Print this page
Tuesday, 18 August 2020 00:00

በአለማችን ከ800 በላይ ሰዎች በተሳሳተ የኮቪድ መረጃ ለሞት ተዳርገዋል ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   ፌስቡክ በ3 ወራት 22.5 ሚሊዮን የጥላቻ መረጃዎችን አስወግጃለሁ አለ

            በመላው አለም በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ800 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በተሳሳቱና ሃሰተኛ በሆኑ የኮሮና ቫይረስ መረጃዎች ሳቢያ ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን፣ አሜሪካን ጆርናል ኦፍ ትሮፒካል ሜዲስን ኤንድ ሃይጂን በተባለው የህትመት ውጤት ላይ ከሰሞኑ ለንባብ የበቃን አንድ ጥናት ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ከጥር እስከ መጋቢት ባሉት ሶስት ወራት ብቻ በተሳሳተ መረጃ ሳቢያ ለሞት ከተዳረጉት መካከል አብዛኞቹ ከኮሮና ያድናሉ በሚል ሜታኖል ወይም ሌሎች ከአልኮል የተሰሩ የጽዳት ፈሳሾችን በመጠጣት ምክንያት መሞታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ 5 ሺህ 800 ያህል የተለያዩ አገራት ዜጎችም በማህበራዊ ድረገጾች በኩል በተሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎች ሳቢያ ወደ ሆስፒታል እንዲገቡ መደረጋቸውን አስታውሷል፡፡ በርካታ ሰዎች በማህበራዊ ድረገጾች የሚሰራጩ ሳይንሳዊ ያልሆኑና በጥናት ያልተረጋገጡ መረጃዎችን በመከተል ከፍተኛ መጠን ያለው ነጭ ሽንኩርት ከመብላት የላም ሽንት እስከ መጠጣት የተለያዩ ለጤና አደገኛ ድርጊቶችን እንደፈጸሙም በጥናቱ ተገልጧል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ ታዋቂው ማህበራዊ ድረገጽ ፌስቡክ እስካለፈው ሰኔ በነበሩት ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ22.5 ሚሊዮን በላይ የጥላቻ ንግግር የጽሁፍና የምስል መረጃዎችን ከገጹ ማስወገዱን አስታውቋል፡፡
ኩባንያው እስከ ሚያዝያ በነበሩት ሶስት ወራት መሰል እርምጃ የወሰደባቸው ከዘር፣ ብሄር፣ ሃይማኖትና ሌሎች ጉዳዮች ጋር የተያያዙ የጥላቻ ንግግር መረጃዎች 9.6 ሚሊዮን ያህል ብቻ እንደነበሩ ያስታወሰው ሮይተርስ፣ ቁጥሩ ሊጨምር የቻለው መሰል መረጃዎችን የሚያሰራጩ ተጠቃሚዎች ከመበራከታቸውና ኩባንያው ለጉዳዩ የሰጠው ትኩረት ከመጨመሩ ጋር በተያያዘ መሆኑንም አመልክቷል፡፡

Read 10986 times
Administrator

Latest from Administrator