Print this page
Saturday, 21 July 2012 10:24

ቱባ ሙታን እና ጥቃቅን ህያዋን

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(0 votes)

(የግል አተያይ)

ትልቁ የበለጠ የሚገዝፈው ትንሹ የበለጠ እያነሰ በሄደ ቁጥር ነው

የሚፈስስ የለውጥ ወንዝን በድሮው ትዝታ እንጂ በዘንድሮ (“ናይኩ” ወይንም “ኤርገንዶ”) ጫማ ደግሞ መርገጥ አይቻልም፡፡ You never step on the same river twice ብሏል የግሪኩ ፈላስፋ ሄራክሊተስ፤ አሳጥሮ፡ ወደ ድሮው ለመመለስ የምናደርገው ጥረት ሁሉ ህያው ሳይሆን የሞትን መሆናችንን ነው የሚያረጋግጠው፡፡ የሞተውን ሃሳብ /ፍልስፍና/ሃይማኖት/ታሪክ…ህያው እንደሆነ የምንቀበል ከሆነ… ህያው ነኝ ብሎ የተቀበለውም ዘመነኛው ሰው የሞተ ነው ማለት ነው፡፡

በአንድ ወቅት ያነበብኩት የገብርኤል ጋርሺያ ማርከስ አጭር ልብ ወለድ ይህንኑ ሀሳብ የሚያንፀባርቅ ይመስለኛል፡፡

…ከእለታት አንድ ቀን …የሆነች ሀገር ወይ መንደር ነዋሪዎች በባህር ላይ ተንሳፍፎ የመጣ አንድ አስከሬንን ከውሃው አውጥተው ወደ መኖሪያቸው ለመቅበር ያስገቡታል፡፡

ነገር ግን፤ ከመቅበራቸው በፊት በሞተው የወንድ አስከሬን በጣም ይመሰጣሉ፡፡ በተለይ ሴቶቹ፡፡ ሟቹ በሁሉም ነገሩ እነሱን ይበልጣቸዋል፡፡ የቁመቱ ትልቅነት፣ የትከሻው ስፋት፣ የበድን እጆቹ ጥንካሬ፣ የማይሰራ ጭንቅላቱ ግዙፍነት… ወዘተ--፡፡ ይህ አስከሬን፤ ሞቶ እንኳን ከሕያዎቹ (እነሱ) በጣም የላቀ ነው፡፡ ሞቶም የት እና የት ያጥፋቸዋል፡፡ ትውልድ በትውልድ ላይ ተደራርቦ ቢነባበር እንኳን ወደ እዛ የሞተ ግዙፍ ጫፍ ሊደርሱበት አይችሉም፡፡ ሬሳውን አልብሰው በተጋደመበት እነሱን እንዲመራ ያደርጉታል (በስተመጨረሻ የታሪኩ አስተላለቅ ትዝ ይለኝ ከሆነ?)

…ግዙፉ ሰው (ጋሊቨር) እንዴት ወደነዚህ አይነት ዘመናዊ (የሊሊፑት) ትንንሽ ሰዎች ተቀየረ? የሚለው አይደለም የዚህ መጣጥፌ ጥያቄ፡፡ …ጥያቄዬ፤ እየሞተ ያለ ነገር ከመሞት መትረፍን ከፈለገ…ህያውን ነገር ነው ወይንስ የሞተን ነገር ነው የሙጥኝ ማለት ያለበት? የሚል ብቻ ነው፡፡ ወይንስ፤ ያለን ሀብት ሞታችን ብቻ ነው? በስተመጨረሻ፡፡ ሞታችን እስኪደርስ የሞቱትን በህያው አንደበት እያደነቅን እንቆይ? እስቲ ሞትን በተለያየ ፈርጅ ልመልከተው፡፡

የትውፊት ሞት

ለውጥ ዘገምተኛ ነው፡፡ የፈለገ ቢሆን እንደ ጥይት በፍጥነት ገድሎ በፍጥነት አይገላግልም፡፡ ግዙፉ የሰው ባህል መጀመሪያ ከመግዘፉ በፊት ይወለዳል፣ ያድጋል…እንደ አስተዳደጉ ቀስ በቀስ ጃጅቶ ይሞታል፡፡ ቱባው ወደ ሽባ ተለውጦ፡፡ ህፃን ሆኖ የተወለደው ባህል ከመዳህ ወደ መራመድ… ቀጥሎ ወደ መሮጥ… ከዛ ወደ መስከን… ከስክነት ወደ ጉብጠት…በስተመጨረሻ ተመልሶ ትንሽ ሆኖ በተወለደበት የህፃንነቱ አልጋ መጠን በተሰራ መቃብር ገብቶ ይመታል፡፡

ከሞተ በኋላ ደግሞ እንደ ግብፃዊያኑ የአምላክ ወፍ (ፊኒክስ) ከራሱ አመድ ሳይሆን ዱቄት ውስጥ ነብስ ዘርቶ እነደገና ይነሳል፡፡ …(አመድ በዱቄት ሊስቅ አይችልም፣ የድሮው ባህላችን አመድ ከሆነ አዲሱ ግን ዱቄት ነው!)

…ዘመናዊው የከተማ ህንፃ በውሃ ውስጥ የራሱን ምስል ሲመለከት በውሃው ነፀብራቅ ራሱን የላሊበላ ውቅር አቢያተ ክርስቲያን ሆኖ ይታየዋል፡፡ በዚሁ ቢያበቃ ጥሩ ነበር፤ ግን ዘመናዊ ህንፃውንም በውሃ ውስጥ እንዳየው የራሱ ምስል አድርጐ የሚቃዥ የንፋስ ህንፃ አለ፡፡ እኛ የንፋሱ ህንፃ ነን፡፡ ድሮ “ኬር” የበጐ አድራጎት ድርጅት በመንደር ውስጥ ያነጥው የነበረው ድንጋይ እንኳን፣ዘንድሮ መጠኑን ቀንሶ “ኮብል ስቶን” ሆኖ የ!

አለት ወደ ጠጠር ከተቀየረ፣ ከጠጠር ደግሞ ወደ አሸዋ መቀየሩ አይቀርም፡፡ ይኼንን የመጨረሻ የዱቄት ደረጃ ነው…የባህል ሞት ያልኩት፡፡ ታላቅ የነበረው የድሮ ትውፊት እንደ ግዙፉ ሰውዬ አስከሬን ከሞተ በኋላ፣ በሌለበትም መኖሩን ሊቀጥልም ይችላል፡፡ ከዱቄትም በታች አመድ አለ፡፡ አመድ ተቦክቶ የማይጋገር ዱቄት ነው፡፡ በንጽጽር ወደ ታች ማደግ ነው የባህል ሞት… ለእኔ፡፡

ምሳሌ ላቅርብ፡- ትዝ ይላችሁ እንደሆነ በአንድ ወቅት ምግብ በጉርሻ መልክ እንደሚሸጥ ሰምተን ነበር፡፡ ከአስራ ምናምን አመት በፊት፡፡ እንግዲህ የሙሉ ምግብ የመመገብ ባህል ሞት የሚጀምረው ምናልባት ሙሉ ምግብ በድሮው አቀራረቡ እና በአሁኑ መሀል የጥራትም ሆነ የዋጋ ማሽቆልቆል ሲያመጣ ነው፡፡ በአምስት ሳንቲም ይገዛ የነበረው እንጀራ ቱባ ባህላችን ከነበረ… በአራት ብር ተገዝቶ አንጀት ጠብ የማይለው ደግሞ የባህሉ መታመም ነው፡፡ ምክንያቱም፤ ባህላችንን ከሀገር ድህነት፣ ከዋጋ ግሽበት፣ ከገበያ ቁጥጥር አቅም ማጠር…ወዘተ ነጥለን ማየት አንችልምና ነው፡፡ በዚህ የማሽቆልቆል ሂደት ውስጥ …በጃንሆይ ዘመን፣ በአብዮቱ፣ በዘንድሮ… እየተባለ የጉርሻ ሽያጭ ደረጃ ላይ ተደረሰ፡፡ …የበቆሎን ዘለላ ከቆረቆንዳው ላይ በረድፍ ተመን ከፋፍሎ …”ይሄንን ያህል ዋጋ” መባል ወደፊት የማይቀር ከሆነ ደግሞ የበለጠ ወደ ሞት እያነሰ የመጣው ባህላችንን ይወክልንናል፡፡

…የእህልን ዋጋ በተመለከተ እኔ ብዙ መዘርዘር አያስፈልገኝም፤ ታውቁታላችሁ፡፡

…ጐጆ የመውጣትም ባህል ከእህሉ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ቱባ የነበረው ባህል ጐጆ ወጪውን ያለ ብዙ ውጣ ውረድ… ሚስት/ምሽት እና መሬት ይሰጠው ከነበረ፤ ከቱባነቱ እየወረደ ያለው ባህል… ለሚስት ብቁ ለመሆን ከተማ ገብቶ መስራት፣ ት/ቤት ገብቶ መማር፣ ወደ ባህር ማዶ ተሰድዶ መስራት… ግድ የሆንበታል፡፡

ቱባው ባህል ከሚስት ባሻገር “መወስለት” ለሚያስፈልገው አባወራ ውሽማ በድብቅ ይፈቅድለት ከነበር …ቱባው ክር ወደ ዘመናዊ ክር ተሸምኖ ሲለብሰው እና ላዩ ላይ ሲያረጅ…. በውሽማ ፋንታ የቡና ቤት ሴት ከወግ እና ማዕረጉ በታች ይሰጠዋል፡፡ በፍቅር ይገኝ የነበረውን ባህል በገንዘብ ከሴት አዳሪ ለመግዛት ይገደዳል፡፡

…ከማዕረጉ በታች የሆነው የሴተኛ አዳሪ ግንኙነቱም ቢሆን ከቱባው የሙሉ ሌሊት የግዢ አዳር…ወደ አጭር ጊዜ (Short) ግዢ ወርዷል፡፡ በዚህም አልበቃም፤ እንደ ምግቡ ጉርሻ የወሲባዊ ተራክቦ አካልን በማጉረስ…የሚፈፀም የአጭር - አጭር የወሲብ ጉርሻ ባህልም ተከስቷል፡፡ ሌላም ብዙ ያነሱ ለመጥቀስ የማያመቹ ድንክ ባህሎች ቢፈለጉ አይጠፉም፡፡

አለባበስም እንደ ባህል ከጋሊቨር ወደ ሊሊፑት ሰዎች ጥቃቅንነት ወርዷል፡፡ ጥቃቅን እና አነስተኛ ባህሎች ሊባሉ ይችላሉ፡፡ ባህል ሲያንስ የሴት የነበረውን ባጊ ሱሪ፤ ወንዱ የወንድ የነበረውን ክራባት ሴቷ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ረጅሙ የሀገር ባህል ቀሚስ ቱባው ባህል ከነበረ…ሚኒ እስከርቱ፣ ወይንም ውስጥ ሱሪን አብዝቶ ማሳየቱ…የወረደው ዱቄቱ ባህል ነው፡፡…ከድሮው ማንነቱ አንፃር የቀነሰውን ትውፊት ነው የባህል ሞት ያልኩት፡፡ ሞት ንፅፅር ነው ባህልን በተመለከተ፡፡

የጥበብ ሞት

የሞቱ ባህሎች የጣሉዋቸው የፈጠራ አሻራዎች…በቅርብ ጠባቂ ከለላ ስር ሳይጠፉ እንዲኖሩ ይደረጋሉ፡፡ የጥንታዊ የሰው ዘርን የሚወክል አጥንትም በሙዚየም ቅርስ ሆኖ ይጠበቃል፡፡ በቅርሶቹ ላይ የዘመናዊ እምነቱን አሳርፎ ህያውነቱን የሚያረጋግጥ የዘንድሮ ሰው ራሱ…. ቅርስ አይደለም ወይ? ነው ጥያቄዬ፡፡

…የግጥም ጥበብን በተመለከተ ቱባው ባህል ቅኔ ላይ ነው የሚገኘው ይላሉ ፤መሰረታዊያን፡፡

…ሰለሞን ደሬሳ፡- …ስሜት ካለ ለፍትወቱ ሀሳብ ካለ ቸርነቱ…ብቀኝ ባልቀኝ ባልመቀኝ…ቅኔ ነኝ ምን ታደርገኝ?... ብሎ የአባቶቹን ቤት ተሰናብቶ (የራሱ አባት ሊሆን) ወጣ፡፡ …የግጥም ዋናው ነገር ቅርጽን መከተል እንጂ ግጥሙን የሚስጢር መስበኪያ ጐተራ ማድረግ አይደለም አለ (እንደ “ጃሉድ” አይነት አቋም ይዞ)፡፡ ቱባን የግጥም ጥበብ ባህል በዘመናዊ ቱባ አመጽ ለመተካት በመንቀሳቀሱ የግጥም ባህል ኪሎ መቀነስ በእሱ ጀመረ የሚሉ አሉ፡፡ እኔ ባልስማማበትም… ውንጀላው አለ፡፡

በአጭሩ፤ ወንጀላው ያነጣጠረው የሃያኛው ክፍለ ዘመን ጥበብ አይነቶች ላይ በአጠቃላይ ነው፡፡ ውንጀላው፡- በስዕሉ ዘርፍ እነ ገብረክርስቶስ ደስታን፣ እነ እስክንድር ቦጐሲያንንም ያካትታል፡፡ ፍቅር እስከ መቃብርም በቅርጽ ሳይሆን በጭብጥ የቱባውን ባህል ለውጥ የሚሰብክ ራሱን የቻለ ቱባ ነው፡፡

እነዚህ ጀማሪዎች፤ የድሮው ቱባ ባህል አይመጥነንም ቢሉም ለመጠናቸው የመረጡት የገለፃ “ሞድ” በራሱ አዲስ ነበር፡፡ ከምዕራብ በአስተሳሰብ የተቀዳ ቱባ ነበር፡፡ …ግን ሁለት ፀሐይ በአንድ ሰማይ ላይ እንደማያባራው ሁሉ ፤ ሁለት በተቃራኒ እይታ ለመራመድ የሚፈልግ ባህልም ተስማምቶ ሊቆይ አይችልም፡፡

ከሁለቱ ቱባ መንገዶች የቱ ትክክል እንደነበር ለመለየት ጥበቡ በአሁኑ ዘመን የት እንደደረሰ መመልከት ብቻ በቂ ነው፡፡ በአሁኑ ዘመን ጥበብ ስዕሉ ከሸራው ላይ ወጥቶ…በህይወት መንቀሳቀስ ጀምሯል፡፡ የትርጉም ፍቺ የሌላቸው፤ የስሜት ሙቀት እና ቅዝቃዜ ብቻ የሚሰጡ የቀለም ስብጥሮች በአስትራክትም ይሁን በሌላ ዘይቤ ተሰቅለው እየተሸጡ ይገኛሉ፡፡ ግጥም በውስጡ ዜማ ካጣ በጃዝ ሙዚቃ ዜማ መደገፍም የዘመናዊ እድገቱ መንገድ ነው፡፡

…በአህያ ጀርባ ላይ የላፕቶፕ ኮምፒውተር ጭኖ…በሸራ ላይም ሆነ በሌላ መንገድ ሊፈጥራቸው ያልቻሉ ነገሮችን በማቀላቀል የስዕል ኤግዚቢሽን ያሳየ ወጣት አለ፡፡ የተግባር ስዕል የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ተመሳሳይ ስእሎችም የዘመኑ እውነት ናቸው፡፡ ቀለምን በመቀባት ፋንታ ቀለም ያለባቸው አልባሳትን በመልበስ ስዕሉንና ሰአሊውን በአንድ ላይ መሆንም በዘመናዊ ባህል ይቻላል፡፡ የወር አበባዋን በመጠቀም ስዕል በሸራ ላይ የቀባች ወጣትም እንዳለች ሰምተናል፡፡ …”ለነፋስ መብት አለው” ብሏል ገጣሚ ኤፍሬም ስዩም፤ በአለት ዘመን ህግ ነፋስ አይተዳደርም፤ …አቅጣጫዬን አለማወቄ የነፋስ የአቅጣጫ ጠቋሚው ስህተት እንጂ የኔ አይደለም ማለቱ ነው፡፡

…ያም ሆነ ይህ… አሁን ያለው የጥበብ ባህል ትርጉመ ቢስ ከሆነ የድሮው ትርጉም ነበረው ማለት ነበር፡፡ የድሮው በአሁኑ የትርጉም እይታ ሞቶ ከሆነ ደግሞ፤ የአሁኑ በራሱ ዘመናዊ የሂደት ሚዛን ብቻ የሚለካ ለራሱ (በራሱ) ቱባ የሆነ (Culture for cultures sake) የሆነ ነው ማለት ነው፡፡ የድሮው የጥበብ ባህል ጤነኛ ከነበረና ከሞተ… የአሁኑ ግዴታ ህያው ሆኖ ለመቆየት ማበድ አለበት፡፡ በእብደት ዘመን እብደት ያልያዘው… ጤንነቱ በሽታውም ነው፡፡ ቅርስ ነው፡፡ መጠበቅ ሳይሆን መጥፋት ያለበት ቅርስ፡፡

የፍልስፍና ሞት

የሞቱትን ለመርሳት ባለመቻል ምክንያት ህያው እንደሆኑ አምኖ መቀመጥ…. ለሀሳብ ባህል ዘርፍም ዝቅጠት ነው፤ እንደኔ እውርነት የሆነ ነገር ነው፡፡ ቱባዎቹ ፍልስፍናዎች ባህልን ወይንም የዘመን መንፈስን ፈጥረው ወይንም በባህል ሂደት ተጨፍልቀው ከጠፉ በኋላ፤ ሀሳቦቹን አሁንም እየሰሩ እንደሆነ አድርጐ ማስተማር… የሞተ ፍልስፍና ህያው ህይወትን አሟሟች …ዱቄትን ወደ አመድ መለወጫ ይሆናል፡፡

…ፍልስፍናን ከወረሰው “ሚስቲሲዝም” ነፃ ለማውጣት በአምክኒዮአዊ ልከኝነት (Logical Positivism) የሞከሩት አሰላሳዮች የመጨረሻዎቹ ፈላስፎች ነበሩ፡፡ የእነሱም ፍልስፍና ነፃ ለማውጣት ተንቀሳቅሶ ነገር ግን በራሱ ገመድ ተተብትቦ ጠፋ፡፡

ጥርስን በጣም ለማንፃት በአሲድ እንደመፋቅ ማለቴ ነው፡፡ ጥርሱም ሟምቶ ይጠፋል፡፡

በአመክኒዮአዊ ልከኝነትም ሆነ በጥርጣሬ እና ጥያቄ ብዛት ሰክኖ እና ረግቶ ሊቆይ የቻለ ፍልስፍና እስካሁን አልተገኘም፡፡ ፍልስፍናም …ትልልቅ የሚባሉትን የቴዎሮቲካል መጠይቆች (ከየት መጣን፣ ለምን መጣን፣ ወደየት ነው የምንሄደው፣ የሰው ልጅ ቦታ በህዋ ውስጥ ምንድነው፣ ህይወት ትርጉም አለው? እውነታ/እውነት ምንድነው?) ወዘተ መመርመሩን ትቶ ቋንቋ እና ፎኔቲክስን ወደ ማጥናት ገባ፡፡…

እኛ የምናስብበት መንገድ ሁሉ የጥንቱ ፍልስፍና በመሆኑ…ህያውን ተጨባጭ አለም ለዛሬ በሚሆን የሀሳብ ባህል ፈጥረን ልንገልፀው አልቻልንም፡፡

…ከፍልስፍና ጉያ የወጡና ያደጉት… ሌሎቹ የሰው ልጅ ከፍታን ጠቋሚ ዘርፎችስ? የሳይንስ ባህል እና ግብረ አበሮቹስ? እነሱስ እንደ ፍልስፍናው ሞተዋል? በተለይ በተለይ ደግሞ ሀይማኖትስ?... ሞቶ ነው እየኖርንበት ያለው? ...በሚቀጥለው ሳምንት…እመለስበታለሁ፡፡

 

 

Read 1647 times Last modified on Saturday, 21 July 2012 10:31