Saturday, 15 August 2020 14:58

አወዛጋቢው የሩስያ ክትባትና የኮሮና መሰንበቻ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   ባለፈው ማክሰኞ ማለዳ…
አለም ከወደ ሩስያ በሰማው በጎ ዜና ተደሰተ፣ ተስፋ አደረገ፡፡
“ምስጋና ይግባ ለታላቋ ሩስያ ተመራማሪዎች፤ ለወራት ነጋ ጠባ ባደረጉት ምርምር እነሆ ለኮሮና ቫይረስ ሁነኛ ክትባት አግኝተናል፤ ስፑትኒክ - 5 የሚል ስያሜ የሰጠነው የአለማችን የመጀመሪያው የኮሮና ክትባት፣ የሩስያ የቀዳሚነት ተምሳሌት ነው!...” አሉ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፡፡
ፑቲን ባለፉት ሁለት ወራት በሰዎች ላይ ሙከራ ሲደረግበት ነበር ያሉት በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በገፍ ተመርቶ ጥቅም ላይ እንዲውል መፈቀዱን ማስታወቃቸውን ተከትሎ ግን፣ ነገሩ ከመላው የአለም ዙሪያ በጥርጣሬ አይን መታየቱና ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም፡፡ ክትባቱ መደበኛውን የምርምር ሂደት ሳያጠናቅቅ በችኮላ በገፍ ወደማምረት የተገባበት ነው በሚል አገራትና ተቋማት የሩስያን አስደሳች ዜና ጥርጣሬና ትዝብት ውስጥ ሲጥሉት ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡
የህክምናው ዘርፍ ባለሙያዎች የሩስያ ክትባት ያሰጋናል ሲሉ ስጋታቸውን በስፋት እየገለጹ ሲሆን፣ የኮሮና ክትባት ምርምር ሚስጥሮቻችንን ልትመነትፈን መሞከሯን ደርሰንበታል ሲሉ ሩስያን ሲወነጅሉ የሰነበቱት እንግሊዝ፣ አሜሪካና ካናዳም የፑቲንን መግለጫ ተከትሎ በሰውዬው ላይ የፌዝና የስላቅ ቃላትን መወርወራቸውን ቀጥለዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ፑቲን ግን ክትባቱ አስፈላጊውን የምርመራ ሂደት ማለፉንና ፍቱን መሆኑን በመግለጽ እንዲሁም የገዛ ልጃቸውም መከተቧን በዋቢነት በመጥቀስ፣ ከያቅጣጫው የሚሰነዘርባቸውን ትችት መሰረተ ቢስ ብለው አጣጥለውታል፡፡
ባለፈው ሳምንት ሩስያ ክትባት በማምረት ሂደት አለማቀፍ አካሄዶችን እንድትከተል ያሳሰበውና በሶስተኛ ደረጃ ላይ ካስቀመጣቸው ክትባቶች ተርታ ያላሰለፈው የሩስያ ክትባት ጉዳይ ያሳሰበው የአለም የጤና ድርጅት፤ በመዲናዋ ሞስኮ የሚገኘው ጋማሊያ ኢንስቲቲዩት የተባለው ተቋም ከተለመደው አሰራር ውጭ የምርምር ሂደቱን ለማንም ትንፍሽ ሳይልና በተጣደፈ ሁኔታ አግኝቻለሁ ብሎ ባወጀው በዚህ በክትባት ዙሪያ ከሩስያ መንግስት ጋር ውይይት መጀመሩ ተነግሯል፡፡
የሆነው ሆኖ ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በስፋት መሰራጨቱን የቀጠለ ሲሆን፣ ቫይረሱ እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ ድረስ በመላው አለም 20.9 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎችን ማጥቃቱንና የሟቾች ቁጥር ከ749 ሺህ ማለፉን የገለጸው ዎርልዶ ሜትር ድረገጽ፤ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች ቁጥርም 13.7 ሚሊዮን መድረሱን አስታውቋል፡፡ እስከተጠቀሰው ጊዜ ድረስ በአሜሪካ ከ5.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ መጠቃታቸውና የሟቾች ቁጥርም ከ169 ሺህ ማለፉን የጠቆመው ድረገጹ፣ በብራዚል 3.17 ሚሊዮን ሰዎች ተጠቅተው ከ104 ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸውን፣ በህንድ ከ2.4 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መጠቃታቸውንና በሜክሲኮ ወደ 55 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ለሞት መዳረጋቸውን አመልክቷል፡፡
ኮሮና ቫይረስ በአፍሪካ አህጉር እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን አጥቅቶ ወደ 25 ሺህ የሚደርሱትን ለሞት መዳረጉን የገለጸው የአፍሪካ የበሽታ ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል፤ ያገገሙት ሰዎች ቁጥርም 769 ሺህ ያህል መድረሱን ባወጣው መረጃ አስታውቋል:: ወደ 569 ሺህ ሰዎች የተጠቁባትና ከ11 ሺህ በላይ ሰዎች የሞቱባት ደቡብ አፍሪካ በአህጉሪቱ ከፍተኛውን ጉዳት ያደረሰባት ቀዳሚዋ አገር ስትሆን፣ ግብጽ በ96 ሺህ፣ ናይጀሪያ በ48 ሺህ፣ ጋና በ42 ሺህ፣ አልጀሪያ በ37 ሺህ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ይከተላሉ፡፡
በሌሎች ተያያዥ ዜናዎች፣ ለ102 ቀናት ያህል በቫይረሱ የተያዘ ሰው ሳትመዘግብ የቆየችው ኒውዚላንድ ከሰሞኑ አራት ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው ማግኘቷን የዘገበው ቢቢሲ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከአጠቃላዩ የእንግሊዝ ህዝብ 6 በመቶ ያህሉ ወይም 3.4 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች እስካለፈው ሃምሌ ወር አጋማሽ ድረስ በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል ተብሎ እንደሚገመት ኢምፔሪያል ኮሌጅ ኦፍ ለንደን ከ100 ሺ በላይ በሚሆኑ በጎ ፈቃደኞች ላይ እንዲሁም በቤት ለቤት ምርመራ ባደረገው ጥናት ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡ የቬንዙዌላው ፕሬዚዳንት የቅርብ አማካሪ የሆኑትና የአገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር ጆርጅ ሮድሪጌዝ በኮሮና መጠቃታቸው መነገሩን የዘገበው ቢቢሲ፤በኬንያም አንድ ከፍተኛ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባለስልጣን በቫይረሱ ሳቢያ ለሞት መዳረጋቸውን አመልክቷል፡፡


Read 2569 times