Monday, 24 August 2020 19:23

ውለታ እና ‘ብድር’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

ንዴት ሰነበታችሁሳ! የሆነ ወዳጅ ታገኙና “ና እስቲ ሻይ አየጠጣን የሆድ ሆዳችንን እናውራ” ይላችኋል፡፡ ፍላጎቱ ባይኖራችሁም... አለ አይደል... “ደግሞ እምቢ ብዬው የማውቃቸውንም፣ የማላውቃቸውንም የጠላቶቼን ዝርዝር እንዳላበዛ” ትሉና ግብዣውን ትቀበላላችሁ፡፡ የሆነች “የአሮጌ እቃዎች የእጅ በእጅ ሽያጭ" የሚል ማስታወቂያ ሳይለጥፉ የረሱባት የምትመስል ቤት ይዟችሁ ይገባል፡፡ መቀመጫዋ ባለ አራት እግር ቀጥ ያለች መደበኛ የሚባለውን አይነት ትሆንና እንደ ‘ሮኪንግ ቼይር’ ነገርም ያደርጋታል፡፡ ቂ...ቂ...ቂ... “ግዴለም እንደምንም አንድ ስኒ ቡናዬን ፉት ልበልና ቶሎ ላምልጥ” ትሉና መቀመጫችሁን ‘የማባባል’ አይነት ቀስ ብላችሁ ትቀመጣላችሁ፡፡ ጋባዣችሁ ሲያጨበጭብ አሳላፊ ሊጣራ ሳይሆን “ስማ፤ እዚህ ሁለት ሻይ”ምን! ምን ያጣድፈዋል? እናንተ መጠጣት የፈለጋችሁት ቡና፣ እሱ የሚያዘው ሻይ::የፈለገ ከፋይ ቢሆንስ... “ልጋብዝህ...” ብሎ ሁለት እንቆቆ ቢያዝ፣ እሺ ብላችሁ ልትጠጡለት ነው! ሻዩ ይመጣል፡፡“ሻይ ትወዳለህ ብዬ ነው”መቼ! አሁን እንዲህ ያለ ቃል ወጥቶኝ ያውቃል! ደግሞ እኮ ከእሱ ጋር አብራችሁ ሻይ የጠጣችሁበት ቀን የምታውሱት ሁለት ጊዜ የረሳችሁት አንድ ቢሆን ነው! “ግዴለም የዛሬውን ልወጣው አንጂ አይለምደኝም” ትላላችሁ ለራሳችሁ፡፡ “ስማ ያቺ ሀይስኩል አብራን የነበረችው ሄለን...ዲሲ ውስጥ ምን የመሰለ ሬስቱራንት ከፍታለች አሉ፡፡” መጀመሪያ እንኳን የሀይስኩሏ ሄለን ትዝ ልትላችሁ፣ የዛሬ ዓመት ገደማ እሱ ራሱ ጠፍቷችሁ በስንት ምልከት ነው ያወቃችሁት፡፡ እና የእሱ የሆድ፣ ሆድ ጨዋታ የዲሲዋ ሄለን ነች!“እውነት! በጣም ደስ ይላል” የዲሲዋ የማትታወሰው ሄለን፣ ሬስቱራንት በመክፈቷ አዲስ አበባ “ርጥብ በአዲስ መልከ ጀምረናል” የሚል ሬስቱራንት መመገብ ያቃተው ሰው፣ ደስ ካለው... አለ አይደል... "ፕሬሚየር ሊግ ሂዩማኒቲ" ይላችኋል ይሄ ነው፡፡ ግን ምን ይደረግ... ሰውየው አክቲቪስት ነገር ከሆነ የመጀመሪያ የስድብ ማሟሻ የምትሆኑት እናንተ ልትሆኑ ትችላላችኋ! የፈረደበት የቴሊቪዥን ስክሪን ላይ ብቅ ይልላችሁና...“ይህች ሀገር ላለማደጓ ምክንያት የሚሆኑት ራሳቸውን ከፍ፣ ከፍ የሚያደርጉ...” ምናምን እያለ ከአብሮ አደጋችሁ በመሰደዳችሁ አንድትቆጩ ሊያደርጋችሁ ይችላል፡፡ እናላችሁ... እንዲሁ የቆጡን የባጡን ሲቀባጥር ይቆይና፣ “የሻዩ ዋጋ ብር ከስሙኒ ነው፡፡ እናንተ ሼራተን ናችሁና ነው ብር ከሀምሳ የምከፍለው!” በሚል “አንጠፋፋ...” ብሏችሁ ትለያያላችሁ፡፡ እናንተም ከአንግዲህ የዲሲዋን ባለ ሬስቱራንት ሄለንን ዋና አጄንዳ ከሚያደርግ ከማንም ጋር ሻይ ላለመጠጣት ትወስናላችሁ፡፡ከዛም ጥቂት ሳምንታት ያልፉና ከዕለታት አንድ ቀን ሥራ ድክም አድርጓችሁ ወደ ቤት ስትመለሱ ከሰማይ ዱብ ይበል፣ ከምድር ሰርስሮ ይውጣ... ብቻ ፊታችሁ ድንቅር ይላል፡፡“አንተ ሰው ጠፋህ እንኳን አትልም! አሁን ለእኔ ስልክ መደወል ይሄን ያህል ያስቸግራል?”አዎ ያስቸግራል፣ በጣም ያስቸግራል! ልክ ኳስ ይዞ ሰርጂዮ ራሞስን ለማለፍ ያስቸግር እንደነበረው! “ሥራ በዝቶብኝ አልተመቸኝም” አሁን ስንት የሚታወስ ነገር እያለ አንተን ላስታውስ!“ይሁን፣ እንዴት ጠምቶኛል መሰለህ፤ እስቲ አንድ፣ ሁለት ቢራ በለኝ; (ቢራ ‘የጠማው’ ሰው አንድ፣ ሁለት ካለ፣ የአስራ አንድና የአስራ ሁለት ‘ሾርት ፎርም’ ነው፡፡)በሻዩ አልቻልኩህ ደግሞ በቢራ! “ዛሬ በጣም ስለደከመኝ ቤት ገብቼ ማረፍ አለብኝ፡፡ ሌላ ጊዜ እንገናኛለን”“አንድ... እኩል ሰዓት ያህል ተጨዋውተን እንለያያለን፡፡ በዛው አናድር!” “እየፈጩ ምናምን...” ማለት ይሄኔ ነው::ሰውየው “አባብለህ አስክረው” ብለው ልከውት ነው እንዴ! ደግሞ በዚህ መጡ! (ስሙኝማ...በፊት እኮ ‘እነሱ ልከውት’ ‘ደግሞ በዚህ መጡ’ የሚባሉት የሚታወቅ ስም፣ የሚታወቅ አድራሻ፣ የሚታወቅ አበልጅ ምናምን ያላቸው ነበሩ፡፡ ዘንድሮ ግራ ገባን እኮ! ስም የለ፣. አድራሻ የለ፣ አበልጅ የለ፣ ብቻ ምን አለፋችሁ በጥቅሉ ‘እነሱ’ ሆኗል፡፡ ‘ቼንጅ አለ’ ስንል እንዲህ አይነቱንም እንደሚጨምር ለመጠቆም የተደረገ ሙከራ!)“እውነቴ ነው፣ ቆይተን ብንጫወት ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ግን ሰሞኑን ከባድ ሥራ ስላለብኝ የግድ ማረፍ ያስፈልገኛል፡፡”“በቃ ዘንድሮ ውለታ እንዲህ ሆነና ቀረ!” ምን?“ይቅርታ፣ ምን አልከኝ!”“የሻይ ውለታዬን ረሳኸው ወይ ለማለት ነው” ይቺ ናት ጨዋታ! የብር ተሀምሳ ሻይ እንደ ውለታ ተቆጥራ በሀያ ምናምን ብር ቢራ ልትመነዘር! ለነገሩ ምን መሰላችሁ...አሱዬ መጀመሪያም ሻይ ሲገዛም... አለ አይደል... ‘ሎንግ ተርም ስትራቴጂ’ ነገር ነድፎ ነው፡፡ ‘ማኖ ማስነካት’ የ‘ቦተሊካ’ ጉዳይ ብቻ አይደለም ለማለት ያህል! ስሙኝማ... በቁም ነገር “ውለታ ከፋይ ያድርገኝ” ብሎ ነገር አሁንም አለ እንዴ! ልከ ነዋ... የሆነ ሰው እኮ አንድ ነገር የሚያደርገው... “እንግዲህ አስር በመቶ ወለድ ጨምረህበት ውለታህን እንደምትከፍል እርግጠኛ ነኝ” አይል ነገር፡፡ ውለታ መክፈል በጎ ሀሳብ እንጂ ያልተጻፈ ግዴታ ነው እንዴ?! እንደዛ ከሆነማ ‘ብድር’ ይሆናል! እኔ የምለው... እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... በቀደም አንድ ወዳጄ አራት፣ አምስት ዓመት ያህል ሳያየው የከረመውን ዘመድ ነገር ያገኝና ተያይዘው ቤቱ ይሄዳሉ::ቤት ሲደርሱም ዘመድ ሆዬ ምን ቢለው ጥሩ ነው... "አንተ ፎቅ መሥራት አቅቶህ ነው አሁንም እዚች ሁለት ከፍል የኪራይ ቤት ውስጥ ያለኸው!” እናላችሁ... ከዚህ በፊት ያወራናት ነገር ትዝ ብላኝ ነው፡፡ሰዎች... አብዛኛውን ጊዜ ስለ እናንተ በጎ ነገር በማሰብ ራሳቸው የወሰኑላችሁ ስፍራ ላይ ያስቀምጧችኋል፡፡ “እሱ ሰውዬ ግን ሳስበው ሮፓክ ቤት ያለው፣ ከሺቫዝ በስተቀር ሌላ መጠጥ በአፉ የማይዞር፣ ሞዛርት ቤቶቨን ምናምን የሚሏቸውን ብቻ የሚያዳምጥ...” ምናምን ሊባል ይችላል::ለተባለለት ሰው እንዳፋቸው ያድርግለት ያሰኛል፡፡ በሌላ በኩል ግን የሆነ ነገር ስለሌላችሁ ልከ የሆነ ወንጀል የፈጸማችሁ ነው የሚያሥመስሉት፡፡ “ብቻ እስካሁን ቪላ ምናምን አልሠራሁም እንዳትለኝ...” ይላችኋል፡፡“እንኳን ቪላ ልሠራ ይኸው አፌን ከፍቼ የኮንዶሚኒየምም እጣ ስጠብቅ ስንት ዘመኔ!” ስትሉ እሱዬው ምን ቢል ጥሩ ነው... “በወር ያንን ሁሉ ብር እያገኘህ!” ከዚህ በኋላ መመላለሱ ወደ አውጫጪኝ አይነት ስለሚለወጥ መተው ነው፡፡ “እስቲ በወር ሠላሳ ሺህ ብር አላገኝም በልና እጄን ምታ!” አይነት ኢንተሮጌሽን፡፡ "በቀደም ቦሌ አካባቢ የሆነች አይጥማ ራቭ ፎር ይዘህ አየሁ ልበል!” “ራቭ ፎር! ምንድነው እሱ!”“እየቀለድክ ነው፣ አይደል!”“ሳይገባኝ ምንድነው የምቀልደው!”“እስካሁን መኪና የለኝም እያልከኝ ነው!”“የለኝም...”“ማንም እየተነሳ ቪኤይቱን ሲቀልድበት አንተ ለራቭ ፎር አቅም የለህም!” ራቭ ፎርን እኮ አውርዶ፣ አውርዶ የሆነች በቆርኪ የምትሠራ የህጻናት መጫወቻ መኪና አስመሰላት! በዛ ይበቃው መሰላችሁ... ‘ከራቭ ፎር አቅም’ መግዛት ስላልቻላችሁ ይስቅባችኋል፡፡ እናላችሁ...‘ክሬዚ’ ምናምን ነገር ላለመሆን ሰምቶ ዝም ሳይሻል አይቀርም!የመሳቅን ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ሰሙኝማ! “መጨረሻ የሚስቀው ሰው ጥሩውን ሳቅ ይስቃል፣” የሚል ነገር አለ...የፈረንሳዩ ቻርለስ ደጎል ምን አሉ መሰላችሁ... “መጨረሻ የሚስቀው ሰው ቀልዱ አልገባውም ነበር ማለት ነው፡፡” አሪፍ አይደለች! ለከፉ ለደጉም ውለታ ‘ብደር’ ባይሆንም ከተቻለ ‘መክፈሉ’ አሪፍ ነው....ቢያንስ እንኳን ለጽድቅ!ደህን ሰንብቱልኝማ

Read 2436 times