Monday, 24 August 2020 19:42

የአፄ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱ የልደት በዓል በደብረብርሃን

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

የአፄ ምኒልክ አረንጓዴ ፓርክ”ን ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ
ባለሀገሩ አስጐብኚ ድርጅት ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት፣ የእቴጌ ጣይቱ ብጡልን፣ የአፄ ምኒልክንና የፊታውራሪ ገበየሁ የልደት ክብረ በዓልን እንዲሁም ደብረታቦርን (ቡሄ) በራሱ ተነሳሽነትና ወጪ በጣይቱ ሆቴል ግቢ ውስጥ በድምቀት ሲያከብር፣ ትውልዱ ታሪኩን እና ባህሉን እንዲያውቅ በትጋት ተንቀሳቅሷል፡፡
ዘንድሮ የነገስታቱን ልደትም ሆነ ደብረታቦርን በሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን ከተማ ለምንለማክበር ተፈለገ? ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች መሆኑን የባላገሩ አስጐብኚ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሾመ አየለ (ባላገሩ) ይገልፃሉ፡፡
“ሸዋ ለማክበር የተነሳንበት ሁለት ምክንያት አለ፤ አንደኛው የኮቪድ ወረርሽኝ መስፋፋትና መሰራጨት ነው፡፡ ሁለተኛው የሸገርን እናስውብ ፕሮጀክትን እንደ ተምሳሌት በመውሰድ በ50ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ሊሰራ የታሰበው “አፄ ምኒልክ አረንጓዴ ልማት ፓርክ” የመሰረት ድንጋይ በዚሁ ዕለት በደብረ ብርሃን የሚቀመጥ በመሆኑ ነው” ያሉት አቶ ተሾመ፤ ኮቪድ 19 እየተስፋፋና እየተሰራጨ አገራችን በጭንቅ ላይ ባለችበት በዚህ ወቅት ቡሄን ጠባብ በሆነው በጣይቱ ሆቴል ግቢ ውስጥ ማክበር ለበሽታው መባባስ ምክንያት እንዳይሆን በመፍራት ነው በደብረብርሃን በሰፊ ቦታ ላይ እንዲከበር የተደረገው ብለዋል፡፡
የፓርኩ የመሰረት ድንጋይ በሚቀመጥበት ሥነ - ሥርዓት ላይ መገኘትም ታሪካዊ በመሆኑ ነው ሲሉ አክለዋል - ዋና ሥራ አስኪያጁ፡፡
ነሐሴ 12 ቀን 12ኛ ወር 2012 ዓ.ም
እቴጌ ጣይቱ ነሐሴ 12 ቀን 1832 ዓ.ም ነው በደብረ ታቦር የተወለዱ፡፡  ነሐሴ 12 ቀን 1836 ዓ.ም ደግሞ የአድዋው ድል አብሳሪ አፄ ምኒልክና የድሉ አጋፋሪና አዋላጅ እየተባሉ የሚጠሩት ፊታውራሪ ገበየሁ በአንድ ቀን በአንድ መንደር የተወለዱበት ዕለት ነው፡፡ እጅግ የሚገርመው አፄ ምኒልክና
“ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ”
መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ”
የተባለላቸው ጀግናው ፊታውራሪ ገበየሁ፤ በአንድ ቀንና በአንድ ቤተ ክርስቲያን (አንጐለላ ኪዳነ ምህረት) ነበር ክርስትና የተነሱት፡፡ ባለፈው ማክሰኞም ብርሃነ ዘኢትዮጵያ እየተባሉ የሚጠሩት የጀግናዋ እቴጌ ጣይቱ ብጡል 180ኛ፣ እንዲሁም የአፄ ምኒልክና ፊታውራሪ ገበየሁ 176ኛ ዓመት የልደት በዓል በድምቀት ተከብሯል፡፡
በልደት በዓሉ አከባበር ላይ የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገ/ፃዲቅ፣  የደብረብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ም/ከንቲባ አቶ ደስታ አንዳርጌና ሌሎች የመንግስት ኃላፊዎች እንዲሁም የ “ፈንቅል” አስተባባሪ አቶ የማነ ንጉስ፣ አርቲስቶቹ ሽመላሽ ለጋስና ችሮታው ከልካይ፣ ከባህልና ቱሪዝም ጋር የሚሰሩት አዘጋጁ ባላገሩ አስጐብኚና ኮከብ ሚዲያ ታድመዋል፡፡
ማክሰኞ ነሐሴ 12 ረፋድ ላይ በከተማው በተለምዶ “መገንጠያ” ተብሎ በሚጠራውና ወደ አንኮበር ቤተ-መንግስት መገንጠያ ላይ በሚገኘው 50ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የ “አፄ ምኒልክ አረንጓዴ ልማት ፓርክ” ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ በሥነስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪና የከተማው ከንቲባ አፄ ምኒልክ ለኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን ለመላው ጥቁር ህዝብ የነፃነት ብርሃን ስለሆነውና ስላስመዘገቡት የአድዋ ድል፣ በዚህ ድል ምክንያት የኢትዮጵያዊያን የአሸናፊነት ስነ-ልቦና ስለመገንባቱ፣ በአፄ ምኒልክ ላይ ስለሚነገረው የተዛባ ትርክትና አሳፋሪነቱን አፄው ከልጅነት እስከ እውቀት የተጓዙበትን መልካምም ሆነ የፈተና ወቅት አብራርተዋል፡፡
የአፄ ምኒልክ አረንጓዴ ልማት ፓርክ በውስጡ የንጉሱን ቤተ - መንግስት፣ ሙዚየም፣ ሃውልታቸውን፣ የህዝብ መናፈሻ፣ የንባብ ሥፍራ እንዲሁም የእቴጌ ጣይቱና የፊታውራሪ ገበየሁ መታሰቢያዎችን የሚይዝ ሲሆን የዛሬ ዓመት የእነዚህ ባለታሪኮች ልደት በዚሁ ፓርክ እንደሚከበር የገለፁት ከንቲባ ደስታ አንዳርጌ፤ ይህን ፓርክ ህዝብና መንግስት በጋራ የሚገነባ እንደመሆኑ መጠን ህዝብ በገንዘብም፣ በእውቀትም ሆነ በጉልበት ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከዚህ በኋላም ከደብረ ብርሃን ከተማ በግምት ስድስት ወይም  ሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የአፄው የጥንት ቤተ-መንግስት ፍርስራሽ ተጐብኝቷል:: ጥንታዊውን “ልቼ” ቤተመንግስትን ጐብኝተናል፡፡ ይህ ቦታ አፄ ምኒልክና አፄ ዮሐንስ  ያለስምምነት 4ኛ የገቡበትን ግጭት በውይይትና በስምምነት ለመፍታት ቁጭ ብለው የተነጋገሩበት ሲሆን እስከ ዛሬም ድረስ “የልቼ ስምምነት” እየተባለ ይጠራል::  በዚህ ቦታ ላይ የጥንቱ ቤተመንግስት ፍርስራሽ በዳዋ ተሸፍኖ የሚታይ ሲሆን አጠገቡ ቤተ ክርስቲያን ተገንብቶ፣ የአካባቢው ነዋሪ እንደሚጠቀምበት ተጠቁሟል፡፡
የከተማ አስተዳደሩና የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ በጋራ በመሆን ይህንን ታሪካዊ ቦታ ከታሪኩ ጋር በሚመጣጠን መልኩ አልምተው አንዱ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግም እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ገልፀዋል፡፡
በዚሁ እለት ከምሽቱ 12፡00 ጀምሮ ደግሞ የቡሄ (ደብረታቦር) በዓል የተዘከረበት ሥነስርዓት በጌትቫ ሆቴል ተካሂዷል፡፡ በዚሁ አዳራሽ ውስጥ ርቀት ተጠብቆ በተደረደረ ወንበር ላይ ታዳሚው ተስተናግዷል፡፡ ማስክ ሳያደርጉ መግባትም ክልክል ነበር፡፡ በፀሎት የተከፈተው ይህ መርሃ ግብር፤ የደብረ ታቦር ሃይማኖታዊ አመጣጥ፣ ትውፊቱና አጠቃላይ ሃይማኖታዊ ይዘቱ በዞኑ ሀገረ ስብከት አባት የተብራራ ሲሆን፤ በሀገረ ስብከቱ ሊቃውንት አፄውን፣ እቴጌይቱንና አጠቃላይ ሸዋን የሚያዋድስ ቅኔ እንዲሁም በማራኪ አለባበስና ጥምረት ወረብ፣ ሆያ ሆዩ ጨዋታ የጅራፍ ማጮህና የችቦ ማብራት ሥነሥርዓት ተከናውኗል፡፡
በሌላ በኩል፤ ፉከራ፣ ሽለላና ቀረርቶ በተሾመ አየለና በወጣቶች በማሲንቆ ታጅቦ የቀረበ ሲሆን አንጋፋዎቹ አርቲስቶች ሽመላሽ ለጋስና ችሮታው ከልካይ አዝናኝ ትርኢቶችን በመከወን ታዳሚን ከማዝናናት ባሻገር ለኢትዮጵያና ለህዝቧ ፈጣሪ መልካም ነገር እንዲያመጣ ምኞታቸውን ገልፀዋል፡፡
ባላገሩ አስጐብኚ ከደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደርና ከሰሜን ሸዋ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ይኸው የነገስታቱ ልደትና የቡሄ ክብረ በዓል መርሃ ግብር ለስኬቱ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ወገኖች ሽልማትና እውቅና በመስጠት ተጠናቅቋል፡፡
ደብረ ብርሃን ከተማ ለአዲስ አበባ ባላት ቅርበት፣ በማራኪ የተፈጥሮ መስህቧና ምቹ መልከአምድራዊ አቀማመጧ እንዲሁም ተመራጭ በሆነው ደጋማ የአየር ንብረቷ አያሌ የውጭና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ኢንቨስት እያደረጉባት ሲሆን፤ በዚህም ከ504 በላይ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ከ35.6 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ካፒታል ተጀምረው ለ74ሺህ ዜጐች የስራ እድል መፍጠራቸው ተነግሯል፡፡ በዕድገት ግስጋሴ ላይ የምትገኘዋ ይህቺ ጥንታዊ ከተማ፤ የአፄ ምኒልክ አረንጓዴ ልማት ፓርክ ሲገነባ በርካታ ወጣቶች የስራ እድል እንደሚያገኙበት  ተቀዳሚ ም/ከንቲባ አቶ ደስታ አንዳርጌ አስታውቀዋል፡፡

Read 1061 times