Print this page
Sunday, 23 August 2020 00:00

ባለፉት ሁለት ሣምንታት በጐርፍ አደጋ ከ130ሺ በላይ ዜጐች ተፈናቅለዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ሣምንታት ውስጥ በጐርፍ ምክንያት ከ130ሺህ በላይ ዜጐች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው የተገለፀ ሲሆን በሰው፣ በእንስሳትና በሰብል ላይም ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሪፖርት ጠቁሟል፡፡
የጐርፍ አደጋው በዋናነት የተከሰተው በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በሶማሌና ጋምቤላ ክልሎች መሆኑን ያመለከተው ሪፖርቱ፤ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥም በአደጋው 130ሺ ያህል ሰዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን አስታውቋል፡፡
በአፋር ክልል 40ሺህ 731፣ በሶማሌ 20ሺህ 868፣ በኦሮሚያ በወለጋ በመሬት መንሸራተት የተፈናቀሉትን 141 ሰዎች ወይም 1.125፣ በደቡብ 25ሺህ 703 እንዲሁም በጋምቤላ 11ሺህ 749 ሰዎች መፈናቀላቸውን ሪፖርት አትቷል፡፡
በምዕራብ ኢትዮጵያ ጐርፍ ክፉኛ ያጠቃቸው አካባቢዎች የጋምቤላ ቆላማ አካባቢዎች፣ ምስራቅ ወለጋ ሲሆኑ በምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል ሶማሌ ክልል ደግሞ 26 ወረዳዎች ላይ ጐርፍ ተከስቶ ሰዎች ተፈናቅለዋል - ብሏል ሪፖርቱ፡፡  ከሁሉም አካባቢዎች የከፋ እንደሆነ የተነገረለት በአፋር ክልል ያጋጠመውና ከ40ሺ በላይ ሰዎችን ያፈናቀለው የጐርፍ አደጋ በ13 ወረዳዎች ላይ መከሰቱን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በደቡብ ደግሞ በዳውሮ፣ ጐፋ፣ ጉራጌ፣ ሃዲያ፣ ከፋ፣ ስልጤና ደቡብ ኦሞ ወረዳዎች ላይ ከፍተኛ ጐርፍ መከሰቱ ተመልክቷል፡፡
በአጠቃላይ ክረምቱ ተጠናክሮ ከገባበት የሐምሌ ወር ጀምሮ በጐርፍ አደጋ 151ሺህ 828 ዜጐች መጠቃታቸውን ያወሳው ሪፖርቱ፤ የጐርፍ ተጠቂዎች በትኩረት ተገቢውን ድጋፍ እንዲያገኙ አሳስቧል፡፡
ከዚህ በኋላም የክረምቱ ሁኔታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና የጐርፍ አደጋውም በነሐሴ አጋማሽና መጨረሻ ላይ የከፋ ሊሆን እንደሚችል የተጠቆመ ሲሆን ይሄን ተከትሎም 2 ሚሊዮን 66 ሺህ ህዝብ ለአደጋ እንደሚጋለጥ ተገምቷል፡፡
ባለፉት ሳምንታት በጋምቤላ በተከሰተው ጐርፍ በ1ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተዘራ ሰብል ሙሉ ለሙሉ መውደሙ የተነገረ ሲሆን በአፋርና በሶማሌ ክልል ደግሞ በሺህ የሚቆጠሩ የቤት እንስሳትን መግደሉ ታውቋል፡፡  

Read 864 times