Monday, 17 August 2020 00:00

ዳያስፖራውና የኢትዮጵያ ፖለቲካ

Written by  ደስታ መብራቱ
Rate this item
(3 votes)

 "--እንደሚታውቀው፣ ‘በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ ሁነቶች በዋነኝነት የተከሰቱት እኩይ አመለካከት ባላቸው ጥቂቶች ጥንካሬ ሳይሆን መልካም አስተሳሰብ ባላቸው ብዙሃኖች ዝምታ ነው’ ይባላል። በቅርቡ በሃገራችን ለደረሰው አሳዛኝና አሳፋሪ ኢ-ሰብዓዊ ወንጀል ጥቂት ጽንፈኛ አመለካከት ያላቸው የማህበራዊ ሚዲያ አርበኞች ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስዱ ቢሆንም፣ የእነኚህን አጥፊ ወገኖች ተግባር በዝምታ ያስተናገድነው ብዙሃንም የራሳችን ድርሻ አለን።--"
              
            በአንድ ወቅት፣ ካንድ ወዳጄ ጋር ኢትዮጵያውያኖች ከሃገራችን ውጪ ስንኖር ከኢትዮጵያዊነታችን ጋር ያለንን ማህበራዊ ትስስር ለማቆየት የምንሄድበትን ርቀት ከሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ዜጎች ጋር እያወዳደርን በመገረም ተወያይተን ነበር። በዚህ ውይይት የደረስንበት ማጠቃለያ፣ በርግጥም እንደሚባለው ‘ኢትዮጵያዊውን በአካል ከኢትዮጵያ ታወጣው እንደሆነ እንጂ ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያዊው ውስጥ ማውጣት እንደማይቻል ነበር’። ይህም፣ የሃገሪቱ ህዝቦች ካሏቸው ጥልቅ ማህበራዊና ታሪካዊ መሰረት ጋር የተያያዘ መሆኑ አያጠያይቅም።  ከዚሁ ጥብቅ ትስስር ጋር በተያያዘ፣ ከሃገር ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተለያየ ወቅት በሃገሪቱ በተከሰቱ አበይት የፖለቲካ ሁነቶችም ንቁ ተሳታፊ እንደነበሩ ይታወቃል። ስለሆነም፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሲነሳ፣ በውጭ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የነበራቸውን ጠቃሚም ሆነ ጎጂ አስተዋጽኦዎች አለማንሳት አይቻልም። ከሺህ ዘጠኝ መቶ ስልሳዎቹ ወዲህ ያለውን የኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ የፖለቲካ ተሳትፎ በምንመለከትበት ጊዜ በዋነኝነት በሚከተሉት ሶስት የዳያስፖራ ፖለቲካ ዘመኖች የሚካተቱ ይሆናል።
የመጀመርያው፣ ከ1966 የህዝብ ንቅናቄ ጋር በተያያዘ ከንቅናቄው በፊትና በኋላ በነበሩ በርካታ ክስተቶች ውስጥ ከሃገራችን ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምሁራንና ተማሪዎች የነበራቸው የመሪነትና ተሳታፊነት ሚና ነው። የየካቲት ስልሳ ስድስቱ የህዝብ ንቅናቄ በተማሪው እንቅስቃሴ ውስጥ ተጸንሶ በመምህራኑ፣ በታክሲ ነጂው፣ በእስልምና እምነት ተከታዩና በመለዮ ለባሹ የመብት ጥያቄዎች በመታገዝ ህዝባዊ ንቅናቄ ለመሆን የበቃ ነበር። ለንቅናቄው መከሰት አብይ ድርሻ ከነበረው የሃገር ውስጥ የተማሪ ንቅናቄ በተጨማሪ በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ የነበረው የኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ማህበር የኢትዮጵያን ቀጣይ እጣ ፋንታ በመወሰን ረገድ ጉልህ ድርሻ ነበረው። ይህ በውጭ ሃገር በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ይካሄድ የነበረ እንቅስቃሴ በፍጹም የሃገርና ህዝብ የመውደድ ስሜት ላይ የተመረኮዘ ቢሆንም፣ ገና ከጅምሩ ትግሉ ሊከተለው በሚገባው አቅጣጫ ላይ የተወሰነ የአካሄድ ልዩነት ነበረው። ይህንን የአካሄድ ልዩነት ለማስታረቅና ለማስማማት የሚያስችል የርዕዮተ ዓለምና የግብ መመሳሰል ቢኖርም፤ ጥቂት መሪዎች ባሳዩትና ከባላባታዊ ፖለቲካ ቅሪቶች አንዱ በሆነው የ‘አልሽነፍም ባይነት‘ አመለካከት የተነሳ አንዱ የሌላውን ሃሳብ ለማዳመጥና ለማስተናገድ ዝግጁ ባለመሆኑ ክፍተቱ እየሰፋ መጠላለፉም እየባሰበት ሊሄድ ችሏል። እነኚህ ወገኖች በመሃከላቸው የነበረውን ልዩነት እንደያዙ ወደ ሃገር ውስጥ በመግባታቸው፣ በሃገር ቤት የነበረው ወጣትም በሁለት ጎራ እንዲሰለፍ አድርጎታል። ይህ ልዩነት፣ በለውጡ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት በተወሰዱ የገጠር መሬትን የህዝብ ያደረገውን አዋጅ በመሳሰሉ ስር ነቀል እርምጃዎች ምክንያት ይበልጥ እየሰፋ በመሄድ ላንድ ትውልድ የእርስ በርስ መተላለቅ የራሱን አሳዛኝ ድርሻ ሊያበረክት ችሏል። በመሆኑም፣ የመጀመሪያው ትውልድ ዲያስፖራ የ1966 ንቅናቄ ይዞት ለመጣው ሃገራዊ የሽግግር እድል በአጭር መጨናገፍ የራሱን አስተዋጽ አድርጓል ማለት ይቻላል።
የ1966 የህዝብ ንቅናቄን ተከትሎ ወደ ስልጣን የመጣው ወታደራዊ መንግስት ስልጣኑን ለማጠናከር በወሰዳቸው ፖለቲካዊ እርምጃዎች በህዝባዊው ንቅናቄ ግንባር ቀደም ተሳታፊ የነበረውን የተማረ የሰው ኃይል በእጅጉ ሊያመናምነው ችሏል። ይህንን ተከትሎ፣ እስከ 1983 ድረስ በነበረው ከፍተኛ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ቀውስ የተነሳ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሃገር ጥለው ለመሰደድ ተገደዋል። ይህም፣ ቀደም ሲል በአብዛኛው ለትምህርት በወጣውና አነስተኛ ቁጥር ባለው ኢትዮጵያዊ የሚታወቀውን የመጀመሪያውን የዲያስፖራ የፖለቲካ ዘመን ገጽታ ቀይሮታል። ከዚህ ከሁለተኛው የዲያስፖራ የፖለቲካ ዘመን ኢትዮጵያውያን አብዛኞቹ በሁለተኛ ዜግነታቸው የሚደርስባቸውን በርካታ ፈተናዎች በመቋቋም ኑሮአቸውን ማሸነፍ ላይ ቢያተኩሩም፣ የተወሰኑት ከኑሮው ትግል በተጨማሪ በሃገሪቱ የወደፊት የፖለቲካ እጣ ፈንታ ላይ መንቀሳቀሱን ቀጥለው ነበር። ይህንን መሰረት በማድረግም ቁጥራቸው ከበፊቱ በዛ ያለ የፖለቲካ ቡድኖች ተደራጅተው የተለያየ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቆይተዋል። ይህም፣ ቀደም ሲል በሃገር ውስጥ ለመንቀሳቀስ የሞከሩትን ህብረ ብሔራዊ ድርጅቶችን ጨምሮ አዳዲስ የፖለቲካ ድርጅቶችና ሃገር ውስጥ በትጥቅ ትግል ይንቀሳቀሱ የነበሩ ‘ነጻ አውጭ ድርጅቶች’ ደጋፊ ቡድኖችን ያካትታል። የነኚህን ድርጅቶች የተናጠል እንቅስቃሴዎች ለማቀናጀት የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም፣ አካታች ለሆነ የፖለቲካ ሥርዓት ባለው አናሳ አእምሮአዊ ዝግጁነት የተነሳ ውጤታማ ሊሆን አልቻለም። በዚህ አይነቱ ሁሉም በየራሱ ጎጆ ተደራጅቶ እርስ በርሱ በሚራኮትበት ሁኔታ እራሳቸውን በትጥቅ ትግል ያደራጁ ‘የነጻ አውጭ ድርጅቶች’ ተሳክቶላቸው ሃገሪቱን ሙሉ ለሙሉ ሊቆጣጠሩ ችለዋል። ኢህአዴግም፣ ከጅምሩ በህብረ ብሔራዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ በነበረው የጠላትነት ስሜት የተነሳ እንዲህ አይነቶቹ ድርጅቶች ወደ ሃገር ውስጥ እንዳይገቡ፣ ከገቡም ትርጉም ያለው እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ ከፍተኛ ጫና አድርጓል። በመሆኑም፣ ሁለተኛው የዳያስፖራ ትውልድ በ1983 በነበረው የሽግግር አጋጣሚ ትርጉም ያለው ድርሻ ለማበርከት ሳይችል ቀርቷል።          
ሶስተኛው የዳያስፖራ የፖለቲካ ዘመን ካንደኛውና ከሁለተኛው የዳያስፖራ የፖለቲካ ዘመን ከተሸጋገረው በተጨማሪ በዘመነ ኢህአዲግ ከሃገር ተሰዶ የወጣውንና በተለያየ ህጋዊ የቪዛ ፕሮግራሞች የሄደውን ኢትዮጵያዊ ያካትታል። ይህ ጊዜ ከ1983 እስከ 2010 የነበረውን የኢህአዴግ ዘመን የሚሸፍን ሲሆን ምናልባትም ቀደም ሲል ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ጽንፈኝነት የበረታበት የፖለቲካ አመለካከት ገኖ የወጣበት ዘመን ነው። ለዚህ ሁኔታ መፈጠር፣ በሁሉም ዘመን ከነበሩት መሰረታዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ህመሞች በተጨማሪ የሚከተሉት ሁኔታዎች አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ይገመታል። የመጀመሪያውና ምናልባትም ዋነኛው ምክንያት፣ ተረኛ ጨቋኝነት (reverse repression) በሚመስል መልኩ በኢህአዴግ ተግባራዊ የተደረገው በብሔረሰባዊ አሃዳዊነት (Ethnicised unitarianism) ላይ የተመረኮዘው ፌደራላዊ ሥርዓት ያስከተለው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ከዚህ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ጥልቅ የተጠቂነትና የተጠቃሚነት ስሜት ነው። ሁለተኛው አቢይ ችግር፣ ፖለቲካውን በቀጥታ ራስንና የራስን ቡድን ለማበልጸጊያ ለመጠቀም የተዘጋጁ ግለሰቦችና የተደራጁ ቡድኖች እየበረከቱ መምጣታቸው ነው። የእነኚህ የፖለቲካ ነጋዴዎች (political entrepreneurs) ህልውና የሀገሪቱ ፖለቲካ የተረጋጋ ካለመሆኑ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ጽንፍ የያዙ የፖለቲካ አመለካከቶችን ማራገብ ዋነኛ መገለጫቸው ሊሆን ችሏል። ሶስተኛው፣ ባግባቡ ያልተብላላና ያልበሰለ መረጃን ለማሰራጨት ማህበራዊ ሚዲያ የፈጠረው አመቺነትና ከዚህ ጋር በተያያዘ እየገነገነ የመጣው ዋልታ ረገጥነት ነው። በይነ መረብ (internet) እና ማህበራዊ ሚዲያ ማንኛውንም መረጃ በእኩልነት ለሁሉም ማዳረስ ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ሰው መረጃን የማመንጨት አቅምንም ፈጥሮለታል። በዚህም የተነሳ፣ ማህበራዊ ሚዲያ አንድን ማህበረሰብ ከፍ ወዳለ እድገት ለማሻገር የሚያስችል የመሆኑን ያህል ለከፍተኛ ጥፋትም ሊዳርግ ይችላል። በዚህ ረገድ፣ የበይነ መረብን አመቺ ሁኔታ ለህዝብና ለሃገር ጥቅም በሚጠቅም መልኩ የሚጠቀሙ በርካቶች የመኖራቸውን ያህል ጥቂቶች በህዝቦች መካከል መቃቃርና ግጭት ለመፍጠር የሚያደርጉት አሳዛኝና አሳፋሪ ጥረት ለሃገሪቱ ፖለቲካ መረጋጋት ከባድ ፈተና እየሆነ መጥቷል።           
ይህ እንዳለ ሆኖ፣ ሶስተኛው የዲያስፖራ የፖለቲካ ዘመን በመሰረታዊ ባህሪያቸው የሚለያዩ ሁለት አበይት ክፍሎች እንዳሉት መገንዘብ ያስፈልጋል። የመጀመሪያው፣ አብዛኛውን ዳያስፖራ ኢትዮጵያዊ የሚወክለውና የሃገሪቱን ሰላምና እድገት በጽኑ የሚመኘው ዝምተኛው ብዙኃን (the silent majority) ሲሆን፣ እነኚህ ወገኖች ለሃገሪቱና ለህዝቡ ይጠቅማሉ ለሚባሉ ጥሪዎች ሁሉ ያለብዙ ጫጫታ ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውንና ዕውቀታቸውን የሚያበረክቱ ናቸው። ከዚህ በተቃራኒው የሚገኙት ጥቂት ጯሂዎች (the noisy minorities) ጽንፈኛ በሆነ የፖለቲካ አመለካከትና ስሜታዊ በሆኑ የፖለቲካ ጥያቄዎች እያደናገሩ የራሳቸውንና የቡድናቸውን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አላማዎች ለማሳካት የሚሯሯጡ ናቸው። ምንም እንኳን፣ በዘመነ ኢህአዴግ የነበረው የዲያስፖራ ፖለቲካ ጽንፈኝነት የበረታበት ቢሆንም፣ ብዙዎቹ ለኢህአዴግ ከነበራቸው ጥልቅ ተቃውሞ የተነሳ ቀጥተኛ ያልሆነ ተደጋጋፊነትም ነበራቸው። ይህም በመሆኑ፣ በ2010 በሃገሪቱ ለተከሰተው ሃገራዊ ለውጥ የየራሳቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል። የ2010 ለውጥንም ተከትሎ፣ ጥቂት የዲያስፖራ ፖለቲካ አቀንቃኞች በሃገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ በቀጥታ ለመሳተፍ የተደረገውን ጥሪ በመቀበል ወደ ሃገር ውስጥ ሊገቡ ችለዋል። ይህ እድል የ1966 ህዝባዊ ንቅናቄን ተከትሎ ከተከሰቱ የፖለቲካ እድሎች ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሲሆን ለተመሳሳይ ውድቀት ሊያጋልጡት የሚያስችሉ ምልክቶችም በመታየት ላይ ይገኛሉ። አሁን የተፈጠረው መልካም የለውጥ አጋጣሚ እንደ ሺህ ዘጠኝ መቶ ስልሳ ስድስቱ የለውጥ አጋጣሚ እንዳያመልጠን  ከዚህ በታች የተመለከቱትን ከዳያስፖራው ፖለቲካ ጋር የተያያዙ መሰረተ ቢስ እምነቶች (myths) ማከም ይገባል።
አንደኛውና ምናልባትም ዋነኛው፣ ጥቂት የ2010 የዲያስፖራ የፖለቲካ ዘመን ጽንፈኛ መሪዎችና አቀኝቃኞች ለተፈጠረው የለውጥ ሂደት ያበረከቱትን አስተዋጽኦ እጅግ አግዝፈው ማየታቸው ነው። ከዚህም የተነሳ፣ በሃገር ውስጥ የነበረው የብዙሃኑን የለውጥ ታጋይ ድርሻ አሳንሶ ከመመልከትም ባሻገር ለውጡ ያለ እነሱ አመራር የትም ሊደርስ አይችልም ብለው እስከማመን ይደርሳሉ። በምህዳራዊ አስተሳሰብ መሰረት፣ በማንኛውም ምህዳር ውስጥ ሊመጣ የሚችል ለውጥ ዋነኛው መሰረቱ (foundation) በዚያው ምህዳር ውስጥ ያለው ውስጣዊ መስተጋብር (internal dynamics) ሲሆን የውጫዊ ሁኔታዎች ድርሻ የዚህን የለውጥ ፍጥነት ከማሳለጥ ወይም ከማዘግየት ያለፈ አይሆንም። በመሆኑም፣ ለ2010 ለውጥ መምጣት የዳያስፖራው የአጋዥነት ድርሻ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ዋነኛው ድርሻ ሊሰጥ የሚገባው በቀዳሚነት በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለነበረው የህዝቦች ትግልና የወጣቶች ንቅናቄ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ የወሳኝነቱን ሚና (determining factor) የሚወስደው በራሱ በኢህአዴግ ውስጥ የተፈጠረው የለውጥ አመራርና ከዚህ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው የኦሮማራ ጥምረት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ፣ የዛሬዎቹም ሆኑ የወደፊቶቹ የዲያስፖራ ፖለቲካ  አራማጆችና አቀንቃኞች ለራሳቸው ከሚሰጡት የገዘፈ የመሪነት ማማ (pedestal) ወርደው ሃገራዊ ለውጡን ወደፊት ለማራመድ በሚያስችሉ ድጋፎች ላይ ቢያተኩሩ፣ የሺህ ዘጠኝ መቶ ስልሳ ስድስቱ የዲያስፖራ ትውልድ ፖለቲካ መሪዎች ካጋጠማቸው የታሪክ ተወቃሽነት ሊድኑ ይችላሉ።
ሁለተኛው፣ ለሃገሪቱ ለውጥ ታላቅ ድጋፍና አበርክቶት ሊያደርግ የሚችለው ዝምተኛው ብዙሃን በጋራም ሆነ በተናጠል እራሱ ሊኖረው የሚችለውን ሚና አሳንሶ ማየቱ ነው። በዚህም የተነሳ፣ የበርካታው ዳያስፖራ ኢትዮጵያዊ በጎ ፈቃድ የጥቂት ብልጣብልጥ ፖለቲከኞችና የማህበራዊ ሚዲያው አርበኞች መጠቀሚያ ሲሆን ይታያል። እንደሚታውቀው፣ ‘በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ ሁነቶች በዋነኝነት የተከሰቱት እኩይ አመለካከት ባላቸው ጥቂቶች ጥንካሬ ሳይሆን መልካም አስተሳሰብ ባላቸው ብዙሃኖች ዝምታ ነው’ ይባላል። በቅርቡ በሃገራችን ለደረሰው አሳዛኝና አሳፋሪ ኢ-ሰብዓዊ ወንጀል ጥቂት ጽንፈኛ አመለካከት ያላቸው የማህበራዊ ሚዲያ አርበኞች ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስዱ ቢሆንም፣ የእነኚህን አጥፊ ወገኖችን ተግባር በዝምታ ያስተናገድነው ብዙሃንም የራሳችን ድርሻ አለን። በዚህ ረገድ፣ በቅርቡ እነኚህ የጥፋት መልእክተኞች የሚኖሩበት ሃገር ህግ በሚፈቅደው መሰረት ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ የተጀመረው እንቅስቃሴ ይበልጥ ሊደገፍና ሊጠናከር ይገባዋል። የሃገራችን ፖለቲካ ለረዥም ጊዜ በጥቂት ጯሂዎች ሲታመስ ቆይቶ ዛሬ ያለንበት አሳዛኝ ሁኔታ ላይ ደርሷል። በተለያዩ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች የተነሳ፣ አሁን ሃገሪቱ ያለችበት ሁኔታ ከዚህ ቀደም ከነበሩት የሽግግር ወቅቶች እጅግ የተለየ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። በዚህ ጸሃፊ እምነት፣ በሚመጡት ጥቂት ዓመታት በሀገሪቱ የሚከሰቱት የፖለቲካ ሁኔታዎች ይህች ሃገራችንን ወይ ወደ ከፍተኛ የልማትና እድገት አቅጣጫ ይወስዳታል አለበለዚያ እንደ ሃገር የማትቀጥልበት ሁኔታ ውስጥ ይከታታል። ስለሆነም፣ የዚህች ሃገር የነገ እጣ ፋንታ የሚያስጨንቀን ወገኖች ዝምታችንን ሰብረን ባለን እውቀትና አቅም እየተካሄደ ያለው ለውጥ ሁሉንም አካታች ወደሆነና የዜጎችን ሁለንተናዊ የዲሞክራሲና የልማት ፍላጎቶችን ሊያሟላ ወደሚችል ሥርዓት እንዲሽጋገር ማገዝ ይኖርብናል።
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ስታለንቦሽ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፈሰር ሲሆኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትም ያስተምራሉ።    



Read 3465 times