Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 21 July 2012 10:04

የትኛዋን ድምፅ?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው ሳምንት በወጣው አዲስ አድማስ እትም ላይ ዶ/ር በፍቃዱ አባይ የተባሉ ግለሰብ የፃፉትን ጽሑፍ በጥሞና አነበብኩት፡፡ ፀሐፊው ከዚህ ቀደም ከተለያዩ ፀሐፍት በተለይም ከሌሊሳ ግርማ ጋር በዚሁ ጋዜጣ ላይ ፍልስፍናን እና እምነትን አስመልክቶ ያደረጉትን ለረዥም ጊዜ የዘለቀ ሙግት በትኩረት እና በፍላጐት እንደመከታተሌ መጠን ለጽሑፋቸው ከቶም እንግዳ አይደለሁም፡፡ ከረዥም እረፍት በኋላ ሰሞኑን ደግሞ ብቅ ብቅ ማለት መጀመራቸውንም አስተውያለሁ፡፡ የሰሞኑ ጽሑፎቻቸው ግን ከነዚያ ጥቂት ፀሐፍት ጋር ያደረጉዋቸውን ፍልሚያዎች በድል ያጠናቀቁ እና ፍልስፍና እና የፍልስፍና ጀሌዎችን አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት መቀመቅ የከተቱ የእምነት አርበኛ (defender of faith) አድርገው ራሳቸውን የሾሙ፤ አስመስሏቸዋል፡፡

እኔ እስከማውቀው ድረስ በሌሊሳ እና በእርሳቸው መካከል የነበረው የጋራ ሙግት የተቋጨው ለሁለቱም “ዱባ እና ቅል አበቃቀሉ ለየቅል” ሆኖባቸው የእርሳቸው “ሃሌ ሉያ” እና የሌሊሳ “ኢዮሪካ” ሳይጣጣም ቀርቶ ለመግባባት ስለተቸገሩ እንጂ በማንም ድል አልያም ሽንፈት አልነበረም፡፡ መቼም ሰው ልቡናው የተረጐመለትን ብቻ ነው እና   የሚቀበለው ምናልባት ይህን የቋንቋ መደበላለቅ እና አለመግባባት የቋጨውን ክርክር በድል ተወጣሁት ብለው አስበው እንደሆነ ቆም ብለው ራሳቸውን ቢጠይቁ መልካም ነው፡፡ አለበለዚያ ለኖቤል ሽልማት እንዳይታጩ ያሰጋል!

ዶክተሩ ባለፈው ሳምንት የወጣውን “ድምፂቱን” የፃፉት “ለእነ…እንዴት እንመኖች” እንደሆነ በአርዕስታቸው ጮክ ብለው ተናግረዋል፡፡ እነ…እንዴት እንመኖች እነማን እንደሆኑ ሲያብራሩም ከሀድያኖች (atheists) እና ኢ-ዐዋቂዎች (agnostics) እንደሆኑ ነግረውናል፡፡ ዶክተሩ ለኢ-አማንያን ያላቸውን ጭፍን ጥላቻ ከሚያስነቁባቸው ብዙ ነገሮቻቸው አንዱ ኤቲስት (atheists) ለሚለው ቃል ትክክለኛ አቻ ቃል ኢ-አማኒ ሆኖ ሳለ እርሳቸው ግን አዘውትረው የሚጠቀሙበት ከአውዱ ውጪ አሉታዊ ትርጓሜ ያለውን እና በተለምዶ እምነቱን ወይንም ሃይማኖቱን በመካድ ሌላ እምነት ለተቀበለ ሰው የሚሰጠውን የስድብ ቃና (tone) ያዘለ “ከሃዲ” (apostate) የሚለውን ስያሜ መሆኑን ልብ ስንል ነው፡፡ ለጊዜው አንድን ሰው ከያዘው አመለካከት የተነሳ ስብዕናውን እና ባህርይውን በሚያጥላላ እና በሚያጠለሽ ቅጽል መጥራት ተገቢ መሆን አለመሆኑን ለህሊና ፍርድ ትተነው ወደ ጉዳያችን እንመለስ፡፡

ዶክተሩ በመግቢያቸው ላይ የሰው ልጅን ለዘመናት ስለተፈታተኑት ጥያቄዎች ሰፋ ያለ ገለጻ ካደረጉ በኋላ በተቀረው ክፍል ለእነ “እንዴት እንመኖች” የፍልስፍናን፣ የሳይንስን እና የኪነጥበብን ኮሳሳነት እና “ቁንጫነት”፤ በተቃራኒው ደግሞ የእምነትን ጡንቻማነት እና ፍርጣሜ ለማሳየት ተግተዋል፡፡ ታድያ ያንን ሁሉ ትጋት ባሳዩበት “ሽንጠ - ረዥም” ጽሑፋቸው ውስጥ ሶስት ደካማ ማስረጃዎችን ብቻ ሊያውም እንደነገሩ ወተፍተፍ ማድረጋቸውን ስናስተውል ከመገረምም አልፈን ማፈራችን አይቀርም፡፡ ነገሬን ያሳምሩልኛል፤ እውነቴን ይመሰክሩልኛል ብለው ያቀረቧቸው ማስረጃዎችም በግርድፉ ይህን ይመስላሉ፤

የህይወት እና የሞት ምስጢር አሁንም ድረስ ለአብዛኛው ሰው እንቆቅልሽ መሆኑ፤

ይህን ምስጢር ለመፍታት አቅም አለን የሚሉ ጥቂቶች መሆናቸው፤

በእነዚህ ጥቂት መላሾች መካከልም የሃሳብ እና የአመለካከት ልዩነት መኖሩ

እንደ እውነቱ ከሆነ ከላይ ያሉት ሁለቱ ማስረጃዎች ፍልስፍና፣ ሳይንስ እና ኪነጥበብ ሃይማኖታዊ ወይንም አጉል እምነታዊ (Superstitious) መሠረት ያላቸውን ስለ ህይወት እና ስለሞት ሲሰጡ የኖሩት ልማዳዊ መልሶች ብቻ ሳይሆን ጥያቄዎቹም ላይ ያሳደሩትን ከባድ ተጽእኖ ሸምጥጦ ለመካድ፣ ያም ካልተቻለ ለማንኳሰስ ከማለም ባለፈ አንዳችም ረብ ያላቸው እንዳልሆኑ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ እንደ እኔ አመለካከት እውነትን ለሰው ለማሳወቅ ተነስቻለሁ ያለ ሰው በመጀመሪያ እርሱ ራሱ እውነትን ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን ማሳየት አለበት፡፡ አንድ አማኝ የፍልስፍናን እና የሳይንስን ግዙፍ ተጽእኖ ማመንን የሽንፈት ጽዋ እንደመጨለጥ ሊቆጥረው አይገባም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ በዘመን መጨረሻ ላይ የሚያምን “አንድ” ሰው ይኖር እንደሆነ አስቦ መገረሙን ማስታወስ ይገባል፡፡ አስገራሚው ነገር ግን ዶክተር በፍቃዱ ለአንደኛው ሀሳባቸው ማጠናከሪያነት ዋቢ የሚጠሩት ብዙኅኑን ሲሆን ለሁለተኛው ደግሞ አናሳነትን ለማጣጣያነት ተጠቅመዋል፡፡ መቼም ጠርዝ እና ደርዝ ባለው ክርክር ውስጥ የቁጥር መብዛትም ሆነ ማነስ የአንድን ሀሳብ እውነተኝነት ሊያረጋግጥ ወይም ሊያጣጥጥል እንደማይችል ለሳቸው እንደ አዲስ ለማስተማር ባልደፍርም አውቀው የዘነጉትን ሀቅ ግን ሳላስታውሳቸው ማለፍ አልፈልግም፡፡

የሶስተኛውን ማስረጃ ደካማነት ለማሳየት ደግሞ በቀላሉ ዶክተሩ ራሳቸው ወደሚከራከሩለት የአሐዳዊ አምላክ ንፅረተ አለም (theistic World View) ማዞር ብቻ ይበቃል፡፡ እርሳቸው በፈላስፎች፣ በሳይንቲስቶች እና በአርቲስቶች መካከል ያለውን የአስተሳሰብ ጐራ ልዩነት (School of thoughts) ነቅሰው በማውጣት የእነርሱን ውዳቂነት ለማጉላት ይጥራሉ፡፡ ነገር ግን በአማኞች መካከል ያለውስ የአስተሳሰብ ጐራ ልዩነትስ? ከዚያም ሲያልፍ ያለው መሰረታዊ የአስተምህሮ ተቃርኖስ? እንዴት ነው ነገሩ - ዶክተሩ ሆን ብለው መርሳት ይችላሉ እንዴ? ሎጂኩን እንኳ ብንተወው መጽሐፉስ የሚለው በአይንህ ውስጥ ያለውን ግንድ ሳታይ የሌላውን ጉድፍ አታንሳ አይደለም እንዴ ዶክተር? ለእምነት እየተከራከሩ ይህችን የመሰለች ግሩም ጥቅስ እንዴት ዘነጓት?

ዶክተር በፍቃዱ በእነዚህ ሶስት ደካማ ማስረጃዎች ፍልስፍናን እና ጓደኞቿን ቀጥቅጠው ከዘረሩ በኋላ በጽሑፋቸው መገባደጃ ላይ በድል አድራጊነት ስሜት እየተንጐራደዱ ለመሰናበቻ ስብከት ቢጤም ጣል አድርገዋል፡፡ ለነገሩ አለቦታው ተደነጐለ እንጂ ስብከቱስ መልካም ነበር፡፡

ነገር ግን የፍልስፍናን እና የጓደኞቿን ውሱንነት እና አቅመ ቢስነት እና የእምነትን ምሉዕነት እና አሸናፊነት ለማሳየት በተንደረደረ ጽሑፍ ውስጥ የራስን ሃይማኖት ስብከት ማጧጧፍ የአንባቢን አይን ለመሳብ ከሚደረግ ተልካሻ ሙከራ ከመሆን ባለፈ ምናልባት በቤተ ዕምነታቸው ምስባክ ተነፍገው ይሆን ብለን እንድናዝንላቸው የሚያደርግ ድርጊት ነው፡፡ እስቲ ከንፈር መጠጣውን ለጊዜው እናቆየውና በገዛ ሀሳባቸው ላይ ያለውን መፋለስ እናጢነው፡፡ ዶክተር በፍቃዱ የህይወት እና የሞት ሚስጥራት የምትገላልጠው “ድምፂቱ” ብቻ እንደሆነችና “ድምፂቱንም” የምንሰማት በእምነት አማካኝነት ብቻ እንደሆነ ነግረውናል፡፡ ጠያቂዋ ፍልስፍና ግን እሳቸው “ቀብሬሻለሁ” ቢሏትም መቃብር ፈንቅላ እየተነሳች አሁንም በጥያቄ ማጣደፏን አትተውም - እንዲህ እያለች - የትኛዋ ድምጽ? በእምነት ስም የሚሰሙ እልፍ ድምጾች በሞሉበት አለም የትኛዋ ድምጽ ነች ወደ ትክክለኛው አምላክ የምታደርሰው? ወይንስ ሁሉም ድምጾች ወደ አምላክ ያደርሳሉ? ከድምጾች መካከል ወደ አምላክ የምታደርስ አንድ ድምጽ አለች? ካለችስ በምን ተለይታ ትታወቃለች? ዶክተሩ ለእነዚህ ጥያቄዎች ሁሉንም የሚያሳምን ቅልብጭ ያለ መልስ መስጠት አይችሉም፡፡ ቢችሉ ኖሮ ያሳዩን ነበር፡፡ እኔ እሳቸውን መጠየቅ የምፈልገው እዚህ ላይ ነው፡፡ አንቺው ታመጪው አንቺው ታሮጪው እንዲሉ በቅጡ ማሳመን ካልቻሉ እና ጭፍን በሆነ ድንጋጌያዊ (Dogmatic) ስብከት ክርክርዎን የሚያሳርጉ ከሆነ ቀድሞውኑ ክርክሩን ለምን ጀመሩት? እንዲያ በማድረግዎ ምን እንደተከሰተ ያውቃሉ? ስለዚህም እኔንም እነ እንዴት እንመንንም አንድ ላይ አጡ፡፡ አይ ዶክተር!

 

 

Read 957 times Last modified on Saturday, 21 July 2012 10:11