Thursday, 20 August 2020 00:00

“ሁሉን አቀፍ ብተና” - አገርን ግራ የሚያጋባ “አገራዊ መግባባት፡፡

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

የዘመናችን ዝነኛ የፖለቲካ ቃላትንና ሐረጋትን ተመልከቱ፡፡ ብዙ ፖለቲከኞች፣ ብዙ ምሁራንም ጭምር፣ በየእለቱ ምን እንደሚያነበንቡ አስተውሉ፡፡ “በአወንታ”ና “በይሁንታ”፣ …በሰፊው ተቀባይነት ያገኙ የዘወትር አባባሎችን አንድ ሁለቱን አስታውሱ፡፡
በጣም ስለተላመድናቸው፣ ገና ድሮ “የተግባባንባቸው ዘላለማዊ እምነት”  መስለው ይታዩናል፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው? የተግባባንባቸው ቃላት፣ መግባባትን የሚያጠፉ ናቸው፡፡ “ለውጥ” እና “ለውጥ ፈላጊ” በሚሉ አገላለፆች ላይ፣ ስንቱ በአወንታ እንደሚስማማ አስቡት፡፡ “ምን አይነት ለውጥ?” ብሎ ሳይነጋገር፣ በደፈናው፣ “ለውጥ” በማለት ብቻ ይግባባል - አብዛኛው ሰው፡፡
አሁን እንደምናየው ግን፣ “ለውጥ” እያለ በደፈናው የተግባባ እልፍ ሰው፣ በየፊናው እልፍ አይነት “ለውጥ” በምናቡ እየፈለፈለ፣ አለመግባባትን ያራባል፡፡ ለምን? ሌሎቹንም የዘመናችን ዝነኛ ቃላትንና የዘወትር ሃረጋትን ጨምረን እንይ፡፡
ብዝሐነት፣ ለውጥ፣ ውይይት፣ ትርክት፣ የህዝብ ጥያቄ፣ ሞጋች አስተሳሰብ፣ የሃሳብ ፍጭት፣ የህዝብ ድምፅ የሚሉ ቃላትና ሐረጋት፣ የብዙዎች መግባቢያ ሆነዋል፡፡
- ለብተና መሰባሰብ፤ ለመበጣበጥ መግባባት::
አገርን የማወክና የመበጥበጥ እቅድ፣ ከዚያም አልፎ አገርን የማተራመስና የማፍረስ ዓላማ፣ ምን ተብሎ ይጠራል? አገርን የማረጋጋትና የማደላደል፣ የማሻሻልና የማሳደግ አላማስ? አገርን የሚያናጋ፣ አገርን ከሚያረጋጋ ጋር፣ በእኩል ስም ይጠራል - “ለውጥ ፈላጊ” በሚል፡፡
“የለውጥ ሃይል”፣ “ለውጥ ፈላጊ” በሚል ስያሜ ተግባብተን ነው፤ ያ ሁሉ ፖለቲከኛና “አክቲቪስት”፣ ያ ሁሉ ፓርቲ፣ ከያለበት የተሰበሰበው፡፡
ታይቶ ወደማይታወቅ እንጦሮጦስ ለመውረድ፣ ቀን ከሌት የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካን እያባባሱ ማጦዝ፤ “የለውጥ ዓላማ” ነው፡፡ የብሔር ፖለቲካን ለማለዘብ መሞከር፣ አገራዊ አወቃቀርን ለማደራጀት መትጋትና ዘረኝነትን ለማስወገድ በፅናት መስራትስ? ይሄም፣ “የለውጥ ዓላማ” ነው፡፡
“ዘረኝነትን እስከጥግ ማጦዝና ዘረኝነትን ለማስወገድ መትጋት…” የሚሉ ገለፃዎችን እየተውን፣ የለውጥን አይነትና ይዘት ለይተን ላለማወቅ እንሸሻለን፣ በድፍኑ፣ ያንንም ያንንም፣ በጭፍን ለማቀፍ፣ በሆታ እንቀበላለን፡፡ “ለውጥ” እና “ለውጥ ፈላጊ” በማለት በጋራ እንዘምራለን:: “የሚያግባባ ቃል አገኘን፣ አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር በቃን” ማለት ነው? ይሄኛውንም ያኛውንም በመደገፍ፣ “ለውጥ ፈላጊ” በማለት እንጮሀለን፡፡ “ይሄኛው የለውጥ አይነትና ተቃራኒው የለውጥ አይነት” ተዳብለው፤ …በእኩል ዓይን፣ “ለውጥ” ተብለው ይጠራሉ፡፡ በዚህ ነው የተግባባነው፡፡ ነገር ግን፣ የመግባባት እድል እንዳይፈጠር ነው ያደረግነው፡፡
ታዲያ፣ ሺ የለውጥ አይነትን አቅፈን፣ አሁን አገር ሲበጠበጥ ይግረመን?
ሁሉን አቀፍ ነው ቃሉ፡፡ ጥፋትንና ልማትን፣ መገንባትንና ማፍረስን፣ መጽናትንና  መፍረክረክን ሁሉ ይጠቀልላል - “ለውጥ” ማለት፡፡ በአድናቆት ስሜትና በጥቅል ስያሜ፣ ሁሉንም አይነት ዓላማና ተግባር፣ እኩል ለመቀበልና በዚሁ ለመግባባት የተጠቀምንበት ቃል ነው፡፡ አዎ፤ “አገራዊ መግባባት” ነው፡፡ ግን፣ ግራ መጋባትን የሚያራባ፡፡ ሁሉን አቀፍ ቃል ነው፡፡ ግን፣ በእልፍ የጥፋት አቅጣጫ የሚበታትን፡፡
ምንነቱን እንዳንሰማና እንዳይገባን ነው፣ መጮሃችንና መግባባታችን፡፡
“ንቅናቄ” መፍጠር፣ “ድምፅ” ማሰማት፣ “ጥያቄ” ማቅረብ…እነዚህንም አባባሎች እዩ፡፡
“ምን አይነት ንቅናቄ፣ ለምን አላማ?” ብለን ሳንመረምር፣ በይሁንታ የምንነቃነቅ መሆናችን ነው ችግሩ፡፡ የጥያቄውን ምንነት ሳናውቅ፣ ጥቅሙን ወይም ጉዳቱን ሳናመዛዝን፣ “የሕዝብ ጥያቄ” ይደመጥ፤ “የሕዝብ ድምፅ” ይሰማ፤ እያልን በሆታ እናጅባለን፡፡ ይሄም፤ የአገር ልማድ ሆኗል፡፡ ሁሉንም ነገር በደፈናው የማቀፍ ልማድ!
አስቡታ፡፡ ወረርሽኝን የመከላከል ንቅናቄ…ተብሎ ሲነገር እየሰማን ነው፡፡ ዓላማው ሳይገለጽ፣ በደፈናው “ሕዝባዊ ንቅናቄ” ተብሎ ቢሰየም ደግሞ አስቡት፡፡ ሊሆን አይችልም:: ፖለቲካ ውስጥ እንደዚያ ሆኗል - በደፈናው መግባቢያ እንዲሆነን፡፡  በአንድ በኩል፤ ኮረና ቫይረስን የመከላከል ንቅናቄ፣ ይኖራል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ በዘር ለአመጽ የማነሳሳት ንቅናቄ አለ፡፡…ልዩነት የሌላቸው ለማስመሰል፣ ያኛውም ይሄኛውም፣ “ንቅናቄ” በሚል የወል ስም ይጨበጨብላቸዋል፡፡ በአድናቆት ወይም “በይሁንታ” ተቀባይነትን ያገኛሉ፡፡
“ድምፃችን ለግድባችን” በማለት፣ ግንባታውን ለማፋጠን የሚነሳሳ ይኖራል፡፡ ሌላስ? በየከተማውና በየክልሉ፣ መንገድ እየዘጉ፣ ግንባታዎችን ለማፍረስና ኑሮን ለማወክ፤ ከየአቅጣጫው የሚራገቡ የቅስቀሳ ድምፆች አሉ፡፡ ልዩነት የላቸውም? የመገንባትና የማፍረስ ድምፆች ይለያያሉ፡፡ ነገር ግን “የህዝብ ጥያቄ”፣ “የህዝብ ድምጽ” ተብለው ይሰየማሉ፡፡
“ተቃውሞ” የሚለውንም ቃል ተመልከቱ:: የማህበር ወይም የጉባኤ ውሳኔ ላይ፣ “የምትደግፉ እጃችሁን አሳዩ” ከተባለ በኋላ፣ “የምትቃወሙ እጃችሁን አውጡ” ተብሎ ይቆጠራል፡፡ ተቃውሞ ነው፡፡ “ይሄኛው ሃሳብ ስህተት ነው፤ እቃወማለሁ፡፡ ይሄኛው ውሳኔ መጥፎ ነው፤ ይሄኛው ድርጊት ጐጂ ነው” ብሎ መናገርስ? ይሄም ተቃውሞ ነው፡፡ ስህተቶችንና ጥፋቶችን በማስረጃ ማብራራት፣ ከተቻለም ማስተካከያ ሃሳቦችን መሰንዘርም፣ “ተቃውሞ” ሊባል ይችላል፡፡
ሌላስ? በየጊዜው እንደየምናየው፣ ዝርፊያና ውድመት፣ ከኑሮ የማፈናቀልና የግድያ ጥቃት …በአጠቃላይ ሁከትና አመጽ ሁሉ፣ “ተቃውሞ” ተብሎ ነው የሚጠራው፡፡ ለዚያውም “በይሁንታ” ስሜት፡፡
“ግጭት” ተብሎ ሲሰየምም፣ ዘወትር እንሰማለን፡፡
የዘራፊና የተዘራፊ ግጭት፡፡
ሁለት አሽከርካሪዎች፣ በእልህ ሲሽቀዳደሙ ቢላተሙ፣ የመኪና ግጭትን ፈጠሩ እንላለን:: ወይም ሁለት ዱርዬዎች፣ መንገድ ላይ የወደቀ መቶ ብር አይተው  በሽሚያ ግብግብ ቢገጥሙ፣…”ተጋጩ” ተብሎ ይወራል - የዱርዬዎች “ግጭት”፡፡
በዘር የተቧደኑ ወጣቶች፣ በየጐዳናው እየዞሩ ሱቆችን ሲዘጉስ? ይሄም “ግጭት” ነው፡፡ “መዋጮ” እያሉ ገንዘብ ሲወስዱ፣ በር ገንጥለው ሲዘርፉ፣ ንብረት ሲያወድሙና ግድያ ሲፈጽሙም፣ …”ግጭት” እየተባለ ይዘገባል:: የዘራፊና የተዘራፊ፣ የገዳይና የሟች ጉዳይ፤ ከመኪና ግጭት ጋር እየተዛመደ፤ “የግጭት መከላከያ” ዘዴ፣ “የግጭት አፈታት ባህል” እየተባለ ይደሰኮራል፡፡
“ትርክት” የሚባል ቃል ደግሞ፣ በአዲስ ትርጉም መጥቷል፡፡ የአሉቧልታ ወሬና የዜና ዘገባ፣…ያው…ምንም ልዩነት የሌላቸው ይመስል፤ “ትርክት” ተብለው ይመደባሉ፡፡ ማስረጃዎችን ያሟላ የአንድ ሰው ወይም የአገር ታሪክም፤ “ትርክት” ነው፡፡ ያለ በቂ ማስረጃ የተዘጋጀ ጽሑፍ፣ በሃሰትና በስሜት የሚተረተር ወሬም ሳይቀር…ያለ ልዩነት፣ ሁሉንም የሚያቅፍ አንድ የጅምላ ስም ተሰጥቷቸዋል፡፡ ትርክት፡፡
ልብወለድ ድርሰትም እንዲሁ፣ “ትርክት” ተብሏል፡፡ ሁሉም፣ ያው ሆነዋል፡፡ የእውነትና የእውቀት ጉዳይ፣ የውሸትና የቅዠት ክምር፣ የኪነጥበብ ፈጠራ ሁሉ፤ ትርክት በሚል ስያሜ ልዩነታቸው እንዲጠፋ መፍጨርጨር ተለምዷል፡፡
የሳይንስና የምርምር ውጤት፣ የግራቪቲ ስርዓት፣ የስነ ሕይወት ግኝት…እነዚህ ሁሉ፤ እውነትን የመጨበጥ የእውቀት ገጽታ ነበሩ:: ዛሬ ግን፣ ከአሉባልታና ከጭፍን እምነት፣ ከኮከብ ቆጠራና ከጥንቆላ፣ ከቁም ቅዠት ጋር ያለ ልዩነት…”ዲስኮርስ” የሚል ስያሜ ውስጥ እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡ “አንዱ ከሌላኛው፣ ምንም ብልጫ የለውም” በማለት ልዩነትን አጥፍተን፤ ሁላችንም ተግባባን ማለት ነው?
እንዲህ ከተግባባን በኋላ፤ በማግስቱ ስንነቃስ? ለካ መግባባትን ለማጥፋት ነው የተግባባነው፡፡ የመግባባት ዋና ስረመሰረቶች፣ ማለትም እውነትና እውቀት፣  ዋጋ ሲያጡ፣ የመግባባት እድል ይጠፋል፡፡ ዛሬ እንደምናየው ማለት ነው፡፡
ቀስቃሽም፣ ቆስቋሽም - “አክቲቪስት” ይሉታል
“ሁሉን አቀፍ ብተና” ምን እንደሆነ ለመገንዘብ፣ የዘመናችን ዝነኛ ቃላትን በምሳሌነት ለማሳየት ሞክሬያለሁ፡፡ … (activist) የሚለውንም ቃል መጥቀስ ይቻላል፡፡
በጭፍን የሚደናበርም ቢሆን፤ አስተውሎ የሚራመድም ቢሆን፤ ወደ ከፍታ አልሞ የሚያተጋም ቢሆን፣ ወደ ቁልቁለት የሚያዋርድም ቢሆን፣ ለድርጊቱ የግል ኃላፊነትን የሚወስድም ቢሆን፣ በ “ሪሞት”ና በዘር ቅስቀሳ ለእልቂት የሚያዘምትም ቢሆን፣… ሁሉንም በእኩል አይን እንድንቀበል የሚገፋፋ ቃል ነው:: activist፣ አልሚውንም አጥፊውንም ሁሉንም ያቅፋል - በይሁንታ፡፡
ለውጥ፣ ንቅናቄ፣ ትርክት፣ ግጭት፣ ዲስኮርስ፣ የሕዝብ ጥያቄ፣ የሕዝብ ድምጽ፣ “activism”፣…በዘመናችን እጅግ የገነኑት እነዚህ ቃላትና ሐረጋት፣ በአጋጣሚ የመጡ አይደሉም፡፡ የጋራ ባሕርይ አላቸው፡፡
“ሁሉንም ለማቀፍ”፣…አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚያስችሉ ይመስላሉ፡፡ ግን፣ የሚበታትኑና የሚያቃውሱ ናቸው፡፡ እውነትንና ሃሰትን፣ እድገትንና ውድቀትን፣ መገንባትንና ማፍረስን፣ ቅንነትንና ክፋትን፣ እውቀትንና ቅዠትን፣ ሁሉንም …በይሁንታና በእኩል ዓይን የሚያቅፉ አባባሎች ናቸው - ሁሉንም በይሁንታ እንድንቀል የሚገፋፉ፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው? ሁሉን ማቀፍ፣ ሁሉን ይበትናል፡፡ ሁሉን በይሁንታ መቀበል፤ ሁሉንም ትርጉም አልባ ረብ የለሽ ያደርጋል፡፡
ብዝሐነት…የእውቀትም፣ የቅዠትም፣…ያው ሆኗል፡፡
እውነትና ሀሰትን፣ ትክክልና ስህተትን፣ እውቀትና ቅዠትን አቅፈን ስንቀበል፣ …ማሰብም መግባባትም ያቅተናል፡፡ “የሃሳብ ብሐሃነት”፣ “ሞጋች አስተሳሰብ”፣ “የሃሳብ ፍጭት”…እነዚህንም አባባሎች አስተውሉ፡፡
“የሃሳብ ብዝሐነት”፣ …የመረጃና የእውቀት መስፋፋት ማለት ነው? አብዛኛው ሰው በተለያዩ ዘርፎችና ደረጃዎች በእውቀት እየበለፀገ ሲሄድ ማለት ነው? ወይስ የዚህ ተቃራኒ ነው? ከአንድ መረጃ ጋር እልፍ አሉቧልታ፣ ከአንድ ማስረጃ ጋር እልፍ የሐሰት ፍረጃ፣ ከአንዲት የሃሳብና የእውቀት ፍሬ ጋር እልፍ ገለባና ቅዠት…ይሄም “የሃሳብ ብዝሐነት” ነው፡፡
ሞጋች አስተሳሰብና የሃሳብ ፍጭት ማለትስ ምን ማለት ነው? ሃሰትን በእውነት፣ አሉቧልታን በማስረጃ፣ ቅዠትን በእውቀት ተጋፍጦ ማጥራት ነው?
ወይስ፣ አንዲቷን መረጃና እውነት ለማፍረስ፣ እልፍ የአሉቧልታና የውሸት ውርጅብኝ መልቀቅ? አንዲቷን ትክክለኛ ሃሳብና እውቀት በጭፍን ለመናድ፣ እልፍ ስህተትና ቅዠት እየፈለፈሉ ማዥጐድጐድም፣ …”ሞጋች አስተሳሰብ” ነው፡፡ ይሄም “የሃሳብ ፍጭት” ነው::
“ውይይት” የሚለው ቃልም እንዲሁ፣ “ሁሉን አቀፍ” የብተና ፈሊጥ ሆኗል፡፡
ከስካር በባሰ ስሜት በዘፈቀደ መቀባጠርና  መዘላበድ፣ “ውይይት” ነው፡፡ ብሽሽቅና ለከፋ፣ ስድብና ውንጀላ፣…ዛቻና የዘረኝነት ቅስቀሳ ጭምር፣ …ውይይት ነው፤ የሃሳብ ብዝሃነትና የሃሳብ ፍጭት ነው፡፡ የአገርን ሁኔታ በየዘርፉ፣ በጥልቅና በዝርዝር፣ መመርመር ይቻላል፡፡ ከአጭርና ከረዥም ጊዜ አንፃር፣ የሚያዋጣውንና የሚያዛልቀውን መንገድ ለመለየት፣ ጥናት ማካሄድም ይቻላል፡፡ በዚህ አይነት ሳይንሳዊ አስተሳሰብ ነው፤ “ውይይት” ትርጉም የሚኖረው፡፡ እውነተኛ መግባባትም ከዚህ ውጭ አይገኝም፡፡
“በማስረጃ የተገነቡ የእውቀት ግኝቶችን”  በየፊናቸው የሚያቀርቡ ሰዎች ሲነጋገሩ፣  ያኔ፣ ሃሳቦች የሚንሸራሸሩበትና የሚብራሩበት፣ የሚብላሉበትና የሚስተካከሉበት ውይይት ይሆናል፡፡
ነገር ግን፣ “ዝጋው፣ ስበረው፣ ዝረፈው፣ አቃጥለው፣ ግደለው” በማለት ሰውን ወደ አውሬነት የሚያወርዱ እኩይ ጩኸቶችም፣…”ውይይት” ና “የሃሳብ ፍጭት” ተብለው እየተጠሩ ነው - በይሁንታ ስሜት፡፡ በእንዲህ አይነት መንገድ የሚፈጠር “አገራዊ መግባባት”፣ ምን እያስከተለብን እንደሆነ፣…በየእለቱና በየቦታው እያያችሁት ነው፡፡  

Read 5416 times