Print this page
Saturday, 15 August 2020 00:00

ብልፅግና - “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ!”

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

          ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረው ለውጥ፣ በየጊዜው በሚነሱ ዐውሎ ነፋሳት እየተናጠ፣ እየተወላገደና እየቆሰለ እዚህ ደርሷል:: በተለያዩ አካባቢዎች የተነሱ ነውጦች የብዙ ሰዎችን ሕይወትና ንብረት ነጥቀዋል፡፡ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ለግጭትና ጥፋት የተመቻቸው የብሔር ፖለቲካ፤ ሀገሪቱን የመበተን አደጋ መጋረጡን በተደጋጋሚ በተግባር አይተነዋል፡፡ ቀደም ባሉት የኢትዮጵያ መንግሥታት የተዘራው የአንድነትና የሀገር ፍቅር ስሜት ግን የሰንሰለቱ አፅቅ እንዳይበጠስ ታድጎታል፡፡   
ሴረኞች ሌትና ቀን በብሔርና በሃይማኖት አቧድነው ሲላቸውም፣ ቅጥረኞችን በገንዘብ ገዝተው፣ እሣት ያልጫሩበት የአገሪቱ ክፍል አለ ለማለት ያዳግታል፡፡ አማራውን ከቅማንት፣ ቤኒሻንጉሉን ከአማራ፣ ኦሮሞውን ከሶማሌ እንዲሁም ከአማራው ወዘተ---ለማባላት ይሁነኝ ተብሎና ታቅዶ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል፡፡
ሥልጣንና ጥቅም ቀረብን ብለው ያኮረፉ የቀድሞ ሹማምንት፤ ህዝብን ከህዝብ የማጋጨትና አገርን የማፍረስ ህልማቸውን ለማሳካት ሴራ በመሸረብ ረገድ በቀዳሚነት ቢጠቀሱም ቅሉ ሌሎች ፅንፈኛ የብሔረሰብ ፖለቲካ አቀንቃኞችም ሀገሪቱን የማያባራ ግጭትና ብጥብጥ ውስጥ ለማስገባት፣ ከተቻለም ስልጣን ላይ ለመፈናጠጥ ያልማሱት ጉድጓድ አልነበረም፡፡  
በተለይ ሰኔ ወርን ታክከው በየዓመቱ የተፈፀሙት የሽብርና የግድያ ተግባራት ለዚህ ሁነኛ ማረጋገጫ ናቸው፡፡ በመጀመሪያው ዓመት ሰኔ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የግድያ ሙከራ የተደረገ ሲሆን  በቀጣዩ ሰኔ ደግሞ የሀገሪቱ ኤታማዦር ሹምና የአማራ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ አሰቃቂ ግድያ ተፈጽሟል፡፡ ይህ አረመኔያዊ የጥፋት ድርጊት በቀዳሚነት የጽንፈኞቹ ሴራ ቢሆንም ቅሉ የመንግሥት ቸልተኝነትም የራሱ ሚና አልነበረውም ማለት አይቻልም:: በወቅቱ የደህንነት ሥራው አለመጠናከሩና መዋቅሩ ከጸረ-ለውጥ ሃይሎች በቅጡ አለመጽዳቱም ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሏል ማለት ይቻላል፡፡  
በእርግጥ ለ27 ዓመታት በመከላከያው፣ በፖሊስ ሠራዊቱ፣ በሲቪል መሥሪያ ቤቶችና በቀበሌ መዋቅሮች ሳይቀር የተሰገሰጉትን ፀረ-ለውጥ አቋም ያላቸው ግለሰቦችና ቡድኖችን ሙሉ በሙሉ የማጥራት ሥራ እንዲህ ቀላል አልነበረም፡፡ የለውጡ ጠላቶች አሁንም ድረስ እጃቸውን እንዳልሰበሰቡ ከአጥፊ የሴራ ተግባራቸው እየታዘብን ነው፡፡
የለውጡ አበሳ ግን ይህ ብቻ አልነበረም፡፡ እንደ ዘመነ ደርግ፤ ጥቂት የለውጡ ሰዎችም፣ በተለያዩ ሃሳቦችና ግፊቶች እየተመሩ፣ ለውጡን ለመገዝገዝ ሲሰሩ እንደነበር የሚጠቁሙ ምልክቶች አልጠፉም፡፡ አንዳንዶች  ደግሞ በለውጡ ባቡር ውስጥ ተሳፍረው፣ በብሔርተኝነትና ጐጠኝነት በመጠለፍ፣ ትግሉን ክደው፣ ለውጡን ወደለየለት ነውጥ ገፍትረው ሲጥሉት ተገኝተዋል፡፡  
ሌላው ቀርቶ የለውጡ የዐይን ብሌን ተብለው የተጨበጨበላቸውና አጽናፋት ያካለለ አድናቆት የጠገቡት አቶ ለማ መገርሣም አንድ ሰሞን የአዲስ አበባን/ፊንፊኔን ዴሞግራፊ ማስተካከል በሚል፣ በየቦታው የተፈናቀሉና ቤታቸው የፈረሰ ሰዎችን ጩኸት ለማርገብ ያደረጉት ያልተገባ ንግግር፤ ከፍተኛ ማዕበል በማስነሳት ብዙዎች ለውጡን በጎሪጥ ማየት እንዲጀምሩ አስገድዷቸው እንደነበር አይዘነጋም:: “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” ያሉት አቶ ለማ፤ መልሰው ወደ ብሔራቸው ገብተው፣ ከእርሳቸው የማይጠበቅ ነገር ማለታቸው የምንወዳቸውን ወገኖች ሁሉ አሳዝኖን አልፏል፡፡ ሆኖም ፖለቲከኛ ሊሳሳት ወይም ምላሱን ሊያዳልጠው እንደሚችል ከታሪክ ተምረን፣ በአቶ ለማ ላይ ሳናመርባቸው ቀረን፡፡ ብዙዎቻችን ሃዘናችንን ከድነን ጀግናችን ከተቀመጠበት መንበር እንዲወርድ አልጠየቅንም፡፡ ዛሬም ቢሆን ለማ መገርሣን እንደ ዋዛ ማጣጣል የሚቻል አይመስለኝም:: ለማ የትግሉ ፊታውራሪ፣ ለጥይት ግንባሩን የሰጠ ጀግና፣ የታሪካችን ኮከብ ነው፡፡
የአቶ ለማ ጉዳይ ግን በዚያ ብቻ አላበቃም፡፡ የብልጽግና ፓርቲ ሊመሠረት ሲል “ለምን በጥድፊያ ሆነ?” በሚልና አንዳንዶች ዶ/ር ዐቢይ አህመድን በኦዴፓ ፓርቲ ሥር አቆይቶ ለማሽመድመድና እጅ ጠምዝዞ የብሔር አጀንዳዎችን ለማስፈፀም ነው በሚሉት የሴራ ፖለቲካ አካሄድ የተነሳ ቅራኔና ውዝግቡ ሊጦዝ በቃ፡፡ አቶ ለማ “መደመር ራሱ አልገባኝም” በሚል አፈንጋጭ ሃሳብም፣ የለውጡን አቅጣጫ ጥርጣሬ ውስጥ የሚከት አቋም አንፀባርቀው ነበር:: ይኸኛው የአቶ ለማ ተቃውሞ ግን በሀገር ደረጃ የዶ/ር ዐቢይን ደጋፊዎች ቁጥር ያሳደገና በብሔርተኝነት የሚጠረጥሯቸውን ሁሉ ሃሳብ ያስቀየረ መልካም አጋጣሚ ሆኖ ነበር፡፡
በነገራችን ላይ የአቶ ለማ ከለውጡ ሂደት ማፈንገጥ ብዙዎችን አበሳጭቶ ነበር - “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው!” እያለ ሸወደን በሚል፡፡ እኔ ግን የእርሳቸው ከለውጡ መስመር መውጣት፣ ከማናደድ ይልቅ አሳዝኖኝ ነበር፡፡ እጅግ የምወዳቸው፣ በዘመኔ ታሪክ “አንቱ” ብዬ የምጠራው፣ እንደ ክርስቶስ ነፍሱን የሚሰጠኝ መሪ አገኘሁ ብዬ ለትውልዴ ሳይቀር ኩራት አድርጌ ያየኋቸው ሰው፣ በአንዲት ቀለበት ውስጥ ታጥረው ሲቀሩ ልቤ የደም እንባ አንብታለች:: የጨበጥኩት የተስፋ ችቦ ዐመድ ሆኖ እጄ ላይ ሲረግፍ ተሰምቶኛል፡፡
ይህ የኔ ብቻ ሳይሆን የብዙ ወዳጆቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ስሜት ነበር:: የአሜሪካው ጀኔራል ሮበርት ሊ. ዕጣ ደረሳቸው! ብዬ አማጥኩ፡፡ አንዳንዴ በታሪክ ውስጥ መሪ ተዋንያን ሳይቀሩ ይሳሳታሉ:: ሮበርት ሊ. አሜሪካን በመውደድ ከሌሎች የዘመናቸው ጀኔራሎች አያንስም ነበር:: ግን ኮንፌዴራሊስቶቹ አሳሳቱት፡፡ ቨርጂኒያ መወለዱ፣ በይሉኝታ ገመድ ስቦት፣ አሜሪካ ላይ ዕጣ ጥሎ፣ ጭራሽ የፌደራል መንግሥቱን ሊወጋ ጠመንጃ ይዞ ተነሳ፡፡ ያ ብቻ አይደለም፡፡ ዋነኛ መሪ ሆኖ ቁጭ አለ፡፡ ሊንከንና የፀኑት ጀኔራሎች ግን ወደ ፊት ገፉ:: አሜሪካም ከሞት ዳነች፡፡ ዛሬም የኢትዮጵያ ዕጣ ከዚህ የተለየ እንደማይሆን አምናለሁ፡፡
በእርስ በርሱ ጦርነት ሁሉም ወደ እግዚአብሔር ሲፀልይም፣ የአንድነትና የፍቅር አምላክ የሆነው እግዚአብሔር አሜሪካ እንዳትበታተን ጣልቃ ገብቷል፡፡ ስለዚህ ጀኔራል ሮበርት ሊ በጀነራል ግራንት እጅ ወድቋል፡፡ ይህ በተለያዩ ሀገራት ታሪክ ውስጥ ሊያጋጥም የሚችል ዕጣ ነው፡፡
የሰሞኑ የኦሮሚያ ብልጽግና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ ከፓርቲው ስልጣን መታገዳቸው ወይም መወገዳቸው በሀገሪቱ በተለይም በለውጡ ሂደት ላይ ትልቅ ኹነት (event) እንደሆነ መካድ አይቻልም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ከታገዱት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ውስጥ የለውጡ ፊታውራሪ መኖራቸው ነገሩን ይበልጥ አስደንጋጭ ያደርገዋል፡፡ የአቶ ለማ መገርሳ ለብዙ ጊዜያት ከአደባባይ መጥፋት ለብዙዎቻችን ጥያቄ ቢፈጥርብንም፣ ልዩነታቸውን አመቻምቸው፣ የጀመሩት የለውጥ ሀዲድ ውስጥ ተመልሰው እናያቸዋለን ብለን ተስፋ አድርገን ነበር፡፡  
ይሁን እንጂ ድንጋጤያችን በአመክንዮና በታሪክ ሚዛን ሲቀመጥ በብዙ ሀገራት የተፈጠረ፣ ወደፊትም የሚፈጠር ነገር ነው:: ሌላው ቀርቶ ባሳለፍናቸው የታሪክ ዘመናት በኢትዮጵያም ውስጥ ተፈጥሮ ያለፈ ነው፡፡ በኃይለሥላሴ ዘመን፣ ልጅ ኢያሱ፣ ኃይለሥላሴ ለፈጠሩት ግጭት ከኢያሱ ወገን የነበሩት መኳንንት ወድቀው፣ ከኃይለሥላሴ የወገኑት በሥልጣን መቀጠላቸውን ታሪክ ይነግረናል፡፡ በዘመነ ደርግም አብዮቱን በአራተኛ ክፍለ ጦር ሆኖ ሲያቀጣጥልና ሲመራ የነበረው አጥናፉ አባተ፣ ከሊቀመንበር መንግሥቱ ጋር እጅና ጓንት ያልነበረውን  ያህል በሃሳብ ተለይቷል ተብሎ በሞት እንደተወገደ እናስታውሳለን፡፡
ከዚያም ወዲህ ድንጋይ ተንተርሰው፣ ስኳርና አፈር ቅመው፣ ቦንብ እየወረደባቸው የታገሉት ሕወሓቶች፣ አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ በተለያዩ ሰበቦችና በሃሳብ ልዩነቶች ሳቢያ፤ በእነ ስዬ የሚመራው ቡድን እንዴት ከማማው ላይ ተገፍትሮ፣ ከፊሉ ወደ እሥር ቤት እንደተላከ እናስታውሳለን፡፡ በረሃ ለበረሃ ሲንከራተቱ የወንድም ያህል የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊና የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔም በ#ስኳር; ሰበብ ወህኒ ገብተው የቀመሱትን ጽዋና የተቀበሉትን ግፍ በአደባባይ ሰምተናል:: #አብዮት ልጆቿን ትበላለች; የሚለውን የኮሚኒስቶች አባባል በገቢር አይተነዋል፡፡
ከሰሞኑ የሰማነው የብልጽግና የእገዳና የማስወገድ እርምጃ፣ ከአስቀያሚው የ60ዎቹ የፖለቲካ አሻጥርና መጠላለፍ ጋር ፈጽሞ እንደማይገናኝ ተስፋ እናደርጋለን:: የመጠፋፋትና የመበላላት ፖለቲካ ባህልም  ተመልሶ እንዳይመጣ እንጸልያለን፡፡ ግን ደግሞ “እኔና አንተን ከሞት በቀር የሚለየን የለም” የተባባሉትና አያሌ መከራዎችን በአንድ ላይ ያሳለፉት አቶ ለማ መገርሣና ዶ/ር ዐቢይ አህመድ መጨረሻቸው እንዲህ ባለ ሁኔታ ባይደመደም እንወድ ነበር:: በግሌ አንድ ጥያቄ አለኝ፡፡ አቶ ለማን በዚህ ወቅት መግፋትና ማግለል ተገቢ ነው ወይ? ሀገሪቱ በተለይም የኦሮሚያ ክልል ቁስልዋ ሳይደርቅ፣ እንባዋ ሳይከተት፣ ቁጭቷ ሳይረግብ ሌላ የቅሬታና የጥርጣሬ በር መክፈት “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” አይሆንም?! ጥያቄ ነው፡፡
በእርግጥ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፣ ሀገሪቱን ወደ ሰለጠነና የበለፀገ ከፍታ ለማድረስ በሚያደርጉት ጥረት ከብሔር ይልቅ፣ አንድነትና መከባበርን፣ ከጥላቻና ቂም ይልቅ ፍቅርና ይቅር ባይነትን  የሙጥኝ ብለው ለሁሉም የምትመች የበለጸገች ገናና ሀገር በመፍጠር ተግባር እንደተጠመዱ ማንም አይስተውም:: ለአንድ ወገን ከማድላት ይልቅ፣ ሁሉም ወደ አንድ የብልጽግና ግብ የሚደርስበትን መንገድ እየጠረጉም እንደሆነ በተግባር እያየን ነው፡፡
ጠላቶቻቸው አንዴ “ግድቡን ሸጠ”፤ ሌላ ጊዜ “ኦነግ”፤ ሌሎቹ “ባንዳ”፤ አንዳንዶች ደግሞ "ነፍጠኛ" ሲሏቸው ሰምተው እንዳልሰማ በመሆን አሻራቸውን ለማስቀመጥ ቀን ከሌት ይተጋሉ፡፡ ስኬትም እየተቀዳጁ ነው፡፡ ይሄን ማድረግ የቻሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የአቶ ለማ መገርሣንና የጓዶቻቸውን ችግሮች በጓዳ መፍታት እንዴት አቃታቸው? ሀገሪቱ ገና ያሸረጠችውን የሀዘን ነጠላ ሳታወልቅ፣ የኦሮሞ ሕዝብ በፖለቲካው ውስጥ ያለው ሥጋት ወደ እርግጠኝነት ሳይመጣ፣ እሥረኞች በየፍርድ ቤቱ በሚመላለሱበት ትኩስ ቁስል ላይ ሌላ ነገር መጨመር ደግ ነው? ሌላ ጣጣ እንዳይጎትት ሰግቼ ነው፡፡   
በዚያ ላይ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ ከሰባት ወራት በፊት የተናገሩት ነው ተብሎ በዚህ ወቅት  የተለቀቀው የንግግር ቪዲዮ፤ ሌላ  አቧራ የሚያስነሳና ለጽንፈኞች ጩኸት የሚመች ነው፡፡ የለውጡን ሃቀኛ ደጋፊዎችም ጥርጣሬና ፍርሃት ውስጥ የሚከት ነው:: ባለፈው ዓመት ከተናገሩት “የአከርካሪ ሰበርን” ዜና "አዲስ አባን Irrelevant እናደርጋታለን” የሚል ሰቅጣጭ ሟርት፣ የባህርዳሩን ጉዞ የConvince እና confusion ትርጓሜ ለመስጠት የተደሰኮረ ዲስኩር---ስንት ሚሊዮን ልቦችን እንደሚያቆስል መገመት አይከብድም፡፡ ፖለቲካ ተንኮል መሆኑን፣ የአንድ ብሔር ፈቃደኝነት የሥልጣን ባለቤት ማድረጉን፣ ለአንድ ወገን ተጠቃሚነት ሆን ተብሎ መሠራቱን ወዘተ---መናገራቸው የቆሰቆሰው እሳት፣ ለባላንጣዎቻቸው የጠረገው መንገድ ቀላል አይደለም! የዚህን ውጤት ዝም ብሎ ከማየት ይልቅ ነገሩ የሚረግብበትን ዘዴ መቀየስ፣ “ይቅርታ” መጠየቅና ማብራሪያ ለመስጠት መሞከር ትንሽ ጉዳዩን ያስተነፍሰዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡
አሁን ለሁለተኛ ጊዜ ከአንድ ክልል መሪ የማይጠበቅ፣ አሣፋሪ ንግግር ያደረጉትን ሰው ጉዳይ ስናጤን፣ የፓርቲውን የምልመላ መስፈርትና የሹመት ሚዛን ተዓማኒነት እንድንመረምር የሚያስገድደን ይመስለኛል:: ወይስ “ሰው የለም” ብለን እንደ ዴዎጋን በቀን ፋኖስ ይዘን እንዙር ይሆን? ግራ ያጋባል!
ብቻ ያሁኑ የብልጽግና ማዕበል፣ ከሌላው ጊዜ የተለየና አንዳች ችግር ከፊቱ ያፈጠጠ ስለሆነ በጥንቃቄና በማስተዋል እንዲሰክን፣ የሁሉንም ጥንቃቄና ብልሃት የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡
በእኔ እምነት፤ ከሁሉ በላይ ሁሉን የሚችለው እግዚአብሔር ሀገራችንን እንዲረዳት መፀለይ አለብን ከሚል ምርጫ ጋር እቆማለሁ! እግዚአብሔር ሀገራችንን ይርዳ! ይታደግም!!   

Read 5738 times