ባማኮን ኢንጂነሪንግ ከእህት ኩባንያዎቹ ጋር በመተባበር ለኮቪድ 19 ህሙማን ከፍተኛ አገልግሎት የሚሰጡ ኦክስጂን ኮንስትሬተሮችን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፈው ረቡዕ ነሐሴ 6 ቀን 2012 ዓ.ም ለገሰ፡፡ ኩባንያው ያበረከታቸው እነዚህ 100 ኮንሰንትሬተሮች እያንዳንዳቸው ለሁለት ታማሚ በበቂ ሁኔታ ኦክስጂን መሰብሰብ የሚችሉ ሲሆን፤ ለዚሁ ተግባር ታቅደው በልዩ ሁኔታ መታሰራቸውን የባማኮን ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢ/ር ግርማ ገላ አስታውቀዋል፡፡
የኦክስጅን መሰብሰቢያ ማሽኖቹ በሶኬት የሚሰሩና ትልቅ ጠቀሜታ ያላቸው ሲሆን፤ ከ10 ሚ ብር በላይ ወጪ እንደወጣባቸውም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ኩባንያው አገራችን አሁን ያለችበትን ተጨባጭ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባትና ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር የተገጠመውን ትንቅንቅ ታሳቢ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት እነዚህን መሳሪያዎች መለገሱንም ኢ/ር ግርማ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩም ለተደረገለት ልገሳ ለኩባንያው ኃላፊዎች ምስጋና አቅርቧል፡፡ ባማኮን ኢንጂነሪንግ በሀገራችን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የረጅም ዓመታት ልምድ ያለው የደረጃ 1 ተቋራጭ ሲሆን፤ በስራቸውና እየሰራቸው ባሉ በርካታ ደረጃቸውን የጠበቁ የህንፃ ግንባታዎች ይበልጥ የሚታወቅ ሲሆን፤ ከዚህም በተጨማሪ የሃይል ንዑስ ጣቢያዎችንና ሃይል ማስተላለፊያ አውታሮችንም የሚሰራ ኩባንያ መሆኑም ታውቋል፡፡