Tuesday, 25 August 2020 04:53

ዳሩን መሃል ማድረግ የሚጠይቀው የጦቢያ ፖለቲካ

Written by  ደስታ መብራቱ
Rate this item
(2 votes)

 ከአንድ ዓመት በፊት፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ሊኖራቸው ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ የፖለቲካ ቡድኖችና የህብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉበት ዓውደ ርእይ ላይ በአስተባባሪነት የመሳተፍ እድል አጋጥሞኝ ነበር። በዚህ ወቅት ከተካሄዱ የቡድን ውይይቶች በአንደኛው፣ አንድ ተሳታፊ ‘የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋነኛው ችግር በአማራው፣ በኦሮሞውና በትግራይ የፖለቲካ ልሂቃን (elits) መካከል ያለው የበላይነት ፉክክር ነው’ የሚል አስተያየት ይሰጣሉ። ይህን በማስከተል፣ በምስራቃዊው የሃገራችን ክፍል የሚገኝ አንድ የፖለቲካ ድርጅትን ወክለው የመጡ ሌላ ተሳታፊ ‘ችግሩ ይህ መሆኑን ከተረዳችሁ ለምን ለተወሰኑ ዓመታት ሥልጣኑን ለእኛ ለቃችሁልን ሃገር እንዴት እንደሚመራ አናሳያችሁም’ የሚል ምላሽ ይሰጣሉ። በወቅቱ፣ እነኝህ አስተያየቶች ብዙም ትኩረት ሳይሰጣቸው እና ቀጣይ ውይይት ሳይካሄድባቸው ታልፈዋል። በዚህ ፀሃፊ እምነት፣ እነኚህ አስተያየቶች በሃገራችን ፖለቲካ ውስጥ ካሉት እና ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገቡ ዋነኛ ችግሮች አንዱ የሆነውን የመሃልና ዳር (centre-periphery) ፖለቲካን የሚያመላከቱ ናቸው። በዚህ ጽሁፍ ከላይ የተጠቀሱት አባባሎች ያላቸውን መልእክት ከምህዳራዊ አስተሳሰብ አኳያ በመተንተን፣ ዳሩን ማዕከል የሚያደርግ ፖለቲካ ለኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ የሚኖረውን በጎ አስተዋጽኦ ለማመላከት ይሞከራል።   
ወደ ወቅቱ የሃገራችን ፖለቲካ ከመግባታችን በፊት ግን ይህ የዳርና መሃል ፖለቲካ ከዚህ ቀደም በነበሩ የፖለቲካ ሥርዓቶች እንዴት ይታይ እንደነበር በአጭሩ እንመለከታለን። ከዘመነ መሳፍንት በኋላ የነበረውን የሃገር ምስረታ ታሪክ ስንመለከት፣ የሌሎች ማህበረሰቦች አስተዋጽኦ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከአማራ፣ ከትግራይና ከኦሮሞው የወጡ ነገስታቶችና የጦር አበጋዞች የመሪነቱን ድርሻ ይወስዳሉ።  ወደ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመን ስንመጣ፣ የንጉሳዊው አገዛዝ መንግስታዊ መዋቅር በአብዛኛው ከላይ በተጠቀሱት የአማራ፣ ኦሮሞና ትግራይ መኳንንቶችና ልሂቃን የተሞላ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያረጋግጣሉ። ከዚህ በተጨማሪም፣ ከሰሜናዊውና ከመሃከላዊው የሃገራችን ክፍል ውጪ ያለው አብዛኛው የሃገራችን ክፍል ዳር ሃገር በሚል አጠራር ውስጥ የሚጠቃለል ነበር። በነዚህ የሃገሪቱ ክፍሎች የሚመደቡ ገዢዎችም፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የነበሩትን ባላባታዊ አስተዳደሮች ከማቆየት ውጭ፣ በአብዛኛው ከነኚሁ ሶስት ብሄረሰቦች በተለይም ከአማራው ወገን እንደነበሩ ይታወቃል። ከዚህም አልፎ፣ ንጉሱ ስልጣናቸውን በመቀናቀን ወይም ለመጋፋት በመሞከር የሚጠረጥሯቸውን መኳንንትና ልሂቃን በሹመት ስም ወደ እነኚህ የሃገሪቱ ክፍሎች ይመድቡ እንደነበር የሚነገሩ ትርክቶችም ነበሩ። ከልሂቃኖቹ ሹመቶች መካከል የ1953 መፈንቅለ መንግስት ጠንሳሽ እንደሆነ የሚነገርለት የአቶ ግርማሜ ንዋይ የወላይታና የጅግጅጋ ሹመት ይጠቀሳል። ስለሆነም፣ በዚህ ዘመን ወደ ዳር ሃገር መሾም ማለት ንጉሣዊ ግዞተኝነት ነው ተብሎ ይገመት ነበር።
የ1966 ህዝባዊ ንቅናቄን ተከትሎ የነበረውን ፖለቲካ በሁለት ዘርፍ መመልከት ይቻላል። አንደኛው ገጽታ፣ ሃገሪቱን የመምራት ስልጣንን ጠቅልሎ የወሰደው ወታደራዊው ደርግ የነበረው ያስተዳደርና አመራር ብሄረሰባዊ ተዋጽኦ ሲሆን፤ ሌላው በወቅቱ የሃገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ቀዳሚ የነበሩት የፖለቲካ ድርጅቶች የነበራቸው የአመራር ስብጥር ነው። የወታደራዊውን ደርግ ስብጥር ስንመለከት፣ ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ ከነኚሁ ሶስት ዋነኛ ብሄረሰቦች የተውጣጡ መሆናቸው ግልጽ ነው። ይህ ሁኔታ በወቅቱ የነበረው የሃገሪቱ የመከላከያ ሰራዊት ስብጥር በአብዛኛው ከነኚሁ ብሄረሰቦች የተገኘ ከመሆኑ አኳያ ሲታይ ብዙም የሚያስገርም አይሆንም።  በጊዜው የነበሩትን የፖለቲካ ድርጅቶችንም ስንመለከት፣ የሌሎች አናሳ ብሄረሰቦችን ትግል ለማስተባበር በሚል ከተመሰረተው የኢትዮጵያ ጭቁኖች አብዮታዊ ትግል (ኢጭአት) ከሚባለው ድርጅት በስተቀር ያብዛኛዎቹ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች አመራሮች ከነዚሁ ሶስት ብሄረሰቦች የወጡ መሆናቸው ይታወቃል። ከዚህም አልፎ አንዳንዶቹ ላንዱ ወይም ለሌላው ወገን በማድላት ሲታሙም ነበር።ለምሳሌ፣ የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) የሚባለው ድርጅት ለኦሮሞው በማድላት ሲታማ፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) አመራርም በአማራና በትግራይ ልጆች ተጽእኖ ስር ነው ይባል ነበር። ምንም እንኳን፣ የመኢሶንም ሆነ የኢህአፓ መሪዎች ላንዱ ወይንም ለሌላው ብሔረሰብ በተናጠል ለማድላታቸው ማረጋገጫ ባይኖርም፣ ከላይ የቀረበው አጭር ትንታኔ የሚያሳየው በመግቢያው ላይ ለተጠቀሰው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር ከሶስቱ ብሄረሰቦች ልሂቃን ጋር መያያዝ በቂ መነሻ እንዳለው ነው።
ይህ የዳርመሀል ሃገር ፖለቲካ በዘመነ ኢህአዴግ ለየት ያለ መልክ ይዞ ቀጥሏል። በአንድ በኩል፣ ሁሉም ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበትና የራሳቸውን እድል በራሳቸው የሚወስኑበት ህገ መንግስታዊ ሥርዓት በመመስረት ህዝቦች በእኩልነት የሚሳተፉበት ሥርዓተ መንግስት እንደተተገበረ ሲነገር ቆይቷል። በሌላ በኩል ግን፣ በፌደራል ደረጃ ወሳኝ የሆነውን የፓርቲም ሆነ መንግስታዊ ስልጣን በሚመለከት በቀድሞው አጠራር ዳር ሃገር፣ በኢህአዴግ አጠራር ታዳጊ ክልሎች የሚባሉትን የአፋር፣ የሱማሌ፣ የጋምቤላና የቤኒሻንጉል ህዝቦችን በአግባቡ ያላካተተ እንደነበር ይነገራል። ከዚህ አለፍ በማለትም፣ በእነኚህ ክልሎች የነበረው ውስጣዊ አስተዳደርም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከማእከል በሚመደቡ ሞግዚቶች ይወሰን እንደነበር የሚያመላክቱ መረጃዎች አሉ። በጥቅሉ፣ በኢህአዴግ ዘመን የነበረው መንግስታዊ አስተዳደርም በሶስቱ ብሄረሰቦች ዋነኛ የፖለቲካ ተዋናይነት ከቀድሞው የዳር መሃል ሃገር ፖለቲካ የቀጠለ መሆኑ ግልጽ ነው። በመሆኑም፣ ለበርካታ ዓመታት በኢህአዴግ ውስጥ ሰፍኖ የነበረው የትግራይ ህዝቦች ነፃ አውጭ ግንባር (ህወሃት) የበላይነት በዋነኝነት በኦሮሞና በአማራ የፖለቲካ ሃይሎች ጥምረት ሊፈርስ ችሏል። ይህም የሚያመላክተው፣ በቅርቡ በነበረው የፖለቲካ ዘመናችንም ቢሆን ከእነኚህ ሶስት ወገኖች በሚወጡ የፖለቲካ ልሂቃኖች መካከል ያለው መስተጋብር የሃገሪቱን የፖለቲካ አቅጣጫ በመወሰን ረገድ ትልቅ ድርሻ እንደነበረው ነው። አሁን ላይ ያለው መልካም ነገር፣ ከላይ የተጠቀሰው ሁኔታ ከ2010 የመንግስት አመራር ለውጥ ወዲህ እየተሻሻለ መምጣቱን የሚያመላክቱ አንዳንድ በጎ እርምጃዎች መታየት መጀመሩ ነው።  
ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ታሪካዊ ሁኔታዎች የሚያመላክቱት በመግቢያው ላይ የተጠቀሰውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግሮች በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አቢይ ድርሻ ከነበራቸው የሶስቱ ብሄረሰቦች ልሂቃን ጋር ያያዘው አስተያየት በቂ መነሻ መሰረት እንደነበረው ነው።  በመሆኑም፣ በየትኛውም የሃገሪቱ ዘመን ለነበረው የፖለቲካ ቀውስ ከእነኚህ ሶስት ብሔረሰቦች የወጡ የፖለቲካ መሪዎችና ልሂቃን የጋራ ተወቃሽነት አለባቸው ማለት ይቻላል። ከምህዳራዊ አስተሳሰብ አኳያ፣ የነኚህ ሶስት ህዝቦች በሀገሪቱ የፖለቲካ ህይወት ጉልህ ድርሻ መያዝ በራሱ የችግር ምንጭ ሊሆን አይገባውም። ይልቁንም፣ እነኚህ ህዝቦች ለሃገሪቱ የረጂም ዘመን ታሪክ ከነበራቸው ጉልህ አስተዋጽኦና ካላቸው ከፍተኛ ማህበራዊ ንዋይ (social capital) አኳያ በጣም ጠቃሚ የሆነ የአካታችነት (inclusivity) እና የአረጋጊነት (stability) ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ። ይህንን ሆኖ ለመገኘት ግን፣ ከዚህ ቀጥሎ ከተጠቀሱት ህመሞች ራሳቸውን ማንጻት ይጠበቅባቸዋል። የመጀመሪያው፣ የፖለቲካ ልሂቃኖቹ ለዘመናት ተብትቦ ከያዘን በሴራና እርስ በርስ በመጠፋፋት ላይ ከተመረኮዘ ባላባታዊ ፖለቲካ ራሳቸውን ማንጻት ይኖርባቸዋል። በሁለተኛ ደረጃ፣ በሃሳብ ልዕልና ላይ ከተመረኮዘ መንግስታዊ ሥርዓት ይልቅ ባላቸው የህዝብ ቁጥር ትልቅነት ላይ ወደተመረኮዘ ጨቋኝ አገዛዝ (tyranny of numbers) የሚወስድ ዝንባሌን በጥብቅ ሊታገሉ ይገባቸዋል። እንዲህ አይነቱ የፖለቲካ ዝንባሌ፣ በዲሞክራሲ ሽፋን፣ በአንዳንድ የብሄር ፖለቲካ ልሂቃንና መሪዎች አካባቢ እየተቀነቀነ በመሆኑ በቶሎ ሊታረም ይገባዋል።  በሶስተኛ ደረጃ፣ ምንም እንኳን በስፋት ባይነገርላቸውም፣ በጠረፍ አካባቢ የሚኖሩ ህዝቦች ለኢትዮጵያ ዳር ድንበር መከበር የነበራቸውን ቁልፍ ድርሻ በመገንዘብ የዳርመሃል የሚባለውን ፖለቲካዊ ዘይቤ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ማስወገድ ይኖርባቸዋል። ይህ ሊሆን የሚችለው፣ የዳርቻው አካባቢ ማህበረሰቦች ሃገሪቱን ወደ መሃል የሚያሰባስበው ሃይል (centripetal force) አካል ሆነው መሃሉ በብዙ መልኩ ዳሩንም መምሰል ሲጀምር ነው። ያለ ዳሩ መሃል የሚባል ነገር እንደማይኖር መረዳትም ለዚህ ሂደት ይጠቅማል።
ይህ ዳሩን ወደ ማዕከል የማምጣት ፖለቲካ ለዘመናት የነበረውን የመብት መዛባት ከማስተካከልም በላይ ከምህዳራዊ አስተሳሰብ አኳያ ለሃገራችን የፖለቲካ ሽግግርም ልዩ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል። የዚህ ዋነኛው ምክንያት፣ በነኚህ አካባቢዎች የሚኖሩ አብዛኛዎቹ ማህበረሰቦች የሌሎቹን ያህል በሃገራችን ፖለቲካ መሰረታዊ ህመሞች ያልተተበተቡ ከመሆናቸውም በላይ የፖለቲካ ልሂቃኖቻቸውም ከሃገር በቀል እውቀቶችና ሥርዓቶቻቸው ጋር እንደሌሎቹ ጠቅልለው ያልተፋቱ መሆናቸው ነው። ለዚህም ማረጋጋጫ የሚሆኑን፣ ከቦረና እስከ አፋር፣ ከጋሞ እስከ ሶማሊ ያሉ ማህበረሰቦች ያላቸው የተሻለ የማድመጥና የመደማመጥ ባህል፣ ውጤታማ የሆኑ የግጭት አፈታት ዘዴዎቻቸውና ማህበራዊ ርትእን የሚያሰፍኑ የዳኝነት ሥርዓቶቻቸው ናቸው። እነኚህ ማህበራዊ ክህሎቶች በጥርጣሬና በበላይነት ስሜት የተተበተበውን የመሃል ሃገር ፖለቲካ በመጠኑም ቢሆን ለማለዘብና ለማስከን እንደሚያግዙ የሚያመላክቱ ወጣት የፖለቲካ መሪዎችም ከነኚሁ አካባቢ ወጥተው ማየት ጀምረናል። እዚህ ላይ፣ እነኚህ ሃገር በቀል እውቀቶችና ሥርዓቶች በዘመኑ የፖለቲካ ህመም የተነሳ ለመሸርሸር አደጋ እየተጋለጡ መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል። ስለዚህም፣ ጊዜው ሳይረፍድ ከእነኚህ ሃገር በቀል እውቀቶችና ሥርዓቶች ሊወሰዱ የሚችሉ ጠቃሚ ልምዶችን በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ አጥንቶ የፖለቲካ ባህላችንና ሥርዓታችን አካል እንዲሆኑ ማድረግ ለሃገራዊው የፖለቲካ ሽግግር ጤናማነት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይታመናል። በዚህ ረገድ፣ በሃገሪቱ የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና የማህበራዊ ሳይንስ ምሁራን ጉልህ ድርሻ ሊኖራቸው እንደሚችል ይገመታል።   
በአጠቃላይ፣ ከምህዳራዊ አስተሳሰብ መርሆዎች አኳያ፣ በማንኛውም ምህዳር ውስጥ የሚገኙ ክፋዮች ምንም ያህል አናሳ ቢሆኑ፣ እንደ ምሉዕነታቸው ለአጠቃላዩ ምህዳር ጤናማነትና ዘላቂነት የራሳቸው የሆነ ድርሻ አላቸው። በተመሳሳይም፣ በሃገራችን ውስጥ ያሉ ማህበረሰቦች፣ ምንም ያህል አናሳ ቢሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚኖረው የፖለቲካ ምህዳር ጤናማነትና ዘላቂነት የራሳቸው የሆነ ድርሻ እንደሚኖራቸው መገንዘብ ይገባል። ባለፉት ሁለት የሽግግር ዓመታት ውስጥ፣ በብዙዎቹ የድንበር ክልሎች የታየው አንጻራዊ መረጋጋትና ሰላም ለዚህ አንድ ማረጋገጫ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ፣ የአንድ የፖለቲካ ሥርዓት ዲሞክራሲያዊነት ከሚመዘንበት ዋነኛ የመልካም አስተዳደር መስፈርቶች አንዱ ለአናሳ የማህበረሰብ ክፍሎች በሚሰጠው የመብት ጥበቃ መሆኑን የፖለቲካ መሪዎቻችን ተረድተው ዳሩን ማዕከል ለሚያደርግ ፖለቲካ መትጋት ይኖርባቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ በእነኚህ የድንበር ክልሎች የሚገኙ ወጣት የፖለቲካ መሪዎች፣ እየተካሄደ ላለው ሽግግር ጠቃሚ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉበት ታሪካዊ ወቅት ላይ መሆናቸውን ተረድተው፣ ለሃገራዊው አንድነት ምስረታ የድርሻቸውን አጠናክረው ማበርከት ይጠብቅባቸዋል።  
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው  ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ስታለንቦሽ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፈሰር ሲሆኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትም ያስተምራሉ።Read 6495 times