Wednesday, 19 August 2020 00:00

የትዳር ወግ

Written by  (ሰለሞን ሳህለ ትዛዙ)
Rate this item
(1 Vote)

ጋዜጠኛው አርባ ዓመት በትዳር የቆዩትን ወ/ሮ እያናገረ ነው፡-
“ከባለቤትዎት ጋር አርባ ዓመት በትዳር ያለ ጸብ የቆዩበትን ምስጢር እስኪ ይንገሩን”
“ምን መሰለህ የኔ ልጅ የሰርጉ ቀን መጀመርያ ከቤተሰቦቼ ቤት ይዘውኝ የወጡ ግዜ በሽልም ፈረስ ላይ አድርገው ነበረ፤ አብረን ሆነን እሳቸው ልጓሙን ይዘው እየጋለቡ እኔ ከኋላቸው ሆኜ ትንሽ እንደሄድን ፈረሱ ለገመ፤ ይሄኔ እሳቸው፡-
“አንተ ፈረስ ተው ብየሃለሁ አንድ” አሉ
ፈረሱ መሄድ ቀጠለና ትንሽ ቆይቶ አሁንም ለገመ፤ ይሄኔ እሳቸው፡-
“አንተ ፈረስ ተው ብየሃለሁ ሁለት” አሉ
ፈረሱ የግዱን ሄደ ሄደና ሲደክመው እንደገና ቆመ፤ ያኔ እሳቸው በንዴት ከፈረሱ ላይ ዘለው ወርደው፣ እኔንም አውርደው ሽጉጣቸውን መዘዙና፡-
“አንተ ፈረስ ተው ብየሃለሁ ተው ሶስት” ብለው በግንባሩ ለቀቁበት፤ ፈረሱ ክልትው አለ፤ እኔም ደንግጬ፡-
“ምን ሆነው ነው አንቱዬ?” ስላቸው ወደኔ ዘወር አሉና፡-
“አንቺ ሴቲዮ ዝም በይ ብዬሻለሁ፤ ዝም በይ አንድ” አሉኝ
በቃ ይሄ ነው አርባ ዓመት በትዳር ያቆየን ምስጢር፡፡
የትምህርት ፖሊሲውና ፖለቲካው
(ፍርድያውቃል ንጉሴ )
እስከ 1993 ዓ.ም የነበረው የትምህርት ፖሊሲ /ከነመማሪያ መፃህፍቶቹ/ እስካልተመለሠ ድረስ የዚህች ሀገር ፖለቲካም ሆነ አጠቃላይ ህልውና እያደር መጎምዘዙና መምረሩ 100% አይቀሬ ነው። ከዚህ ውጭ ያለ ሁሉም ተግባር እስከ ዛሬ እንዳየነው ቅንጣት ለውጥ የማያመጣ Quick Fix ነው የሚሆነው፡
(ያውም እንደነ አይ.ቲ አይነት ዘመኑን የዋጁ ትምህርቶች እንዲሁም ከአማርኛና ከእንግሊዝኛ ጎን ለጎን ኦሮምኛ፤ ግዕዝ፤ ትግርኛ በመደበኛ የቋንቋ ትምህርትነት ተካተው!)
በነገራችን ላይ ኢህአዴግ በወቅቱ በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት ከመጀመሩ በፊት በሁሉም የሀገራችን ክልሎች በየአካባቢው ከሚገኙ ወላጆችና አዋቂዎች ጋር ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ በሁሉም አካባቢ የነበሩ ወላጆች የተመካከሩ ይመስል ...
 “ምንድን ነው የምታወሩት? የራሳችንን፣ እኛ የምንችለውን ቋንቋማ እኛው እቤት ውስጥ እናስተምራቸዋለን። ይልቁንስ እኛ ልናስተምራቸው በማንችላቸው የሀገራችንም ሆነ የአለም ቋንቋዎች አስተምሯቸው። ወጉና ደምቡ እንዲያ ነው።” ... በማለት በመድረኩ ላይ ምላሽ የሠጡ የተለያዩ ዜጎቻችን እየታደኑ መጨረሻቸው አላማረም። ኢህአዴግም ይሄን በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማርን ተግባራዊ አድርጎ Divide & Ruleን የበለጠ አጥብቆ እመንበሩ ላይ የበለጠ ተደላድሎ ተቀመጠ። መዘዙንም እያየነው ነው። እልባት እስካልተገኘለት ድረስ የማያቆም መዘዝ!
“Much education today is monumentally ineffective. All too often we are giving young people cut flowers when we should be teaching them to grow their own plants.” - John W. Gardner
ፋሽኑ ያለፈ ፖለቲካ
(ሙሼ ሰሙ)
ሕገ መንግስታዊ መብታችን ይከበር፤ ጥያቄያችን ጆሮ ይሰጠው በማለት መሳርያ ሳይታጠቁ፣ ገጀራ፣ ሜንጫና ጦር ሳይሰብቁ፣ የማንንም ንብረት ሳያወድሙና ሰው ሳይገድሉ፣ ልዩ ሃይል አደባባይ ሳያወጡ፣ አቤት በሚሉ የወላይታ ሕዝቦች ላይ ሰራዊት ማዝመት ለምን አስፈለገ? ለሕዝብ ጥያቄ፤#መልሱን የማውቅልህ እኔ ነኝ; ማለት ፋሽኑ ዛሬስ አላለፈበትም ማለት ነው?!
የዜጎችን የመብት ጥያቄ “ከዚህ በላይ አልታገስም” በማለት በሀይል መቀልበስ እንደማያዛልቅ ከቀደምት ገዢዎች ተሞክሮ በመውሰድ ወደ ክብ ጠረጴዛ ተመልሶ፣ ጥያቄውን በድርድር በመፍታት፣ ክቡር የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ፣ ጊዜና ሀብት እንዳይባክን ማድረግ ብልህነት ነው ።
የደቡብ ክልል ሕዝብ ሕገ መንግስታዊ ጥያቄ፤ በሕዝብ ፍላጎትና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ዘለቄታ ያለው መፍትሔ መስጠት በየጊዜው ከሚያገረሽ የግጭት አዙሪት እንደ ሀገርም ሆነ ሕዝብ ሁላችንንም ይታደገናል። ለ27 ዓመት ጥያቄያቸው ተገፍቷል፣ በውጣ ውረድም ከድህነት የመላቀቂያ ጊዜያቸው ባክኗል፣ አሁንም ኢትዮጽያዊ ናችሁ ማለት ብቻ አይበቃም። ጥያቄያቸው ፈጣን ምላሽ አግኝቶ ወደ ስራ ይግቡ። እንደ ሌላው ሕዝብ ከመብት ጥየቃ ተላቀው ትኩረታቸውን ወደ ድህነት ቅነሳና ልማት ያድርጉ።

Read 468 times