Tuesday, 25 August 2020 05:02

ወዴት እየሄድን ነው? …

Written by  አበባው ከበደ
Rate this item
(1 Vote)

    አንዲት የሦስት ዓመት ህጻን የእናቷን ቀሚስ ለብሳ፤ ትልቅ ተረከዝ ያለውን የእናቷን መጫሚያ ተጫምታ፤  ቀሚሷን ወደ ላይ ሰብስባ ለመጓዝ ስትታር ከሚያሳይ ምስል ጎን  ̋ወዴት እንደምሄድ አላውቅም፤  ሆኖም ግን ጉዞ ጀምሬያለሁ፡፡ ” (I don’t know where I’m going, but ‘am on the way) የሚል መልዕክት አዘል ጽሁፍ በሸራ ላይ ተወጥሮ አስተዋልኩ፡፡ ከጠቢቡ እጅ፣ ቀለምና ብሩሽ ጀርባ አገሬን ዐየኋት፤ እማማን!፡፡ ይህ መጠንን መሰረት ያላደረገ ቀሚስና ጫማ፤ በዚህ ከፍና ዝቅ፣ ወጣና ገባ ባለ የብስ ላይ፤ በዚህ ወዲያና ወዲህ ጎታች በበዛባት ምድር፤ በዚህ … ምን ያህል ያስጉዛት ይሆን? አገሬን፡፡ መርከቧ ኢትዮጵያ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በዕድሜ፣ በጾታ ሳትለይ:- ምሁሩን፣ ማይሙን፣ እኩዩን፣ መልካሙን፣ ቸሩን-ንፉጉን … ሁሉንም በአንድ አሳፍራለች፡፡ ወጀቡ ከወዲህ ወዲያ ይንጣታል፡፡ ከተሳፋሪው አንዳንዱ፡-  ሞፈር ለመቁረጥ ወደ ተራራ በወጡት፤ ሦስት ሞኞች ይመሰላል፡፡ ከተራራ አናት ላይ የወጡት ሦስት ሞኞች ለሞፈር የሚሆን ተስማሚ እንጨት ሲፈልጉ ቆይተው አገኙና የዛፉን ውድቀት ለማፋጠን፤ ሁለቱ ከላይ ሆነው ሊያወዛውዙ አንደኛው ከመሬት ሆኖ ሊቆርጥ ስምምነት ላይ ደረሱ፡፡ በመጨረሻም እንጨቱ ተቆረጠ፤ ሆኖም ሁለቱ የላዕላይ አወዛዋዦች ከእንጨቱ ጋር ወደ ገደል ወረዱ፡፡ ይህን የተመለከተው ሦስተኛው ሞኝ "ሞፈሩን ይዘው ጠፉ" ብሎ ተከተላቸው፤  የት እንደሚሄድ አያውቅምና:: ሌሎቹ  ”… ለአንተ ከማደርግልህ በእጥፍ ለጓደኛህ አደርግለታለሁ” የተባለውን ይመሰላሉ፤ ወዳጁ ሲጠቀም ከማየት የራሱን ጉዳት የመረጠውን ዓይነት፡፡ የተቀሩቱ "የሰራችሁት ኃጢያት ተሰርዮላችኋል" ሲባሉ "ወደፊት የምንሰራውን ጭምር ካልሆነ" የሚሉቱ፤ ሳትዋጋ ንገስ ቢሉት ወግ አይደለም ብሎ ሲዋጋ እንደሞተው ዓይነቶችም ተካተዋል …. ሌሎችም ሌሎችም፡፡
የመርከቧን ጎዞ ለመግታት በየቦታው ሽንቁር እያበጁ ውሃ ወደ ውስጥ የሚያስገቡት ተሳፋሪዎች፤ ያ ሽንቁር ሲበጅ ደግሞ ሌላው ጋ፣ ሌላ ቦታ…. እየሸነቆሩ የመርከቧን ጉዞ ቢገቱም ሊያሰምጧት ግን አልተቻላቸውም፤ የቃልኪዳን አገር ናትና!  ክፉ በህሪያችን ተሞርዶ መልካምነትን ካላላበሰን፤ ስግብግብነትን በመተሳሰብ ካልተካን፣ አስተውለን መራመድ ካቃተንና በደመነፍስ መመራትን ካላቆምን፤  እንዴት ምልዓተ-ፈውስን እናስባለን? …. ሌላው ቀርቶ ሃያ  ሰባት ዓመታት በክፋት ያበጁን እጆች ትላንታችንን አጠልሽተው ነጋችንንም ሊያቆሽሹ  ባይታገሉን እንኳን፤  ዛሬ ላይ እየሆነው ባለነው ሁኔታ  ምን ያህል ርቀት ሳንወድቅ እንጓዛለን?
 ለፍትህ፣ ለዴሞክራሲና ለእኩልነት እጅ ለእጅ ተያይዘን በአንድ ተሰልፍናል:: በትግሉ ያደረግነው አስተዋጽኦ ሊለያይ ይችላል፤ ክቡር ህይወታቸውን ያጡቱ፣ የአካል ጉዳተኛ  የሆኑቱ፣ የመንፈስ ስብራት የደረሰባቸው፣ በእስር የተንገላቱቱ፣ የተኮላሹቱ … ወዘተ--::  ራሳችንን የቀደሙቱ አሳንሰው በሰፈሩን መልክ አንሰን ካየነው፤ ዜግነትን በብሔር  ከተካን … በዚህም ሳቢያ አምርሬ የታገልኩት እኔ ነኝና የእኔ ድርሻ ይህ መሆን አለበት፤  አንተ ደግሞ ያ ይበቃሃል … ዓይነት እሳቤን ካቀነቀንን ያኔ ተሸንፈናል፡፡ ከበደ ሚካኤል በታሪክና ምሳሌ መጽሐፋቸው፤ "ሁለት አፍ ያለው ወፍ" በሚል በግጥም ያቀረቡትን ፅሁፍ እኔ በስድ ንባብ እዚህ ላይ ጠቆም አድርጌ ማለፍ ወደድኩ፡፡ የወፉ አንደኛው አፍ በግለኝነትና በእኔነት እሳቤ የታመመ ሲሆን፣ ያገኘውን ሁሉ ቀደም ቀደም እያለ ይውጣል፤ ሌላኛው አፍ ግን ከዛሬ ነገ ይለወጥ ይሆናል እያለ በትእግስት ጠበቀ፣ የተቃውሞ ድምፅም ለማሰማት ሞከረ፣ አዲስ ነገር የለም፡፡ የዚህ አፍ ትዕግስት አልቆ ነበርና፣ እንደ አጋጣሚ አንድ መርዘኛ ፍሬ ያለው ዛፍ ላይ ሲያርፉ፡- ቻዩ የወፉ አፍም ፍሬውን ለቀም አደረገ፡፡ በተራው፤ ራስ ወዳዱና ግለኛው አፍም  “እባክህን ወንድሜ እንዳትውጠው፣ ሁለታችንም እንሞታለን::” እያለ ሲማፀነው ትዕግስተኛው የወፉ አፍም “ወንድምነትህ የታወቀህ ዛሬ ነውን? … ረፍዶብሃል:- እስከ ዛሬ በረሃብ ስሰቃይ በጭካኔ ተመልክተኸኛል፤ ዛሬ ደግሞ ተራው የእኔ ነው፡፡” ብሎ ፍሬውን ዋጠውና ወፉ ሞተ::   ወገኔ አስተውል! ጥቂት የማንባል የዚች ምድር ፍሬዎች፡-  የሁለት ወይንም ከሁለት በላይ ብሔሮች ቅይጥ ማንነት አለን፡፡  እኔ በሩቁ  የማውቃቸው ጀግናው ሌ/ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ እንደተናገሩት የሚጠቀሰው የነጩን ጤፍና የቀዩን ጤፍ ውሁድ የመለየት ስራን እንዴት በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ለመስራት እንታትራለን?! በዚህስ ከተጋን ራሳችንና ልጆቻችንን የምንመግብበት ጊዜስ ከወዴት ይመጣል? …  እናስተውል!! ለምን ይመስልናል ፕሬዚዳንት ትራምፕ  “ከቆሻሻ አገራት የሚመጡትን እነዛን ጥቁሮች ለምን እንቀበላቸዋለን…” የሚል መልዕክት ያዘለ ከአንድ መሪ የማይጠበቅ የወረደ ዘለፋ የሰነዘሩብን፤ ምናልባትም ሌሎቹ ምዕራባውያን ደፍረው አይናገሩት እንጂ ከዚህ በተለየ ዐይን ዐያዩንም ይሆናል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ መገለጫችን እርስ በርስ መናከስ በመሆኑ ነው፡፡  
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ይህንን ምሳሌያዊ አነጋገር ለትላንት ባለ ትላንቶች እንዲህ ሲል አስተላልፎ ነበር፤ ዛሬ ደግሞ እኔ ለዛሬ ወር-ተረኞች እነሆ፡-  ̋ … የኢትዮጵያ ሕዝብ ሽሮ ወጥን መስራትን ያውቅበታል፡፡ ሽሮ ወጥን ለመስራት መጀመሪያ ሽንኩርት ይቁላላል፣ ቀጥሎ ዘይት፣ አስከትሎ በርበሬ፣ እናም ውሃ፣ ውሃው ሲፈላ ደግሞ ሽሮ…   ሽንኩርት እኔ ቀድሜ ገብቼ ያን ሁሉ እሳት ተቀብዬ እንደነ ሽሮ ዓይነቱ በመጨረሻ የተሳተፉበት ነውና ሽሮ ወጥ መባል ሳይሆን ሽንኩርት ተብሎ ነው መጠራት ያለበት ቢል … ሽሮም በመጨረሻ በመግባቱ ሳቢያ ሚናው ቢንኳሰስ … ሌሎቹም በየቅል በየቅላቸው ቢሆኑ፤ ያው የተናጠል ስያሜያቸውን ይዘው ይቀጥላሉ እንጂ ወጥ ሆነው ጣፍጠው ሊበሉ አይችሉም፡፡”
 እኛ እንደ እንድ ትልቅ አገር በክብር ማማ ላይ ልንቆም ከሆነ፤ እንደ ጠብታ ውሃ ተጠራቅመን ኩሬ ልንሆን ይገባል፤ አልፈንም ውቅያኖስ፡፡ "ትልቅ ነበርን ትልቅም እንሆናለን!!; የሚለውን በእውን ለማየት የምንሻ ከሆነ  እንደ ትልቅነታችን ልናስብ ይገባል፡፡ የግዙፍ ቁመና ሚጢጢ ሃሳብ እንዳይሆንብን፡፡
አንሰን እንየው ብንል፤ በመከራ እንመከር ብንል፤ ሩቅ ሳንሄድ ጎረቤት ሶማሊያ፣ የመን፣ ሊቢያ፣ ሶሪያ … ዛሬም ያሉ ምሳሌዎች ይሆኑናል፡፡ ሩዋንዳንም ያልሻረ የትላንት ጠባሳዋ  ሁቱ፣ ቱትሲ ብሎ የዘር መጠሪያን መጠቀም በአዋጅ የሚያስቀጣ  ድንጋጌን እንድታወጣ አስገድዷታል፡፡ ምርጫው የእኛ ነው፤ ሲዖል ወይስ ገነት??
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው የአለም ቼስ ፌዴሬሽን  ኢንስትራክተር ናቸው፡፡

Read 452 times