Monday, 24 August 2020 17:54

ኮስሞስ እቅዱን ወደ መሬት ማውረድ ይፈልጋል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

  ከ20 ሚ. ብር በላይ በማውጣት በአዲስ አበባ የአትሌቲክስ ማዕከል ለመገንባት

               የኮስሞስ ኢንጅነሪንግና ኮሜርስ ኃ/የተ/የግ/ ማህበር በስሩ በሚንቀሳቀሰው የአትሌቲክስ ክለብ አማካኝነት ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር በአዲስ አበባ ከተማ ግዙፍ የአትሌቲክስ ማዕከል ለመገንባት ተነስተዋል፡፡ ከሳምንት በፊት ከኮስሞስ ኩባንያ ስራ አስኪያጅና የአትሌቲክስ ክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ ሙሉጌታ ኢደአና ሌሎች አጋሮቻቸው ጋር ላይ ውይይት አድርገናል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃውን የጠበቀ የአትሌቲክስ ማዕከል ወይንም  መንደር ለመገንባት በያዙት የፕሮጀክት እቅድ ላይ ባተኮረው ውይይታችን ሁሉም የተሰማቸው ቁጭት ገልፀዋል፡፡ በኮስሞስ ኢንጅነሪንግና ኮሜርስ ኩባንያ በኩል የአትሌቲክስ ማዕከሉን ለመገንባት የሚያስፈልጉ መስፍርቶች መሟላታቸው መስክረዋል፡፡  የፕሮጀክት እቅዱንም በጥሩ ሁኔታ አዘጋጅተው አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግላቸው ለሚመለከታቸው አካላት አቅርበዋል:: አስፈላጊዎቹን የድጋፍ፤ እውቅናና ትብብር ደብዳቤዎችም ሰብስበው ይዘዋል፡፡ ፈተና የሆነባቸው  የፕሮጀክት እቅዱን ወደ መሬት ለማውረድ ነው፡፡የአትሌቲክስ ስፖርትን ከማሳደግ አንፃር የስፖርት ማዘወተርያ ግንባታ ለማከናወን የሚያስችል የቦታ ጥያቄ ካቀረቡ በኋላ ነው፡፡ ያለፉትን 10 ዓመታት የአትሌቲክስ ማዕከልን የመገንባቱ እቅድ ከወረቀት ማለፍ ባይቻልም ኮስሞስ ኢንጅነሪንግና ኮሜርስ ኩባንያ ራእዩን ሳይቀይር በየአቅጣጫው ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ ያስደንቃል፡፡ ስለእቅዳቸው ከስፖርት አድማስ ጋር  ሰፊ ውይይት ያደረጉት የኮስሞስ ኩባንያ ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ ኢደአ እና አጋሮቻቸው ዛሬም ተስፋ የቆረጡ አይመስሉም፡፡ ግንባታቸውን ለመጀመር ያቀረቡት የመሬት ጥያቄ በሚመለከተው አካል አስቸኳይ ምላሽና መፍትሄ እንዲያገኝ ተስፋ አድርገዋል፡፡
የስፖርት መሰረተልማት ከመንግስት ከቀድሞ ስፖርተኞች ባሻገር በኩባንያዎች
ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ያላትን ክብር እና ስኬት ለማስጠበቅ የስፖርት መሰረተ ልማቶች እጅግ ወሳኝ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ መንግስት ከሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ባሻገር ሌሎችም በዚህ ዘርፍ መሳተፋቸው የሚጠበቅ ይሆናል፡፡ በስፖርቱ ላይ ኢንቨስት አድርጎ ለመስራት ደግሞ ከመንግስት ባሻገር በስፖርቱ ውስጥ ያለፉት ሃላፊነት ብቻ አይደለም፡፡ በማናቸውም መንገድ ስፖርትን ለመደገፍ የሚያስቡ የግል ባለሃብቶች ለሚያደርጉት ተሳትፎም ትኩረት መስጠት ይገባል፡፡ በሁሉም ወገን የሚደረጉ ርብርቦች ደግሞ የስፖርቱን እድገትና ልማቱን  ያቀላጥፈዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በአዲስ አበባ፤ በቆጂ እንዲሁም በሌሎች የክልል ከተሞች  ግዙፍ የስፖርት መሰረተልማቶችን መገንባቱ ይታወቃል፡፡ በመንግስት በጀት የተገነቡ እና አገልግሎት እየሰጡ ያሉት የአትሌቲክስ ማዕከሎች ባሻገር በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ የቀድሞ ታዋቂ አትሌቶችም በተወሰነ መልኩ በአትሌቲክሱ ኢንቨስት በማድረግ ሰርተዋል:: ውድድሮችን ከማካሄድ በላይ ልዩ የአትሌቲክስ የስልጠና ልምምድ ማዕከሎች በአዲስ አበባ አቅራቢያ በሚገኙ ከተሞች በመገንባትና በማቋቋምና እየሰሩ ቆይተዋል፡፡ የስፖርት ኢንቨስትመንትን በማካሄድ እና ልማቶችን በማስፋፋት የግል ባለሃብቶችም ተሳትፏቸውን ሊያጠናከሩ ይገባል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ በሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች የሚንቀሳቀሱ ትልልቅ ኩባንያዎችም ወደዚሁ ዘርፍ እንዲያተኩሩ ግን  ማበረታቻዎች ተገቢ ናቸው፡፡
በውይይታችን መግቢያ ላይ የኮስሞስ ኢንጅነሪንግና ኮሜርስ ኩባንያ ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ ኢደአ  የአትሌቲክስ ማዕከሉን ለመገንባት ምን እንዳነሳሳቸው ማብራርያ ሰጥተውናል፡፡ ‹‹በኮንስትራክሽን ስራዎች ለበርካታ ዓመታት ስንሰራ ቆይተን፤ ተጨማሪ ሃገራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት ስናስብ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መስክ የአትሌቲክስ ክለብን ማቋቋም እና ማዕከልም ለመገንባት ሆነ::" ብለዋል፡፡ አቶ ሙሉጌታ በስራ እሰኪያጅነት የሚመሩት ኮስሞስ የኢንጅነሪንግና ኮሜርስ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የተመሰረተው  ከ13 ዓመታት በፊት ነው፡፡ ኩባንያው በግዙፍና በተለያዩ ግዙፍ የግንባታ ፕሮጀክቶች በመላው ኢትዮጵያ ተንቀሳቅሶ በምስራት ልምድ ያካበተ ነው:: በውሃና የሲቪል ኮንስትራክሽን ስራዎች የተለየ ተመክሮ ያለው ኩባንያው  በአማካሪነትና በንግዱ ኢንዱስትሪውም የሚንቀሳቀስ ነው፡፡
አቶ ሙሉጌታ እንደሚያስረዱት ኮስሞስ የስፖርቱን መስክ በመሰረተልማት ለማጠናከር ሲያስብ በመጀመርያ አገርን እንደሚጠቅም ለኮንስትራክሽን መስኩም የሚተርፍ ውጤት እንደሚኖረው ስላመነበት ነው፡፡  በዚህ መሰረት ኩባንያው በኢትዮጵያ ስፖርት ላይ አትኩሮ መስራት ከጀመረ 10 ዓመታት ሊሞላው ነው፡፡ በተለይም የአትሌቲክስ ስፖርትን መሰረት እድርጎ የሚንቀሳቀስበትን ራዕይ አስቀምጧል፡፡ የአትሌቲክስ ስፖርትን ክብር ጠብቆ ለማቆየት፤ ምርጥ አትሌቶችን ለማፍራት፤ በኢትዮጵያ ስፖርት የእድገት አቅጣጫዎች ላይ አስተዋፅኦ ማበርከት ይፈልጋሉ፡፡  
ኢትዮጵያ ውስጥ የአትሌቲክስ ማዕከልን በገዘፈ ፕሮጀክት ለመገንባት በግል ኩባንያዎች ብዙም ጥረት ሲደረግ አይስተዋልም፡፡ ብዙዎቹ ፕሮፌሽናል  የአትሌቲክስ ክለቦች በግል ኩባንያዎች ስር የተያዙ በመሆናቸው በርካታ የማሰልጠኛ ማዕከሎች ያስፈልጋሉ፡፡ አትሌቶች በሳይንሳዊ ስልጠናዎች፤ ልምምድ እና የዝግጅት ሁኔታዎች የሚያልፉትና ውጤታማ የሆኑት በዘመናዊ ማዕከሎች ነው፡፡ የአትሌቲክስ ስፖርት በዚህ አቅጣጫ ከመጠናከሩም በላይ በአካል ብቃት ስልጠና እና ልምምድ ወጣቱን ትውልድ መገንባት ይቻላል፡፡
ለአትሌቶች የተሟሉ መሰረተልማቶች
በአሁኑ ወቅት የኮስሞስ ኢንጅነሪንግ አትሌቲክስ ክለብን ጨምሮ በአዲስ አበባ የሚንቀሳቀሱ ከ30 የማይበልጡ ክለቦች ናቸው፡፡ ባለፉት ስምንት ዓመታት በአገር አቀፍ ደረጃ በሚደረጉ ውድድሮች ላይ ሲሳተፍ መቆየቱን የክለቡ አሰልጣኝ ይገልፃሉ፡፡  በሁለቱም ፆታዎች ከ25 በላይ አትሌቶችን በመያዝ የኮስሞስ አትሌቲክስ ክለብ  በዓመታዊዎቹ የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች፡ በአዲስ አበባና በኢትዮጵያ አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች በፔፕሲ ማራቶን መሳተፉን አሰልጣኙ ለስፖርት አድማስ አብራርተዋል፡፡
ኮስሞስ ኩባንያ እና ባለድርሻ አካላቱ ኢትዮጵያ የምትታወቅበት አትሌቲክስ ስፖርትን በክለብ ደረጃ በማንቀሳቀስ ባደረጉት ጥረት ደስተኞች ናቸው፡፡ በመጀመርያ ደረጃ በክለቡ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከፍተኛ ልምድ ያለው አሰልጣኝን በመቅጠር የስፖርቱ ሂደት አስቀጥለዋል፡፡ በኩባንያው ስም የሚተዳደረውን ክለብ አትሌቶችን ይዞ እንዲሰራ በማድረግም የፕሮጀክት እቅዳቸው እንዲጠነሰስና እየዳበረ እንዲቆይ አድርገዋል፡፡፡ በኢትዮጰያ አትሌቲስ ውስጥ ያላቸው ልምድ ታድያ ባለፉት 5 እና 6 ዓመታት ፍሬ እንዳለው እየተረጋገጠ ነበር:: የአትሌቲክስ ክለቡ የስፖርት መሰረተ ልማቶች የተሟሉ ባይሆንም፤ ባሉት ባለሙያዎችና ብርቱ አትሌቶች በትኩረት እየሰራ ቆይቶ  በአማተር እና በፕሮፌሽናል ደረጃ ብዙ አትሌቶችን ለማፍራት ችሏል፡፡ የኮስሞስ ኩባንያ ስራ አስኪያጅ  ሙሉጌታ እንደሚናገሩት በክለባቸው ያፈሯቸው አትሌቶች ወደተሻለ ደረጃ ወዳላቸው ክለቦች መሄዳቸው ሲደጋገም አሳስቧቸዋል፡፡ በኩባንያቸው ድጋፍ በሚንቀሳቀስ ክለብ ጥሩ ደረጃ ላይ የደረሱ አትሌቶች  የተሻለ ደሞዝና ጥቅም ፍለጋ መኮብለላቸውን ያን ያህል ባይቆጩበትም ስፖርተኞቹ በየሄዱበትም የተሟላ ነገር አለማግኘታቸው ግን መፍትሄ እንደሚያስፈልገው ያስቡበት ነበር፡፡
አትሌቶች ከኮስሞስ ክለብ ወጥተው ሌሎች ክለቦች ሲቀላቀሉ የተለየ እድገት ውስጥ የሚገቡበት ሁኔታ የለም፡፡  የተሟላ የስፖርት መሰረተልማት፤ ስልጠና፤ የህክምና እና የስነልቦና አገልግሎት ስለማያገኙ ችግርና ፈተና እንደሚገጥማቸው አስተውለዋል፡፡ በተለይ ዘመናዊ የስልጠና እና የውድድር ሜዳዎች በአዲስ አበባ አለመገኘቱ  አትሌቶችን እንደጎዳቸው አቶ ሙሉጌታ ተገንዝበዋል፡፡ ስለዚህም ለአትሌቶች ማሰልጠኛ የሚሆን ማዕከል ለመገንባት ከመንግስት ባሻገር ሌላ አካል ቢሰማራ የላቀ አስተዋጽፅኦ እንደሚኖረው በማመናቸው ለዚሁ መፍትሄ መንቀሳቀስ እንደጀመሩ ገልፀዋል፡፡
ዘመናዊ የአትሌቲክስ ማዕከል ለአዲስ አበባ
በኮስሞስ ኩባንያ ስር የአትሌቲክስ ክለብ ሲቋቋም  በሌሎች ሙያ ውስጥ የሆኑ ባለድርሻ አካላት ተሰባስበዋል፡፡ የአትሌቲክስ ስፖርቱን ለመደገፍ ኢንጅነሮች፤ የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች፤ ነጋዴዎች እና ሌሎች ባለሙያዎች በጋራ መነሳታቸው ከጅምሩ የሚያስደስት ነው፡፡ በኮስሞስ ኩባንያ ስር አትሌቶችን በማፍራት  እንቅስቃሴ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ክለቡ የራሱ ማዕከል ስላልነበረው ይህ ሁኔታ ባለድረሻ አካላቱን የሚያስጨንቃቸው ነበር፡፡  የአገሪቱ አትሌቶች በጫካ እና በአስፋልት ስፖርቱን መስራት መቀጠላቸውን ለማቆም  አስበውታል፡፡ የማዕከሉን የግንባታ ፕሮጀክት ለመቅረፅ በተለይ አንድ አጋጣሚ ሁኔታውን እንዳቀጣጠለውም በውይይታችን ወቅት ጠቅሰዋል፡፡ በሰበታ አስፋልት ላይ የኮስሞስ አትሌቶችና ሌሎች ተሰባስበው ልምምድ በሚሰሩበት ወቅት ያጋጠማቸው የመኪና አደጋ ነው፡፡ ይህ አሳዛኝ ክስተት በድጋሚ ማጋጠም እንደሌለበት በማመናቸን ማዕከሉን ለመገንባት ቆርጠን ተነስተናል ብለዋል- አቶ ሙሉጌታ፡፡ በመንግስት በኩል የወጣው አዋጅም ማዕከሉን ለመገንባት መነሻ አድርገውታል በየደረጃው የሚመለከታቸውን ተቋማት በር በማንኳኳትም ሰርተናል ብለዋል፡፡
በኮስሞስ ኩባንያ የታቀደውን የአትሌቲክስ ማዕከል ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አቶ ሳህሉ ለስፖርት አድማስ እንደሚናገሩት አዲስ አበባ የአትሌቶች መገኛ እና መኖርያ በመሆኗ ከተማውን የሚወክል ማዕከል እጅግ አስፈላጊ መሆኑን መታመን አለበት:: አቶ ሳህሉ በስነልቦና፤ በመኔጅመንት፤ በህፃናት እና ወጣቶች እድገት ላይ በመስራት ረጅም ልምድ ያካበቱ እና ከ10 ዓመታት በላይ በመምህርነት ሙያም ያገለገሉ ናቸው፡፡ የኮስሞስ ኩባንያ ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ የአገርን ሁኔታ በሚቀይር አጀንዳ ለመስራት መነሳታቸውን ያመሰገኑት አቶ ሳህሉ፤ በዚሁ ራእይ ላይ በትእግስት ያለፉትን 10 ዓመታት ስንሰራ መቆየታችን የሚያስገርም ነው ብለው፤ ሁላችንም ለአገራችን አስተዋዕኦ እናበርክት ብለን መነሳታችን ሊደነቅና ሊበረታታ ይገባው ነበር ብለዋል፡፡
የኮስሞስ ኢንጅነሪንግ አትሌቲክስ ክለብ እቅድ
በኮስሞስ ኩባንያ የቀረበው የአትሌቲክስ ማዕከል የስራ እቅድ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ህገ ደንብን የተንተራሰ ነው፡፡ በፌደሬሽኑ እንደተደነገገው ማንኛውም ክለብ የራሱን ማዕከል መገንባት ይኖርበታል፡፡ የቀረበው ከአትሌቲክስ ክለቡ የምስረታ ሰነድ፤ ከኩባንያው የንግድ ፍቃድ፤ ከአገር የክለብ ውድድሮች ተሳትፎ እና ከአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን የምዝገባ ማስረጃዎች ጋር ተያይዞ ነው፡፡ ኩባንያው በአዲስ አበባ ከተማ የአትሌቲክስ ማዕከሎችን መገንባት ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንደሚኖረው አምኖበታል፡፡ በተለይ ደግሞ በግል ባለሃብት የማዕከሉ ግንባታ መከናወኑ ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ግልጋሎት መስጠት ያስችላል በሚል ነው፡፡
የኮስሞስ ኩባንያ አዲስ አበባ ዘመናዊና ደረጃውን የጠበቀ የአትሌቲክስ ማዕከል ለመገንባት  የፕሮጀክት እቅዱን ከ10 ዓመታት በፊት አቅርቧል:: መሬቱን ከአዲስ አበባ መስተዳድር እንደሚያገኝ ተስፋ አድርጓል፡፡ የኢንጅነሪንግና የንግድ ኩባንያው ማዕከሉን ሲገነባ የኮስሞስ ኢንጅነሪንግ አትሌቲክስ ክለቡን፤ ከኢትዮጵያ መንግስት፤ የአዲስ አበባ እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች_፤፤ ከዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ማህበርና ከስፖንሰር አድራጊ ኩባንያዎች ጋር በማስተሳሰር ነው፡፡ ሁለገብ ጥቅም የሚሰጠውን አትሌቲክስ ማዕከል ለመገንባት የሚያስፈልገውንም በጀት ኩባንያው እንደሚሸፍን ገልጿል፡፡ የአትሌቲክስ ማዕከሉን ለመገንባት ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ኩባንያው በእቅዱ የገለፀ ሲሆን ፤ ግንባታው ካለቀ በኋላ ሙሉ አገልግሎት እንዲሰጥ በዓመት እስከ 10 ሚሊዮን ብር ወጭ ማዕከሉ እንደሚያስፈልገውም አመልክቷል፡፡
በኮስሞስ እቅድ መሰረት የማዕከሉን ግንባታ በሁለት ምዕራፎች ለማከናወን ነውየታሰበው:: በመጀመርያው ምዕራፍ ሁለት ዘመናዊ የስልጠና ትራኮች፤ ሁለት ግዙፍ የጅምናዚየምና የልምምድ ስፍራዎች እንዲሁም የአትሌቶች መኖርያዎችን ይገነባሉ፡፡ በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ዘመናዊ የመወዳደርያ ትራክ፤ የኦሎምፒክ ደረጃን የሚያሟሉ የሩጫ ትራኮች እና የአትሌቲክስ ሜዳዎች፤ የፈረስ መጋለቢያና የጎልፍ መጫዎቻ ሜዳዎች እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ መሰረተልማቶችን ገንብቶ ለመጨረስ ነው፡፡     የኮስሞስን የአትሌቲክስ ማዕከል ግንባታን በአንድ ጊዜ ጨርሰን የምናስረክበው ሳይሆን፤ በተለያዩ ምዕራፎች ግንባታውን በመከፋፈል እየሰራን፤ አገልግሎት እየሰጠን በምናልፈው ሂደት ነው የሚሉት  አቶ ሙሉጌታ፤ የግንባታውን የመጀመርያ ምዕራፍ ስናጠናቅቅ ከውጭ አጋር ኩባንያዎችን የምናሳትፍበት እድል መኖሩንም ጠቅሰዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ባለቤቶች እንደዘረዘሩት የአትሌቲክስ ማዕከሉ  ከተገነባ በኋላ በዓመት ከ100 በላይ አትሌቶች በስልጠና፤ በምግብ፤ በአካል ብቃት እና በስፖርት ስነልቦና በፕሮፌሽናል ደረጃ  ይዞ ለውጤት የሚያበቃ ይሆናል፡፡ የማዕከሉ ሰልጣኝ አትሌቶች ከዘመናዊ የስፖርት ክትትልና ልምምዳቸው ባሻገር በቋንቋ፤ በኮምፒውተር ክህሎት በመሰረታዊ የአስተዳደርና የሙያ እውቀቶችን ይቀስማሉ፡፡ እንደ አቶ ሙሉጌታ አገላለፅ ማዕከሉ ሙሉመሉ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ከኮስሞስ አትሌቶች ባሻገር ለመላው የአዲስ አበባ ከተማ እና ወጣት ትውልድ የሚሰጠው ጥቅም ይበዛል፡፡ በማዕከሉ ያሉትን የስፖርት መሰረተ ልማቶች የተለያዩ የስፖርት ቡድኖችና ክለቦች በተመጣጣኝ ዘመናዊ አገልግሎት ያገኙበታል፡፡ ከስፖርት ኢንዱስትሪው ጋር የተያያዙ ፌስቲቫሎችን የሚያስተናግድ፤ የአትሌቲስ ስፖርትን የተመለከቱ ሴሚናሮችን የሚያስተናግድ ማዕከልም ይሆናል፡፡ ለአዲስ አበባ ከተማ የሚያኮራ የስፖርት መሰረተልማት ነው የምናስበው የሚሉት የኮስሞስ ኩባንያ ሰዎች አትሌቶችን ከማፍራት ባሻገር በስፖርት ህክምና፤ በቢዝነስ እና ሌሎች የትምህርት ዘርፎች ለተማሩ ባለሙያዎችም የስራ እድሎች መፍጠሩን አንደ ውጤት ተመልክተውታል፡፡
የመሬቱ ጉዳይ
የኮስሞስ ኩባንያን የፕሮጀክቱን ራእይ ሰቅዞ የያዘው የመሬት ጥያቄያቸው እልባት አለማግኘቱ ነው፡፡ የአትሌቲክስ ማዕከሉን ለመገንባት ኩባንያው የሚያስፈልጉትን ሁሉ ሁኔታዎች ደረጃ በደረጃ እያሟላ ቢቀርብም በተለይ በመሬት አስተዳደር በኩል ምላሽ የሚሰጥ በመጥፋቱ መጉላላት ተፈጥሯል፡፡ አቶ ሙሉጌታን አሁን እያሳሰባቸው የሚገኘው የፕሮጀክት እቅዳቸው  ከጠረጴዛ ላይ ሊነሳ ባለመቻሉ በዙርያቸው የሚገኙ አጋሮቻቸውን በትግስት እንዲጠባበቁ የሚያሳምኑበት ሁኔታ ነው::
የፕሮጀክት እቅዱ ከቀረበ በኋላ በየደረጃው የሚገኙ እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት የድጋፍ እና የትብብር ደብዳቤዎችን ከመስጠት ያለፈ ሃላፊነት ነበረባቸው፡፡ በማዕከሉ መገንባት ላይ የሚኖራቸውን አስተያየትና ግምገማ በደብዳቤያቸው ቢያካትቱ ለፕሮጀክቱ እቅድ አቅራቢዎች የተሻለ ግብዓት በሆነ ነበር፡፡ ለሁሉም የፕሮጀክት ጥያቄ የሚሰጠው ምላሽ ለዚህ አትሌቲክስ ማዕከል ግንባታም እንደዘበት መሰጠቱ ተግባራዊነቱን ያሰናከለው አሰራር ይመስላል:: በአጠቃላይ ከመንግስት አካላቱ ለኩባንያው የተሰጡት ደብዳቤዎች በማዕከሉ ግንባታ ላይ ያለውን ፍላጎት ቢያመለክትም ተግባራዊነቱን የሚያቀላጥፍ ነገር ግን ይጎድላቸዋል፡፡ በደፈናው ትብብር ይደረግላቸው አይነት መመሳል ይሰተዋልባቸዋል፡፡ የኮስሞስ ኩባንያ ያቀረበውን ፕሪጀክት አስፈላጊት፤ የግንባታውን የጥራት ደረጃ እና አቅም የሚገመግም አስተያየት በየደብዳቤዎቹ አለመስተዋሉ ሁኔታዎች እንዳይፋጠኑ አድርጓቸዋል፡፡ እንደ ኮስሞስ ኢንጅነሪንግ አትሌቲክስ ክለብ ስራ አስኪያጅ ማብራርያ የአትሌቲክስ ማዕከሉን ለመገንባት በተቀረፀው ፕሮጀክት ላይ ገንዘባቸውን እና ግዚያቸውን በመሰዋት ሲሰሩ የቆዩት በአገራችን ሁለንታናዊ እድገት ላይ አስተዋጽፅኦ ለማድረግ ሲሆን፤ አዋጁ እና ህጉ የሚጠይቀውን ሁሉ በማሟላት ያቀረብነውን ፕሮጀክት በፈጣን ምላሽ ወደ መፍትሄ ሊያስገባን አለመቻሉ  አሳዝኖናል ብለዋል፡፡
በማዕከሉ ግንባታ ላይ የመንግስት ጉጉት መንፀባረቅ የሚችለው በኩባንያው ለቀረበው ጥያቄ ፈጣን ምላሽ በመስጠት ነበር፡፡
በኮስሞስ የአትሌቲክስ ክለብ በአሰልጣኝነት የሚሰሩት አሰልጣኝ ገዛኸኝ ቢራ በአትሌቲክስ ማዕከሉ ስራ ለመጀመር ከፍተኛ ጉጉት ውስጥ ሆነው መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ የአሰልጣኝነት ፈቃድ ያላቸው፤ በፖሊስ አትሌትነት የሰሩ እና በስፖርቱ ከ25 ዓመታት በላይ ልምድ ያላቸው አሰልጣኝ ገዛኸኝ፤ በኢትዮጵያ  የስፖርት እንቅስቃሴ ላይ በኩባንያዎች ለሚሰራ ኢንቨስትመንት ትኩረት መጥፋቱ ስፖርተኞቹን ለአደጋ አጋልጧል በማለት ያስባሉ፡፡ በተለይ በአትሌቲክስ ስፖርት ከፍተኛ ስኬት በተመዘገበባት አገር አትሌቶች የስፖርት መሰረተልማቶች ሳይሟሉላቸው ለዘመናት መቀጠላቸውም ያሳዝናቸዋል፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ምርጥ ውጤት ለማግኘት የሚችሉ ወጣቶችን የሚያፈሩ የስፖርት ማዕከሎች በብዛት ያስፈልጉናል:: ዘመናዊ ስልጠና ባለማግኘት በሜዳ ላይ እየቀሩ ያሉ አትሌቶችን ህይወት ለመቀየርም ጠንካራ አቋም ያስፈልገናል በማለት አሰልጣኙ ተናግረዋል፡፡
‹‹ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ በሙያችን አስተዋፅኦ ለማበርከት ስንነሳ በኮስሞስ ኩባንያ ስር ክለብ አቋቁመን መስራትን የመጀመርያ መፍትሄ መሆኑን አምነንበት ነው፡፡ በመሰረትነው ክለብ በአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ስር እየተወዳደርን ቆየን:: በስልጠና እና በውድድር በየዓመቱ መሻሻል እንዳሳየን የሚያመለክተው በየዓመቱ  የአዲስ አበባ ምርጦችን እያፈራን ስለነበርን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሻምፒዮና ላይ አዲስ አበባን ወክለው ውጤታማ ሆነናል፡፡ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከልን ለመገንባት የተነሳነውም ከዚሁ ሁሉ ሂደት ጋር ነው›› በማለት አሰልጣኝ ገዛኸኝ ለስፖርት አድማስ ይናገራሉ፡፡
በርግጥም ለኮስሞስ ኩባንያ የማዕከል ግንባታ ዋናው መነሻ መንግስት በነጋሪት ጋዜጣ ያወጣው አዋጅ ይሆናል፡፡ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ዋናው መፍተሄ የማዕከሎች ግንባታ መሆኑንም የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ አዲስ አበባ በቂ የስፖርት ማዘወተርያ ስፍራ የላትም፤ ከተማዋ ሜዳ የላትም፤ ሜዳዎች ቢኖሩ በጣት የሚቆጠሩና ለዘመናዊ የአትሌቲክስ ስልጠና ያልተዘጋጁ ናቸው፡፡ የሚሉት አሰልጣኝ ገዛኸኝ፤ ለማዕከል ግንባታው ከአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ለመሬት አስተዳደር ደብዳቤ መፃፉ ትልቅ ርምጃ ቢሆንም በመሬት አስተዳደር በኩል በሚሰጡት ምላሽ በደፈናው አዋጅ የለም በሚል ማመላለስ ከሆነ የባለሃብቱንና የባለሞያውን ሞራል የሚነካ ነው ይላሉ፡፡
በኮስሞስ ኩባንያ እና ባለድርሻ አካላቱ አዲስ አበባ ላይ የአትሌቲክስ ማዕከል ለመገንባት የተያዘ እቅድ ላይ አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥበት አሰራር መቀየስ ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያ በምትታወቅበት ስፖርት ላይ ኩባንያዎች ኢንቨስት በማድረግ ለመሳተፍ ፍላጎት ሲኖራቸው መንግስት ሸክሙ እንደቀለለት ማሰብ ይኖርበታል፡፡ ለአገር በሚጠቅም የመሰረተልማት ግንባታ ላይ ለቀረበ የመሬት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ዓመታት መቆጠራቸው ተገቢ አልነበረም፤ ለስፖርት መሰረተ ልማት የሚጠየቅ መሬትን ቢሮክራሲያዊ አሰራሮች መንፈግ የለባቸውም፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በየክልሎቹ በከፍተኛ በጀት የገነባቸውን  የስፖርት መሰረተ ልማቶች ብቻ በቂ አይደሉም፡፡ በግል ባለሃብቶች እና ኩባንያዎች የስፖርቱን መስክ የሚያነቃቁ መሰረተልማቶችና ኢንቨስትመንቶችም ተግባራዊ እንዲሆኑ መደገፍም ይጠበቅበታል፡፡

Read 1160 times