Sunday, 23 August 2020 00:00

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by  (ሚኪያስ ጥላሁን)
Rate this item
(0 votes)

 ብቸኛው መፍትሄ ውይይት ነው
                      
            ይህች ሃገር ውስብስብ ነች። በቋንቋ ቢለያዩም፣ በአኗኗር የተጋመዱ ህዝቦች የሚኖሩባት ምድር ነች። ልምላሜዋ ያልተዳሰሰ፣ መሬቷም ያልተነካ ምድረ-ገነት ነች። ሆኖም ፖለቲከኞች ባመጡባት ዳፋ ምክንያት እንደ መፃጉዕ አጎንብሳ እንድትሄድ ተገድዳለች።
ዛሬ ከትናንት አልተሻለም። ነገ ደግሞ ምን እንደሚመስል አይታወቅም። ምናልባት፣ ከዛሬ ሊብስ ይችላል። ትናንት - ዛሬ እና ነገ የሚገናኙበት አማካይ ድልድይ የላቸውም። ሶስቱም በየፊናቸው ተበትነዋል። ለሃገራችን የሶስቱ ትርጉም አንድ ነው። ዛሬንም ሆነ ነገን ለማሻሻል የሚረዳ አማካይ መንገድ አልተዘረጋም። የዛሬዎቹ ፖለቲከኞች የትናንቶቹን ፈለግ ለመከተል ዓይናቸውን ያላሹት በዚሁ ምክንያት ይመስለኛል።
ዞሮ ዞሮ የነገው ቀና መንገድ የሚሰራው በዛሬው እርምጃችን ልክ ነው። በስልጣን ላይ ያሉት ወገኖች የአምባገንነት መንገዳቸውን ገትተው፣ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት፣ የፖለቲካ እስረኞችን ወደ መፍታት ካላመሩ በስተቀር፣ የሃገሪቱ የመንገዳገድ እርምጃ በመበተን (balkanization process) ሊደመደም ይቻላል። ከኤርትራ ጋር ያለው ግንኙነት ትግራይንና ህዝቡን እስካልዳሰሰ ድረስ፣ ሰላም አይኖርም። በሌላው አካባቢ ያለው የአማራና ሌላው ሕዳጣን ወገን፣ በቂ አስተዳደራዊ ውክልና እስካላገኘ ድረስ፣ መረጋጋት አይኖርም።
ይህ ሁሉ ችግር የሚፈታው በውይይት ብቻ ነው። ኮማንዶ ልኮ የንፁሃንን ደም ማፍሰስ ግን ወደ ዴሞክራሲ ሳይሆን ወደ አመፃ ነው የሚያሸጋግረን። በመሆኑም፣ በፖለቲካ አመለካከታቸው ሰበብ የታሰሩ ወገኖችን ከእስር በመፍታት፣ በቅድሚያ ወደ መሃል መንገድ የሚደረገውን ጉዞ ማመቻቸት የገዢው ቡድን የመጀመሪያ ግዴታ ነው። ምክንያቱም የሚበቃትን ያህል ደም ላነባችው ሃገር የሚገባት ውይይት ብቻ ነው። የሚገባትን ያህል ላላደገችው ሃገር የሚገባት ልማት ነው። ሁሉም በዚህ አስተሳሰብ ዙሪያ ተሰባስቦ መታገል ግዴታው ነው። እናስተውል!

Read 1101 times