Monday, 24 August 2020 17:09

በወህኒ ቤቶች የእስረኞችን ቁጥር በመቀነስ የኮሮና ስጋትን መከላከል እንደሚገባ ተጠቆመ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

የአቶ ጀዋር መሃመድ አያያዝ ደረጃውን የጠበቀ ነው ተባለ

            በእስር ቤቶች የእስረኞች ቁጥር በመቀነስ የኮሮና ስርጭት ስጋትን መከላከል እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አመለከተ፡፡
ብዙ እስረኞች በአንድ ጠባብ ክፍል ውስጥ ተጨናንቀው እንደሚኖሩ ለአዲስ አድማስ የጠቆሙት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ ይህ ሁኔታ በእስር ቤቶች የኮሮና በሽታ ስጋትን እንዲጨምር እያደረገው ነው ብለዋል፡፡
እስረኞች በተጨናነቀ ሁኔታ ውስጥ ሆነው የፊት መሸፈኛ ጭንብል ማድረጋቸው እምብዛም ትርጉም የለውም ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በተለይ በፖሊስ ጣቢያ ደረጃ ያለውን መጨናነቅ ለመቀነስ ጉዳያቸው በፍጥነት ታይቶ በዋስ የሚለቀቁ በዋስ እንዲለቀቁ፤ ይህ የማይሆን ከሆነም መጨናነቅን መቀነስ የሚችሉ የመፍትሔ አማራጮችን መተግበር እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
ለችግሩ ዋነኛ መፍትሔው የእስረኞችን ቁጥር መቀነስ እንደሆነ የሚገልፁት ኮሚሽነሩ፤ የፍርድ ጊዜያቸውን ለመጨረስ ጥቂት ጊዜ የቀራቸውን ጉዳያቸውን አይቶ በይቅርታ በመልቀቅና በዋስ መውጣት ያለባቸውን አፋጣኝ ዋስትና በመስጠት ነው ስጋቱን መቀነስ የሚቻለው ብለዋል በተጨማሪም በእስር ቤቶች ውስጥ ምርመራ በስፋት ማካሄድንም እንደ መፍትሔ ይጠቁማሉ፡፡
የኮሮና ምርመራ ማካሄድና የክፍሎችን ንጽህና በተመለከተ በአብዛኞቹ እስር ቤቶች መልካምና አበረታች ሁኔታ ላይ እንዳሉ የገለፁት ኮሚሽነሩ አዲስ የሚገቡ እስረኞችን በተመለከተ ግን የሙቀት ምርመራ ከማድረግ ባለፈ ተገቢው ሙሉ ምርመራ ተደርጐላቸው ከነባሮቹ ጋር ሊቀላቀሉ እንደሚገባ ጠቁመዋል::
ኮሚሽኑ የእስር ቤቶችን የኮሮና መከላከል ሁኔታና የእስረኞችን አያያዝ በየጊዜው እየገመገመ መሆኑን ለአዲስ አድማስ ያብራሩት ኮሚሽነር ዳንኤል፤ “የማረሚያ ቤት ጠባቂዎችም ጭምር በቫይረሱ እየተያዙ መሆኑ አሳሳቢ ቢሆንም፤  ሁኔታዎችን ለመቆጣጠር አቅም የፈቀደው ጥረት ሁሉ እየተደረገ መሆኑን አስተውለናል” ብለዋል፡፡
የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሣን ግድያ ተከትሎ፣ በኦሮሚያና በአዲስ አበባ በተፈጠረው ሁከትና ግርግር ከ9ሺ በላይ ሰዎች መታሠራቸውን፣ ይህ ሁኔታም በእስር ቤቶች የኮሮና ስጋትን እንዳባባሰው የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፤  አፋጣኝ ፍትህ በመስጠት በዋስትና መለቀቅ ያለባቸውን መልቀቅ  ይገባል ብለዋል፡፡
ለመንግስትም ይህ ምክረ ሃሳብ መቅረቡንና በዚህም መሠረት የተወሰኑት በዋስትና እየተለቀቁ መሆኑን ያስታወቁት ኮሚሽነሩ፤ አሁንም አፋጣኝ ፍትህ በመስጠት ስጋቱ የሚቀንስበት ሁኔታ መፈጠር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ ሁከት በማስነሳት ተጠርጥረው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት በመታየት ላይ የሚገኙትና እንደታመሙ የተገለፀው የእነ አቶ ጀዋር መሐመድ የእስር ቤት አያያዝ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን ማረጋገጣቸውን የተናገሩት ኮሚሽነሩ፤ ከኮሮና አንፃር ያሉበት እስር ቤት ያን ያህል አሳሳቢ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የአቶ ጀዋር መታመምን ኮሚሽኑ እንደተረዳም አፋጣኝ ህክምና እንዲመቻች መጠየቁንና የሚመለከታቸው አካላትም ህክምና ለማመቻቸት ቃል መግባታቸውን አስታውቀዋል፡፡ የህክምና ሁኔታቸውንም ትኩረት ሰጥተን እንከታተላለን ያሉት  ዶ/ር ዳንኤል፤ አጠቃላይ የእስር ቤቱ አያያዝ ግን ብዙም ነቀፌታ የሚቀርብበት አይደለም ብለዋል፡፡ “በብዙ መልኩ ደረጃውን የጠበቀ አያያዝ መሆኑን አረጋግጠናል” ብለዋል - ኮሚሽነሩ፡፡
በኢትዮጵያ ያሉ እስር ቤቶች ደረጃቸው የተለያየ መሆኑን በመጠቆም፤ መንግስት አቅም በፈቀደ ሁሉ ንጽህናቸውን በመጠበቅና የእስረኛ ቁጥርን ለመቀነስ ጥረት በማድረግ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በእስር ቤቶች ውስጥ ቀውስ ከመፍጠሩ በፊት መላዎችን መዘየድ እንደሚገባ ኮሚሽነሩ አስገንዝበዋል፡፡

Read 7551 times