Saturday, 21 July 2012 10:04

የእኛ ተማሪነት“ለተማሪ 100 አይሰጥም!”

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(0 votes)

“አረጀህ እንዴ?...ምነው ‘ዱሮ…ዱሮ’ ማለት አበዛህ?” አለኝ ስለ ያኔው የእኛ ተማሪነት የሚያትቱትን ያለፉት ሳምንታት ጽሑፎቼን ያነበበ አብሮ አደግ ወዳጄ፡፡ እውነቱን ሳይሆን አይቀርም፡፡ በ”መሬት ላራሹ” ደብተር የተማረ ሰው፣ የ”ፓልምቶፕ ኮምፒውተር” ዘመን ላይ ከደረሰ ማርጀቱ ይቀራል?...

እንግዲህ ምን ይደረግ ልጅ ተሁኖ አይቀር፡፡ ለነገሩ ገጣሚው እንዳለው እኔና አብሮ አደጌ “ልጅነት ተመልሶ አይመጣም” ብለን የምንቆጭ አይደለንም፡፡ ሃይሌ ሩትስ “እባክህ ተመለስ፣ ልጅነት በሞቴ…” ያለው ‘የሚናፈቅ ልጅነት’ ቢኖረው ነው፡፡ የእኔና የአብሮ አደጌ ልጅነት ግን ተመልሰው ሊያወሩት እንጂ ተመልሰው ሊኖሩት አያስመኝም፡፡

ወዳጄ ሆይ…እርግጥ ነው እያረጀን ነው፡፡ ያንን ፈታኝ ልጅነት፣ ያንን “ዘይገርም ተማሪነት” በፈጣሪ ፈቃድ አልፈን እዚህ የደረስን እኔና አንተ ማርጀታችንም መሞታችንም አይቀርም፡፡

እኔን የሚገርመኝ ማርጀቴም፣ መሞቴም አይደለም፡፡ ሞቴን ተከትሎ የሚነበበው የህይወት ታሪኬ እንጂ፡፡

“…አቶ አንተነህ ይግዛው እድሜው ለትምህርት እንደደረሰ ደብረ ማርቆስ ከተማ ውስጥ በሚገኘው ንጉስ ተክለሃይማኖት ት/ቤት እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምሯል…” ተብሎ የሚነበበውን ታሪኬን እያሰብኩ ይገርመኛል፡፡

እውነቴን እኮ ነው!... “…እድሜው ለትምህርት እንደደረሰ” ብሎ ነገር እኔንና ከእኔ ጋር የተማሩ አብሮ አደጐቼን አይመለከተንም፡፡

እኔም፣ ቻሌም፣ ጌትዬ የኋላም፣ ብርቱካን ከበደም… ሁላችንም ትምህርት የጀመርነው እድሜያችን ለትምህርት ሲደርስ አይደለም፡፡

እድሜያችን ለትምህርት እንደደረሰ አረጋግጦ አይደለም ትምህርት ቤቱ የአንደኛ ክፍል ተማሪ አድርጐ የመዘገበን፡፡

በእኛ ዘመን አንድ ልጅ የንጉስ ተክለሃይማኖት ት/ቤት መደበኛ ተማሪ መሆን የሚችለው ዕድሜው ለትምህርት መድረሱ ሳይሆን፣ እጁ ከጆሮው መድረሱ ሲረጋገጥ ነበር፡፡

የትምህርት ቤቱ አዳዲስ ተማሪዎች መዝጋቢ ባለሙያ (?) በተማሪነት ሊመዘገብ የሚመጣን ተማሪ “ንካ!” የማል መመሪያ ይሰጡታል፡፡ ይሄኔ የመማር ጉጉት ያደረበት ብላቴና እንደምንም ብሎ ነክቶ በተማሪነት ለመመዝገብ ይፍጨረጨራል፡፡

ግራ እጁን በአናቱ በኩል አዙሮ የቀኝ ጆሮውን የነካ፣ ወይም በተቃራኒው የግራ ጆሮውን በቀኝ እጁ የነካ…ከሁለት አንዱን ማድረግ የቻለ፣ የአንደኛ ክፍል ተማሪ ሆኖ ይመዘገባል፡፡ ያልቻለም “እጅህ ለጆሮ አልደረሰም…ዕድሜህ ለትምህርት አልደረሰም” ተብሎ ለቀጣዩ አዲስ አመት ቀጠሮ ይሰጠዋል፡፡

ስለዚህ…የህይወት ታሪኬን የሚጽፈው ሰው “…አንተነህ እድሜው ለትምህርት ሲደርስ…” ቢላችሁ እንዳታምኑት፡፡ ዕድሜዬ ሳይሆን እጄ ከጆሮዬ ሲደርስ ነው አንደኛ ክፍል የገባሁት፡፡

ሌላው ደግሞ ምን መሰላችሁ…ምንም እንኳን የግለሰቦች የህይወት ታሪኮች (በተለይ ከቀብር በኋላ የሚነበቡት) የሚፃፉበት ስልት ተመሳሳይ መሆኑን እያወቅሁ “ለእኔ አዲስ ስልት ይፈጠርልኝ” ለማለት ባልደፍርም ቅሬታዬን ግን ከወዲሁ (ከመሞቴ በፊት) ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

“…እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምሯል…” የሚለው ነገር ራሱ አይመቸኝም፡፡ ታሪኬን በሚያድበሰብስ “ጥቅል” አረፍተ ነገር፣ ክፍል መቁጠሬን ብቻ ጠቁሞ የማለፍ ግፍ እንደተሰራብኝ አድርጌ እቆጥረዋለሁ፡፡ እርግጥ የዛሬ ዘመን ተማሪነት ይሄን አቋሜን ስትሰማ “እስከ ስምንተኛ ክፍል መማር በአንተ ነው እንዴ የተጀመረው?...የምን ዲቴል ማብዛት ነው!” ብላ ሙድ ልትይዝብኝ ትችላለች፡፡

የደላት የዛሬ ዘመን ተማሪነት!...እሷ እኮ ሞቴን ሰምታ ለመቅበርና የህይወት ታሪኬን ለመስማት ጊዜ የላትም፡፡

“ለምን ‘እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምሯል’ በሚል ብቻ የተማሪነት ታሪኬ ተድበስብሶ አለፈ?” ብዬ መንገብገቤን የሰማች የዛሬ ተማሪነት “አካባጅ” ልትለኝ ትችላለች፡፡

ምክንያቱም በቴክስት ሜሴጅ “ሶሪ” ብላ ለቅሶ የምትደርስ የዛሬ ዘመን ተማሪነት፣ የእርሻ መምህር አጐት ሲሞቱ በነፍስ ወከፍ 25 ሳንቲም አዋጥታ፣ ቆሎና ጠላ ገዝታ መምህሯን ዕዝን የምትደርሰዋን የእኛን ተማሪነት አታውቃትም፡፡

የዛሬ ዘመን ተማሪነት “የእርሻ መምህር አጐት ሲሞቱ ተማሪዎቹ ሳንቲም አዋጥተን ዕዝን እንደርስ ነበር” ስላት “ኮንፊዩዝድ” መሆኗ አይቀርም፡፡

ሌላው ይቅርና “የእርሻ መምህር” የሚለው ራሱ ለእሷ “ኦድ” ነው!

ምን መሰለሽ የዛሬ ተማሪነት…

በእኛ ጊዜ “እርሻ” የሚባል ትምህርት ነበር፡፡

በትምህርት ቤታችን የአትክልት ስፍራ የየራሳችንን “መደብ” አለስልሰን ሽንኩርት፣ ካሮት፣ ቀይ ስር…እናበቅል ነበር፡፡ በቀየኑ ጧትና ማታ ውሃ እያጠጣን፣ እየከተኮትን፣ እያረምን ለፍሬ ያበቃነውን የጓሮ አትክልት መምህራኑ በነፃ ይከፋፈሉት ነበር፡፡ ይቅርታ…”በነፃ” እንኳን አይደለም፡፡ በምላሹ “ማርክ” ይሰጡናል፡፡ በእርሻ ትምህርት ከ50ው 20 አገኘሁ ማለት፣ ምን ማለት እንደሆነ ታውቂያለሽ? ከቤቴ ባሊ እያመጣሁ ወረፋዬን ጠብቄ አትክልት አላጠጣሁም ማለት ነው!

ለነገሩ የእርሻ ትምህርት ውሃ ማጠጣት (Practical) ብቻም አልነበረም፡፡ ቲዎሪም ነበረው፡፡

ይሄውልሽ የቲዎሪ ጥያቄ…

“አባ ሰንጋ ምንድን ነው?”

አይ አንቺ!...ደረቅ ጥያቄና ደረቅ ኬክ አይመችሽም አይደል?...ተይው በቃ…አትጨናነቂ፡፡ “አባ ሰንጋ” አንቺ ከቴዲ አፍሮ ዘፈን በኋላ እንዳወቅሽው እንደ “አባ ነፍሶ” የፈረስ ስም አይደለም - እንደ “አባ ጐርባ” የከብት በሽታ ነው፡፡

“ከብት ምንድ ነው?” አልሺኝ?

ጥሩ ጥያቄ ነው…

የእርሻ መምህር እንደነገሩን ከብት የተወሰኑ እንስሳት የጋራ መጠሪያ ነው፡፡ የጋማ ከብት አለ፣ የቀንድ ከብት አለ፣ የዳልጋ ከብት አለ…በቃ ብዙ ነገር አለ - አንቺ የማታውቂው፡፡

ብዙ የማታውቂው ነገር ስላለ ነው “እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምሯል” ተብሎ በደፈናው የታለፈው ታሪኬ ለምን እንዳንገበገበኝ ያልገባሽ!...ገባሽ?...እሺ፣ ከገባሽ የክፍል ስራ ልስጥሽ…በጐደለ ሙይ…

አበራ ታዬ አለሙ ……..ነው፡፡

ለዛሬ ተማሪነት የክፍል ስራ ሰጥተናት ወደ እኛ ተማሪነት እንመለስ፡፡

እና እንዳልኳችሁ…የህይወት ታሪኬን የሚያነበው ሰው በተለመደው መልኩ “እስከ 8ኛ ክፍል ተምሯል…” ብሎ ይዝለለው እንጂ፣ እኔ ግን አልዘለውም፡፡

እስከ ስምንተኛ ክፍል በመማር ውስጥ ብዙ ስቃይ፣ ብዙ ግፍ፣ ብዙ መከራ፣ ብዙ ሌላ ነገር አለ - አንድም የሚበጅ አንድም የሚፈጅ፡፡

ከወራት በፊት አንድ ማለዳ እግር (ታክሲ) ጥሎኝ የሆነ ስሙን የማላስታውሰው “አካዳሚ” አካባቢ ተገኘሁ፡፡

የሚገርም ነገር አየሁ፡፡ የአካዳሚው ተማሪዎች ከወላጆቻቸው የቤት መኪና ወይም ከተመደበላቸው “ሰርቪስ” እየወረዱ ዘና ባለ እርምጃ ወደ መግቢያው በር ያመራሉ፡፡ በሩ ላይ በፈገግታ የተሞላች ሴት (“ሚስ እከሌ”) ተማሪዎቹን በፍቅር እየተቀበለች ግንባራቸው ላይ እየሳመች በ”ዎተር ፕሩፍ” ደብተር፣ በ”ፔርሙዝ ላንች ቦክስ” ና በሌሎች ቁሳቁስ (ይመስለኛል) የተሞላ ቦርሳቸውን ተቀብላ ወደ ግቢው ውስጥ ትመራቸዋለች፡፡

ይሄን እያየሁ ወደ እኛ ተማሪነት በትዝታ ተመለስኩ፡፡

የእኛ ትምህርት ቤት እንደዚህኛው አካዳሚ፣ የእኛ ተማሪነት እንደዛሬዋ ተማሪነት፣ እኛም እንደ እነዚህኞቹ አልነበረንም፡፡

ከየቤታችን አንስቶ ትምህርት ቤታችን ደጃፍ ላይ የሚጥለን የእኛ “ሰርቪስ” እግራችን ነው፡፡ ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጠን ት/ቤት የምንደርሰው በሩጫ ነው፡፡ እነሱ ዘና ባለ እርምጃ፣ እኛ በጥድፊያ ሩጫ እንደርሳለን፡፡ በሩ ላይ “ሚስ እንትና” አይደለችም የምትጠብቀን፡፡ ዘበኛችን ጋሽ እከሌ እንጂ፡፡ ጋሽ እከሌ እንደ ሚስ እከሌ እንደሚስ እከሌ በፈገግታ ሳይሆን በአለንጋ ነው አቀባበል የሚያደርጉልን፡፡

ያለ የሌለ አቅማቸውን ተጠቅመው በአለንጋቸው ጀርባችንን ሾጥ እያደረጉ ያስገቡናል፡፡

ይቅርታ አድርጉልኝ!

ሳይማር አስተምሮ ለወግ (essay) ያበቃኝን ወገኔን ውለታ ለማጣጣል ፍላጐት የለኝም፡፡ የቀለም አባቶቼን በጐ ስራ ማንቋሸሽም አልፈልግም፡፡

“አስተማሪ” የሚባል “ቀጪ” ፍጡር አሳር መከራዬን ሲያሳየኝ እንደኖረ የማውቀው እኔ ነኝ፡፡

ለምን እንደሆነ ባላውቅም ብዙዎቹ አስተማሪዎቻችን “ክፉ” ነበሩ፡፡

ለምሳሌ የ4ኛ ክፈል ሂሳብ አስተማሪያችን - ጋሽ ሉሌ፡፡ መንግስት ለጋሽ ሉሌ ደመወዝ የሚከፍለው ሒሳብ ላስተማሩበት ሳይሆን እኛን ለገረፉበት እስኪመስል ድረስ ክፍለጊዜው ተጀምሮ እስኪያልቅ ትኩረታቸው ገረፋ ላይ ነው፡፡

ወደ ክፍል እንደገቡ የተለመደ ትዕዛዝ ያስተላልፋሉ፡፡

“የቤት ስራ ያልሰራችሁ ተነሱ!” ይላሉ ኮስተር ብለው፡፡ የቤት ስራ ያልሰራ ተማሪ ሁሉ እየተቁለጨለጨ ቀስ በቀስ ከመቀመጫው ይነሳል፡፡ አንድ ሁለት እያለ፡፡

“ተናግሬያለሁ…ተቀምጦ ያገኘሁት ተማሪ ጉዱ ይፈላል” በማለት ያፈጡብናል፡፡ ነገሩ ያስፈራው ተደብቆ ሊያመልጥ የሞከረ ተማሪ ቀስ እያለ ብድግ ይላል፡፡

“ሌላስ?...የቤት ስራ ያልሰራ?” ያፈጣሉ፡፡

“የቤት ስራ ሰርተናል” ብለው ወደተቀመጡት ተማሪዎች እየቀረቡ ደብተራቸውን ይፈትሻሉ፡፡ ሲጨርሱ የቤት ስራ አለመስራታቸውን ያመኑ ተማሪዎችን አንድ በአንድ ይጠይቃሉ፡፡

“ለምን አልሰራሽም?”

ሁሉም ምክንያቱን ይገልፃል፡፡ የሚገርሙ ሰበቦች ይደመጣሉ፡፡

መብራት ጠፍቶ

እከሌ መፅሐፍ ስላልሰጠኝ

(በጋራ ነበር  የምንጠቀመው)

ሰርቼ ነበር፣ ደብተር ረሳሁ

ጉንፋን አሞኝ…

ይህ ሁሉ ሲሆን ክፍለ ጊዜው ይገባደዳል፡፡

ጋሽ ሉሌ ይሄን አይተው ወደ መደበኛ የማስተማር ስራቸው አይመለሱም፡፡

“ጥሩ ለበቅ ቆርጣችሁ አምጡ!” ብለው ከተቀጪ ተማሪዎች መካከል የተወሰኑትን ይልካሉ፡፡ የሚገርመው ግን ለራሳቸው መገረፊያ እንዲያመጡ የሚላኩ ተማሪዎች ደህና አድርጐ የሚያሳምም ለበቅ መርጠው ማቅረባቸው ነው፡፡ ምክንያቱም ተልካሻ ለበቅ ካመጡ ቅጣቱ ከበድ ሊል ይችላል፡፡

አንዳንድ መምህራን ደግሞ ነበሩ…እንደ ጋሽ ሉሌ ተማሪው በቆረጠው ለበቅ ተማሪውን ከመግረፍ ይልቅ ቋሚ አለንጋ ይዘው ወደ ክፍል የሚመጡ፡፡

“ጋሽ ጣፍጤ” ከእነዚህ አንዱ ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ “ጣፍጤ” የእሳቸው ስም አይደለም፡፡

የአለንጋቸው እንጂ፡፡ እሳቸው እንግሊዝኛ ሊያስተምሩ ወደ ክፍል ሲገቡ ጠመኔ፣ ቀይ እስክርቢቶ፣ ዳስተር ወይም ሌላ ነገር ሊረሱ ይችላሉ፡፡ ፍፁም መርሳት የማይችሉት “ጣፍጤ”ን ነው፡፡

“ጉድ ሞርኒንግ ክላስ” ብለው በእንግሊዝኛ ሰላምታ የሚሰጡን እኒህ መምህር ሊቀጡን ሲፈልጉ ግን በአማርኛ ነበር የሚናገሩት፡፡

“ጣፍጤን ያልቀመሰ

እያደረ ባሰ!...መጽሐፍ የረሳሽ ሁሉ አንድ ባንድ እጅሽን አውጭ!” በማለት፡፡

አቤት የቅጣቱ ብዛትና ክፋት!..

ታዲያ መምህራኑ ብቻ እንዳይመስሏችሁ በቅጣት የሚያማመርሩን፡፡ ዘበኛውም “ለምን ቧንቧውን በግራ እጅህ ከፈትክ!” አይነት ሰበብ ፈልገው ይገርፉናል፡፡

በጣም ከሚገርሙኝ የያኔ ቅጣቶች አንዱ “ሴት ከወንድ መቀላቀል” የሚባለው ነው፡፡

እውነቴን እኮ ነው!...በእኛ የተማሪነት ጊዜ የክፍሉ ተማሪ እያወራና እየረበሸ ሲያስቸግር አፉን ለማስዘጋት የሚወስድበት እርምጃ መቀላቀል ነበር፡፡

ምን ማለት መሰላችሁ…

ተማሪው ትንፋሹን ውጦ ቁጭ እንዲል አቀማመጡ በአዲስ መልክ ይዋቀራል፡፡ ሁለት ሴት ከዳር አንድ ወንድ ከመሀል፣ ሁለት ወንድ ከዳር አንድ ሴት ከመሀል…እንዲህ አድርጐ ሴትን ከወንድ ቀላቅሎ ማስቀመጥ ሌላው የረባሽ ተማሪ ቅጣት ነው፡፡

ይሄው እንግዲህ …በእኛ የተማሪነት ጊዜ ሴት የወንድ አፍ ማስዘጊያ፣ ወንድም የጥፋተኛ ሴት መቅጫ ነበሩ!... በዚህ ዕድሜዬ ከቺኮች ጋራ ዘና ብሎ መነጋገር የሚጨንቀኝ፣ ተማሪ እያለሁ በሴት ተቀጥቼ ስላደግኩ ሳይሆን ይቀራል?

የእኛ ተማሪነት ፈርኒሽድ በሆነ ክላሰሩም ዘና ብላ ስትማር የምትውል እንዳይመስላችሁ…

የአመቱ መጀመሪያ ላይ ተማሪው ሳንቲም አዋጥቶ መጥረጊያና ቅርጫት የመግዛትና በወረፋ አቧራ እየቃመ ክፍሉን የማጽዳት ግዴታ አለበት፡፡

ወረፋውን ጠብቆ ክፍል ያልጠረገ ተማሪ፣ በነጋታው ጧት ከቢጤዎቹ ጋር ተቀላቅሎ እስከ 3ኛው ክፍለ ጊዜ ድረስ የት/ቤቱን ግቢ የማጽዳት “ቆሻሻ ለቀማ” የተባለ ቅጣት ይጣልበታል፡፡

በነገራችን ላይ “ቆሻሻ ለቀማ”፤ ትምህር ቤቱ ለግቢ ጽዳት በጀት ከመመደብ ይልቅ በተማሪው ሃይል የመጠቀም ኢፍትሃዊ ስትራቴጂ ነው፡፡

የዛሬ ዘመን ተማሪነት ኮንደሚኒየም በመሰለ ባለፎቅ ክፍል ውስጥ ፊደል ስትቆጥር፣ የእኛዋ ግን በአፈር ወለል ውስጥ አሳሯን ስትቆጥር ኖራለች፡፡

አስተማሪ ለእኛ የፍርሃት ምንጭ ነበር፡፡ ከትምህርት ሰአት ውጭ፣ ከትምህርት ቤት ውጭ ኳስ ስንጫወት እግር ጥሎት ወደ እኛ የመጣ መምህር ሲገጥመን ከእይታ ለማምለጥ የምንሮጠውን ሩጫ ሳስብ እስከ አሁንም ግርም  ይለኛል፡፡

ኧረ ብዙ ብዙ የሚገርም ነገር ነበር…ለምሳሌ “ለተማሪ 100 አይሰጥም” የሚለው የዚያ ዘመን የውጤት ህግ! ግን ምን ለማለት ነው?...ከቻለ መቶ ቢሰጠው ምን ነውር አለው?...

የዛሬ ዘመን ተማሪ በመምህሩ ላይ “ሙድ” እንደሚይዝ በ”ገመና - ሁለት” ድራማ ተመልክቻለሁ፡፡ የሚገርም ለውጥ ነው፡፡ ተማሪ አፍ አውጥቶ መምህሩን የሚገዳደርበት ይሄኛው ዘመን ከመምጣቱ በፊት ግን በድራማም ቢሆን ይሄን ማድረግ የሚታሰብ አልነበረም፡፡

እንኳን መምህርን፣ የመምህርን ልጅ አፍ አውጥቶ መናገር ትልቅ ወንጀል ነበር፡፡ መምህሩ በተማሪው ላይ የፈለገውን የማድረግ ስልጣን ነበረው፡፡ ተማሪውም የሚደረግበትን ሁሉ በፀጋ የመቀበል ግዴታ፡፡

“ለምን?” ብሎ የጠየቀ ተማሪ አሳር መከራውን ያያል፡፡

አስተማሪ ሲጠራህ “አቤት”፣ ሲልክህ “ወዴት” ማለት ግዴታህ ነው፡፡

ለምሳሌ - ጋሽ ሰውነት ድንገት ወደ ክፍላችሁ መጥተው ከተማሪው መካከል ፈርጠም ፈርጠም ያሉትን ስም ይጠራሉ፡፡ ስምህ ከተጠራ “አቤት”፣ ትላለህ፡፡ እንዳንተ ስማቸው ከተጠራ ጓደኞችህ ጋር ጋሽ ሰውነትን ተከትለህ ከክፍልህ ትወጣለህ፡፡ ስፖርት ሜዳ አጠገብ ስትደርሱ “በሉ እንግዲህ ይቺን ነገር ቤት አድርሳችኋት ተመለሱ” ይላሉ፡፡ ትምህርትህን ትተህ መምህሩ ለከብቶቻቸው ያሳጨዱትን (ከገጠር አካባቢ በሚመጡ ተማሪዎች) ሳር እንድትሸከም ስትታዘዝ መቀበል ብቻ ነው፡፡ ይሄ …”ጉልበት ብዝበዛ” ምናምን የሚሉትን አጉል ሙግት ብታነሳ ሰሚ የለህም፡፡

ደሞስ የምን ጉልበት ቁጠባ ነው? ለቀለም አባትህ ያልሆነ ጉልበት ለምን ሊሆን ነው?...

ለዚህ ነው ልክ መምህሩ ብቅ ሲሉ ሮጠህ “ዳስተር” የምትቀበላቸውና ጥቁር ሰሌዳውን የምታፀዳው፡፡

በእኛ ጊዜ መምህር ወደ ክፍል ሲገባ ከመቀመጫ መነሳት ግዴታ ነበር፡፡ ተነስቶም የጋራ ሰላምታ መስጠት፡፡ የሳይንስ መምህርህ እንደትናንት ‘መገልፈጥ አበዛህ’ በሚል ሰበብ ጆሮህ እስኪቀላ ቆንጥጠውህ ቂም ይዘህባቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ዛሬ ወደ ክፍል ሲገቡ ግን ፈገግ ብለህ ሰላምታ መስጠት፣ እሳቸውንም የሚያስተምሩትን ትምህርትም የምትወድ መምሰል አለብህ፡፡

ሳይንስ የሚባል ትምህርት ፈጽሞ የማትወደው አንተ፣ የማትወዳቸው የሳይንስ መምህር ወደ ክፍል ሲገቡ ግን በመዝሙር ደስታህን ትገልፃለህ፡፡

“ሳይንስ ሳይንስ መድሃኒቴ

አስታወሰኝ ጤንነቴን

እጄን ታጥቤ ቁርሴን ስበላ

ሳይንስ ትዝ አለኝ ከጤና ጋራ…” እያልህ፡፡

ቀደም ብዬ ለዛሬ ተማሪነት የቤት ስራ ሰጥቼ ነበር፡፡

ጥያቄውም “አበራ ታየ አለሙ -- ነው” የሚል ነበር፡፡

የዛሬ ተማሪነት ከአንዱ ዜሮ ብታገኝም “ደደብ” ልላት አልፈልግም፡፡ ምክንያቱም እሷ “ትምህርት በፕላዝማ” እንጂ “ትምህርት በሬዲዮ” አልተማረችም፡፡

ብትማር ኖሮ አበራ ታየ አለሙን ይቅርና መስቲካ ነጋሽ እና እጀታ ነገሬን ሳይቀር ታውቃቸው ነበር፡፡ እርግጥ እኛም በስም እንጂ በአካል አናውቃቸውም፡፡ በ”ትምህርት በሬዲዮ” ነው የምናውቃቸው፡፡

እውነቱን ለመናገር በተማሪነት ዘመኔ የምናፍቀው “ፔሬድ” ቢኖር ትምህርት በሬዲዮ ነበር፡፡ ክፍለጊዜው ሲደርስ በጨርቅ ቦርሳ የምትንጠለጠለዋን ሬዲዮ ከመምህሩ እጅ ለመቀበል ሩጫ ነበር፡፡

ትምህርት ቤታችን የተወሰኑ ሬዲዮዎች ብቻ ስለነበሩት ብዙ ጊዜ የሬዲዮ እጥረት ይከሰት ነበር፡፡ አንድ የትምህርት አይነት በሬዲዮ 15 ደቂቃ ብቻ ነበር የምንማረው፡፡ ስለዚህ ሌላውን 15 ደቂቃ ሌላ አይነት ትምህርት ስለሚተላለፍበት ሬዲዮው ወደ ሌላ ክፍል ይወስዳል፡፡

“ትምህርት በሬዲዮ” የምወድበትን ትክክለኛ ምክንያት ባላውቅም፣ እንደሚመስለኝ ግን ከመምህሩ ንዝንዝ ሬዲዮው ፋታ ስለሚሰጠኝ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ትምህርቱ ከመጀመሩ በፊትና በኋላ ሙዚቃ ነበር፡፡

ለነገሩ ልክ ሙዚቃው ሲጀምር ሬዲዮውን ይዘጉና የራሳቸውን ወሬ ይከፍቱብናል!

የዛሬ ዘመን ተማሪነት ሙዚቃ ለመስማት የግድ የ “ትምህርት በሬዲዮ” ክፍለ ጊዜን አትጠብቅም፡፡ ንፉግ መምህር የመንግስት ንብረት የሆነውን ሬዲዮ ዘግቶ ስለወሰደ ሙዚቃ እንዳማረን የምንቀር እኛ የድሮዎቹ እንጂ፣ የዛሬዎቹማ “MP3” ይዘው ነው “ክላስ”

የሚገቡት፡፡

እኔ እምለው…የ”ደብተር ማርክ” አሁንም አለ እንዴ?

ለነገሩ ቢኖርም ጣጣ የለውም!...”ዎተር ፕሩፍ” ሽፋን ባለው “ፓድ” የሚማር ትውልድ “ደብተሬ ቆሸሸ፣ ተገነጠለ” ምናምን ብሎ አይጨናነቅም፡፡

እኛ ግን የ”ደብተር ማርክ”ን በማሰብ መጨነቅ የምንጀምረው ገና በመስከረም ነው፡፡ “መሬት ላራሹ” የሚል ሽፋን ያላትን ደብተር እንደየአቅማችን አሳምረን እንለብጣታለን፡፡ ተማሪን ከደብተሩ ሽፋን አንፃር በ3 መመደብ ይቻላል፡፡ ደብተሩን በካኪ ወረቀት (የተለያየ ቀለም አለው) እና በላስቲክ በ”ስቴፕለር ሽቦ” የለበደ - የሃብታም ልጅ፡፡

በ”ሠርቶ አደር” ወይም በ”ዛሬይቱ ኢትዮጵያ” ጋዜጣ የለበደ - የኢሰፓ ልጅ፡፡

በሲሚንቶ ከረጢት ቅዳጅ የለበደ - የሰፊው ህዝብ ልጅ፡፡

የሴሚስተሩ መጨረሻ ላይ እያንዳንዱ መምህር የእያንዳንዱን ተማሪ ደብተር እየገለጠ ጥራቱን በማየት “ማርክ” ይሰጣል፡፡ የአብዛኛው ሰነፍ ተማሪ ውጤት ማሳደጊያ ተስፋ የደብተር ማርክ ነበር፡፡

መምህሩ ተማሪውን የሚገመግሙት ደብተሩ ውስጥ በሚገኘው የ”ራይት” ና “ኤክስ” መጠን ሳይሆን የ”ቆሻሻ” መጠን ነውና፡፡

የዛሬ ዘመን ተማሪነት 12ኛ ክፍልን ስታጠናቅቅ “ባይ ባይ ሃይስኩል” እያለች ፓርቲ ትደግሳለች አሉ፡፡ እኛ ግን ፓርቲ ባንደግስም ከትምህርት ቤታችን ግቢ የመውጣታችንን የነፃነት ሰአት በደማቅ ሁኔታ ነበር በየዕለቱ የምናከብራት፡፡

እውነቴን እኮ ነው!...

ስድስት ሰአት ደርሶ ከትምህርት ቤት የምንለቀቅበትን ደወል ተከትለን የምናሰማውን ጩኸት፣ በምህረት የተለቀቁ የዕድሜ ይፍታሽ ፍርደኞች እንኳን አያሰሙትም፡፡

በዘበኛ ዱላ፣ በተማሪ ፖሊስ ጨንገር፣ በዩኒት ሊደር አለንጋ፣ በመምህር ቀበቶ፣ በክፍል አለቃ ለበቅ… አሳር መከራችንን ስናይ እንደምንውል ለማረጋገጥ ደወሉን ተከትሎ የሚያስተጋባውን የደስታ ጩኸት መስማት ብቻ ይበቃል፡፡

“ወደቤት!” የሚል የጋራ ድምጽ ይሰማል፡፡

ተማሪው ከክፍሉ ወጥቶ ለመብረር ይሽቀዳደማል፡፡

የጥያቄና መልስ ውድድር ኖሮ ከመደበኛው ክፍለጊዜ ደቂቃ ሲቀናነስ፣ መምህር ጉዳይ (ለቅሶ፣ ስብሰባ፣ እቁብ ምናምን) ኖሮበት ወደ ክፍል ሳይመጣ ሲቀር፣ በበአል ምክንያት ትምህርት ሲዘጋ….በደስታ የምንፈነድቀው ከተማሪነት ይልቅ ታሳሪነት ስለሚሰማን ሳይሆን ይቀራል?

ስለ እኛ ተማሪነት ብዙ ብዙ ማለት ፈልጌ ነበር….ምን ያደርጋል ታዲያ….በመሃል ላይ “እስክርቢቶዬ ገነፈለ”፡፡

(እናንተ…የገነፈለ እስክርቢቶ ካየሁ ስንት ጊዜ ሆኖኛል መሰላችሁ!)

“ትርፍ እስክርቢቶ ይኖርሃል ጀለሴ?”

“ኢትዮ” ወይም “ቀጭ ቀጭ”… አጀብ የእኛ ተማሪነት!

ደወል ተደወለ…”ወደ ቤት!”

 

 

Read 3172 times Last modified on Saturday, 21 July 2012 10:11