየው የሚያሰኝ ነው፡፡ ይሁንና የዛሬውን ዳሰሳ ከመደምደሜ በፊት ደራሲውን የምወቅስበት ነገር አለኝ፡፡
በአማርኛ የስም አረባብ ላይ በሚያሣየው ቸልተኝነት ሣልወቅስ እንዳላልፍ የአሁኑ ንባቤ አስገድዶኛል:: ይህንን ነገር በአፍ ባነጋገር “ይሁን ብዬ” የማርያም መንገድ በሰጠሁት ነበር፡፡ ግን እንዲያ አይደለም፤ ሁለቴ አውርተናል:: ዛሬም ደግሞታል፤ ስለዚህ ቸልታውን በአንባቢያን ፊት መናገር ለኔ ግድ ነው፡፡ ምክንያቱም በጋዜጠና ሬድዮና ቴሌቪዥን እንደሚታዩትና እንደሚደመጡት ስህተቶች በደራስያን መጽሐፍት የሚያዩ አንባብያን ስህተትን እንደ ትክክል እንዳያ ኬላ ማበጀት ግድ ይላል፡፡  
ገጽ 80 ላይ መዛግብቶች፣ ገጽ 134 ላይ ቃላቶቹ፣ ገጽ 148 እና 158 ላይ መጽሐፍቶቹ፣ ገጽ 126 እና 279 ፍጡራኖቹ -- የሚሉት የርቢ ርቢ ናቸውና እነዚህ ዐይነት ስህተቶች እንዳይደገሙ ማሳሰብ ግድ ይለኛል፡፡ ሁለት ቦታ ያየኋቸው “እምነ በረድ” የሚሉት ቃላትም “እብነ በረድ” በሚሉት መተካት አለባቸው፡፡ እነዚህ ስህተቶች በአማርኛ ስነ ጽሑፍ ደራሲያን በእጅጉ እየተለመዱ የመጡ ስለሆኑ አደብ ልናበጅላቸው ይገባል::
በተረፈ ለደራሲ አለማየሁ ገላጋይ የተሻለ የጥበብ፣ የስኬትና የምልዐት ዘመን እመኛለሁ፡፡ ደግሞ ምን ይዘህልን ትመጣ ይሆን በሚል የወርቃማ ዘመንህን ትሩፋት እጠብቃለሁ፡፡ ረዥም ዕድሜና ጤና ተመኘሁ!!



Read 2144 times