Saturday, 21 July 2012 10:34

ሕዝብ የጠ/ሚኒስትሩን የጤንነት ሁኔታ የማወቅ መብት አለው!

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(1 Vote)

ለተፈጠረው ወሬና አሉባልታ ተጠያቂው ማነው?

ድንገት ከአይን እይታ የመጥፋትን (absentism) ነገር በተመለከተ የተለያዩ ሀገራት ህዝቦች እንደየሀገሮቻቸው ሁኔታና አመለካከታቸው የሚገልፁበት የተለያዩ አባባሎች አላቸው፡፡ አይሁዶች ድንገት ከአይን እይታ መራቅ ወይም መጥፋት የግራ መጋባት እናት ናት ይላሉ፡፡ ይህ አባባላቸው እንከን የማይወጣለት ገላጭ አባባል ነው፡፡ ማንም ቢሆን ሁሌም የሚያየውንና ስለ እሱም የሚነገረውን ዘወትር የሚያዳምጠው ሰው ድንገት ምስሉ ከአይኑ፣ ወሬውም ከጆሮው ሲርቅና ሲጠፋ “ይህ ሠው የት ገባ? የት ደረሠ? ምን ሆኖ ይሆን?” ወዘተ… እያሉ መጨነቅና በድንገተኛው ሁኔታ ግራ መጋባቱ የማይቀር ነው፡፡

ሌላ ነገርም አለ፡፡ ከተለመደው የአይን እይታ ድንገት የራቁ ሠዎች የአራራቃቸው ሁኔታ ግራ የማጋባቱን ያህል ስማቸው፤ ስራቸውና ጠቅላላ እንቅስቃሴአቸው ሁሉ በግራ ጐን እየዋለ ለተለያዩ ጥርጣሬዎች፣ ሀሜቶችና ትክክለኛነታቸው ጨርሶ ላልተረጋገጠ፤ በቀላሉም ሊረጋገጥ ለማይችሉ የተለያዩ አሉባልታዎች ተጋልጠው መክረማቸው መቸም ቢሆን አይቀሬ መሆኑን እድሜ ዘመናችንን ሁሉ ስንታዘበው የኖርነው ነገር ነው፡፡

ይህ እውነታ ዘር፣ ቀለም፣ ባህልና እምነት ሳይለይ አዳሜ ሁሉ የሚገጥመውና የሚከፍለው እዳው ነው፡፡ የእዳውና የክፍያው መጠን ግን ከእንጨት መርጠው ለታቦት እንደሚያደርጉት ሁሉ፣ ከሠውም ሠው አለና እንደየሰው ማንነት ይለያያል፡፡ የተለያየ የልዩ ተሰጥኦ፣ ችሎታና ሙያ ባለቤትነታቸው፣ ከሌላው ሰው ሁሉ የላቀ ስራቸውና ገድላቸው፣ የናጠጠ ባለፀግነታቸው ወዘተ ….የህዝብ አይን የዘወትር ማረፊያና የመነጋገሪያ ርዕስ እንዲሆኑ ያደረጋቸው Public figures የሚባሉት አይነት ሠዎች ድንገት ከህዝብ እይታ ሲርቁ የሚከፍሉት እዳ ከፍ ያለ ነው፡፡

በተለይ ደግሞ የሀገርና የህዝብ መሪነትን ከባድ የሀላፊነት ቀንበር የተሸከሙ መሪዎች ድንገት ከለመዳቸው ህዝብ አይን እይታ ሲርቁ የት ደረሱ? የት ገቡ? ከሚለው ግራ መጋባት በተጨማሪ ስማቸውና እንቅስቃሴአቸው ሁሉ በሁሉም መስክ በግራ እየዋለ እንዲከፍሉት የሚገደዱት የሀሜት፣ የጥርጣሬና የአሉባልታ እዳ መጠኑ ከሁሉም በእጅጉ የላቀ ነው፡፡

ካለፉት ጥቂት ሳምንታት ወዲህ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የተለመደ ምስልና እንቅስቃሴአቸው ከህዝቡ አይን እይታ፤ ዜና መዋዕላቸውም ከህዝቡ ጆሮ ድንገት ርቋል፡፡ ጠፍቷል፡፡ በምትኩ የነገሠው የት ሄዱ? የት ገቡ? ምን ሆኑ? ወዘተ የሚል ግራ መጋባት፣ ጥርጣሬና ማንም ትክክለኛነታቸውን ማረጋገጥ የማይችላቸው የተለያዩ አሉባልታዎች ናቸው፡፡ ድንገት ከአይን እይታ መጥፋት ወይም መራቅ የጥርጣሬዎች ሁሉ እናት ናት የተባለው እርግጥም ያለነገር አይደለም፡፡

ድንገት ከአይን እይታ የራቀ ወይም የጠፋ መሪ ወይም Pubic figure የሆነ ሠው፤ ስሙ ስራውና ጠቅላላ እንቅስቃሴው ሁሉ በሁሉም መስክ በግራ ጐን ይውላል የተባለውም እርግጥ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን በተመለከተ ሰሞኑን የተፈጠረው ነገር በሚገባ አረጋግጧል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን ድንገት ከህዝብ አይን መራቅ በተመለከተ እስካሁን የተወራባቸውና አሁንም ድረስ እየተወራባቸው ያለው አሉባልታና ጥርጣሬ በጠቅላላ ለሞት መድሀኒት የሚሆን አንዲትም እንኳ በጐ ነገር የለበትም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስን በተመለከተ ድፍን ከተማው በግራ መጋባት እየታመሠበት ያለው ጥርጣሬና አሉባልታ እጅግ ብዙና የተለያየ ርዕስና መረጃ የያዘ ነው፡፡ በጠና በመታመማቸው የተነሳ ሁነኛ ሀኪምና ህክምና ፍለጋ ከቤልጅየም እስከ እስራኤል፣ ከእስራኤል እስከ ቻይና ድረስ ባለቤታቸውን አስከትለው መሄዳቸው፣ የተጠናወታቸው ክፉ ደዌ ከሠውነት ተራ እንዳስወጣቸው፣ የየትኛው ሀገር መሆናቸው ያልተጠቀሰ ዶክተሮች ቀሪ ጊዜአቸው አጭር (አንዳንዶች በጥቂት ወራቶች ብቻ የሚቆጠር ያደርጉታል) እንደሆነ፣ ከአሁን በሁዋላ እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ያለ ሀገርና እንደ ኢትዮጵያውያን ያሉ ህዝቦችን እንዲሁም እንደ ኢህአዴግ ያለ የፖለቲካ ድርጅት መምራት ይቅርና ካልጋ መነሳት እንኳ  እንደማይችሉ፣ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴን በመኖሪያ ቤታቸው ሰብስበው ከኢህአዴግ ሊቀመንበርነታቸውም ሆነ ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣናቸው መልቀቃቸው ወዘተ… ወዘተ… በሰፊው ተወርቷል፡፡

ሌሎች ጨከን ያሉት ደግሞ ፌስቡክና ሌሎች የማህበራዊ ግንኙነት የኢንተርኔት ድረገጾችን በመጠቀም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውጭ ሀገር ህክምናቸውን በመከታተል ላይ ሳሉ በተወለዱ በ57 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት መለየታቸውን… ራሳቸው ፈጥረው  አሉባልታ አሰራጭተዋል፡፡

እንግዲህ ባነሳነው ጉዳይ ላይ ወግ ያለውና ፈር የያዘ ውይይት ማድረግ እንችል ዘንድ ይህን ሁሉ የአገር ጥርጣሬና አሉባልታ “የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጤና የማጣት ወሬ” በሚል አንድ ዶሴና አንድ ርዕስ ስር ማጠቃለል ይቻላል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መታመም ጉዳይ ጥርጣሬውና አሉባልታው እንዲህ እንደአሁኑ ከመጦዙ በፊት፣ የጉዳዩን እውነትነት አሊያም መሠረተቢስ ወሬነት ለማረጋገጥ ይመስላል ከጥቂት ሳምንታት በፊት የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዲኤታ ለሆኑት ባለስልጣን ጥያቄ ቀርቦላቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በሙሉ ጤንነት መደበኛ ስራቸውን እያከናወኑ እንደሚገኙ እንደሚያውቁ ሳይሆን እንደሚገምቱ በመግለጽ መልስ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በጠና መታመም ጉዳይ በይፋ ከተወራበትና እኒህ ባለስልጣን ግምታዊ መልሳቸውን ከሠጡበት ጊዜ ወዲህ በነበሩት ሁለትና ሶስት ሳምንታት ውስጥ ህዝቡ ራሱ አይቶና ሰምቶ እንዳይወስንና ትክክለኛውን አቋም እንዳይወስድ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ምስላቸውም ሆነ ዜና መዋዕላቸው ከህዝቡ አይንና ጆሮ ድንገት እንደራቀ ቀረ፡፡ ጥርጣሬውና ከላይ የተገለፀው አይነት  መአት አሉባልታም ፈነዳና ተጋግሎ መወራቱን ቀጠለ፡፡

የሚገርመው ደግሞ ወሬውና አሉባልታው በከፍተኛ ፍጥነትና ብዛት የመላ ሀገሩን አየር ሲሞላውና የህዝበ አዳሙን ጆሮ ሲያጥለቀልቀው፣ ትክክለኛውን መረጃ በመስጠት ለህዝቡ ወቅታዊ መረጃ ለማቅረብ “እኔ አለሁ” የሚል ጉዳዩ የሚመለከተው የኢህአዴግም ሆነ የመንግስት ባለስልጣን ወይም የስራ ሀላፊ ያለመገኘቱ ነው፡፡

እንዴ! እንዴት ነው ነገሩ? የሀገሪቱና የህዝቦቿ መሪ የሆኑት የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጉዳይ የህዝብና የሀገር ጉዳይ መሆኑ ቀርቶ ነው ወይስ ህዝቡ ስለእሳቸው ጉዳይ አያገባውም ተብሎ ነው? ወይንስ ደግሞ የአጤ ምኒልክ ነገር ከዘመናት በሁዋላ እንደገና ተመልሶ አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ገባ? እነዚህ ጉዳዮች አስቸኳይና ወቅታዊ ምላሽ ያስፈልጋቸዋል፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ወይም ጉዳይ የሚመለከተው ሌላ የኢህአዴግም ሆነ የመንግስት አካል፤ ህዝብ ማንኛውንም ተገቢ መረጃ በትክክልና በወቅቱ የማግኘት መብት እንዳለው መቼም ቢሆን ይዘነጉታል ብሎ ማሰብ ያስቸግራል፡፡ የሀገሪቱና የህዝቦቿ መሪ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ድንገት ከህዝብ አይንና ጆሮ የራቁበትን ምክንያትና የጤንነታቸውን ጉዳይ የጉዳዩ ባለቤት ለሆነው ህዝብ በወቅቱና በትክክል አለማቅረባቸው አንድም ሀላፊነትንና ስራን በቅጡ መስራትና መወጣት አለመቻል አሊያም ለህዝብና ለመብቱ ተገቢውን ክብር አለመስጠት ነው፡፡ እነዚህ መስሪያ ቤቶች፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን ጉዳይ በሬዲዮ በቴሌቪዥንና በጋዜጦች እስኪሰለቸን ድረስ እንደሚዘገብልንና እንደሚወራልን የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ቆጥረውት ከሆነ በእውነቱ በእጅጉ ያስተዛዝባል፡፡

ህዝብ እንኳንስ ስለመሪው ጉዳይ ይቅርና ስለሌላም ጉዳይ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ የማግኘት መብት እያለው ሲነፈግ ሊፈጠር የሚችለው ቀጣይ ነገር ምን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት የምጡቅ አዕምሮ ባለቤት ወይም ደግሞ እውቀትና ማስተዋል ሞልቶ የፈሰሰበት ሊቅ መሆንን ጨርሶ አይጠይቅም፡፡ የደቡብ አፍሪካ ዙሉዎች ድፍን አገሩንና ህዝቡን ያጥለቀለቀውን ጥርጣሬና አሉባልታ ትክክል ነው ብሎ ማረጋገጫ አሊያም ሀሰት ነው ብሎ ማስተባበያ የሚሰጠው ሁነኛ ሰው በሀገሩ መድረክ ላይ ሲያጡ ሁኔታውን የሚገልፁበት አንድ አባባል አላቸው፡፡ “ለገበያ ከቀረበው ላይ ይሸመታል” ይላሉ፡፡

እድሜ ለመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤትና ለሌሎች ለሚመለከታቸው የፓርቲም ሆነ የመንግስት አካላት ይሁን እንጂ እኛም ሀገር በትክክል የሆነው ይሄው ነው፡፡

ህዝቡ ስለመሪው ወቅታዊ ጉዳይ ትክክለኛውን ነገር የሚነግረውና የሚያስረዳው ሁነኛ ሰው ከሀገሩ የፖለቲካ መድረክ በማጣቱ ገበያውን ያጥለቀለቀውን ጥርጣሬና አሉባልታ እርግጠኛ ነገር ቢሆን ነው እያለ ሲሸምት ቆይቷል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን የወቅቱ ትክክለኛ ሁኔታ የሚገልጥለት ያጣው ህዝብ አምኖ ለመቀበል ወይንም ግራ ለመጋባት የተገደደበት የአርሴናልን አሰልጣኝ አርሰን ቬንገርንና ደጋፊዎችን ብቻ እያስጨነቃቸው እንዳለው የኮከቡ ተጨዋቻቸው የሮበን ቫን ፐርሲ ክለቡን የመልቀቅና የአለመልቀቅ አይነት ዜና ከቶውንም አይደለም፡፡ ይህ ዜና እንደመናኛ ነገር ተደርጐ የሚቆጠርና ችላ ተብሎ በቀላሉ የሚታለፍ ሳይሆን በሀገሪቱና በጠቅላላ ህዝቧ ወቅታዊና የወደፊት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ስነልቦናዊ እጣ ፋንታ ላይ ቀላል የማይባል ተጽእኖ የሚፈጥር ነው፡፡

ይህን ደግሞ እስካለፈው ረቡዕ ድረስ በህብረተሰቡ ዘንድ ሲንፀባረቅ የቆየውን ስሜት በመረዳት በቀላሉ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ባለፈው ረቡዕ ግን ጭርሱኑ ከቀረ የዘገየ ይሻላል በሚል አይነት ይመስላል፤ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለአስርት አመታት የተጣለባቸውንና የተሸከሙትን ከባድ ሃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት የአንዲት ቀን እረፍት እንኳ ሳያገኙ ሲባትሉ መኖራቸው ያስከተለባቸውን የጤና እክል ለመቋቋም ተገቢውን ህክምናቸውን ህክምናው በሚገኝበት ቦታ ሲከታተሉ መቆየታቸውንና በአሁኑ ወቅትም የጤንነታቸው ሁኔታ በእጅጉ ስለተሻሻለ ለሀኪሞቻቸው የሰጧቸውን እረፍት ሲጨርሱ በአጭር ጊዜ ውስጥ መደበኛ ስራቸውን ማከናወን እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል፡፡

በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን ጤንነትና የእክላቸውን ምንነት በተመለከተ የተለያዩ ዝርዝር ጉዳዮችን የሚመለከቱ ጥያቄዎች ለሚኒስትሩ  ቢቀርብላቸውም፤ ጠቅለል ያሉና ተመሳሳይ መልሳቸውን ሰጥተዋል፡፡ የኖሆ ሆኖ የሚኒስትሩ መልሶች የፈለገውን ያህል ጠቅለል ያሉና ተመሳሳይ ቢሆኑም ከአራት ሳምንታት አሉባልታና ግራ መጋባት በኋላ ከፈረሱ አፍ የተገኘ መልካም ዜና ነው፡፡ በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ከቀረቡት በርካታ ጥያቄዎች ውስጥ ላለፉት ጥቂት ሳምንታት ያን ያህል ክፉ ክፉ አሉባልታዎች የአገሩን አየር ሞልተውት፣ ህዝቡ ክፉኛ እስኪደናገርና ግራ እስኪገባው ድረስ መንግስት ትክክለኛውን መረጃ ለመስጠት ያልፈለገውና የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ ያለበት ምክንያት ምንድን ነው? ያለውን መረጃ ለህዝቡ ለመስጠት መንግስት ይህን ያህል የዘገየበት ምስጢርስ ከቶ ምንድን ነው? ለሚሉት ጥያቄዎች ሚኒስትሩ በሰጡት መልስ በእርግጥም አስገራሚና በቀላሉ ለመረዳት የሚያስቸግር ነው፡፡

ለእነዚህ ሁለት ጥያቄዎች ሚኒስትሩ በሰጡት መልስ፤ “በኢህአዴግ አመራር ዘንድ በጤናም ሆነ በሌላ ጉዳይ በግለሰብ ደረጃ የሚሆነውን ወይም የተፈጠረን ነገር የህዝብ ግንኙነት ጉዳይ የማድረግ ባህል ስለሌለ ነው፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የጤንነት ሁኔታ እኛው ብቻ ይዘነው መቆየትን የመረጥነው፡፡ በህዝቡ  መካከል የተፈጠረውን አሉባልታና ውዥንብ የፈጠሩት ሰዎች ያላቸውን የተለየ አላማ ለማስፈፀም በማሰብ ነው፡፡” ብለዋል፡፡

ኢህአዴግ ሊቀመንበሩን አቶ መለስ ዜናዊን እንደ አንድ ግለሰብ መሪ ሊቆጥራቸውና የጤናቸውም ሆነ ሌላ ጉዳያቸውን እንደ አንድ የግለሰብ ጉዳይ አድርጐ ሊያየው ይችላል፡፡ ለህዝቡ ግን ይህ የኢህአዴግ አቋምና አመለካከት በቀላሉ የማይገባ ምናልባትም እንደ ስህተት የሚቆጠር አቋምና አመለካከት ነው፡፡ ለምን ቢባል ለህዝቡ አቶ መለስ ዜናዊ ከአንድ ግለሰብ በላይ ናቸው፡፡

ለህዝቡ አቶ መለስ አንድ ግለሰብ ብቻ ሳይሆኑ ካለፉት ሃያ አንድ አመታት ጀምሮ የመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው፡፡ የጤናም ሆነ ማናቸውም አይነት የእሳቸው የሆነ ጉዳይንም ህዝቡ የሚያየው እንደ አንድ ግለሰብ ጉዳይ አድርጐ ሳይሆን እንደራሱ ጉዳይም አድርጐ ነው፡፡ ይህ ተጨማሪ ማብራሪያና መግለጫ የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም፡፡ አንድ መሪ በተመሪዎቹ የእለት ተዕለት ሁለንተናዊ ህይወት ላይ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ በጐም ሆነ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳለው መናገር ምናልባት የአንባቢን የመረዳት ችሎታ አቃሎ እንደመገመት ሊቆጠር ይችላል፡፡ ስለዚህ ሚኒስትሩ የሰጡት መልስ በኢህአዴግ አመራሮች ዘንድ የመሪዎችን የፓርቲና የህዝብ ሚና ለይቶ ያለማየት ከሃያ አንድ የመሪነት አመታት በኋላም እንኳ ያልተፈታ ችግር እንዳለ አመላካች ነው፡፡

በህዝቡ መካከል የተፈጠረውን ውዥንብርና ግራ መጋባት አስመልክቶ የተለየ አላማና አጀንዳ ያላቸው ሰዎች የፈጠሩት ነው በሚል የሰጡት መልስም ከፓርቲያቸው አመለካከትና አሠራር ውጪ ከፍና ሰፋ አድርጐ ህዝባዊውን ሃላፊነት ካለማየትና ይህንንም ህዝባዊ ሃላፊነት በትክክልና በአግባቡ ካለመወጣት የተከሰተውን የራስና የራስ ብቻ (እንደ ፓርቲም እንደ መንግስትም) ስህተት ደብቆ እዳውን ሌሎች እንዲያወራርዱት ለማድረግ የተሞከረ ቀሽም መልስ ነው፡፡ ትክክለኛውንና ተገቢውን መረጃ በወቅቱ ያላገኘ ህዝብ ለአሉባልታና ለጥርጣሬ በመጋለጡ የተነሳ አሉባልታውንና ጥርጣሬውን እውነት ነው ብሎ ቢቀበልና በተቀበለው የአሉባልታና የጥርጣሬ መረጃ ግራ ቢጋባ ምኑ ያስገርማል? ቀድሞውኑ ተገቢውንና ትክክለኛውን መረጃ መንፈግ ለእንዲህ አይነት አላስፈላጊ ውዥንብር እንደሚዳርግ ከተረሳ ሃላፊነትን በወጉ የመረዳት ችግር መኖሩን በግልጽ ያሳያል፡፡

ከጥቂት ወራት በፊት ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ አጋጥሟቸው በነበረው የጤንነት መጓደል የተነሳ የተፈጠረው ውዥንብር፣ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ላይ እንዳይደገም ትምህርት መሆን ይችል ነበር፡፡ መንግስት ግን ከዚህ መማር እንዳልቻለ ወይም ለመማር እንዳልፈለገ በድጋሚ የተፈጠረው ሁኔታ ግልጽ አድርጐታል፡፡ እንዲህ አይነት ተመሳሳይ ችግር ለሶስተኛ ጊዜ እንዲፈጠር ግን ህዝቡ ፍላጐት የለውም፡፡

የህዝብን መረጃ የማግኘት መብት ለማስከበር መመኘትም ሆነ ህግ ማውጣት ብቻውን እንደመጨረሻ ግብ ተደርጐ ሊወሰድ ይችላል፡፡

ይህ ብቻውን ግን ጠብ የሚል ውጤት ማምጣት ግን ጨርሶ አይችልም፡፡ ውጤት ለማግኘትና ከከፍተኛ ውዥንብር ለመዳን በተግባር የሚገለጽ እንቅስቃሴ ማድረግ ብቸኛው አማራጭ ነው፡፡ እናም መንግስትም ሆነ ኢህአዴግ ይህን ቁም ነገር እባካችሁ ልብ በሉት!

እንደ አንድ መሪ የፖለቲካ ድርጅት ከኢህአዴግ አመራሮችም በተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲገለጽ የሚጠበቅ አንድ ቁልፍ ጉዳይ አለ፡፡ ሁሉንም ነገር በኢህአዴግኛ ማሰብና በኢህአዴግ አይን ብቻ ማየት ከፍተኛ ችግር አለው፡፡ ሀገርና ህዝብን ከኢህአዴግ ለይታችሁ ሠፋና ረዘም አድርጋችሁ መመልከትና ማሰብ ጀምሩ፡፡

 

 

Read 2554 times Last modified on Saturday, 21 July 2012 10:40