Sunday, 23 August 2020 00:00

ኢዜማ ለፖለቲካ ሃይሎች በትብብር የመስራት ጥሪ አቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 ለቀጣይ ምርጫ ከወዲሁ ውይይት መጀመር አለበት ብሏል

           የኢትዮጵያ ዜጐች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ለሁሉም የሀገሪቱ የፖለቲካ ሃይሎች  በትብብር አብሮ የመስራት ጥሪ ያቀረበ ሲሆን ለቀጣይ ምርጫ ዝግጅትም ከወዲሁ ውይይት ሊጀመር ይገባል ብሏል፡፡
ፓርቲው ከተመሠረተ ጀምሮ እስካሁን የተጓዘበትን ሂደትና የወደፊት አቅጣጫ ያመላከተበትንና ራሱን በባለሙያዎችና በአመራሮቹ የገመገመበትን ሰነድ ትናንት ለመገናኛ ብዙሃን ይፋ ያደረገ ሲሆን ኢዜማ የሀገሪቱ አንድ ጠንካራ አማራጭ ፓርቲ መሆኑን በግምገማው ማረጋገጡንም ጠቁሟል፡፡
ከፖለቲከኞች፣ ከአክቲቪስቶችና ከፖለቲካ ተንታኞች  “ስልጣን ላይ ካለው ፓርቲ ጋር መስመር ያለፉ ግንኙነት ፈጥሮ የህዝቡን ጥያቄ ዘንግቶታል” በሚል የሚሰነዘረው ትችት ፓርቲው ራሱን በአጽንኦት እንዲፈትሽ ገፊ ምክንያት እንደሆነው የጠቆመው መግለጫው፤ በጥናት ውጤት በተደገፈ መልኩም ራሱን በገለልተኛ ምሁራን ማስገምገሙን አመልክቷል፡፡
በግምገማው ከተገኙ ግብረመልሶች መካከልም በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ዝምታ ማብዛቱ፣ የገዥውን ፓርቲ ክፍተት አሳንሶ ማየቱ የሚሉት እንደ ድክመት ከተጠቀሱት ውስጥ ይገኙበታል::  በሌላ በኩል፤ ፓርቲው ከወረዳ የጀመረ ሰፊ አደረጃጀትና መዋቅር መዘርጋቱ፣ የተለያዩ ፖሊሲዎች ማዘጋጀቱ በጥንካሬ የተጠቀሱለት ናቸው፡፡ በቀጣይም በድክመቶች ላይ ማሻሻያ በማድረግ ራሱን ይበልጥ ለማጠናከር እንቅስቃሴ  መጀመሩንም ኢዜማ በዚህ መግለጫው አመልክቷል፡፡
በተጨማሪም ሀገሪቱ ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ተወያይቶ አቋም መያዙን የጠቆመው ኢዜማ፤  ለውጡ እስካሁን የመጣበት መንገድ ተስፋ ሰጪ መሆኑን እንዲሁም፣ የገዥው ፓርቲ ወደ አንድ ውህድ ፓርቲነት መለወጥንም በበጐ እንደሚያየው አመልክቷል፡፡ በሌላ በኩል፤  ገዥው ፓርቲ አንድ ውህድ ከመሆኑ አንፃር  ለሚፈፀሙ ጥፋቶች  ሙሉ ለሙሉ ኃላፊነት ሊወስድና ተጠያቂ ሊሆን እንደሚገባ  አቋም መያዙን  በሌላ በኩል፤ በቀጣይ በትኩረት ሊያከናውን ካቀዳቸው መካከል ዋነኛው ከሌሎች የሀገሪቱ ፓርቲዎች ጋር በትብብር የመስራት ጉዳይ መሆኑን በመግለጫው የጠቆመው ፓርቲው፤ ለዚህም ለሁሉም የሀገሪቱ የፖለቲካ ድርጅቶች አብሮ በትብብር የመስራት ጥሪ አቅርቧል፡፡
ይህን ጥሪውን ከሚቀበሉ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በሀገር አንድነት፣ በዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታና በዜጐች በሰላም የመኖር ጉዳይ በትብብር ለመስራት መወሰኑንም አስታውቋል፡፡ ይህን እቅዱን የሚያስፈጽም 5 አባላት ያሉት ኮሚቴም አዋቅሯል። ለችግኝ ተከላና መሰል ተግባራት ትኩረት የተሰጠውን ያህል በምርጫና ዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ላይ ለሚደረጉ ውይይቶችም ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ፓርቲው በመግለጫው አመልክቷል።
ምርጫው በትክክል መቼ ይካሄዳል የሚለው በውል አለመታወቁ እንደሚያሳስበው የጠቆመው ፓርቲው፤ ሃገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ታካሂደዋለች ተብሎ ለሚጠበቀው ዲሞክራሲያዊ ምርጫም በመንግስት በኩል የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው በማለት ይወቅሳል። ስለ ምርጫ ጉዳይ ከወዲሁ ውይይት መጀመር አለበትም ሲል ያሳስባል - ኢዜማ፡፡
መንግስት በተለያዩ አካባቢዎች ለሚፈጠሩ የፀጥታ መደፍረሶች የህግ የበላይነትን ለማስከበር እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ፓርቲው በበጐ እንደሚመለከተው ጠቁሞ፤ በህግ ማስከበርና በአምባገነንነት መካከል ያለውን ልዩነት መንግስት ፈልጐ ሊያገኝ እንደሚገባው አሳስቧል፡፡  



Read 4043 times