Saturday, 21 July 2012 10:31

የኢትዮጵያ ትጋት ለአፍሪካ የኦሎምፒክ ጽዋ ማኅበርተኝነት

Written by  ሰሎሞን አበበ ቸኮልSaache43@yahoo.com
Rate this item
(0 votes)

ኢትዮጵያ ከፓሪሱ 8ኛ ኦሎምፒያድ እስከ ሜልቦርኑ 15ኛ ኦሎምፒድ (ድረስ) ከሠላሳ ዓመት በላይ የኦሎምፒክ አባል ለመሆን ስትጠይቅ ቆይታለች፡፡ ይህን ያህል የደከመችበት የአባልነት ጥያቄ፣ ለመላው የአፍሪካ ሀገራትም ጭምር በሩን አስከፈተ፡፡ እነሆ ዛሬ ለንደን ላይ የኦሎምፒኩ ድግስ ተደግሶ አፍሪካውያንም በዚህ ግብዣ የግድ መገኘት ያለባቸው ሆነው ይጠበቃሉ፡፡ እንዲህ ያለ፣ አፍሪካውያን ከድግሱ እንዲቀሩ የማይፍለግበት ዘመን ላይ መደረሱን ስናስብ፣ አስቀድማ  በኦሎምፒክ ለመሳተፍ የጠየቀችው ኢትዮጵያ መሆኗንም እናስታውሳለን፡፡ ያኔ ታድያ፣ አፍሪካውያን በሙሉ ለስፖርትም ያልበቁ እንደሆኑ እየተነገረ፣ “ለኢትዮጵያም ቦታ የለንም፣” ተባለ፡፡

የአባልነቷን ጥየቄዋን አልቀበል ያለውን ዓለምአቀፉን የኦሎምፒክ ማኅበር አሸንፋ ኢትዮጵያ ቀዳሚቱ ጥቁር አፍሪካዊት ሀገር ሆነች፡፡

እንዲህ በአንድ ዓረፍተ ነገር እንደተገለፀው ግን የቀለለ አይደለም፡፡ ስድስት ዓመተ ኦሎምፒያድ፣ ወይም 24 ዓመት ያስቆጠረ ፍላጐትና ጥረት፣ ራሱን የቻለ የዲፕሎማቲክ ብልጠት ሁሉ የጠየቀ ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ ሌሎች አፍሪካውያን የኦሎምፒክ ድግስ ተጋባዦች ሊያውቁት የሚገባው፡፡

ዛሬ ለሦስተኛ ጊዜ ደጋሽ የሆነችው ለንደን ከመሆኗም አኳያ፣ ከዚህ በፊት የዛሬ 64 ዓመት ላይም የኦሎምፒክ ጽዋው የርሷ ሆኖ በደገሰች ጊዜ በሃይድ ፓርክ የተሰበሰበው የማኅበርተኞቹ ኮሚቴ፣ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር የት እንደምትገኝ ጠይቀው፣ ምሥራቅ አፍሪካ መሆኗ ሲነገራቸው ቅስም የሚሰብር ምላሽ እንደሰጡ ማሰቡ ኢትዮጵያ ምን ያህል ዋጋ እንደከፈለች ያሳውቀናል፡፡

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት 14ኛው ኦሊምፒያድ ዊምብሊ ስቴድየም ላይ ሲካሄድ፣ ለዩናይትድ ኪንግደም በ400 ሜትር ወርቅ ሜዳልያ ያስገኘው የቅኝ ግዛቷ የጃማይካው ልጅ ዊንት ነበር፡፡

ከዚህ በፊት ፌንጣው ኦዌንስ ደጋግሞ በማሳየት በዝላይ ወርቅ ያገኘ የመጀመሪያው ጥቁር ሰው ሆኗል፡፡

ሂትለር በሱ አንገት የሜዳሊያውን ሐብል አላንጠለጥልም አለ፡፡ ጥቁሮች ለስፖርትም ቢሆን ብቁ አይደሉም የሚለው ሐሳብ እንዲህ ያለው ከኦዌንስም በፊት በፓሪሱ ኦሊምፒያድ ለኢትዮጵያውያን ማመልከቻ የተሰጠ ምላሽ ነበር፡፡ ያም “አፍሪካውያን” በሚል ቃል በደብዳቤ የተጻፈ ነበር፡፡

በሂትለር ላይ የታየውም ይኼው ነበር፡፡ ሂትለርንና የሱን አክሰሶች ያሸነፉት መንግሥታት፣ ቀንደኛይቱ የቃል ኪዳን ሀገር የነበረችው እንግሊዝ ከተማ ላይ ደግሞ ያሰለፈችው ዊንት ወርቅ አመጣላት፡፡ግና አሁንም የጥቁሮች ብቃት በኦሊምፒክ ኮሚቴው ዘንድ ሊታይ አልቻለም፡፡

የዊንትን ማሸነፍ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ኦሊምፒከ ቁጥር 2 ባለውለታ ሊባል የሚችለው ስዊድናዊው ሻለቃ ኦኒ ኔስካነን የኢትዮጵያን የኦሎምፒኩ ማኅበርተኝነት ጥያቄን እንዲቀበሉት መከራከሪያው አደረገ፡፡ ይህ የሆነው ዛሬ ለሦስተኛ ጊዜ ደጋሽ የሆነችው ለንደን ለሁለተኛ ጊዜ በደገሰችበት ጊዜ ነበር፡፡

ያን ጊዜ አንዲት አፍሪካዊት ሀገር አልነበረችም - ከደቡብ አፍሪካ በቀር፡፡ የደቡብ አፍሪካው ፕሪቶሪያ መንግሥትንና ሀገርን የወከሉት ደግሞ እንዳሉ ነጮች ነበሩ፡፡ የሃይድ ፓርኩ ጉባኤ አፍሪካዊት መሆኗን ሲረዳ የኢትዮጵያን አባልነት ውድቅ አደረገ በለንደን፣ የ1948 ኦሎምፒክ፡፡

በቀጣዩ የሄልሲንኪ ኦሎምፒክ ላይ ብልሁ ንጉሠ ነገሥት ነጩን ኔስካነንን ነበር መልሰው የላኩት፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ገብተው ከነበሩ ነጮች መካከል ከነጆን ቤል፣ ከነሙሴ ኢልግ ጋር ሊመዘገብ የሚገባው፣ በትውልድ ፊንላንዳዊ፣ በዜግነት ስዊድናዊ የነበረው ሻለቃ ኦኒ ኒስካነን ሽንጡን ይዞ ለኢትዮጵያውያን ቆመ፡፡

አሁን በሄልሲንኪ ውድድር ዊንት አላሸነፈም፡፡ ጥቁሮች ለስፖርት ብቁ አይደሉም ያሉትን አሻሽለው፣ “ጥቁሮች በአጋጣሚ ቢያሸንፉ፣ አቋማቸው ይዋዥቃል፣” ብለው ራሱን ዊንትን ጠቅሰው ተሟገቱ፡፡

ያም ሆኖ ንጉሠ ነገሥቱ የነበራቸው ዓለምአቀፋዊ ክብርና ዲፕሎማሲያዊ ብልጠት ሁሉ ተጨምሮ ኔስካነን በሄልሲንኪው ጉባዔ መልካም ምላሽን አገኘ፡፡ የሜልቦርን 16ኛው ኦሊምፒያድ ሊጀመር አንድ ዓመት ሲቀረው ኢትዮጵያ - አፍሪካ አባል መሆኗን በደብዳቤ ተገለፀ፡፡

ያኔ ኔስካነን ከስዊድናውያን ጋር ከሚኖርበት ቤት ወጥቶ አዲስ ቤት ቀይሮ ነበር፡፡ በቤቱ ውስጥ ሳውና ባዝም አበጅቶ ነበርና የኢትዮጵያ ስፖርት ሰዎች የነበሩት ወጣቶቹን ይድነቃቸው ተሰማንና ፍቅሩ ኪዳኔ እንዲመርቁለት ጋብዟቸው በርሱ ቤት ተሰብስበው ነበር፡፡ ፍቅሩ ኪዳኔ ከውጭም ከሀገር ውስጥም የተላኩ የስፖርት ፌዴሬሽኑን ደብዳቤዎች ተሸክሞ ነበር፡፡ እዚያው ሆኖ ደብዳቤዎቹን በዓይነት ዓይነታቸው መለየት ጀመረ፡፡ ከነዚያ ደብዳቤዎች መካከል 5ቱ ቀለበቶች ተጠላልፈው የሚታዩበት የኦሎምፒክ ምልክት የሚታይበት ደብዳቤም ነበረ፡፡

ፍቅሩና ይድነቃቸው ኦኒ ኒስካኔንን አቀፉት፡፡

“መቸም ግርማዊነታቸው እንዴት አድርገው እንደሚያመሰግኑህ!” አለ ፍቅሩ ለሻለቃ፡፡

“ይህ ለንጉሱ የክብር ጉዳይ ነው፡፡ (የፖሊቲክስ) ስልታዊ ጥያቄም ነው፡፡ ኢትዮጵያ የኦሎምፒክ የወንድማማችነትን ክለብ መቀላቀሏ የንጉሱን ሥልጣንንም ያጠነክራል” ይላል ስለ አበበ ቢቂላ የተጻፈው ታሪክ፡፡ ትግሉ የተጀመረው ግን ከ30 ዓመት በፊት ነበር፡፡ 1913 ዓ.ም (1924 ኤ.ዲ) የፓሪስ ኦሊምፒክ

8ኛው ኦሊምፒያድ በፓሪስ ነበር የተካሄደው፡፡ በዓለምአቀፋዊ ግንኙነት ከተቀረው የዓለም መንግሥታት ጋር ራሷን ማወዳጀትም ልትጀምር ያሰበችው የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ኢትዮጵያ ደግሞ ልዑክ ወደ አውሮፓ ልካ ነበር፡፡ በተፈሪ መኮንን የሚመራው ልዑክ ፓሪስ የደረሰው በኦሎምፒያዱ ነበር፡፡

ማንኛውም የፈረንሳይ መንግሥት ባለሥልጣን በውድድር ማካሄጂያ ቦታው ታድሞ ይውላል፡፡ ከአፍሪካ ቀንድ ለሥራ የሄደው የንግሥቲቱ እንደራሴና ዐልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንንን በይፋ የሚቀበልም አልነበረም፡፡

ይህ በዚች ዓለም ልዩ ሆኖ በፈረንሳዩ ፒየር ደ ኩበርቱን ሐሳብ፤ ከ28 ዓመት በፊት የተጀመረው ኦሊምፒክ፣ እስኪያበቃም የባለሥልጣናቱ ቢሮ አይከፈትም፡፡ ስለዚህ ንጉሥ ተፈሪ መኮንንም የሚካሄደውን ውድድር ይመለከቱ ዘንድ በክብር ተጋበዙ፡፡ በኦሎምፒክ ሜዳ በመገኘት በዓለም ከሚገኙ መንግሥታት ባለሥልጣናት ጋር የዓለም ዓቀፍ ኦሎምፒክ አባል የሆኑ ሀገራት ስፖርተኞች የሚያደርጉትን የውድድር ጨዋታ በመመልከት ልዑኩ በፈረንሳይ የሚያደርገውን የሥራ ጉብኝት፤ ጀመረ፡፡

ግብዣው የፈረንሳይ ባለሥልጣናትን ማግኘት ባለመቻላቸው “ፈቃደኛ ቢሆኑ” እርሳቸውም ቢገኙና ጨዋታዎችን ቢከታተሉ ተብለው እንደተገኙና እንደተመለከቱ በሚያስገነዝብ መንፈስ ነው በ1992 ዓ.ም የታተመው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ መጽሔት ያቀረበው፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽን እንደራሴ የነበሩት፣ በኋላ ንጉሠ ነገሥት በሆኑበት ዘመን ኢትዮጵያን የኦሎምፒክ አባል እንድትሆንና አትሌቶችን ለውድድሩ በማብቃት ተሳታፊ እንድትሆን ትልቅ ሚና የተጫወተውን ሻለቃ ኦኒ ኒስካነን በቤተ መንግሥታቸው የነገሩት ግን በዚያ መንፈስ እንዳልሆነ ያሳውቃል፡፡

የኦሎምፒክ ሀገርነቱን ጉዳይ በልዩ ትርጉም የያዙት ንጉሠ ነገሥቱ፣ ከስዊድን ለክብር ዘቡ የስፖርት አሠልጣኝ ሆኖ ተቀጥሮ ለመጣው፣ በትውልድ ፊንላንዳዊ ለሆነው ሻለቃ ኔስካነን ራሱን ኦሎምፒክ ዐይቶ ያውቅ እንደሆነ ጠይቀውት፣ ዕድሉን አግኝቶ እንደማያውቅ ሲነግራቸው፣ “በ1924 በእንደራሴነት ዘመናችን በታዛቢነት ተገኝተን እንድንመለከት ተደርገን ዐይተናል፣” ብለው ነበር የነገሩት፡፡ ይህ እንግዲህ በ1939 ዓ.ም (እ.ኤ.አ በ1948) ላይ በለንደን ለሁለተኛ ጊዜ ሊካሄድ በነበረው 14ኛ ኦሊምፒያድ ሊከናወን በተቃረበበት ጊዜ ላይ ነበር፡፡

ከዚሁ ከፓሪስ፣ 1ኛ ኦሊምፒያድ ጀምሮ ነው እንግዲህ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ታሪክ የሚጀመረው፡፡ በዚያ ወቅት አልጋ ወራሽና እንደራሴ የነበሩት ተፈሪ መኮንን የኦሎምፒክ መሥራች አባትና የጊዜው ፕሬዚዳንት ከነበሩት መሌይ ፒየር ደ ኩበርቲን ጋር ኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ተሳታፊ መሆን በምትችልበት ሁኔታ ላይ በሚገባ ተነጋገሩ፡፡ ንጉሥ ተፈሪ ከሚያዩት በተጨማሪ ከደኩበርቲን ያገኙት ገለጻም ማረካቸው፡፡ ኢትዮጵያም መካፈል የማትችልበት ምንም ዓይነት ምክንያት እንደሌለ ኩበርቲን ነገሯቸው፡፡ በሀገሯ የባርያ ንግድ ዓይነቱ የማይካሄድ ከሆነ ወይም በመንግሥት ደረጃ ባርነት የማይፈቀድ ከሆነ ኢትዮጵያም ከተቀሩት የዓለም ሀገሮች ጋር በአንድነት ተሳታፊ እንደምትሆን ነበር የነገሯቸው፡፡

ይህን ታላቅ ሀሳብ አልጋ ወራሹ ከዚያች ወቅት ጀምረው በልባቸው አኖሩ፡፡ ወደ ሀገር ሲመለሱ ከሚፈጽሟቸው ሥራዎቻቸው አንዱም ሆነ፡፡ የኢትዮጵያን መልክ ለመኳል ማድረግ ከሚገባቸው ዋና ዋና ሥራዎቻቸው መካከል ኢትዮጵያን በዓለም ዓቀፉ የስፖርት መስክ ማሰለፍም አንዱ ሆነ፡፡ ባዩአቸው ውድድሮችም ኢትዮጵያውያን የራሳቸው የሆነ ባሕልና ብቃት እንዳላቸውም ያውቃሉ፡፡

1918 ዓ.ም (1926 ኤ.ዲ)

“አፍሪካውያን ገና ስፖርትን መማር አለባቸው”

ተፈሪ መኮንን ወደ ሀገር እንደተመለሱ በርካታ ተቋማትን እንደ አስፈላጊነቱ ደረጃ በቅደም ተከተል አቋቋሙ፡፡ እንደነ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤትን ማጠናከር፣ በስማቸው ለመክፈት ያስጀመሩት በአዲስ አበባ 2ኛው የተፈሪ መኮንን አስኳላ ት/ቤት ግንባታ ከዋነኞቹ ግንባር ቀደሞች ነበሩ፡፡ በዚህ ት/ቤት ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ የሰውነት ማጐልመሻም እንደ አንድ መደበኛ ትምህርት ሆኖ የተያዘው፡፡

በኢትዮጵያ የአካል ጥንካሬና ቅልጥፍና እንዲሁም ልዩ ልዩ የውድድር ጨዋታዎች በየመንደሩ ሁሉ ከታላቁ እየወረሰ የሚቀጥለው ነበር፡፡ አንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍል እና ብሔረሰቦችም ለየት ያሉ የአካል ብቃትና የጥንካሬ ሥልጠናና ውድድሮችን ያካሂዱ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በነገሥታቱም አካባቢ ይኼ በጣም የሚፈለግ ነበር፡፡ ለምሣሌ ያህል አንድ፣ ሁለቱን እናንሳ የነገሥታቱ ልጆች በፈረስ ጉግሥ፣ ጦር ውርወራ እና በሌሎች የግድ መሠልጠን ነበረባቸው፡፡ ነፃ ትግልንም ያካትት እንደነበር ይታወቃል፡፡

በአንዳንድ ብሔረሰቦች ትግል፣ ድብድብ፣ የፈረስ ጉግሥ፣ ዝላይ የመሳሰሉት በየዓመቱ የሚከናወንባቸው የታወቁ ጊዜም ነበሯቸው፡፡ ዛሬም ድረስ አሉ፡፡

እጅግ በራቀ ዘመን፣ በግሪክ የስፓርታዎች ትግልና የአካል ጥንካሬ ውድድሮች መከናወን ባልጀመረበት ጊዜ፣ በየ10 ዓመቱ በቤተመንግሥት አካባቢ የሚከናወን የአካል ብቃትንና ብርታትን የሚጠይቅ በትግል የመጋጠም ፈተና፣ “ልነግሥ ይገባኛል” ያሉ ልዑላን ሁሉ ይጠብቃቸው ነበር፡፡ ይህን ያደረገው አፄ ነበር፡፡

እንደዚህ ባለው ልዩና አስገራሚ ታሪኩ ምንጊዜም ስሙ እንዲጠራ በማሰብ አክሱምን የቆረቆራት አክሱማይ ራሚሱ (ኦፊላስ) (ከልደት በፊት በዘጠነኛ መቶ መፈፀሚያ እንደተቃረበ አካባቢ) ንጉሠ ነገሥት የሆነ ሁሉ ከስመ መንግሥቱ አስቀድሞ ይህን ስም መጠሪያው እንዲሆን አውጆለት፣ እስከ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ድረስ የነገሱት ሁሉ “ዓፄ” ተባሉ፡፡ ይህ መጠሪያ የእርሱ የልደት ስም እንደነበረ የሚተረክለት ከንግሥተ ሳባ በፊት የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት በመሆን፣ ራሱ በቆረቆራት ሳባ የተባለች ከተማው የነበረው ንጉሠ ነገሥት አክናሁስ/አንጋቦስ ነበር፡፡ በነበረው ፍልስፍና መሠረት በየ10 ዓመት መሪዎች የሚፈራረቁበትና የሚታወቁበት ይህን በታላቅ ሥነ ሥርዓት ይካሄድ የነበረ የአካል ጥንካሬና ብርታት መፈተኛ እና መለያ አደረገ፡፡

ምናልባት አብዛኛው አዲስ ነገር ሊሆንበት እና ሊገረምበት የሚችለው፤ ዛሬም ድረስ “ኑብያን ሬስሊንግ” ተብሎ  የሚታወቀው የለየለት ድብድብ (ትግል) ከዚያ ዘመን ጀምሮ የተያዘ ወግ ነበር፡፡ ትግሉ ይካሄድባቸው በነበሩ የዓባይ ሸለቆች ውስጥ በትውፊት ወርዶ ዛሬም ድረስ ያለ ውድድር ነው፡፡ በዚሁ ስሙ በየድረገጹ የሚገኝ ስለሆነ ከዚያ መቃረም ይቻላል፡፡

እንግዲህ ይህ ወቅትን ጠብቆ በይፋ ይከናወን የነበረ ነፃ ትግል ከልደት በፊት ብቻ 1500 ዓመት ያህል ዕድሜ ሲያስቆጥር፤ የስፖርትነት መለያ የሆነው የግሪክ አንዲት ከተማ አካባቢ ሰዎች ያደርጉት የነበረው ስፖርታዊ ውድድርም ሆነ፣ በኦሎምፒያኖችም በአራት ዓመት ይከናወን የነበረው ኦሊምፒያድም ጭምር ከዚህ “ኑብያን ነፃ ትግል” ተብሎ ለመጠራት ከቻለው የኢትዮጵያውያን ውድድር በኋላ የታወቁ ነበሩ፡፡

አሁንም ከዚህ በፊትም ወደ አራትና አምስት መቶ ዘመን ወደ ኋላ በመሄድ ደግሞ ሌላ አስገራሚ የሯጭ ኢትዮጵያውያንን ታሪክ እንገናኛለን፡፡ “ናኢ ጀር” የሚል ስም የተሰጣቸው ጐበዛዝት ተለይተው ልዩ በሆነው የሯጭነት ብቃታቸው ይፎካከሩ፣ ይወዳደሩ ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የኢትዮጵያውያን ጥንታዊ ታሪክ ያንንም ያህል የተገለጠ አይደለም፡፡ በጊዜው ቋንቋ “ናኢጀር - ናይጀር” የሚለው ልዩ ስማቸው፣ “ፈጣን ሯጭ” ማለትም ነበር፡፡ (ዛሬ ድረስ በኦሮምኛ ውስጥ ከዚሁ ጋር የሚገናኝ ቃል አለ፡፡)

ተደብቆ ኖሮ፣ በአንድ የሱዳን ባድማ፣ በወጥ የድንጋይ ሣጥን ውስጥ እንደታሸገ ተገኝተው፣ በአንድ ኢትዮጵያዊ እጅ ሊገቡ የቻሉ ጥንታዊ መጻሕፍት መዝግበውት የተገኘ ነው፡፡ ኤም. ኤ በላይ ወደ አማርኛ በመተርጐም ካቀረቧቸው መጻሕፍት አንዱ የሆነው “ሁለተኛው የሱባዔ መጽሐፍ“ ይህን ይናገራል፡፡

አሁን ስለ ኦሎምፒክ አጀማመርና ኢትዮጵያ ከኦሎምፒክ ጋር የተያያዘውን ስሟን ልታገኝበት የቻለችውን የመሳተፍ ዕድል ለማግኘት ምን ያህል ልፋትና ጥረት እንዳደረገች፣ በነማን ምን እንደተደረገም ይገልጽልናል ብለን በያዝነው በዚህ ጽሑፍ፣ ይህን የምንጠቅሰው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ የንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ ዓፄ ኃይለሥላሴ ለኦሎምፒክ ዓመታትን ያስቆጠሩ ድካም ሲደክሙ በዘረኞቹ አውሮፓውያንና ሌሎች ዘንድ ይሰማ የነበረው የአፍሪካውያን የስፖርት ባሕልና ብቃት የለሽነት ጩኸት ሊያስገርማቸውም እንደሚችል የምናይበትም ነው፡፡ እንዲያውም አበበ ቢቂላ ከሮም ሲመለስ፣ “ኢትዮጵያ የስፖርትም ሀገር መሆኗን አሳይተሃልና እናመሰግንሃለን” ማለታቸው እንዲሁ ባዶ ቃል አድርገው ያላሰሙት መሆኑን እናይበታለን፡፡

በሌላ በኩል የአካል ማጐልመሻና የአካልና አእምሮ ብቃትን የሚጠይቁ ጨዋታዎችም ቢሆኑ በሀገር የሞሉ መሆናቸውን ለመናገር ነው፡፡ ያው እንደሌላው ትምህርት አውሮፓውያን ከጊዜ በኋላ በየትምህርት ቤቶቻቸውና በሌሎች ተቋሞች መደበኛ ትምሕርት አድርገው አለመያዛቸው ብቻ ነበር ልዩነቱ፡፡ ዐልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ይህንንም ባሰሩት ት/ቤታቸው እና ቀደም ብሎ በተከፈተው ዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት እንደ አንድ ትምሕርት እንዲሰጥ አደረጉ፡፡ ከደ ኩበርቲን ጋር በተቀመጡበት ጊዜ እና በአውሮፓ አገሮች ባደረጉት የሥራ ጉብኝት ካስተዋሉዋቸው ቁምነገሮች ይህ አንዱ ነበር፡፡

ለዓለም ዓቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴም የአባልነት ጥያቄን ለማቅረብ አልዘገዩም፡፡ ከአውሮፓ እንደተመለሱ ለአባልነት ማሟላት የሚገባቸውን አስተካክለው፣ ከቀጣዩ ኦሊምፒያድ ጀምሮ ከአፍሪካ የመጀመሪያይቱ ሀገር ሆና ልትካፈል የምትችልበትን ዕድል ለማግኘት ጥያቄያቸውን አቀረቡ፡፡

የጥያቄው ምላሽ የመጣው በ1918 ዓ.ም ነበር (1926 ኤዲ)፡፡

በወቅቱ የደ ኩበርቲን የፕሬዚዳንትነት ዘመን አብቅቶ ነበርና በአዲሱ ፕሬዚዳንት “በመሴ፣ ሄንሪ ዲ ቢያ ላቶ ፊርማ የተላከልን ወረቀት፣” በማለት ግ.ቀ.ኃ ሥላሴ፣ ኒስካነን ባነጋገሩበት ወቅት አሳይተውታል፡፡

በ1948 ዓ.ም 14ኛ ኦሊምፒያድ ድረስ ዓለም ዓቀፉ የኦሎምፒክ ማህበረሰብ በእንቢተኝነቱ እንደፀና ቆይቶ፣ ትግላቸውን ያለመታከተ የያዙት የአፍሪካና የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቁጥር 1 ባለውለታ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፣ ለኒስካነን በደብዳቤው ላይ የሰፈረውን እንዲህ ነበር የገለጹት፡፡

“ከሁለት ዓመት በኋላ ይኼውልህ በዚህ ደብዳቤ ነበር አለመፍቀዳቸውን የገለፁልን” ይሉትና ወረቀቱን አንስተው ያሳዩታል፡፡

“ፈረንሳይኛ ትችላላችሁ” ሲሉት ኔስካነን እንደማይችል ሲነገራቸው፣

“እኔው እያነበብሁ በትርጉም አሉትና ፈረንሳይኛውን ያነብለት ጀመሩ፡፡ “Les African’s doivent partiguer lesprt dans leilr pays d abord pure le comprende.” አንዲቷ ዓ.ነገር ብቻ በቂ ነበረችና እሷኑ አንብበው ተረጐሙለት፡፡

“አፍሪካውያን በመጀመሪያ በአገሮቻቸው ስፖርትን መማርና ማዘውተር አለባቸው፡፡ ለኢትዮጵያም ቦታ የለንም፣ አሉትና ሲያበቁ፣ “ይህ እንግዲህ በመሴ ሄንሪ ዲ ቢያ ላቶ ፊርማ የተላከልን ወረቀት ነበር፣” አሉት፡፡

እንግዲህ፣ በ1920ዓ.ም በሚደረገው ዘጠነኛው አሊምፒያድ ላይ እምትካፈልበት ዕድል አስገኝ ብለው የሞከሩት እንዲህ ሆኖ፣ ደ ኩበርቲን ከነገሯቸው ውጭ የሆነ ምላሽ አገኘ፡፡ ከዚህ በኋላስ?

 

 

Read 1762 times Last modified on Saturday, 21 July 2012 10:36