Error
  • The RokSprocket Module needs the RokSprocket Component enabled.
Saturday, 21 July 2012 10:11

“እግዚአብሔር አለ …ካለስ ምን እየሰራ ነው… !?”

Written by  ፍቅር ለይኩን
Rate this item
(0 votes)

Love is the Answer no matter what the question! ለየትኛውም፣ ለማንኛውም ጥያቄዎቻችን ፍቅር መልስ ነው!

አፄ ቴዎድሮስ ብዙ ከተባለለትና ከተጻፈለት አፍሪካዊው ናፖሊዮን ካሰኛቸው ከጀግንነታቸው፣ ከጭካኔያቸው፣ ከፍርድ አዋቂነታቸውና ኢትዮጵያን ለማዘመን ከነበራቸው ታላቅ ራእይ ባሻገር በተለያዩ ጊዜያት ስለ ፈጣሪ ህልውና ከቤተ ክህነቱ ተጠሪዎች ነን ባዮች ደብተራዎችና ካሕናት ጋር ያደረጓቸው እንደ አንዳንድ የዋኃን አገላለጽ ‹‹ፈጣሪን መፈታተን›› ዓይነት ጥያቄዎችን እያነሱ ካሕናቱንና የቤተ ክርስቲያኒቱን ሊቃውንቶች በጥያቄ በማጣደፍ ያስጨንቁ ነበር ይባላል፡፡ እናም በአንድ ወቅት አፄ ቴዎድሮስ በዙፋናቸው በተሰየሙበት ግብር ገብቶ መኳንንቱና መሳፍንቱ፣ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንቱና ካሕናት በታደሙበት ግብዣ ላይ ንጉሡ አንድ ጥያቄ አነሱ እንዲህ ሲሉ፡-‹‹ለመሆኑ እግዚአብሔር አለ… ካለስ ምን እየሰራ ነው…!? በማለት ጥያቄያቸውን ወርወር አድርገው የሊቃውንቱንና የካሕናቱን መልሳቸውን ለመስማት ጓጉተው መይሳው ካሳ ከዙፋናቸው ላይ ተመቻቹ፡፡

ሊቃውንቱና ካሕናቱ ሁሉ የመሰላቸውንና የንጉሥን ልብ ያሳርፋል ያሉትን መልስ ሁሉ ወደ አፄ ቴዎድሮስ መወርወር ጀመሩ፤ ይሁን እንጂ ከእነዚህ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ነን ከሚሉ ሊቃውንትና ካሕናት ዘንድ ንጉሡ ቴዎድሮስ ልባቸውን የሚያሳርፍ በቂ ምላሽ አላገኙም፡፡ እናም በቁጣ ሆነው ሊቃውንቱንና ካሕናቱን በመገላመጥ ከግብር ቤቱ በራፍ ላይ ደበሎውን ለብሶ አኩፋዳውን ይዞ ከንጉሥ ገበታ የሚተራርፈውን እንጀራ የሚጠብቀውን አንድ ምስኪን የቆሎ ተማሪ ወደ ዙፋናቸው አስጠርተው ተሜ፡- ‹‹እግዚአብሔር አለን… ካለስ ለመሆኑ ምን እየሰራ ነው…!? አሉት፡፡

 

ተሜም ለጥ ብሎ እጅ ከነሳ በኋላ ‹‹ንጉሥ ሆይ ሺህ ዓመት ይንገሱ! እግዚአብሔር መንግሥትዎን  ያስፋ፣ ጠላትዎን ያጥፋ! ጃንሆይ እግዚአብሔርማ እንዴታ አለ እንጂ…! የቀን ተሌት ሥራውም ለእያንዳንዳችን መልካም ሆነ ክፉ ስራችን ምላሽ/ብድር ሰፍሮ የሚመልስበትን ቁና ሲሰፋ ይውላል!›› በማለት መለሰ፡፡ ንጉሥም በተሜ መልስ እጅግ ተደንቀው “ትክክል ብለሃል” በማለት ያን ተማሪ እንደመረቁትና እንደሸለሙት በአፈ ታሪክ ይነገራል፡፡ እግዚአብሔር አለ… ካለስ ምን እየሰራ ነው!? የሚሉ ጥልቅ የሆኑ በእግዚአብሔር ህልውና እና የእጆቹ ሥራዎች ላይ የሚያሟግቱ ፍልስፍናዊ ጥያቄዎች ትናንት ተጠይቀዋል፣ ዛሬም  የጠይቃሉ፣ ምናልባት ወደፊትም እስከ ፍጻሜ ዓለም ይኸው ጥያቄ ይቀጥል ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ፤ በዚህ ምድር ላይ እንደ ሰው ያለ ነፍሱ በጥያቄ መአት የተሞላች ጠያቂና አዋቂ ፍጥረት የለምና!!

ዶ/ር ፈቃደ የተባሉ ፀሃፊ፤ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ‹‹ድምፂቱ›› በሚል ርዕስ ስለ ህላዌ እግዚአብሔር ወይም መኖር በውስጣችን በለሆሳስ ስለምትደመጠው የኅሊና ጩኸትና ‹‹እንዴት እንመን…›› ለሚሉና በጥያቄ ማእበል ነፍሳቸው እየተናወጠች ላሉ ሰዎች በፈጣሪ ስለማመን ያቀረቡትን ጠንካራ የመከራከሪያ አሳብ በተመስጦ ካነበብኩ በኋላ፣ ለመሆኑ በታሪክ ውስጥ የሰው ልጆች የፈጣሪን ህልውና/መኖር ለመጠራጠር እንዲገደዱ የሚያደርጋቸው ምክንያቱ ምን ይሆን በማለት ራሴን ለመጠየቅ ተገደድሁ፡፡ ለዚህ የሰው ልጆች የዘመናት ጥያቄ/እንቆቅልሽ ምላሽ ለማግኘት ሁሌም ከአጠገቤ ከማይለየውና የሕይወቴ መመሪያ የሆነውን ከታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ ከዚሁ መጽሐፍ የቃረምኩትን እውቀት ከአእምሮዬ ጓዳ ለመፈተሽና ለማገላበጥ ሞከርኩ፡፡

እናም ከአዳም ውድቀት በኋላ እሾህና አሜክላ ታብቅል ተብላ በተረገመች ምድር ላይ የሰውን ልጅ የትንቅንቅ፣ የመከራና የሰቆቃ ሕይወት ለአፍታ ለመቃኘት ሞከርኩ፣ ለመሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደ እኛው ንጉሥ አፄ ቴዎድሮስ ‹‹እግዚአብሔር አለ … ካለስ ምን እየሰራ ነው?!›› በማለት የጠየቁ ሰዎች ወይም ሕዝቦች ነበሩ ይሆን? ከነበሩስ እንዲህ ዓይነቱን በፈጣሪ ህልውና ላይ የሚገዳደር ጥያቄ እንዲያጭሩና ባስ ሲል ደግሞ እንደ ጀርመናዊው ፈላሳፋ ኒቼ ‹‹God is Dead!›› ወይም ‹‹እግዚአብሔር የለም፣ ሞቷል!›› የሚል አብዮት በእግዚአብሔር ህልውና እና በአማኞቹ ልብ ላይ እንዲያፋፍሙ ምክንያቱ/ምክንያታቸው ምን ነበር!? በሚል የግሌን አስተያየት በዚህ በፈጣሪ ህልውና እና በእርሱ ስለ ማመን ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ውይይት ከከፈቱ ወገኖቼና አንባቢያን ጋር ለመካፈል ወደድሁ፡፡

በእግዚአብሔር ህልውና እና ታላላቅ በሆኑ የእጅዎቹ ሥራዎች ላይ በተደጋጋሚ ጥያቄ በማንሳት በጥርጣሬና ባለማመን ታሪካቸውን ካደመቁና ካዥጎረጎሩ ከሕዝበ እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ሕዝብ ቀደምት ታሪክ ጥቂት ቁም ነገሮችን በመጥቀስ አሳቤን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ በእግዚአብሔር አስደናቂ ተአምራት፣ በጸናች እጁና በተዘረጋች ክንዱ ከ430 ዓመታት መራርና እንደ መርግ ከከበደ ከግብጽ የባርነት ሕይወት ነጻ የወጡ እስራኤላውያን፤ ቀይ ባሕርን ከፍሎ በማሻገር ጠላቶቻቸውን ፈርኦንና ሠራዊቱን ዓይናቸው እያየ በባሕረ ኤርትራ ሲሰጥም ያዩ ሕዝቦች፣ ለዚህም ታላቅ ተአምርና የያሕዌን “ማዳን” ንሴብሆ! ብለው የዘመሩ ሕዝቦች መሪያቸውና ነቢያቸው ሙሴ፤ ከአምላኩና/ከአምላካቸው ጋር ለመነጋገር ሲና ተራራ ወጥቶ ለአርባ ቀን የቆየበት ጊዜ ከግብጽ የ430 ዓመታት የባርነት፣ የግዞት ዘመን በእጅጉ ረዝሞባቸው፣ አታክቶአቸውና አበሳጭቶአቸው፡-

‹‹…ይህ ሙሴ ምን እንደሆነ፣ ምን እንደገጠመው አናውቅምና በፊታችን የሚሄዱ አማልክትን ስራልን›› ሲሉ አሮንን መውጫ መግቢያ፣ መቆሚያ መቀመጫ አሳጡት፡፡ የወገኖቹ ጥያቄ ፋታ ያሳጣውና ነፍሱን ያስጨነቀው አሮንም የወርቅ ጌጦቻቸውን እንዲያመጡ ካዘዛቸው በኋላ እንደ ምኞታቸው በፊታቸው የሚሄድ የጥጃ አማልክትን ሰራላቸው፡፡ እነርሱም ከግብጽ ያወጣን አምላክ በማለት በገዛ ሀብታቸውና በእጆቻቸው ስራዎች በተሰሩ ጌጦቻቸው በተሰራ የጥጃ ምስል ፊት እየበሉ፣ እየጠጡ፣ እየዘፈኑ፡- ‹‹ክብር ይገባሃል፣ ከጠላቶቻችን እጅ ነጻ ያወጣኸን አምላካችን…!›› በማለት ለወርቁ የጥጃ ምስል የአምልኮና ስርዓተ ስግደት ላይ ተጠምደው ባሉበት፣ ሙሴ ከፈጣሪ ጋር የቆየበትን አርባ ቀንና ሌሊት ጨርሶ አስርቱ ትእዛዛት በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈባቸውን የቃል ኪዳኑን ጽላት ይዞ ወደ ወገኖቹ ሲመጣ ሕዝቡ በባእድ አምልኮ ተጠምዶ አያቸው፡፡ ሙሴም ዓይኑ የሚያየውን አምኖ ለመቀበል ወኔው ከዳው፣ መንፈሱም ተበሳጨበት… እናም ከአምላኩ ያሕዌ እጅ የተቀበለውን ሁለቱን ጽላቶች ለአምላኩ ቀንቶና በንዴት ጦፎ ከመሬት ላይ ከሰከሰው፣ ጽላቱም ተሰባብሮ ዶግ አመድ ሆነ፡፡

በዚህም ገና ከባርነት ማግስት ከፈጣሪ ጋር ግብግብ የገጠሙ እስራኤላውያን በፈጣሪ ህልውና፣ ታላላቅ የእጆቹ ሥራዎችና ተአምራቶቹ ላይ እንደተጠራጠሩና እንዳመጹ ነው መላው ዘመናቸውን ያሳለፉት፡፡  እስራኤላውያን ከፈጣሪ ጋር ፊት ለፊት ሙግት የገጠሙ፣ ህልውናውንና ስራውን የተገዳደሩ አንገተ ደንዳና፣ እልኸኛ፣ የአለት ልብ ያላቸው፣ ሕዝቦች መሆናቸው በመጽሐፍ በግልጽ የተነገረላቸው ሕዝቦች ናቸው፡፡ የአርባ ቀኑ ጉዞ አርባ ዓመት እንዲፈጅባቸው የሆነውም በዚሁ የእግዚአብሔርን ሥራ ለማመን የዘገየ ልብ ያላቸው በጥርጣሬ ማእበል ውስጥ የሚዋዥቁ ሕዝቦች በመሆናቸው ነው፡፡ እስራኤላውያን በአርባ ዓመት የምድረበዳ ጉዞአቸው እግዚአብሔርንና አገልጋዩን ሙሴን በእጅጉ የተፈታተኑና ያስመረሩ አመጸኛ ሕዝቦች እንደነበሩ የብሉይ መጻሕፍት በግልጽ ያስነብቡናል፡፡

ለእስራኤላውያን በእርግጥ ሙሴ ታላቅ፣ ሊገዙለትና ሊታዘዙለት የሚገባ መሪ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሙሴ የሚመራው ሕዝብ አመጸኛ፣ ገልበጥባጣና ነውጠኛ ሕዝብ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ሙሴን፡- ‹‹ይህን እንደ ቀስት የሚገለባበጥ ጠማማ፣ አመጸኛና ሸንጋይ ሕዝብ ከምድረ ገጽ አጥፍቼ አንተን ለሌላ ታላቅ ሕዝብ እሾማሃለሁ፡፡›› ባለው ጊዜ እንኳን ‹‹ይህን ሕዝብ በምድረ በዳ አጥፍተህ የአሕዛብ መሳለቂያ ከምታደርገን እኔን ከሕይወት መጽሐፍ ደምስሰኝ!›› ያለ የፍቅር ጀግና፣ ትሑትና የእግዚአብሔር ሰው ነበር፡፡ የሚመራውን ሕዝብ ከራሱ በላይ አስበልጦ የሚወድ፣ ትሕትና የሞላበት እጅግ ትሑትና የፍቅር ሰው ነበር ሙሴ፡፡ ግና ትሑቱና የዋሁ ሙሴ ብዙ ዋጋ የከፈለላትንና የናፈቃትን የተስፋይቱን ምድር በሩቅ ከመሳለም ባለፈ ለማየት አልታደለም፤ አጥብቆ ፈጣሪውን ቢማጸንም አልሆነም፡፡ የገዛ ሕዝቡና ወገኑ አምላኩን በተፈታተነበት ግብዝ ጥያቄ ተሰነካክሎ፣ ሙሴ ቅዱሱን የያሕዌን ስም ባለመቀደሱ ምክንያት ከተስፋይቱ ምድር እንዲጎድል ሆነ፡፡ ሙሴ ብቻ ሳይሆን ከግብጽ ባርነት ከወጡት ስድስት መቶ ሺህ ከሚሆኑ ሕዝቦች መካከልም የተስፋይቱን ምድር በዓይናቸው ለማየት፣ በእግራቸው ለመርገጥ ዕድሉን ያገኙት ሁለት ሰዎች ብቻ ነበሩ፡፡ አይደንቅም አዎን ከ600ሺ ሕዝብ ሁለቱ ኢያሱና ካሌብ ብቻ፡፡ ሌሎቹና የሚበዙት ባለማመንና ባለመታዘዝ ጠንቅ በበረሃ በድናቸው የአሸዋ ሲሳይ ሆኖ ነው የቀረው፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ እነዚህ የእግዚአብሔር ሕዝቦች እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ህልውና፣ በእጆቹ ሥራዎቹና በታላላቅ ተዓምራቶቹ ላይ በነበራቸው ተለዋዋጭ አቋም፣ ጥርጣሬና ያለማመን የተነሳ፣ በኃጢአታቸውና ባለመታዘዛቸው ጠንቅ ምክንያት፣ በጠላቶቻቸው ፊት ሲሸነፉና ሲዋረዱ ለምርኮና ለግዞት ሲዳረጉ ቆም ብለው ይህ በአባቶቻችን የተነገረለት፡- ‹‹ባሕር ከፍሎ፣ ጠላቶቻችንን አዋርዶ፣ ጠል ዘርግቶ፣ መና አውርዶ፣ ደመና ጋርዶ፣ ጸሐይን አቁሞ፣ እሳት አዝንቦ …ወዘተ ሕዝቡን ነጻ አወጣ፣ ሕዝቡን አዳነ…! ተብሎ የተነገረለት የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ወዴት አለ…!?›› በሚል በአባቶቻቸው የተነገረለት ተአምረኛው እግዚአብሔር አድራሻው የት እንደሆነና ምንስ እየሰራ እንዳለ ደጋግመው የጠየቁበትን ታሪካቸውን ከመጽሐፍ ቅዱስ እናነባለን፡፡ እነዚህ ሕዝቦች በፈጣሪ ህልውና እና ሥራዎቹ ላይ ባለመተማመናቸውም ፊታቸውን ወደ ጣዖታት ዞር ያደረጉበትንና አምላካቸውን ያሕዌን ያስቀኑበትን (አበው እግዚአብሔር በመለኮቱ፣ ንጉሥ በመንግሥቱ፣ ጎልማሳ በሚስቱ ቀናተኛ ናቸው! እንዲሉ) ታሪካቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብዛት ተጠቅሷል፡፡

ከዚሁ ከእስራኤላውያን ታሪክ ሳንወጣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የፈጣሪን ህልውና ከመካድ ባለፈ እንዲህ ዓይነቱን እግዚአብሔር ከሆነ አምላክ ብለን ስናመልክና ስንገዛለት የኖርነው በእውነት ተሳስተናል እናም ይህን ‹‹እግዚአብሔርን ስደበውና ሙት›› በማለት በምሬትና በብስጭት የስንፍና ንግግርን የተናገረች የአንዲት ሴትን ታሪክ እናገኛለን፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እጅግ ቅን፣ ጻድቅ፣ እግዚአብሔርን የሚፈራ ተብሎ የተነገረለት ኢዮብ የተባለ ሰው ነበር፡፡ ይህ ሰው እጅግ ተመችቶት በሀብትና በዝና ዙፋን ላይ ተንደላቆ፣ ከቤተሰቡና ከወገኑ ጋር እጅግ ደስ ብሎት የሚኖር ሰው ነበር፡፡ ግና ይህ በሀብትና በዝና ምንጣፍ ላይ ሲራመድና ሲንቀባረር የነበረ፣ በእግዚአብሔር አንደበት ‹‹ጻድቅና ቅን!›› ተብሎ የተመሰከረለት ሰው ፤ በአንድ ጀምበር ሀብት ንብረቱን፣ ቤተሰቡንና ጤናውን አጣ፡፡ በአንድ ጊዜ ሰማይ ምድሩ ተደፋበት፡፡ የልጆቹ እልቂት የሀብት ንብረቱ መውደም፣ ከራስ ጠጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ በቁስል ንዳድ በመመታት በትል መወረሱ፣ በመርዶ ላይ መርዶ፣ በሐዘን ላይ ሐዘን የተከታተለበት ኢዮብ ፤ በታላቅ ድምጽ ጮኾ አለቀሰ፤ ከክብር ሰገነቱ ወርዶ በአመድ ላይ ተቀምጦ፣ በራሱ ላይ ትቢያን ነስንሶ፣ የተወለደበትን ቀን በምሬት እንደረገመ ታሪኩ ሰፋ ተደርጎ ተጽፎለታል፡፡

ጻድቅ ኢዮብ የመከራውና የዚህ ሁሉ መከራ ውርጅብኝ መንስዔ ምን እንደሆነ ለማወቅ ብዙ ጣረ፣ ደከመም፡፡ ምነው ቃሌ በአለት ላይ ቢጻፍ ብሎም ተመኘ፣ እንደውም ምናለ በእኔና በአምላክ ፊት የሚቆምና ክርክራችን የሚዳኝ ዳኛ በተገኘ ሲልም ተማጸነ፡፡ ኢዮብ አንቱ በተባለበት ምድር የከበሬታ ስፍራ ያገኘን ንግግር አዋቂን፣ ፍርድንና ፍትህን ለማድረግ የሚሟገት፣ ሰው መልካሙን ስጠብቅ ክፉን አገኘሁ፤ በእውን ድሀኃውን ገፍቼ፣ ፍርድ አጉድዬ ነበር እንዴ፣ ለችግረኛውና ለምስኪኑስ አባትና ጠበቃ አልነበርኩ በማለት ተሟገተ፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ደግሞ የአካሉ ክፋይ ረዳቱ የምትሆነው ይህን በቃላት ሊገለጽ የማይችል የመከራ ዶፍና ውርጅብኝ የታዘበችው ሚስቱ፤ የአካሉ ክፋይ እንዲህ አለችው፡- ‹‹አሁንም በታማኝነትህ እንደጸናህ ነውን… እግዚአብሔርን ስደብና ሙት!›› ስትል ልብን በሌላ የሐዘን ሰይፍ የሚመትር፣ አጥንቱ ድረስ ዘልቆ ነፍሱን የበረበረ ንግግር ተናግራው፣ ከእንግዲህ አልተገናኘንም በማለት እንደ ዋዛ በዛ የመከራና የጭንቅ ቀውጢ ዘመን ጥላው እብስ አለች፡፡

ኢዮብን ለማጽናናት ከሩቅ የመጡ ወዳጆቹም መጽናኛ ቃል ሳይሆን በቁስሉ ላይ ጥዝጣዜን የሚጨምር የምላስ ጅራፋቸውንና የቃላት ውርጅብኛቸውን በየተራ እየተቀባበሉ ያወርዱበት ጀመር፡፡ አንድ የሰራኸው ኃጢአትና በደል ቢኖር እንጂ መከራ እንዲሁ ከሰማይ አይወርድም ሲሉ በሐዘን የደከመችና ተስፋ የቆረጠች ነፍሱን በእጅጉ አጎሳቆሏት፣ አሳቀቋትም፡፡ ኢዮብ ግን በዚህ ሁሉ ስቃይ፣ መከራና ሰቆቃ ውስጥ ሆኖ ብሞትም እንኳን እርሱን እጠብቃለሁ ሲል ለነፍሱ ተናገራት፡፡ በታላቅ የጥያቄና የእንቆቅልሽ ማእበል ውስጥ ነፍሱ ከወዲህና ከወዲያ እየተላጋችም ቢሆን ኢዮብ በታማኝነቱ ጸና፡፡ ኢዮብ ምንም ‹‹ጻድቅና ቅን›› ተብሎ በአምላኩ የተመሰከረለት ሰው ቢሆንም ‹‹እግዚአብሔር የት ነህ ያለኸው?›› ሲል በምሬት ጠይቋል፡፡ የኢዮብን ጥያቄ እግዚአብሔር በጥያቄ ነበር የመለሰለት፤ እናም በስተመጨረሻ ኢዮብ ያለው ነገር ቢኖር ‹‹እጄን በአፌ ላይ እጭናለሁ፤ ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ እንደሆንክ አሳብህንም የሚከለክለው እንደሌለ አውቅሁ፡፡›› በማለት በአምላኩ ፊት ተጸጸተ፡፡ በመከራው ፍጻሜ እግዚአብሔር በምሕረትና በበረከት እንደጎበኘው ይኸው የኢዮብ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡

ሰዎች በመከራቸው ዘመንና ለመልካም ውለታቸው ምላሹ ‹‹ወርቅ ላበደረ ጠጠር›› ሲሆንባቸውና ነፍሳቸው በጥያቄ ማእበል ስትመታ ‹‹እግዚአብሐር ወደየት አለ ካለስ ምን እየሰራ ነው?›› በማለት ይጠይቃሉ፡፡ በሀገራችንም እንዲህ ዓይነቱን ጥያቄ አፄ ቴዎድሮስ ብቻ ሳይሆኑ ሕዝባቸውንና ሀገራቸውን ወክለው ይህን ‹‹እግዚአብሔር አለን ካለስ? እንዲህና እንዲህ ሲሆን እርሱ የት ነው፣ ምንስ እያደረገ ነው?›› በማለት የጠየቁ ሰዎች ትናንት ነበሩ፣ ዛሬም ከጥንቱ እንደዚህ ዓይነት ጠያቂ ሰዎች በሀገራችን በእጥፍ በዝተው እንዳሉ ይሰማኛል፡፡ እንደሚታወቀው ሀገራችን ክርስትናንም ሆነ እስልምናን ከተቀበሉ የዓለም ሀገራት ግንባር ቀደም በመሆኗ በአብዛኛው ሕዝቦቿም ሃይማኖተኛ ናቸው ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም፡፡ ስለሆነም ብዙ ታሪካችን ከፈጣሪ ምሕረትና መዓት ጋር የተያያዘ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

በ1930ዎቹ ሀገራችን ኢትዮጵያ በፋሽስት ጣሊያን በተወረረችበት ዘመን የጣሊያን ጦር ያሰማራቸውን የጦር አውሮፕላን የታዘበ የሀገሬ ሰው፤ እነዛ በሰማይ ላይ እየተምዘገዘጉ የእሳት አሎሎ በሚተፉና የመርዝ ጭስ እየረጩ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሕጻን፣ ወጣት፣ አረጋዊ ሳይል እጅግ በሚዘገንን ሁኔታ እንደ መኸር እህል እያጨደ የከመረውን ሞትን በሚተፉ እንግዳ ፍጡሮች ግራ በመጋባቱና እነዚህ አውሮፕላኖች በሕዝባችን ላይ እንደ መአት ያፈሰሱትን የመከራ ውርጅብኝ የተመለከቱ አንዲት የሸዋ መነኩሴ በሀላዌ እግዚአብሔር/በፈጣሪ መኖር ላይ ጥርጣሬ ያጫረባቸውንና ይህ ሁሉ ሲሆን እግዚአብሔር ዝም ብሎ ያያልን በሚል የሀገራቸውን መጥፎ የታሪክ ክስተትና እልቂት በቅኔያቸው እንዲህ በማለት ፈጣሪን ሞግተውት ነበር፡-

የለህም እንዳልል ይመሻል ይነጋል፣

አለህም እንዳልል እንዲህ ይደረጋል፡፡

አምላክ ለአንተው ፍራ፣

በቤትህ አግድመት ጎዳና ተሠራ፡፡ በማለት እነዚህ በሰማይ የሚምዘገዘጉ የፋሽስት ጣሊያን የሞት አበጋዞች፣ በእውነት ካለህ የአንተንም ህልውናን ጭምር እየተፈታተኑ እንደሆነ ተመልከት ሲሉ አሳስበዋል፡፡

በሀገራችን በተደጋጋሚ በተከሰቱ ጦርነቶች፣ ራብና ስደት ምክንያት ከጣእረ ሞት ጋር  ግብግብ የገጠሙ ወገኖቻችን፡- ‹‹እግዚአብሔር አለን? ካለስ ይህ ሁሉ መከራና ግፍ በምድር ላይ ሲሆን ምን ምላሽ አለው›› በማለት ፈጣሪን የሞገቱበት በርካታ ግጥሞችና ቅኔዎች በታሪካችን ውስጥ በሽበሽ ናቸው፡፡ ጠዋት ማታ አንተን የምትማጠን ኢትዮጵያንና ሕዝብህን እንዲህ ለአሰቃቂ ሞት፣ ለቅጥየለሽ መከራ የዳረግበህት ምክንያቱ ምንድን ነው በማለት ፈጣሪን የሚሞግቱ ዛሬም ድረስ በመቅደሱ አደባባይ አይጠፉም፡፡

እናም እነዚህ ወገኖች በእውነት የሚያይ የሚፈርድ አምላክ ቢኖርማ እንዲህ ዓይነቱን ግፍ አይቶ በዝምታ ሊያልፍ አይችልም በማለት በፈጣሪ ህልውና ላይ ትልቅ ጥርጣሬን የሚያጭር ‹‹በወይ ፍረድ ወይ ውረድ›› ስሜት ፈጣሪን የሚሞግቱና ‹‹በእውነት በዙፋንህ አለህን›› በማለት የሚከራከሩ በርካታ ወገኖች አሉ፡፡

በቅርቡ ‹‹ፍልስፍምና›› በሚል በታተመ በጋዜጠኛ ቴዎድሮስ መጽሐፍ ውስጥ ስለ ሃይማኖት እና ስለ ፈጣሪ በተነሱ እሳቤዎች ላይ መልስ ከሰጡ ምሁራን መካከል የፍልስፍናው ምሁር ዶ/ር ዳኛቸው፤ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እንደገለጹት በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ስለ እግዚአብሔር መኖር ጥርጣሬ ካስነሱ ምክንያቶች መካከል በምድራችን ላይ ስለነገሰው መከራና ግፍ፣ ምድሪቷን ባለቤት የሌላለት እስኪመስል የሰቆቃ፣ የእዬዬ፣ የእሮሮና የስቃይ ምድር ያደረጋትን አሰቃቂ ክስተት በተለያዩ ጊዜያት የተነሱ ፈላስፋዎችና የስነ መለኮት ምሁራን በመጥቀስ በእርግጥ የሰው ልጅ ሕይወትና ደኅንነት የሚገደው አምላክ ቢኖር እንዲህ አይሆንም በማለት፣ እግዚአብሔር በምድረቱ እጣ ፈንታም ሆነ በሰው ልጆች ሕይወት ታሪክ ውስጥ ምንም ድርሻ የሌለው፣ አንዳንዴም ጨካኝ እና ስሜት አልባ ተደርጎ እንዲሳል ሆኗል በማለት አብራርተዋል፡፡

እናስ እግዚአብሔር አለ ወይስ… ካለስ ይህ ሁሉ ክፋት፣ አመጻና ቀውስ ሲነግስ በንጹኃን ደም ምድሪቱ ስትጨቀይ ፍቅር ነው ተብሎ የተነገረለት ፈጣሪ እርሱ ምን እያደረገ ነው?

ምድራችን ስለተራበቸው ፍቅር፣ ምሕረትና ፍትህ እንዲሁም በሰው ልጆች መካከል ስለነገሰው መከራ፣ ዋይታና ሰቆቃ ነፍሳችን በእጅጉ እያነባች፣ በዚሁ ሁሉ ምስቅልቅልና ቀውስ ውስጥ እግዚአብሔር የት እንዳለና ምን እየሰራ እንደሆነ ግራ በመጋባት ፈጣሪን የምንጠይቅ ሰዎች ፤በኢዮብ ሕይወት እንደታየው እግዚአብሔር መልሶ እኛኑ ስለ ኃይሉ ፍጹምነት፣ ስለ ታላላቅ የእጆቹ ስራዎቹ፣ ስለማይመረመር ፍርዱና ምሕረቱ በመጠየቅ አፋችንን በመገረም አስይዞን ምንኛ ምስኪን መሆናችን በመግለጽ በፍቅር፣ በእምነት ኃይል፣ በማስተዋል ልቦና ስራውን በአንክሮ እንድናስተውል ይነግረናል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ፤እግዚአብሔር በሰው ልጆች ሕይወት ታሪክ ጉዞ ውስጥ በግለሰብ፣ በሀገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለሚያከናውናቸው ክስተቶች ብንጠይቅም ብንመራመርም ልንደርስብት ስለማንችለው የእውቀቱ፣ የጥበቡ፣ የማስተዋሉና የፍርዱ ነገር ሲናገር፡-

‹‹የእግዚአብሔርን ባለጠግነት ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፣ ፍርዱ የማይመረመር ነው፣ ለመንገዱም ፍለጋ የለውም፡፡

የጌታን ልብ ያወቀው ማን ነበር? ወይስ ብድራቱን ይመልስ ዘንድ ለእርሱ አስቀድሞ የሰጠው ማን ነው?» በማለት በአድናቆት ተናግሯል፡፡ የሁሉን ቻዩን የፈጣሪን አሰራር ወደማወቅ ፍጹም የከበረ እውቀት፣ ማስተዋልና ጥበብ ለመድረስና ለጥያቄዎቻችን ሁሉ ምላሽ ለማግኘት በፍቅር ሰረገላ መሳፈር እንዳለብንና በዚህ ፍቅር ውስጥም እምነታችንን ፍጹም ለማድረግ የሚያስችል ጸጋ፣ ኃይልና ብርታት እንዳለ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡

በዚህ ፍጹም ፍቅር ውስጥ ለጥያቄዎቻችን ሁሉ መልስ እንዳለና ወደ እግዚአብሔር ፍጹም እውቀት ጥበብና ማስተዋል የምንደርስበት ብቸኛ መንገድም ፍቅር መሆኑንና እግዚአብሔር ራሱ በፍቅር ስለ ፍቅር እኛን ሆኖ ለሰው ልጆች ሁሉ ፍቅሩን ገልጧል፡፡

ክርስትናም የዚሁ የፈጣሪ ፍጹም ፍቅር፡- ውበት፣ ኃይልና ጸጋ የሚገለጽበት ሕይወት ነው!

‹‹Love is the Answer no matter what the question!›› ለማንኛውም ሆነ ለየትኛውም ጥያቄዎቻችን ፍቅር ምላሽ ነው! ፍቅር ደግሞ ፈጣሪ ነው! መጽሐፍም እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር፡፡ እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፡፡ ከእነዚህም የሚበልጠው ግን ፍቅር ነው እንዲል፡፡ ስለዚህም በፍቅር ውስጥ ለሁሉም ጥያቄዎቻችን መልስ፣ ለሕይወት እንቆቅልሽም ነፍስንና መንፈስን የሚያሳርፍ ፍቺ አለ፡፡

ሰላም! ሻሎም!

 

 

Read 2575 times Last modified on Saturday, 21 July 2012 10:21