Tuesday, 18 August 2020 16:42

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ሆነው ተሾሙ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

የፌደራል አቃቤ ህግ የነበሩት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፤ የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሆነው ተሾሙ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በዛሬው እለት ባካሄደው አስቸኳይ ጉባዔ ነው የምክትል ከንቲባነት ሹመቱን ያፀደቀው።

ቀደም ሲል በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ሃላፊነቶችና የአዳማ ከንቲባ በመሆን  ያገለገሉት ወ/ሮ አዳነች፤ የለውጡን መምጣት ተከትሎ የፌዴራል ገቢዎች  ሚኒስትር እንዲሁም  የመጀመሪያዋ ሴት የፌደራል አቃቤ ህግ ሆነው  ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡

ወ/ሮ አዳነች በተለይ የገቢዎች ሚኒስትር ሳሉ በተሾሙ በአጭር ጊዜ ውስጥ በግብር አሰባሰብ ባስመዘገቡት አመርቂ ውጤት ከመንግስት አድናቆትን ማግኘታቸው አይዘነጋም፡፡

ላለፉት ሁለት ዓመታት አዲስ አበባን በምክትል ከንቲባነት ያገለገሉትን ኢንጂነር ታከለ ኡማን በመተካት ነው ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የተሾሙት፡፡ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ የኢንጂነር ታከለ ኡማን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሚኒስትርነት ሹመት ጨምሮ በዛሬው ዕለት 10 አዳዲስ ሹመቶችን እንደሰጡ የጠ/ሚኒስቴር ጽ/ቤት  አስታውቋል፡፡

Read 10189 times